ምድር የሰውን ልጅ ጨምሮ አያሌ የተፈጥሮ ፀጋዎችን አድላናለች። ሰው ደግሞ ከሁሉም ፍጥረታት ልቆ ይህን እድል ይጠቀማል። ምድራችን ከአደለችን ገፀ በረከቶች ውስጥ ዋነኛው በገፀ ምድርና ከርሰ ምድር ውስጥ የሚገኙ ዕንቁ ማዕድናት ይገኙበታል።
በዓለም ላይ በለፀጉ የሚባሉት አገራትም ይህን የተፈጥሮ ፀጋ በአግባቡ በመለየትና ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መለወጥ የቻሉ ናቸው። ታዲያ ረቂቅና በቀላሉ መለየት የማይቻሉ፤ ቢለዩ እንኳን በሚፈለገው መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚቸግሩ ማዕድናት በምድራችን ላይ እልፍ ናቸው።
ምንም እንኳን አስቸጋሪ ሂደት ማለፍን ቢጠይቁም ምስጋና ለሰው ልጅ እውቀትና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሁሉም ነገር ከትሪ ላይ እንጀራ ቆርሶ የመብላት ያህል እየቀለለ መጥቷል።
አህጉረ አፍሪካ በምድራችን ላይ የበለፀጉ ማዕድናትን ከታደሉት ውስጥ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። ይሁን እንጂ በጦርነት፣ በቅኝ ግዛት፣ በኢኮኖሚ ጫናና አያሌ ምክንያቶች እንደሌሎቹ ዓለማት ይህን ሃብት ለብልፅግና መንደርደሪያ ከመጠቀም ይልቅ እርግማን ሆኖባት ዘመን ከዘመን እያለፈ እዚህ ደርሰናል።
በዋናነት ግን ሳይንሳዊ እውቀትን ተከትሎ ማዕድናትን አለማበልፀግና ለዚያ የሚሆን የቴክኖሎጂ ውጤት የመፍጠር አቅም ውስንነት ዘርፉ እንዳያድግና የእድገት መወጣጫ መሰላል እንዳይሆን ማነቆ ሆኖ ይታያል። በበለፀጉ ማዕድናት ክምችት በሚታወቀው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምትገኘው ኢትዮጵያም ይህን ችግር ከሚጋሩት መካከል ትገኝበታለች። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ላለፉት ዘመናት ሳይንሳዊ እውቀትንና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የማዕድን ዘርፉን ለማልማት የሚደረገው ጥረት በእጅጉ ውስን ነው።
ከዚያ ይልቅ የምዕራባውያን የሚዘውሯቸው ታላላቅ የማዕድን ካምፓኒዎች የቴክኖሎጂና እውቀት አቅማቸውን ከድልብ ኢኮኖሚያዊ ጡንቻ ጋር ደምረው የአንበሳውን ድርሻ ሲወስዱ ተመልክተናል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ቴክኖሎጂን ዘመኑ የፈቀደውን ሳይንሳዊ ጥናትና የመረጃ አሰባሰብ ዘዴን ተጠቅሞ በራስ አቅም ማዕድናትን ማልማት አልተለመደም። ከዚያ ይልቅ በባህላዊና ኋላ ቀር መንገድ ለሺህ ዘመናት አመርቂ ያልሆነ መንገዶች ግን ነበሩ።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት አሁን አሁን የነዳጅና ጋዝ ሃብትን ጨምሮ አያሌ ማዕድናትን ጥቅም ላይ ለማዋል መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ለዘርፉ ጠቀሜታ የሚሰጡ ቴክኖሎጂዎችን በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ እንዲለሙ ድጋፍ እየተደረጉ መሆኑን መመልከት ይቻላል። ከዚያ በላይ በኢትዮጵያ እምቅ ማዕድን የሚገኙባቸውን ስፍራዎች በሳይንሳዊ መንገድ ለመለየት የሚደረገው ጅምር ጥረትም ይህንኑ ነው የሚያመለክተው።
ኢትዮጵያ ማዕድኖቿን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ መንገድ ለማልማት የምታደርገውን ጥረት የሚደግፉ ተስፋዎች እየተመለከትን ነው፤ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን ደግሞ ከሰሞኑ በወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች የወርቅ ማዕድንን ለማጥለልና ለመለየት የሚያስችል ማሽን በግል ጥረት መሠራቱ ነው።
ስለዚህ ጉዳይ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሲናገሩ፤ የትኛውም ቴክኖሎጂ በጥልቀት የማሰብና ያሰቡትንም የመተግበር ውጤት ነው፤አገራችንም እንዲህ አይነት ቴክኖሎጂን መረዳት የሚችል ድንቅ አዕምሮ ያላቸው ወጣቶች አሏት።
በቡራዩ ከተማ የሚገኙ አራት ወጣቶች የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ሠርተዋል። ማሽኑ በቀን ብዙ ቶን አፈርን ማጠብ የሚችል ነው:: ወጣቶቹ የሠሩት በዓለም ገበያ 200 ሺህ ዶላር ዋጋ ያለውን የወርቅ ማጠቢያ ማሽን የሚተካ ማሽን ሲሆን በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት ላይ ለማዋልም ውጤታማነቱ ተረጋግጧል።
ከነዚህ ወጣቶች በማዕድን ዘርፍ የጎደሉንን የሚሞሉ ፣ አገራችንን ከውጪ ምንዛሪ የሚያድኑ ብዙ ፈጠራዎች ይጠበቃሉ። የእነዚህ ወጣቶች ስኬት ጥቅሙ የአገር ነውና ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋል በማለት ነበር። ይህንን የፈጠራ ውጤት ለዛሬ ርዕሰ ጉዳያችን እንደማሳያ አነሳነው እንጂ መንግሥት ለዘርፉ ከሰጠው ትኩረት አኳያ በርካታ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች በራስ አቅም እየበለፀጉ መሆኑን መገንዘብ እንችላለን።
በተለይ ሳይንሳዊ ምርምር ከማድረግና ዘርፉን በእውቀት ለመምራት የሚደረጉ ጥረቶችም የዚሁ ጥረት አካል ናቸው። ይህንን ጉዳይም በተመለከተ ሚኒስትሩ ሲናገሩ “ኢትዮጵያ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ተሳትፎዋ ከፍ እንዲል ካሰብን አሉን የምንላቸው ሀብቶቻችን በጥናት የተረጋገጠ ዓለም አቀፍ እውቅና ያስፈልጋቸዋል ፡፡
ያለንን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ መጠንን የሚያሳውቅ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ግምገማን የሚያሳይ ጥናት እንዲደረግ ስምምነቶችን አድርገናል” ብለዋል። ይህ የሚያመላክተው አገሪቱ ከማዕድን ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን ሳይንስና ቴክኖሎጂ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ነው።
ዘርፉን ለማሳደግ መንግሥት ተመራጭ ያደረገውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ አማራጭ በዚህ መልኩ ከተመለከትን በቀጣይ ደግሞ የዓለምን ማዕድን ዘርፍ የላቀ ውጤት ላይ እንዲደርሱ ስላስቻሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በዝርዝር ለመመልከት እንሞክራለን።
ከነዚህ ሳይንሳዊ ምርምሮች፣ ዲጂታልና የፈጠራ ውጤቶችና ቴክኖሎጂዎች አንፃር ኢትዮጵያውያን የፈጠራ ባለሙያዎች ምን መሥራት እንደሚኖርባቸውም ለመጠቆም እንወዳለን። የማዕድን ሚኒስትሩ እንዳሉት ዓለም አቀፋዊ እውቅና ያላቸው ቴክኖሎጂዎችን ከማላመድና ወደ ዘርፉ ከማምጣት ባሻገር በአገር በቀል የፈጠራ ውጤቶችን እንዴት ማበልፀግ እንደሚኖርብን ጠቋሚ መረጃ ይሆናል የሚል እምነት አለን።
የማዕድን ቴክኖሎጂ አብዮት
ዓለማችን ላይ እያየለ የመጣውን ከምድር ሃብት የመጠቀም ፍላጎት “የማዕድን ቴክኖሎጂ” አሁን ላይ በበቂ ሁኔታ እየመለሰው ይመስላል። በተለይ ዲጂታል ቴክኖሎጂው ቀጣይነት ያለው፣ ምርታማነትን ያረጋገጠ፣ ለመለየት ቀላልና ጥቅም ላይ በሚፈለገው መጠንና ዓይነት እንዲውል የሚያስችል ሀብት እንዲኖር ቴክኖሎጂ ግዙፉን ድርሻ እየወሰደ ይገኛል።
ከዚህ መካከል የመጀመሪያው ተደርጎ የሚጠቀሰው “የጂስፓሻል ቴክኖሎጂ” የእርቀት ምልከታን፣ ቦታንና የመሬት አቀማመጥ ላይ ልዩ ልዩ ሳይንሳዊ መረጃዎችን በመስጠት ለማዕድን ዘርፉ እድገት የበኩሉን ድርሻ ከሚወጣ የቴክኖሎጂ አይነት ውስጥ የሚመደብ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ሆነ ዓለማችን ላይ ማዕድኖች ይገኛሉ ተብሎ በሚታሰብበት ስፍራ በአጠቃላይ ይህ ቴክኖሎጂ ተመራጭ ነው። በሙያውና ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ረገድ በቂ ባለሙያ አለ ተብሎ ባይታሰብም በአገሪቱ መሰል ሲስተምንና እውቀትን ተግባር ላይ በማዋል የማዕድን ዘርፍ እድገትን ለማረጋገጥ እየተሠራ እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም ዘመኑ በሚፈቅደው በዚህ መሰል ቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ እውቀት የተፈጥሮ ማዕድናትን ለመለየት መሠራት ቢችል የላቀ ውጤታማነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ይታመናል። ጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂ የመሬት ክፍለ አካልን በሶስት አቅጣጫ አሊያም “Three-dimensional (3D)” በማመላከት ውጤታማ ግኝትና ምልከታ እንዲኖር ያደርጋል። ለሰው አዕምሮም ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮችን ለማቅለል ተመራጭ ነው። ሌላው በ “Virtual Reality (VR)” ምስሎችን ቦታው ላይ እንዳሉ በማስመሰል አዳዲስ የማዕድን ምርት ዘዴን ለመቀየስ ያስችላል። ይህ በተለይ ማዕድኑ ቦታ ላይ መገኘትን ሳይጠይቅ ቅድመ እቅድ ለመንደፍ አይነተኛ ተመራጭ ነው።
ታዲያ ይህንን ቴክኖሎጂ ማላመድና ለኢትዮጵያ ባለሙያዎች በሚመች መልኩ መሥራት ከተቻለ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና በራስ አቅም የማዕድን ልማትን ለማቀላጠፍ በእጅጉ ይጠቅማል። ከጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂ ሌላ የመልክዓምድር መረጃ ዘዴ “Geographic information systems” ሌላው በማዕድን ዘርፉ ላይ አሻራቸውን እያሳረፉ ከሚገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል አንዱ ነው። ይህ ጂአይ ኤስ የምንለው ቴክኖሎጂ የዘርፉ ባለሙያዎች በመሬት ሆድቃ ውስጥ የሚገኙ ማዕድናትን መገኛ፣እምቅ አቅምና የቀጣይነት ሁኔታ መለየት ስለሚችል ትልቁን ሥራ ያቃልላል።
ሌላው በማዕድን ዘርፉ ላይ ውጤታማ ተሞክሮ መሆኑ የሚነገርለት በኮምፒውተርና ሮቦቶች የሚታገዝ ሶፍትዌር አሊያም “Artificial intelligence” ኤ አይ የምንለው ሲሆን የዕለት ተዕለት ምርት ሂደትን በማቀላጠፍ፣ የሠራተኞችን አቅምና ቅልጥፍና በመጨመር እንዲሁም በየቀኑ በማዕድን ማውጣት ሂደት ላይ የሚኖሩትን መረጃዎች በመመዝገብ አሁን ላይ ተመራጭ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እንደሆኑ ይታመናል።
በዓለማችን ላይ ተዓምር በሚመስል መልኩ እያደገ የመጣውን የምድርን ሃብት የመጠቀም ሂደት ካዘመኑት ቴክኖሎጂዎች ተርታም የሚመደብ ነው።
ታዲያ ይህን መሰል ቴክኖሎጂ በቀላሉ ከሰለጠኑት አገራት ለማግኘት ከማዳገቱም በላይ እውን ማድረግ ቢቻል እንኳን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪና መዋዕለ ንዋይ የሚያስወጣ ይሆናል። ለዚህ ነው በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ላይ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል በማፍራት ይህን መሰል ቴክኖሎጂን በአገር ውስጥ በራስ አቅም ለማበልፀግ ጥረት መደረግ የሚኖርበት።
አሁን አሁን በማዕድን አምራች አገራት ውስጥ “ድሮን” አሊያም ትናንሽ ካሜራዎችንና የመረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያዎች የተገጠሙላቸው ድሮኖችን መጠቀም እየተለመደ መጥቷል። ይህ ቴክኖሎጂ ለአያሌ ዘርፎች እፎይታን የፈጠረ ሲሆን በማዕድን አውጪ ካምፓኒዎች ደግሞ በልዩ ሁኔታ ይፈለጋል። በዋናነትም አደገኛ የሆኑ ቦታዎች ላይ ሠራተኞችን ከማሰማራት እነዚህን መሰል ድሮኖች ጥቅም ላይ ይውላሉ።
በዚያም ምንም ጉዳት ሳይከሰት መረጃዎችን መሰብሰብ ያስችላል። በኢትዮጵያ ውስጥ ለተለያየ ግልጋሎት ሊውሉ የሚችሉ ድሮኖች ለማምረት በወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ሙከራ እንዳለ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ እምቅ አቅም ላለው የማዕድን ዘርፍ መሰል ሙከራዎች መደረጋቸውን የሚገልፅ መረጃዎች እስካሁን ድረስ አይስተዋልም።
መንግሥት ለማዕድን ቴክኖሎጂ ከሰጠው ትኩረት አንፃር ይህን የዘመኑን ቀላልና ቀልጣፋ ግልጋሎትን የሚሰጥ ቴክኖሎጂ በፈጠራ ባለሙያዎች እንዲሠራ ማበረታታት ይኖርበታል ብለን እናምናለን። ድምር ውጤቱም ኢትዮጵያን ተወዳዳሪና የማዕድን ሃብቷን በአግባቡ እንድትጠቀም የሚያስችላት ቀላል መንገድ መፍጠር ይሆናል። እንደ መውጫ
የማዕድን ሃብት ለአያሌ አገራት ጥቅምን ከመስጠቱ ባለፈ ለብዙዎቹ ደግሞ መርገምትን ይዞ የሚመጣና በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። በሌላ መልኩ ከዘርፉ በዘላቂነት ተጠቃሚ ለመሆን ቅድሚያ ከፍተኛ መዋዕለንዋይ ማፍሰስ፣ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት እንዲሁም ሳይንሳዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰሳን ማካሄድ የሚጠይቅ ነው።
በዚህ ምክንያት አገራት በዚህ ዘርፍ ላይ ደፍረው ለመግባትና እምቅ ሃብትን ለመጠቀም ሲያዳግታቸው ይታያል። አሁን አሁን ግን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት በቁርጠኝነት ዘርፉን ለማሳደግ በጥረት ላይ ይገኛሉ። አሁን የደረስንበት ዘመን ደግሞ ቀደም ካሉት አስቸጋሪ ጊዜያት በተለየ ጉልበትን ሳይሆን እውቀትን፤ እውቀትን ብቻ ሳይሆን ከዚያ የሚገኝ የፈጠራ ክህሎትን በማዳቀል ከባድ መስሎ የሚታይን ዘርፍ ፈጣን እድገት እንዲያሳይ ማድረግ የቻለ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥትም የማዕድን ዘርፉን ለማነቃቃት በቁርጠኝነት የተነሳበት ጊዜ በቴክኖሎጂና ጥልቅ ሳይንሳዊ ጥናት መታገዝ ያለበትን መስፈርት ያስቀመጠ በመሆኑ ከባህላዊው የምርትና ፍለጋ ሂደት በተለየ የወቅቱን የገበያ ሁኔታ ያማከለ እንዲሆን መሥራት ይጠበቅበታል።
ለዚህም ይመስላል ዘርፉን የሚመሩት ኢንጂነር ታከለ ኡማ “የማዕድን ምርታችን በመጠንና ጥራት አሳድገን ለዓለም ገበያ የምናቀርብበትና ለአገራችን የውጪ ምንዛሪ ማገር የምንሆንበት እንዲሁም ከውጭ የሚናስገባቸውን ምርቶችም በሂደት እየተካን የምንሄድበት ነው” በማለት ነው ቀጣይ ተስፋዎችን የሚያመላክት ሃሳብ ያነሱት።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 /2014