ሰላም ጤና ይስጥልን ውድ የአዲስ ዘመን ቤተሰቦች፤ እንደምን ከረማችሁ? ይህንን ሰላምታ ያቀረብኩት በመጠፋፋታችን ብቻ አይደለም፤ በየሳምንቱ አዳዲስ አጀንዳዎችን ማስተናገድ የዘወትር ባህላችን እየሆነ በመምጣቱ ነው። እድሜ ለቴክኖሎጂ ወለዱ ማህበራዊ ሚዲያ ይሁንና አዳዲስ አጀንዳዎቻችን በየጊዜው መቀያየራቸው አዲስ አይደለም፡፡
አሁን አሁን ሳምንት አልፎ ሳምንት ሲተካ አጀንዳዎቻችን በዚያው ልክ ሲቀያየሩ ማየት እየተለመደ ነው። የአጀንዳዎቻችን ፈጣሪዎች ደግሞ አንድም ማህበራዊ ሚዲያውን የገቢ ምንጭ ያደረጉ የወሬ ነጋዴዎች ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዴ መንግስት፤ ሌላ ጊዜ መንግስት ገሸሽ ያደረጋቸው ስልጣን ፈላጊዎች፤ የአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አልያም ህብረተሰቡ ራሱ ነው፡፡
ሰሞኑን ጥቂት ሳምንታት ዘለግ ላለ ጊዜ መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው የኑሮ ውድነት ነው። በተለይ የዘይት ዋጋ መናር ከመነጋገሪያነትም አልፎ የቀልድ ምንጭ ሲሆን ተመልክተናል። ይህ መሰረታዊ የሸቀጥ ምርት በድንገት ተነስቶ ጣሪያ የመንካቱ ምስጢር እስካሁን በግልጽ ባይታወቅም የተለያዩ መላምቶችና ምክንያቶች ሲሰነዘሩ ግን ሰምተናል። ከነዚህም ውስጥ የአምራቾች ጥሬ እቃ ማጣት፣ የሃይል አቅርቦት ችግር፤ የሩስያና ዩክሬን ጦርነት፣ በነጋዴና በሸማች መካከል ያለ ደላላ፤ ወዘተ የመሳሰሉት ምክንያቶች ከተነሱት ነጥቦች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በእኔ እምነት እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ይነስም ይብዛ የየራሳቸው ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። ነገር ግን ሁሉም ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው የሚል እምነት የለኝም። በተለይ የሩስያና ዩክሬን ጦርነት ለዘይት ዋጋ መናር ምክንያት ነው የሚል እምነት የለኝም።
በቅድሚያ የኔን ገጠመኝ ላንሳ። የዘይት ዋጋ አንድ ሺህ ብር ገባ በሚል መወራት የጀመረው ቅዳሜ እለት ከሰዓት በኋላ ነበር። በእለቱ እንዳጋጣሚ ሆኖ ጠዋት ላይ ለቤታችን የሚያስፈልግ ዘይት ገዝተን ነበር። በእለቱ አምስቱ ሊትር ዘይት የተገዛው በ650 ብር ነበር፡፡
ከዚያ ከሰዓት በኋላ የዘይት ዋጋ አንድ ሺህ ብር መግባቱ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ተጥለቀለቀ። ከዚያ በየመንደሩ የማህበራዊ ሚዲያ የሚጠቀመውም ሆነ የማይጠቀመው ይህን ወሬ በብዙ እጥፍ አባዛው። ለካ የሰፈር ወሬ ከማህበራዊ ሚዲያው በላይ የመስፋፋት አቅሙ ከፍተኛ ነው።
ከዚያ ጥቂት ጎረቤቶቻችን በመምጣት ዘይት ከዚህ ሳይብስ ለምን አትገዙም በሚል ግማሹ በምክር መልክ፤ ከፊሉ ደግሞ ካለን ቅርበት የተነሳ በራችንን ማንኳኳት ጀመሩ። ከዚያ እኛ ጠዋት ከገዛንበት ቤት ከሰዓት በኋላ በአንድ ሺህ ብር መቸብቸብ ተጀመረ፡፡
እንግዲህ እነዚህ ነጋዴዎች በ650ም ሆነ በ1000 ብር ሲሸጡ የነበረው ዘይት በተመሳሳይ ዋጋ የተገዛ መሆኑ እሙን ነው። ለዋጋ መጨመር ምክንያት የሆናቸው የገበያው ሁኔታ ሳይሆን ገና ለገና ዘይት ጨምሯል የሚለው ወሬ ነው። እና ከትክክለኛ ዋጋ ይልቅ ወሬ የአገራችንን ዋጋ እየተቆጣጠረ ስለመሆኑ ልብ እንበል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ከእነዚህ ስግብግብ ነጋዴዎች ባልተናነሰ የስግብግብ ሸማችም ለዋጋ ንረቱ አስተዋፅኦ እንዳለው ልብ ልንል ይገባል። በአገራችን ገና ለገና አንድ እቃ ከገበያ ይጠፋል በሚል ከዋጋው በላይ ለመግዛት መሯሯጥ የተለመደ ነው። በተለይ ‹‹እንዲህ አይነት እቃ ጠፋ፤ ዋጋ ሊጨምር ነው›› ከተባለ አብዛኛው ሰው ወዲያው ተበድሮም ቢሆን ከመግዛት አይመለስም። ገና ዋጋ ጨመረ ሲባል ተሰልፎ ለመግዛት ይወጣል። የሚያሳዝነው ደግሞ አንዳንዱ ለማከማቸት እንጂ ለመብላት የሚገዛ እስከማይመስል ድረስ በጅምላ ለመግዛት መሯሯጡ ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ በተለይ በህገወጥ መንገድ ገንዘብ የሚያገኙ ሰዎች በተገኘው ዋጋ በመሸመት ዋጋ ለማናር ዋነኛ ምክንያቶች ይሆናሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት ያጋጠመኝን ላካፍላችሁ። የበዓል ሰሞን ነው። ከዚያ አንድ ወዳጃችን ባለው አቅም በግ ለመግዛት ወደ አዲሱ ገበያ ይሄዳል። እዚያ ሲደርስ ሸማቹ እና ነጋዴው እየተተራመሰ ነው። ይህ ወዳጃችንም ዞር ዞር ብሎ የበግ ዋጋ መጠየቅ ይጀምራል። ከዚያ በአጋጣሚ አንድ ቦታ ላይ የሚፈልገው በግ ያገኛል።
ከዚያ ዋጋ ሲጠይቅ በወቅቱ ዋጋ 2500 ብር እንደሆነ ይነገረዋል። ከዚያ እሱ ዋጋ እንዲቀነስለት፤ ነጋዴው ደግሞ ብዙ ላለመውረድ ወደ ክርክር ይገባሉ። ከዚያ ከ2300 ብር በፍጹም እንደማይቀንስ እየተናገረ እያለ፤ ከነሱ አቅራቢያ አንድ የመንግስት ታርጋ የለጠፈ መኪና ይቆማል። ከዚያ ነጋዴው ከዚህ ቀደምም ያውቃቸው ኖሮ ፈጠን ብሎ ወደነሱ ይሄዳል። ከዚያ ቀደም ብሎ በጉን ለመግዛት ተቃርቦ የነበረው ወዳጃችን ነጋዴውን እንዲሸጥለት ቢጠይቀውም፤ ፊት ነስቶት በቀጥታ ከአዲሶቹ ደንበኞች ጋር ማውራቱን ይቀጥላል፡፡
ከዚያ አዲሶቹ ሸማቾች በአጋጣሚ ወዳጄ ሊገዛ የነበረውን በግ ይዘው ዋጋ ይጠይቃሉ። ከዚያ ነጋዴው ያለምንም ይሉኝታ ሶስት ሺህ ብር ነው ሲል ይመልስላቸዋል። ከዚያ እነሱ አንተ በቃ ሁሌም ዋጋህ አይቀመስም በሚል ከቀለዱ በኋላ ሁለተኛ እንኳ ለመጠየቅ ሳይፈልጉ በል መኪናው ላይ ጫነው በሚል ትዕዛዝ ይሰጣሉ። ከዚያ ወዳጄ እያየ ሊገዛው የነበረውን በግ ተቀማ። ከዚያ ጥቂት ቆይቶ ሁኔታው ሲጣራ በአንድ ክፍለከተማ የሚሰሩ ኃላፊዎች እንደሆኑ ተገነዘበ።
በእርግጥ እነዚህ ሰዎች ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል የተለየ ገቢ የሚያገኙ አይደለም። ነገር ግን እነሱ ምናልባት በህገወጥ መንገድ የሚያገኙት ገቢ ሊኖር እንደሚችል አሰበ። ይህንን ለማለት ያደረሰው ደግሞ ሰዎቹ ቋሚ ደንበኞች መሆናቸውና በዚህ መልኩ ሁሉም በተጠየቁት ዋጋ የሚገዙ መሆናቸው ነው፡፡
ቅድም ወዳነሳሁት የዘይት ጉዳይ ልመልሳችሁ። አንዳንዶቹ ሶሞኑን የዘይት ዋጋ መናር በተለይ የምርት ማነስ፤ በሩስያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የጥሬ እቃ መወደድ ወዘተ በሚል ያነሳሉ። እንዲህ አይነት ምክንያቶች ግን ጤናማና የሚጠበቁ ናቸው። ውጤታቸው በሂደት የሚያጋጥም እንጂ በድንገት ከላይ ዱብ የሚል አይደለም። እናም ዋናው ምክንያት ሰው ሰራሽ ለመሆኑ ምስክር የሚሻ አይደለም፡፡
የእኛ አገር የንግድ ስርዓት ብዙ ችግሮች ውስጥ የሚያልፍ ነው። አጋጣው ደግሞ ዋነኛ አምራቹም ሆነ ተጠቃሚው የሚጎዱበት ነው። ለምሳሌ የሙዝ ምርትን ስንመለከት አርሶ አደሩ ከስድስት ብር እስከ አስር ብር እየሸጠ ተጠቃሚው የሚገዛው ደግሞ ከ35 እስከ አርባ ብር የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ከቁጥር አንጻር ስንመለከት አብዛኛው አምራች እና ተጠቃሚ ነው። ነገር ግን የዋጋ ንረቱን በማባባስ ሂደቱ ላይ ያሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል መንግስት ህብረተረሰቡ እንዳይጎዳ ከውጭ በሚገቡ የሸቀጥ ምርቶች ላይ ቀረጥ ቢያነሳም ይህ ግን ለውጥ አላመጣም። ይህ ደግሞ መንግስትም የሚገባውን እንዳያገኝ፤ ሸማቹም በአግባቡ ገዝቶ እንዳይጠቀም የሚያደርግ በመሆኑ በዚህ አካባቢ ያለውን ችግር ከመሰረቱ አይቶ ትክክለኛ መፍትሄ መስጠት ይገባል፡፡
በተለይ መንግስት አንዳንድ ጊዜ ዋጋ ሲንር በመሃል ጣልቃ እየገባ የጥቂት ነጋዴዎችን ሱቅ ብቻ በማሸግ ውጤት አመጣለሁ ብሎ ማሰብ የለበትም። የችግሩን ፈጣሪዎች በአግባቡ አጥንቶ የሚያስተምር ተገቢውን ቅጣት ካልሰጠ አገር የማተራመስ ሃይል ስላለው ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ከሁሉ በላይ አንድ የተለመደ ባህል ደግሞ አለ። ዋጋ አንዴ ከናረ በኋላ መልሶ ወደታች መውረዱ የሚታሰብ አይደለም። በዚህ የተነሳ ምክንያት እየፈጠሩ ዋጋ ማናር ከተቻለ ከዚያ በኋላ የሚያወርደው አለመኖሩን የተገነዘቡ ጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች እንዲህ ገበያውን ሲያተራምሱ ዝም ብሎ ማየት እና ለጥቂት ጊዜ ብቻ እቃ በማቅረብ ዋጋን ለማረጋጋት ከመሞከር ይልቅ መፍትሄው ዘላቂ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል። ምክንያቱም ይህ ከሽብርተኝነት ተለይቶ የማይታይ አገርን የማተራመስ ተግባር ነው።
ውቤ ከልደታ
አዲስ ዘመን መጋቢት 22 /2014