ቀዳሚ መደላድል፤
ኢትዮጵያ የእምነትና የሃይማኖቶችን የኅብር ፀጋ የተጎናጸፈችና የቆነጀች ሀገር ስለመሆኗ ሕዝቧ፣ ታሪኳም ሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት የጸኑ ማረጋገጫዎቿና ምስክሮቿ ናቸው። ምስክርነት ደግሞ በሦስት ዋቢዎች ስለሚጸና ተጠራጥሮ በይግባኝ መሟገቱ እጅግም የሚያዋጣ አይሆንም።
እስታትስቲክሱም ቢሆን የሚያረጋግጥልን 99 ከመቶ ያህል ሕዝቧ በአንድም ሆነ በሌላ ሃይማኖቶች ውስጥ በቤተሰብነት መሰባሰቡን ነው። እውነታው ይህ ከሆነ ዘንዳ አልፎ አልፎ ከሀገራዊ ሁኔታዎች ጋር የሚገጥሙና የሚስማሙ አንዳንድ ጣፋጭና ወቅታዊ ዐውድ ገላጭ ታሪኮችን ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እየመረጡ ጣል ጣል ማድረጉ ርዕሰ ጉዳይን ለማጎልበት ይበጅ ካልሆነ በስተቀር ጉዳት አይኖረውም።
አዘውትሮ በአነታራኪ ፖለቲካዊ ሬቶሪኮች (ትርክቶችና መሟገቻዎች) ላይ ብቻ ከመቆዘም ይልቅ እንደነዚህ ዓይነቶቹን እምነት ነክ ታሪኮች በእምነት ለጸና ሕዝብ ማስታወሱ ለስሜትና ለመንፈስ መስከንና ተስፋን ለማለምለም ሊያግዝ እንደሚችል ይህ ጸሐፊ ያምናል።
ስለዚህም አንድ ብለን የምንጀምረው የዛሬው የቅዱስ መጽሐፍ ትረካ ለወቅታዊው የሀገራችን ሁኔታ ጥሩ ገላጭ ታሪክ ስለሆነ እንደሚከተለው እናስታውሳለን። በአይሁዶችና በክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ “መጽሐፈ አስቴር” በሚባል ርዕስ የሚታወቅ አንድ ድንቅ ታሪክ ይነበባል።
ይህ ታሪክ መንፈሳዊ ጠቃሚነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በዓለም ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ውስጥ ሳይቀር በሥነ ጽሑፍ ቅርጹና ይዘቱ በዘርፉ ተመራማሪዎችና አጥኚዎች ዘንድ ተወዶ ይመረመራል፤ እየጣመም ይተነተናል። በታሪኩ ውስጥ “የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ” ስም ተደጋግሞ ስለተጠቀሰም በተለይም ለእኛ ስሜት ይበልጥ ቅርበት ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል።
እነሆ የታሪኩ ጭምቅ፡- ታሪኩ እንደተፈጸመ የሚታመነው በጥንታዊቷ የፐርሽያ ንጉሥ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት (ቅድመ ልደተ ክርስቶስ 486 – 465) ሲሆን ዋነኛ የታሪኩ ማጠንጠኛም ከይሁዳ ምድር ተማርከው በሄዱ አይሁዳውያን ዙሪያ የሚያተኩር ነው።
ከምርኮኞቹ አይሁዳውያን መካከል መርዶክዮስና እንደ ልጁ ያሳደጋትና በኋላም የንጉሥ አርጤክስስ ሚስት የሆነችው ንግሥት አስቴር ዋናዎቹ የታሪኩ ተወዳጅ ገጸ ባህርያት (Protagonist characters) ናቸው። በአንጻሩ ንጉሥ አርጤክስስና ዋናው አማካሪው ሐማ የሁለቱ ተጻራሪ ገጸ ባህርያት (Antagonist characters) እንደሆኑ እናነባለን። ምርኮኛው መርዶክዮስ የንጉሡን ቤተ መንግሥት ከሚጠብቁት የክብር ዘቦች መካከል አንዱ ሲሆን፤ የንጉሡ ተቀዳሚ ባለሟል ደግሞ ሐማ ይባል ነበር። በፐርሺያዊያን ባህል መሠረት የተሾመበት ሥልጣን ግድ ስለሚል ሐማ ሲገባና ሲወጣ የክብር ዘቦቹ በሙሉ ተደፍተው እንዲሰግዱለት ሕጉ ያስገድዳቸው ነበር። ለመርዶክዮስ ግን ይህን ትዕዛዝ እንዲፈጽም የአይሁዳዊ እምነቱ ስለማይፈቅድለት ትዕዛዙን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልነበረም።
የመርዶክዮስን “ለፈጣሪ እንጂ ለፍጡር ያውም ለማራኪያችን አልሰግድም” ጽናትን ሐማ ከተረዳ በኋላ ንጉሡን አሳስቶ አንድ ክፉ አዋጅ በንጉሡ ስም ያሳውጃል። አዋጁ አይሁዳዊያን በሙሉ እየታደኑ እንዲጨፈጨፉና መርዶክዮስም ለሐማ ባለመስገዱ ለመቀጣጫ እንዲሆን ተሰቅሎ እንዲገደል ፈቃድ የሚሰጥ ነበር። የታሪኩ አንኳር ሃሳብ ይህ ቢሆንም የተደመደመው ግን በተወጠነው የጥፋት ትራጄዲ ተፈጻሚነት አልነበረም።
መርዶክዮስ በአንድ ወቅት በዘብ ሥራው ላይ እንዳለ ሁለት ባልደረቦቹ ንጉሡን ሊገድሉ ሲማከሩ ሰምቶ ሴራው ከንጉሡ ጆሮ እንዲደርስ በማድረጉ ሁለቱ አድመኞች እንዲገደሉና ታሪኩም በሀገሪቱ መዝገብ ላይ እንዲሰፍር ተደርጎ ነበር። በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት በታሪክ መዝገብ ላይ የሰፈረውን ያንን የመርዶክዮስ ውለታ ንጉሡ እንቅልፍ አምቢ ሲለው በሌሊት ተነስቶ በማንበቡና እስከዚያች ሰዓት ድረስ ምንም ውለታ እንዳልተከፈለው በመረዳቱ ለዚህ ለነፍሱ ታዳጊ በጎነት ለማድረግ ይወስናል።
በዚህም መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት በሐማ የተቀነባበረው የተሰወረ ሴራ ሊከሽፍ ግድ ሆኗል። በመሆኑም ለምስኪኖቹ አይሁዳዊያን የተደገሰው የጥፋት ሴራ ወደ ራሱ ወደ ሐማ ቤተሰብ ዞሮ ተገድለዋል፣ መርዶክዮስም የሐማን ሥልጣን ሊረከብ ችሏል። መርዶክዮስን ለማጥፋት ሐማ ባዘጋጀው መስቀያ ላይም የራሱ አንገት እንዲጠልቅ ተደርጎ ታሪኩ በዚህ ድንቅ ፍጻሜ ይጠናቀቃል። “ሥራን ለሠሪ እሾህን ለአጣሪ” እንዲሉ መሆኑ ነው።
ኢትዮጵያን ለማሰቀል የተጠነሰሰው የዘመናችን “የሐማዊያን ሴራ”፤
የነጻነት ታጋይ የነበረው ማልኮም ኤክስ (እ.ኤ.አ ከ1925 – 1965) አሜሪካንን በገለጸበት መሠረታዊ አባባል እንንደርደር። “አሜሪካንን የማያት በመከረኞች ዓይን ነው። አሜሪካ ህልሜ ይህ ነው ብላ የምትኩራራበት አንዳችም ርዕይ የላትም። በነጋ በጠባ ከድርጊቷ የሚስተዋለው፣ የቀን ቅዠቷና ትምክህቷ ጭምር ሌሎች ሀገራትን መግደልና ማዋረድ ነው።” ይህቺን አሜሪካ አንዳንዶች የሚጠሯት፡ – “The problem child of our planet” እያሉ ነው። “የዓለማችን ክፉና ሞገደኛ ልጅ” እንደማለት ነው። እርግጥ ነው ለመሪዎቿ እንጂ ለሕዝቧ ይህ ገለጻ ላይሰራ ይችላል።
ሕዝቧማ በዓለም ላይ በሚደርሱ መከራዎች ሁሉ ቀድሞ አለን በማለት ለእርዳታ ሲፈጥን ይታወቃል። የርህራሄ እጁን ዘርግቶ የተጎዱትን መታደግም ባህሉ ነው። ችግሩ ያለው ተንኮል ሳያውጠነጥኑ የማያድሩትና የበላይነት ሥልጣን ተጠናውቷቸው ጥፋትና ጦርነት ለመቀስቀስ ሲቃዡና ሰላማዊ ሀገራትን ለማፈራረስ ቀንና ሌሊት ሴራ ሲጎነጉኑ ውለው የሚያድሩት መሪዎቿና የሚያወጧቸው ፖሊሲዎች ናቸው። አሜሪካ በእብሪትና በሴራ ተለክፋ የለከፈቻቸው ሀገራት ቁጥር የትዬለሌ ነው።
ልክ እንደ ሐማ “ካልሰገዳችሁልኝ” በሚለው ትዕቢቷ ብዙ ሀገራትን አፈራርሳለች፣ ሕዝቦቻቸውንም ለከፋ መከራና ስደት ዳርጋለች። አንዲቱ ኮሪያ ሰሜንና ደቡብ በመባል ለሁለት ተከፍላ (እ.ኤ.አ ከ1950 ጀምሮ) የአንድ እናት ልጆች በጠላትነት እየተያዩ እንዲኖሩ የፈረደችው ይህቺው አሜሪካ ነች። ዶሚኒካ ሪፑብሊክን (1965)፣ ካምቦዲያን (1970)፣ ላኦስንና ቪዬትናምን (1971)፣ ግሪናዳን (1983)፣ ፓናማን (1989)፣ በጦርነት ለማንበርከክ ሞክራ ውርደት ተከናንባ ተሸንፋለች።
ኩባን ለማስገበር ሞክራ (1961) የእሳት አሎሎ ስለሆነችባት ዛሬም ድረስ ጥርስ እንደነከሰችባት አለች። ሶማሊያን (1993) ለመውረር ሞክራም በውርደት ተባርራ ወጥታለች። የኢራቅን ሕዝብ (ከ1991 ጀምሮ) ድሃ አደግ አድርጋ ፈርዳባቸዋለች። ሊቢያን አፈራርሳ ተሳልቃባታለች።
ሶሪያን (ከ2017 ጀምሮ) እርስ በእርስ እያባላች አጨብጭባለች። አፍጋኒስታንን በ2001 ወርራ አልሆነ ሲላት በዚሁ ዓመት ክብሯን አስጥላ ለአውሬዎች አስረክባት ወጥታለች። የሰሞኑ የሩሲያና የዩክሬን መከራ እንዲግለበለብና ሁለቱንም ሀገራት ረመጡ እንዲያቃጥላቸው ከጀርባ ሆና እሳቱን የምታጋግለው ይህቺው የዓለማችን የክፋት ምንጭ የሆነችው አሜሪካ ነች።
ዛሬ ዛሬ ደግሞ አይኗ በቅንዓትና በክፋት የቀላው በኢትዮጵያ ላይ ነው። ሰሞኑን የአሸባሪው ህወሓት ሞት “የእኔም ሞት ነው!” ብላ በመንፈራገጥ በሀገራችን ላይ የመከራ ዝናብ ለማዝነብ በሉዓላዊነታችን ላይ ክፉ ደመና እንዲያንዣብብ H.R 6600 እና S 3199 የሚሉ ስያሜዎች የተሰጣቸውን ሕጎች በማርቀቅ የሬት እንጀራ ካላጎረስኳችሁ እያለች በመፎከር ላይ ነች። H.R. 6600 ፌብሩዋሪ 4 2022 ተረቆ የቀረበው በሪፐብሊካኑ ቶም ማሊኖውስኪ ሲሆን የኋላ ደጀን ሆነው የሚገፉት ደግሞ የካሊፎርኒያዎቹ ኪሚ፣ ሚክስና ማክካውል የተባሉ የሕዝብ ተመራጭ ነን ባይ ግራ ገቦች ናቸው። ለዚህ የክፋት ማጠንጠኛ ረቂቅ ሕግ የሰጡት ምክንያት “በሰላምና በዲሞክራሲ የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለማየት” የሚል ነው።
የሕጉ ዝርዝር ይዘት ከኢትዮጵያም ተሻግሮ በእህት ሀገር ኤርትራም ላይ ያነጣጠረ መሆኑ የሴራውን የረቀቀ ስልት ጠቋሚ ነው። S 3199ም የተረቀቀው በዴሞክራቱ የኒው ጄርሲ ሴናተር ሮበርት ሜንዴዝ ሲሆን በይዘቱ ያው የኢትዮጵያ “ተንበርካኪነት ናፍቆት” የተገለጸበት ሰነድ ነው። ሕጎቹ በዋነኛነት በሉዓላዊነታችን ላይ ያነጣጠሩ ሆነው “የእርስ በእርስ ጦርነቱንና ግጭቶችን ለማስቆም፣ በጅምላ እየተፈጸሙ ያሉና ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጻረሩ ኢሰብአዊ የሆኑ ድርጊቶችን ለማስቆም፣ የጦር ወንጀለኝነትን ለመግታት፣ በሰብዓዊ ፍጡሮች ላይ የሚደረጉ እኩይ ተግባራትንና የጅምላ ግድያዎችን ለማስቆም ወዘተ.” የሚሰኙ በሴራ የወረዙ የሀሰት ትርክቶችን እንደመከራከሪያ በማቅረብ ነው።
እነዚህ የተዘረዘሩት ድርጊቶች በሙሉ በአሸባሪው ህወሓትና በመጋለቢያ ሰንጋ ፈረሶቹ መፈጸማቸው እየታወቀ ለወንጀለኞቹ ከሃዲያን ሽፋን ለመስጠት ታስቦ ኢትዮጵያን የኃጢያት ማስተሰርያ የመስዋዕት በግ አድርጎ ለማቅረብ መድከም “ሐማዊ ጭካኔ” ካልሆነ በስተቀር ምን የተለየ ስም ሊሰጠው ይችላል? ከግለሰብ ዜጎችና መሪዎቻችን በነፃነት የመንቀሳቀስ ማዕቀብ እስከ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ወታደራዊና በዓለማአቀፋዊ ትብብር ድጋፍ ጭምር ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እንድትሽመደመድ የተወጠነው “ሐማዊው ሴራ” ጉዳቱ ዞሮ ዞሮ ጠባሳውን አሳርፎ የሚያልፈው በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን የኋላ ኋላ የራሷን የአሜሪካንን አንገት በሸምቀቆ ውስጥ አስገብቶ በአደባባይ ለስቅላት እንደሚዳርጋት ጭምር የገባት አይመስልም።
የራሷን ቀብር አስፈጻሚ ያልናትም ስለዚሁ ነው። ይህ ሕግ እንደቋመጡት መጽደቁ ቢያጠራጥርም እንደ ቅዠታቸው ሆኖ እንተግብረው ቢባል እንኳን መዘዙ የአፍሪካን ቀንድ፣ በቀጣናውና በመላው የአፍሪካ አህጉር ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን የተቀሩትን የአውሮፓ ሀገራትንና ራሷንም አሜሪካንንም ጭምር ለብልቦ እንደሚፈጃት በብዙ ማሳያዎች ማመላከት ይቻላል።
ይህ ሕግ ካልጸደቀ እያሉ ዶላራቸውን ሆጨጭ በማድረግ “የገዳዮቻችንን ኪስ የሚያሳብጡት” የዘመናችን የአስቆሮቱ ይሁዳዎች የወጡትና የተገኙት ከዚህቺው ምስኪን ሀገር መሆኑ በራሱ ተወዳዳሪ የሌለው የዘመናችን የክህደት ጫፍ ተደርጎ ሊታይ የሚገባው ነው። እነርሱ ማክዶናልድ እየገመጡ በማግሳት መላው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በሀገር ቤት ያሉት የራሳቸው ትግራዋይ ቤተሰቦች ሳይቀሩ በዚህ ሕግ እንዲቀጡ ማስተባበራቸውና በየአደባባዩ እየጮኹ ማሽቃበጣቸው የክፋታቸው ጥግ ምን ያህል የከረፋ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
ዳሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ እንግዳ አይደለም። ብዙ የክፋት ቅንብሮች፣ ስውር ሴራዎችና ጦርነቶችን ተቋቁመን ዛሬን ዘልቀናል። ለነገውም ቢሆን የኢትዮጵያ አምላክ ፈራጃችንና ተሟጋቻችን እንደሆነ በጽኑ እናምናለን። ከውስጥ እያባሉን፣ ከውጭ ሊያሸማቅቁንና ሊያፈራርሱን መድከማቸው የኋላ ኋላ በዛሬውም ሆነ በነገው ትውልዳቸውና ታሪካቸው ላይ ጥሎ የሚያለፈውን ጠባሳ ቀድሞ ለመገመት ሰከን ብለው ለማጤን ያለማሰባቸው ለልባቸው ድንዳኔ ጥሩ ማሳያ ነው።
ከላይ ለመጠቃቀስ እንደተሞከረው አሜሪካ በበርካታ ሉዓላዊ ሀገራት ወጭት ውስጥ እጆቿን ነክራ ለመፈትፈት ሞክራ በአንዱም እንኳን እንዳልተሳካላት ከቀደምት ታሪኳ መረዳት ይቻላል። ዛሬም በኢትዮጵያ ላይ ዓይኗን አጉረጥርጣ በዲሞክራሲ ስም የበግ ቆዳ ለብሳ በተኩላዊ ባህርይዋ የስቃያችንን ጠረን ለማሽተትም ማቆብቆቧ ላይገርም ይችላል። በእኛ በኩል መልሳችን ግልጽ ነው።
ሽንፈት ቀለቧ የሆነው አሜሪካ እንደ ትናንቱ ዛሬም በአደባባይና በታሪክ ፊት “የራሷን ቀብር አስፈጽማ” መዋረዷ አይቀሬ ነው። የኢትዮጵያ እናቶችና አባቶች በዕለት ውሏቸው በየቤተ እምነቱ መሬት ላይ ተደፍተው ወደ ፈጣሪያቸው እየቃተቱ እንደሚውሉ አላወቁ ከሆነ ይወቁት። የእምነታቸው ጽናት እንደሚታደገንም ያዩታል። አሜሪካ አስተዋይ አማካሪዎች ያስፈልጓታል። ቀደም ሲል ወደ ጠቀስነው የቅዱስ መጽሐፍ ታሪክ እንመለስና መጨረሻው ያላማራቸው ጠቢባኑ የሐማ ጓደኞችና በስም የተጠቀሰችው ሚስቱ ዞሳራ የሰጡት ምክር እንዲህ የሚል ነበር፡- “ሐማ ሆይ! በፊቱ መውደቅ የጀመርክለትን ይህንን ንፁሕ ሰውና ሕዝብ ፈጽሞ ታግለህ አታሸንፈውም።
አንተ ትወድቃለህ እንጂ እርሱን አትጥለውም።” አሜሪካን ሆይ ሰማሽን!? ትናንት አፍጋኒስታንን ዛሬ ደግሞ ዩክሬንን አለሁላችሁ ስትይ ከርመሽ በጋለ ምድጃ ላይ ከጣድሻቸው በኋላ ክደሻቸዋል። ዛሬም ይህንን ክህደት በኢትዮጵያ ላይ ለመፈጸም የሌት እንቅልፍ፣ የቀን እረፍት አጥተሽ መወራጨቱን አቁሚ። ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲውንም ታውቅበታለች። በመላው ዓለም የተበተኑ ልጆቿም ለጊዜው በተለያዩ ጉዳዮች ቅር ቢሰኙም በሀገራቸው ሉዓላዊነት ጉዳይ ግን በሰይፍ ፊትም ቢሆን ተወራርደው እንደሚጨክኑ ታሪካቸውን ታውቂያለሽ።
የአንቺ የጠላትነት ድርጊት ሌሎች ወዳጆቻችንን አጠንክሮ ከጎናችን እንደሚያሰልፍም አይጠፋሽም። ከሁሉም በላይ ግን የኢትዮጵያ አምላክ ተፋራጃችን ብቻ ሳይሆን ተዋጊያችንም ጭምር ነው። ለእኛ ያቆምሽው የመሰቀያ ማማ ነገ በአንቺ አንገት ላይ እንደሚጠልቅ አስበሽ ከሐማዊ ድርጊትሽ ተቆጠቢ።
የረቀቀውን ሰይጣናዊ ሰነድም በአደባባይ ቀደሽ ጣይ!? ምክራችንም ተማጽኗችንም ይሄው ነው። ይህ የአንድ ዜጋ ድምጽ ሳይሆን የመቶ አስራ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ እምነት ነው። ጸሐፊውም ቢሆን አሜሪካንን የተማረባት፣ የሕዝቧቿን መልካምነት ያየበትና በጎ የተደረገለት ስለሆነ ለመካሪነትም ሆነ ለመገሰጽ የሞራል ብቃት አያንሰውም። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 /2014