አንድ ነገር መጥፎም ጥሩም የሚያደርገው ተጠቃሚው ነው። ኦሪት ዘፍጥረትን ስታነቡ «እግዚአብሔር የፈጠረውን በጎ እንደሆነ አየ» ይልና ሌላውን ፍጥረት ሲፈጥር ጥሩ ነው፣ ጥሩ ነው እያለ አልፎ ሰውን ሲፈጥር የዛሬውን አያድርገውና እጅግ በጣም ጥሩ አለ። ዛሬ መጥቶ ቢያይ ግን እጅግ በጣም መጥፎ የሚል ይመስለኛል። በእርግጥ እርሱ እንደኛ አይደለም ተሸካሚ ነውና አይልም። በእውነት በዚህ ዓለም ላይ መብትና ግዴታ መኖር አለበት እላለሁ። ምክንያቱም ቀሪ ንብረታችን ኢትዮጵያችን ናት። ኢትዮጵያችንን እናስብላት አናቁስላት፤ አናድማት፤ አናራቁታት!
አሁን የብሔር ብሔረሰቦች መብት የሚለውን እሰማለሁ። ለመንግሥት መጠቆም የምፈልገው ጫፏ ላይ «ግዴታ» የሚል ቢጨመርና «የብሔር ብሔረሰቦች መብትና ግዴታ» ቢባል መልካም ነው። ሁልጊዜ የምናገራት አንድ አባባል አለችኝ «ሰው ምንም መብት ከሌለው ባሪያ ነው፤ ምንም ግዴታ ከሌለው ደግሞ የአዕምሮ በሽተኛ ነው!» አሁን የአዕምሮ በሽተኛ ታውቃላችሁ ሠርግ የሚጠራው የለም። ለቅሶ ቀረህ ብሎ የሚወቅሰውም የለም። ምክንያቱም ግዴታ እንዳንለው ግዴታ የለበትም፤ ባሪያ እንዳንለው መብት የለበትም። እኛ ደግሞ የአዕምሮ በሽተኞችም አይደለንም፤ባሪያዎችም አይደለንም። ስለዚህ መብትና ግዴታ አለብን ብዬ አምናለሁ።
እንግዲህ በፌስቡካችን ምን እንደሚደረግ ከኔ በላይ እናንተ ታውቁታላችሁ። እኔ ተጠቃሚ አይደለሁም። ተጠቃሚ ያልሆንኩት አያስፈልገኝም ብዬ አይደለም። መብራት ስለሌለኝ ነው። እናም መብራት ያላችሁ ተጠቀሙበት። እኔ አውሮፓና አሜሪካ ስሔድ ፌስ ቡክ ከገንቢነቱ ይልቅ አፍራሽነቱ ነው የሚወራው።
አሁን ለፍቶና ደክሞ ያገኘ ሰውና ለፍቶና ደክሞ ያላገኘ ሰው የገንዘብ አወጣጡ እኩል አይደለም። ለፍቶ ያላገኘ ሰው ውስኪ ሊያወርድላችሁ ይችላል። እንደውም ውስኪ ቤት ሁሉ ሊከፍትላችሁ ይችላል። ግን ሳያስበው ነውና ያወጣው ነገ ተመልሶ ያለቅሳል። እናም መብትና ግዴታውን የሚያውቅ ትውልድ መፍጠር አለብን። ይቅርታን ብንሰብክ፤ ፍቅርን ብንሰብክ፤ ሕዝቡን ብናግባባው፤ ብናደማምጠው፤ እንደው ረሐቡ ሳያንሰው፤ ጥሙ ሳያንሰው፤ ብርዱ ሳያንሰው፤ ድህነቱ ሳያንሰው፤ የቤት ማጣቱ ሳያንሰው፤ ለዘይት ለስኳር ወረፋ መጠበቁ ሳያንሰው፤ እንደው እውነት ለመናገር ተግባብቶ እንኳን ስቆ እንዳያድር አደረግነው።
ድሮ ቆሎ ቆርጥሞ ቡና፣ ጠጥቶ ጨጓራው እየተላጠ እንኳን እፎይ ብሎ ይተኛ ነበር። ዛሬ ከአውሮፓ ከአሜሪካ የሚፈሱት መረጃዎች የቡና ስኒ የሚያሰብሩ ናቸው። ጀበና የሚያሰብሩ ናቸው። እናም በጣም ከባድ ሥራ እየተከናወነ ነው። የ3000 ዓመት ታሪካችን በሙሉ ገድለን የሚያስፎክሩ ናቸው።
አሁን ሬድዮና ቴሌቪዥን ተመልከቱ፣ በዓል ሲመጣ በተለይም እነዚህ የድልና የአሸናፊነት በዓላት ሲከበሩ ሁልጊዜ ምን ያህል እንደተገደለ ምን ያህል እንደቆሰለ እንለፍፋለን። እስኪ ደግሞ ምን ያህል እንዳቆሰልን መለፍለፉን አቁመን፤ ገድለን መፎከሩን አቁመን። ሁለተኛውን አማራጭ እንሞክረው። እስኪ ቆም ብለን ፍቅርን ሰብከን እንሞክረው፤ ይቅር ተባብለን እንሞክረው።
ባለፈው በየክልሉ ትንሽ ግጭት ነበር፤ ግጭቱን ከሰዎች ጭንቅላት አጥበው የሚጥሉ የሐይማኖት ሰዎች የታሉ? እውነቱን ለመናገር፤ ሕዝቡ ኪሱ እየተራቆተ፤ እየተራበ መኪና የገዛላቸው ካህናት፤ ጳጳሳት፤ ፓስተሮች፤ ኡላማዎች ምን ያደርጉለታል?
በአውሮፓ አንድ ጥያቄ እየተነሳ ነው ይባላል። ታውቃላችሁ ፈረንጆቹ የእምነት ተቋሞቻቸው ላይ ምን ስላደረጉልን ነው ገንዘብ የምናዋጣው? ምን ፈጠሩልን? የሞራል ዝቅጠት፤ የስነ ምግባር ዝቅጠት፤ ባዶነትን ነው ያተረፉልን። ታንቀን ብንሞት፣ በጭንቀት ብንታመስ ፣ራሳችንን ስናጠፋ አልደረሱልንም የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው። ስለዚህ አየሩን ተራራውን የሚቋቋም መኪና ከተገዛልን መቀሌ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ ቆላ ደጋውን እየወረድን በተለይም እንደየ እምነታችን መስበክ አለብን።
ስለዚህ ጥላቻውን ቆም አድርገን በተለይም ፌስቡክ እጃችሁ ላይ የወደቀባችሁ ሰዎች፤ ጠመንጃውን ያገኛችሁ ሰዎች የት እንደምትተኩሱ ብታውቁ ጥሩ ነው። አንዳንድ ጊዜ ራስ መጠበቂያ የሚሰጠው ራሱን ለሚጠብቅ ሰው ነው። ሰውን እየተኮሰ ለሚገድል የራስ መጠበቂያ አይሰጥም። እናም ፌስቡክን በትክክል መጠቀም ብንችል? ይቅርታ ብንሰብክበት፤ ብልፅግና ብንሰብክበት፤ ዕድገትን ብንሰብክበት መልካም ይሆንልናል።
ዛሬ አይደለም በፖለቲካው መስክ የእምነት ተቋማት ራሱ የጦር ሜዳ ሆኗል። ስንት እንባ ይፈሳል፤ ስንት ዋይታ ይሰማል። ይሄ እንባ ደግሞ ተጠራቅሞ… ተጠራቅሞ አገር ጎርፍ ሆኖ ይወስዳል። የደሐ እንባ ተጠራቅሞ ጎርፍ ይሆናል። የአክአብ መንግሥት የተገለበጠው በአንድ ናቡቴ ደም ነው። ሌላ ጥይት ተተኩሶ ቦንብ ፈንድቶበት አይደለም። ኃጢአት እየበዛ፤ ወንጀል እየበዛ፤ ግፍ እየበዛ፤ ጭካኔ እየበዛ፤ አረመኔነት እየበዛ በሔደ ቁጥር ሰዎች ባዷቸውን ይቀራሉ። ይሞታሉ፤ የተሾሙ ይሻራሉ፤ ያገኙ ያጣሉ፤ ጤነኞች ይታመማሉ።
እንደው ወገኖቼ በዚህ በፌስቡክ የተሰማራችሁ እንደው ሌላው የበሰለ ነገር ለመናገር አይደለም። እንደው አስበን ብንናገር ብንፅፍ፤ ታውቃላችሁ እኛ ሐገር ኔትወርክ ውድ ነው። የኛ አገር ሰው ምን ያህል ዋጋ ከፍሎ፣ ጊዜውን ሰውቶ፣ ገንዘቡን ከስክሶ እንደሚያነብላችሁ ማወቅ አለባችሁ። አንድ ቪድዮ ባዳመጠ ቁጥር ቴሌ ላፍ ያደርገዋል። ኪሱን ያራቁትበታል። ይሄን መስዋእትነት ከፍሎ ፤ ሻይ አልጠጣም ብሎ እናንተን እያዳመጠ ያለ ነውና ከሻይ የበለጠ ልብ የሚይዝ ነገር ስጡት፤ አዕምሮን የሚያሯቁት ነገር ባትፅፉለት እንደውም ምርጥ ፅሑፍ ካጣችሁ ዝም ብትሉ። እውነቴ ነው አንዳንድ ጊዜ የሚፃፍ ሲጠፋ እኮ ዝም ይባላል።
አንዳንድ ሰው ይገርማችኋል እጁ ላይ ስላለና መፃፍ ስለቻለ ብቻ የሚፅፍ ሰው ያጋጥመናል። እንደው በእግዚአብሔር ስም፤ በአላህ ስምም ካላችሁ በአላህ እንደው በሁሉም ስም በምታመልኩት አምላክ ስም ይሁንባችሁ ፌስቡክ እጃችሁ ላይ የወደቀ ሰዎች እዘኑለት።
እንደው እባካችሁ ገንቡን፤ አንጹን፤ አፋቅሩን፤ ደሙን አድርቁት፤ ጥላቻውን አድርቁት፤ ይቅርታ ይሰበክ፤ ፍቅር ይሰበክ፤ እንግባባ፤ እንደማመጥ፤ አንተላለቅ ማንም የለ ማንም ሊኖር አይችልም። በእውነት ምናልባት ዛሬ የምንነጋገራቸው ንግግሮች የዛሬ 10 እና 15 ዓመት እንደ ፀበል ይፈለጉ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
በቀደም አንድ ወንድማችን አንድ ነገር እየነገረኝ ነበር። አንድ ጭፈራ ቤት ገባን አለ፤ አንድ ጥናት ያደርጋልና ሊቀርፅ ነው። እዚያ ጭፈራ ውስጥ የሆነ አካባቢ ዘፈን እንዳይዘፈን ተባለ። በእውነት ቤቴ ገብቼ አለቀስኩ። ለምን ዘፈኑ ቀረ ብዬ አይደለም እንኳን ቀረ የቀረበት ምክንያት ግን ያሳስበኛል። የታገደበት ምክንያት ያሳስበኛል። ስለዚህ ወገኖቼ ይቅርታ… ይቅርታ… ይቅርታ… አስፈላጊ ነው።
ከድጃም ወለተማርያምም ከሳዑዲ አረቢያ ተባርረው መጥተዋል። እነ ከድጃ እስላም ስለሆኑ ሳዑዲ አረቢያ ይቅሩ አልተባለም። ቀሪ ንብረታችን ኢትዮጵያችን ናት። ለወልደማርያም ቀሪ ንብረቱ ኢትዮጵያችን ናት፤ ለመንግሥትም፤ ለደጋፊም፤ ለተቃዋሚም ኢትዮጵያችን ናት። ኢትዮጵያችንን እናስብላት አናቁስላት፤ አናድማት፤ አናራቁታት። መሬቷ ድንግል ነው አስተሳሰባችን ድንግል ነው። ግን መሬቱ ሲለማ እኛ ባዶ ሆነን መሬቱ የሚጠቀምበት አጥቷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011