በአትሌቲክሱ ዓለም ረጅም ርቀት ውድድሮች የስፖርቱ ድምቀቶች ናቸው። በተለይም አምስትና አስር ሺ ሜትር ውድድሮች በዓለም ላይ ከፍተኛ ተቀባይነትን እያገኙ ለመጡ የማራቶን ውድድሮች መሰረት ናቸው። እንደ አጠቃላይ ለአትሌቲክስ ስፖርትም ቢሆን የጀርባ አጥንቶች ናቸው። በታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክም ቢሆን የረጅም ርቀት ውድድሮች የማይረሳ ታሪክ ያላቸውና ከስፖርት ቤተሰቡ ምናብ ወደ ፊትም ቢሆን የማይፋቁ ናቸው።
እአአ 2000 ሲድኒ ኦሊምፒክ ላይ ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴና ኬንያዊው ድንቅ አትሌት ፖል ቴርጋት በአስር ሺ ሜትር ቁጭ ብድግ የሚያደርግ ግሩም ፉክክር ማን ይረሳዋል? ይህን ከህሊና የማይፋቅ ውድድር ጨምሮ በርካታ የአምስትና አስር ሺ ሜትር ውድድሮች የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮና መገለጫዎች መሆናቸውን የሚክድ ይኖራል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። በእነዚህ ውድድሮች ላይ ምሥራቅ አፍሪካውያን ፍፁም የበላይነት እየጎላ መምጣቱም ለምዕራባውያን ምቾት እንዳልሰጣቸው ምልክቶች መታየት የጀመሩት ዛሬ አይደለም። ለዚህም ጠንክረው ሠርተው የበላይነት ከመያዝ ይልቅ በሴራ ለማመናቸው በርካታ ማሳያዎችን ማስቀመጥ ይቻላል።
እኛ ብቻ በሁሉም ነገር የበላይ እንሁን የሚል ክፉ አባዜ የተጠናወታቸው ምዕራባውያን በመጀመሪያ የአገር አቋራጭ ሩጫን ከኦሊምፒክ ድራሹ እንዲጠፋ አደረጉ። ቀጥሎም ቀስበቀስ የአስር ሺ ሜትር የመም(ትራክ) ውድድሮችን ከገበያ ጋር በማስተሳሰር ‹‹አዋጭ አይደሉም›› በሚል በዓመት አንድ ጊዜ እንኳን የሚካሄዱበትን መንገድ ጥርቅም አድርገው ዘጉ። በዚህም በርካታ የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች በለጋ ዕድሜያቸው ፊታቸውን ወደ ጎዳናና ማራቶን ውድድሮች አዙረው ሮጠው ሳይጠግቡ ከፉክክር ውጪ እንዲሆኑ አደረጉ።
የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች አስር ሺ ሜትርን እርግፍ አድርገው በጎዳና ውድድር በተጠመዱበትና በተዘናጉበት ወቅት ግን የቤት ሥራቸውን ውስጥ ለውስጥ ሠርተው በሞፋራህና በጋለን ሩፕ አማካኝነት ስንት የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮና ሜዳሊያዎችን እንደሰበሰቡ የምንዘነጋው አይደለም። የሞፋራህና ጋለን ሩፕ የጀግንነት ጀምበር እየጠለቀ ሲመጣም ችላ ብለውት የቆየውን አምስትና አስር ሺ ሜትር ከኦሊምፒክ የማስወጣት አጀንዳ ዳግም አራገቡት። ‹‹ውጣ አትበለው እንዲወጣ አድርገው›› እንደሚባለው አስር ሺ ሜትርን እንዳኮላሹት ሁሉ የቀራቸውን አምስት ሺ ሜትር ውድድርን ለመቅበር ከሰሞኑ ሌላ ስልት ይዘው ከች ብለዋል።
የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬ ሽኖች ማህበር (አይ.ኤኤ.ኤፍ) ባለፈው ማክሰኞ ኳታር ዶሃ ላይ አምስት ሺ ሜትር ውድድር ከ2020 ጀምሮ ከዳይመንድ ሊግ ፉክክሮች እንዲሰረዙ ወስኗል። ይህ ውሳኔ አምስት ሺ ሜትር የአስር ሺ ሜትር ዕጣ ፋንታ እንዲደርሰው የሚያደርግ በመሆኑ ከአፍሪካውያን የስፖርት ቤተሰቦች ተቃውሞና ወቀሳ እየቀረበበትም ይገኛል።
የኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬ ሽኖችን ጨምሮ ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ውሳኔውን ከተቃወሙት መካከል ይገኙበታል። ባለፉት ሁለት ቀናትም አንዳንድ የጃማይካ የቀድሞ አትሌቶች ድምፃቸውን ማሰማት ጀምረዋል። ይህ ውሳኔ አፍሪካ በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ተሰሚ የሆነ ወካይ እንደሌላት አሳይቶናል። ያም ቢሆን ረጅም ርቀት ውድድሮች የበለጠ አፍሪካውያንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በመሆኑ የአፍሪካ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ሲ ኤኤ)፤ የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ(አኖካ) ውሳኔውን ለማስቀየር አልረፈደባቸውም።
የአበበ ቢቂላ ታሪካዊ ድል የኢትዮ ጵያውያን ብቻ እንዳልሆነው ሁሉ ይህ ጉዳይ የምሥራቅ አፍሪካውያኑ ጎረቤታሞች ብቻ አይደለም። አፍሪካውያን በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ ሰንደቅ ዓላማቸው ከፍ ብሎ ሲውለበለብ፣ ብሔራዊ መዝሙራቸው በክብር ሲዘመር ማየት ከፈለጉ ይህን ውሳኔ ለማስቀየር በአንድ ላይ መቆም አለባቸው።
ረጅም ርቀት የአፍሪካውያን ታሪክ በወርቅ ቀለም የተፃፈበት ዛሬም ነገም መገለጫቸው ሆኖ የሚኖር ህልውናቸው ነው። እንደ ኃይሌ ሁሉ ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን አትሌቶች ድምፃቸውን ማሰማት ይኖርባቸዋል። በኬንያዊው ድንቅ አትሌት ፖል ቴርጋት የሚመራው የአፍሪካ አትሌቶች ኮሚሽንም እዚህ ጋር አቅሙን ማሳየት አለበት።
ምዕራባውያኑ እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ በራሳቸው ላይ እንዲደርስ ማድረግ አይደለም በኦሊምፒክ እንዲስፋፋና የበላይነታቸውን ይዘው እንዲዘልቁ ያገኙትን ዕድል ከመጠቀም ወደኋላ አይሉም። አሁንም በቀጣዩ የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ እንኳን የነሱ ፍላጎት ያለባቸው ወይም ሜዳሊያ ያስገኝልናል ብለው ያሰቡትን ማንኛውንም እንቅስቃሴ የኦሊምፒክ ስፖርት እንዲሆን እያደረጉ ነው።
በቀጣዩ ኦሊምፒክ ብሬክ ዳንስ ሳይቀር እንዲካተት አድርገዋል። አፍሪካውያንም ከምዕራባውያን ጋር በኦሊምፒክ ተፎካካሪ ሆነው ለመገኘት እንደ አገር አቋራጭ ሩጫ ዓይነት ውድድሮችን ከመጠቀም ባለፈ ረጅም ርቀቶች ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለማስቀረት በጋራ መጋፈጥ ግድ ይላቸዋል።
የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዚዳንትና የቀድሞ የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የኦሊምፒክ አሸናፊ እንግሊዛዊው ሴባስቲያን ኮ ወደ ስልጣን ሲመጡ እዚሁ አዲስ አበባ ላይ የረጅም ርቀት የቀድሞ ዝናና ስም ለመመለስ እንደሚሠሩ ቃል ቢገቡም አሁን ቃላቸውን አጥፈዋል። አፍሪካውያን በአንድነት ካሁኑ ካልታገሉም እንደ አገር አቀራጭ ውድድር ሁሉ አስርና አምስት ሺ ሜትር ውድድሮች በቅርቡ ከኦሊምፒክ ላለመሰረዛቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 /2011
ቦጋለ አበበ