ስፖርት በዘመናችን አንድን ማህበረሰብ ከማዝናናት ባለፈ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ መሆን ችሏል። በርካቶች በስፖርት አማካኝነት የራሳቸውን ህይወት ከመለወጥ አልፈው የአገራቸውንና የህዝባቸውን ኑሮ ማሻሻል ችለዋል። ከፍ ሲልም ስፖርት በዘመናችን የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመፍጠር በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አሻራ ማሳረፍ እየቻለ ነው። በተለይም እአአ ከ1920 ወዲህ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን በፍጥነት መስፋፋታቸውን ተከትሎ ስፖርት ባለሀብቶችንና የመንግሥታትን ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ እያገኘ መጥቷል። ይህም ዘርፉን እጅግ አስፈላጊ በማድረጉ የገቢ አቅሙ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲመነደግ አስችሎታል።
አንድን ዘርፍ ለማሳደግ በተለያዩ ማዕዘኖች ሳይንሳዊ ጥናቶችን ማካሄድ የግድ ነው። እነዚህን ጥናቶች ማካሄድ አንድን ዘርፍ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ከማስቻሉ ባሻገር የተለያዩ ችግሮችን ለይቶ ጠንካራ ጎኖችን ይዞ ለመቀጠል ያስችላል። ከዚህ ጎን ለጎን እንደ አገርና መንግሥት ያለውን ተቀባይነት ወይንም ትኩረት ለመጨመር ወሳኝ መሆኑ ማብራሪያ አያስፈልገውም።
ይህን በአግባቡ የተረዱ በርካታ ያደጉ አገራትና መንግሥታት በስፖርትና በኢኮኖሚ ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ የማይናቅ ቁጥር ያለው የማህበረሰብ ክፍላቸውን ህይወት ለውጠውበታል። በሥራ ፈጠራ እንዲሁም የአገርን ኢኮኖሚ ከመደገፍ አኳያ ስፖርት ለአንድ አገር ያለው ፋይዳ እንዲታወቅ በማድረግም በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ አሁን የደረሱበት የመጠቀ ደረጃ ላይ ሊቀመጡ ችለዋል።
እአአ 2014 ላይ በሰሜን አሜሪካ ስፖርት ከ60 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማመንጨት እንደቻለ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን በተያዘው 2019 ወደ 73 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ከፍ ሊል እንደሚችል ይገመታል። ለዚህም ዕድገት በስፖርቱ ዙሪያ ፕሮጀክቶች መስፋፋታቸው፣ ከመገናኛ ብዙሃን መብት ጋር በተያያዘ ስፖርቱ የሚያመነጨው ገቢ እየጨመረ መሄዱ ምክንያት ተደርጎ ተቀምጧል። ስፖርት ለአንድ አገርና መንግሥት ከውድድርነት ባለፈ ከግለሰቦች ህይወት አንስቶ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሚናው የጎላ ስለመሆኑ ከተለያዩ ጥናቶች ውጤት መረዳት ይቻላል።
እአአ 2010 ላይ ስፖርት በእንግሊዝ ኢኮኖሚ ውስጥ 20 ነጥብ 3 ቢሊየን ዩሮ ድርሻ እንደነበረው መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህም ከአገሪቱ ጠቅላላ ኢኮኖሚ 1 ነጥብ 9 በመቶ ይይዛል። ስፖርት በዚህች አገር ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር በሥራ ፈጠራ ረገድ ያለው ሚና የበለጠ ጉልህ እንደሆነም መረጃዎች ያትታሉ።
ስፖርትና ከስፖርት ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎች በእንግሊዝ ከአራት መቶ ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሙሉ ሰዓት ወይንም ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ይህም ከጠቅላላ የአገሪቱ የሥራ ዕድል 2 ነጥብ 3 በመቶ የሚይዝ ነው። በሌላ በኩል እንግሊዛውያን በስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ በመሆናቸው ጤናና ጤና ነክ ለሆኑ ጉዳዮች በዓመት የሚያወጡት 11 ነጥብ 2 ቢሊየን ዩሮ ከብክነት እንደሚድን በጥናት አረጋግጠውታል።
የሥራ አጥነት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በመጣባት ኢትዮጵያ የስፖርቱ ዘርፍ ከሥራ ዕድል ፈጠራና ከአገር ኢኮኖሚ ጋር ያለው ትስስር በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚጠቁም አንድም ጥናት የለም። በአጭሩ የአገራችን ስፖርትና የኢኮኖሚው ዘርፍ መልክ አልባ ናቸው። ስፖርት በአገራችን ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ሚናው ምን ያህል ነው? ስፖርት በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ያሳረፈው አሻራ በምን ይገለፃል? ለሚሉ ጥያቄዎች የዘርፉ ተቋማትም ይሁኑ ሌሎች መልስ የላቸውም።
እርግጥ ነው የአገራችን ስፖርት በራሱ ገና ዳዴ እያለ የሚገኝ ቢሆንም በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ የራሱን ሚና አይጫወትም ማለት አይቻልም። የስፖርቱ ዕድገት ራሱን የቻለ ጉዳይ በመሆኑ ከዚህ ጋር በተያያዘ የራሱ ጥናት ይደረግበታል። ከአገር ኢኮኖሚ ጋር ያለው ሰንሰለት ምን ያህል እንደሚዘልቅ ለመቃኘትም የግድ ስፖርቱ ማደግ አይጠበቅበትም። ከሃያ በላይ ብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማሕበራት ባላት አገር ከአንድና ሁለት ፌዴሬሽኖች በስተቀር ራሳቸውን ችለው የቆሙ ማግኘት አይቻልም። ያም ሆኖ ራሳቸውን ችለዋል በሚባሉት የአትሌቲክስና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች የሚንቀሳቀስ ኢኮኖሚ ቀላል አይደለም።
የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ዓመታዊ መደበኛ በጀቱ በዘንድሮው ዓመት ብቻ ከዘጠና ስድስት ሚሊየን ብር በላይ ነው። ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ያላነሰ ካፒታልም ያንቀሳቅሳል። ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖችም ከስምንት ሚሊየን ብር በላይ በየዓመቱ ድጋፍ ያደርጋል። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የአገሪቱ ስፖርት ከአገር ኢኮኖሚ ጋር ያለው ትስስርና የሚጫወተው ሚና ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ግን ጥናት አድርጎበት አያውቅም።
በአገራችን እግር ኳስ በፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች ብቻ በዓመት ከሃምሳ እስከ ሰማንያ ሚሊየን ብር የሚያንቀሳቅሱበት ደረጃ ደርሰዋል። ኢኮኖሚውን ከመደገፍ ይልቅ ብክነቱ ስለሚበዛ ለአገራችንና ለውጭ ተጫዋቾች ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ የሥራ ዕድል ተደርጎ ቢታለፍ ይሻላል።
በአትሌቲክሱ ግን የአገራችን አትሌቶች በዓለም አቀፍ መድረኮች ስኬታማ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አትሌቲክስ የሙያ ፈቃድ የሚጠይቅ ሙያ ባለመሆኑ ምን ያህል አትሌቶች እንዳሉን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲሳተፉ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በኩል አልፈው የመሆኑን ያህል በራሳቸው መንገድ ወደ ተለያዩ አገራት ሄደው የሚወዳደሩም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። በፌዴሬሽኑ በኩል የሚያልፉትም ቢሆኑ ቁጥራቸው ይህን ያህል ነው ብሎ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው። በኢትዮጵያ ከሺዎች የሚቆጠሩ አትሌቶች እንዳላት ይነገራል። ከእነዚህ አትሌቶች መካከል ምን ያህሎቹ ከአገር ወጥተው ውጤታማ ሆነው እንደሚመለሱ ማወቅ አይቻልም። ይሁን አንጅ እያንዳንዱ አትሌት ውጭ አገር ሄዶ በመወዳደሩ ብቻ ይብዛም ይነስም የውጭ ምንዛሬ ይዞ እንደሚመለስ ግልፅ ነው። ስለዚህ አትሌቲክሱ ብቻ ከውጭ ምንዛሬ አኳያ የሚያመነጨው አቅም ጥናት ቢደረግበት ከአገራችን ኢኮኖሚ ጋር ያለውን ትስስር ማወቅ ይቻላል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለማችን የተለያዩ ከተሞች እንደ አሸን በፈሉ የማራቶን ውድድሮች አትሌቶቻችን ሰፊ የውድድር ዕድል በማግኘታቸው በየሳምንቱ የሚያስመዘግቡት ውጤት እጅግ አስገራሚ ነው። በሌሎችም ውድድሮችም ቢሆን ክብረወሰኖችን በማሻሻል ጭምር ውጤታማ የሚሆኑ አትሌቶችን ቁጥር ጨምሯል። ከፍተኛ እውቅናና ስም ያላቸው የአገራችን አትሌቶች ብቻ «የኮቴ»፣ የክብረወሰንና ሌሎች ክፍያዎችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያገኙት ስንቶች እንደሆኑ ይታወቃል።
ለዚህም ህዝብና መንግሥት በደንብ የሚያውቃቸው አትሌቶች ብቻ በአገራችን የፈጠሩትን የተለያየ የሥራ ዕድልና እያስፋፉ ያለውን ኢንቨስትመንት መመልከት በቂ ነው። ስለዚህ በጥናት አልተደገፈም እንጂ አትሌቲክስ ለአገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ዘርፎች ከቀዳሚዎቹ ደረጃ ሊሰለፍ ይችል ይሆናል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፅህፈት ቤት ሐላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ አትሌቲክሱ ከአገር ኢኮኖሚና የውጭ ምንዛሬ ከማመንጨት አኳያ ያለው ተፅዕኖ ምን እንደሆነ ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት ጥናት እንዳልተካሄደ በማስታወስ፤ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶች ቢደረጉ ስፖርቱ የሚሰጠውን ትኩረት ለማሳደግ እንደሚረዳ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሲቋቋም በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ጥናትና ምርምር በማካሄድ ጠቃሚ ውጤቶችን ማሰራጨት ከዋና ዋና ዓላማዎቹ አንዱ ነው። አካዳሚው ከዓመት በፊት ሁለት አገራዊ ሜጋ ጥናቶችን እንደሚያስጠና አሳውቆ ነበር። አንደኛው በኢትዮጵያ ስፖርት አደረጃጀት ዙሪያ ሲሆን ሌላኛው በስፖርትና በአገራችን ኢኮኖሚ ትስስር ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው። ይህ ጥናት እስከአሁን አልተጠናቀቀም።
በዚህ ጥናት ዙሪያ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽንና አካዳሚው ‹‹እኔ ነኝ የሚመለከተኝ›› በሚል እሰጥ አገባ ውስጥ እንደገቡ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ሲናገሩ ይደመጣል። ይሁን እንጂ የአካዳሚው ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው ከእውነት የራቀ መሆኑን በመናገር አስተባብለዋል። የተጀመረው ጥናትም ሰፊ ከመሆኑና የጥናት ቡድኑም አገር ውስጥ ወጣ ገባ እያለ የሚሠራ በመሆኑ ሰፊ ጊዜ እንደሚፈጅ ገልጸውልናል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2011
ቦጋለ አበበ