የሰውነት አንዱ መገለጫም፤ መነሻና መድረሻውም አገር ነው። ሰው ያለ ሀገር፣ አገርም ያለ ሰው ምንም ናቸው። ይሄ በዓለም ላይ የተጻፈ የሰው ልጅ ሁሉ የጋራ እውነት ነው። ዓለም ከዚህ የሚበልጥ እውነት የላትም። ሁሉም የሰው ልጅ እውነቶች ከአገርና ህዝብ ቀጥለው የሚመጡ ናቸው። የአንድ አገር ሉዓላዊነት የሚለካው በሕዝቦቿ የአንድነትና የመተማመን መንፈስ ነው። ሕዝቦች በጋራ ጉዳያቸው ላይ አንድ አይነት ሀሳብና አመለካከትን ካላዳበሩ ጠንካራ አገርና ትውልድ መፍጠር አይቻላቸውም። ጠንካራ አገርና ህዝብ መፈጠሪያቸው ጠንካራ አንድነት ውስጥ ነው።
ጠንካራ አንድነት ደግሞ ዝም ብሎ አይመጣም። ጠንካራ አንድነት እንዲመጣ ሕዝቦች ልዩነቶቻቸውን በውይይት መፍታት ይጠበቅባቸዋል። ተነጋግሮ መግባባትን ልማድ ማድረግ ግድ ይላቸዋል። በጋራ ጉዳያቸው ላይ የጋራ ህልምና ራዕይ ሊኖራቸው ይገባል። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ የሚፈጠር ጠንካራ አገር አይኖርም። የምዕራባውያንን የሥልጣኔ ታሪክ መነሻው አንድ አገርና ህዝብ ነው። ዛሬ ላይ ከራሳቸው አልፈው በሁሉ ነገራቸው ተጽዕኗቸውን እያሳረፉ ያሉ አገራት ይሄን የሀይል ክንድ ያገኙት ተባብሮ በመስራት፣ ተባብሮ በማሰብ፣ ተባብሮ በመቆም ነው።
ሁሉም መንግሥት፣ ሁሉም ዜጋ ከአገሩ የሚጠብቀው ነገር አለ። ግን ደግሞ የትኛውም ግለሰባዊ ፍላጎት ከአገርና ሕዝብ አይበልጥም። አሁን ላይ አገር ለመፍጠር በምንሮጠው ሩጫ ያልተረዳነው አንድ ነገር ቢኖር ይሄ ነው እላለሁ። የምንሮጠው ከፍላጎቶቻችን ጋር ነው። ሁሉ ነገራችንን ለአገራችን ሰጥተን በታማኝነት ስንታገል አንታይም። አገር ትቅደም እኔ ልከተል ስንል አንደመጥም። የዜጎች ግለሰባዊ ፍላጎቶች ከአገር መፈጠር በኋላ የሚፈጠሩ ናቸው።
አገር ሳንፈጥር፣ ተነጋግረን ሳንግባባ የምንፈጥረው ግለሰባዊ ፍላጎት የለም። አሁን ላይ ችግር እየሆነ ያለው ከአገር በፊት ፍላጎቶቻችንን ማስቀደማችን ነው። ያለፉትን ዓመታት የጦርነትና የመገፋፋት ታሪኮች መለስ ብለን ብናይ በፍላጎቶቻችን በኩል የመጡ ሆነው እናገኛቸዋለን። ከአገር ፍላጎት ሲቀድም አደጋ አለው። ከፍላጎት አገር ሲቀድም ግን ጥያቄዎቻችን መልሶቻችን የሚያገኙበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። አሁን ላይ አገራችን ባላት አቅም፣ ባላት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ምህዳር የእያንዳንዳችንን ፍላጎት የመመለስ አቅም የላትም። መጀመሪያ ተነጋግረን እንግባባ።
በአንድ ሀሳብ አንድ አገር መፍጠርን እንልመድ። ከዛ ሁሉም ነገር በራሱ ጊዜ መስተካከል ይጀምራል። ምክንያቱም የዛኔ አገራችን የእያንዳንዳችንን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ ችግሮቻችንን የመፍታት አቅም ታዳብራለች። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ ከጥያቄ በቀር መልስ የምናገኝበት ሁኔታ አይፈጠርም።
አገር ለመፍጠር የምንሄድባቸውን ያልተገቡ አካሄዶች ማስተካከል ይኖርብናል። ለስሜቶቻችን ቅድሚያ ሰጥተን፣ ለፍላጎቶቻችን ተገዢ ሆነን፣ ተነጋግሮ መግባባት ሳንለምድ የምናጣው እንጂ የምናገኘው ትርፍ አይኖርም። የአገር ጉዳይ ሁሌም ከፊት ነው። ከየትኛውም የግል ጉዳያችን ጋር ሊስተካከል አይገባም። ከፍ ብዬ እንዳልኳችሁ በኢኮኖሚያቸውና በሥልጣኔአቸው ከፊት የቀደሙ አገራት ለልዕልና ያበቃቸው አንድ ሚስጢር ቢኖር ለጋራ ጥቅም በጋራ መስራታቸው ነው።
እኛም በጋራ በማሰብ፣ በጋራ በመስራት ያጣናቸውን መልካም እድሎቻችንን መመለስ እንችላለን ባይ ነኝ። ብዙ ጥያቄዎች አሉን፣ እንዲስተካከሉ የምንፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ እነዚህ ጥያቄዎች፣ እነዚህ ፍላጎቶቻችን መልስ የሚያገኙት የጋራ የሆነ ህልምና ሀሳብ ሲኖረን ነው። ፍላጎቶቻችንን ወደ ጎን ብለን ጠንካራ አገርና ሕዝብ መፍጠሩ ላይ ብንበረታ ኖሮ ዛሬ ላይ እነዚያ ሁሉ ጥያቄዎቻችን ባልኖሩ ነበር እላለው። ከእኔነት ወጥተን ከሁሉ በፊት ለአገርና ሕዝብ ብንለፋ አገራችን ለእኛ ፍላጎት መልስ ታጣለች ብዬ አላስብም። አብዛኞቹ የዓለም አገራት ታሪኮቻቸውን የገነቡት ከፍላጎታቸው ቀጥለው ነው። አብዛኞቹ የዓለም ስልጡን አገራት ሕዝባቸውን አርነት ያወጡት ፍላጎታቸውንን ችላ ብለው ነው። አገር ጠንካራ መሰረት ላይ እንድትቆም ሕዝቦች ልዩነታቸውን፣ ፍላጎታቸውን፣
ጥያቄዎቻቸውን ለአፍታም ቢሆን መግደል ይኖርባቸዋል እላለው። የፍላጎት ጉዳይ የእኛን አገር አሁናዊ ሁኔታ በደንብ ይገልጸዋል ብዬ አስባለው። ከትላንት እስከዛሬ በዚህ እውነት ውስጥ የተጓዝን ነን። አገር ከመፍጠር ይልቅ ራሳችንን ለመፍጠር የምንታትር ነን። ከአገር የቀደመ እንጂ ከአገር የቀጠለ ምንም ነገር ሳይኖረን እስካሁን ከርመናል። ግለሰባዊና ቡድናዊ ፍላጎቶች ከአገር ፍላጎቶች በላይ ዋጋ ያላቸው ቢሆኑ ኖሮ ከየትኛውም አገርና ሕዝብ በላይ እኛ ነበር የምንጠቀመው። አሁን ላይ እየተገበርናቸው ያሉት ነገሮች ዘመናዊው ዓለም ጥቅም የላቸውም ብሎ የተዋቸውን ነገሮች ነው። ለምሳሌ ብናይ ፍላጎቶቻችንን በተገቢው መንገድ የማቅረብና የማስረዳት ልምድ አላዳበርንም። በየትኛውም አገራዊም ሆነ ግለሰባዊ ጉዳዮች ላይ ተነጋግሮ መግባባትን አለመድንም። ለምንም ነገር ዘልማድን ከመጠቀም ባለፈ በጥናት የተደገፉና ሳይንሳዊ የሆኑ የመረጃ ምንጮች ስንጠቀም አንታይም። እየተጎዳንባቸው ያሉ ነገሮች መግባባት ብንችል በቀላሉ ልናሸንፋቸው የምንችላቸው ነገሮች እንደሆኑ ገና አልደረስንበትም።
ሀይልና ጉልበት የሰላም ምንጭ የሚመስለን አለን። ታሪክ ከመስራት ይልቅ ታሪክ በማውራት የተጠመድን ነን። በነዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች እንደ አገር መድረስ ካለብን ሳንደርስ እየተፍገመገምን የቆምን ነን። አሁን ሁላችንም ወደራሳችን ማየት ትተን ወደ አገራችንና ወደ ህዝባችን ማየት ይኖርብናል። ከፍላጎቶቻችን የሚቀድሙ በርካታ አገራዊ ጉዳዮች አሉ። ለነዛ የጋራ ጉዳዮቻችን ቅድሚያ በመስጠት መንቀሳቀስ ነው የሚያዋጣን። የለያዩንን ነገሮች በባህላዊና በሳይንሳዊ መንገድ እየፈተሽን ከፍላጎቶቻችን በላይ የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር ይጠበቅብናል። እስከዛሬ ተንገዳግደናል። ከፍላጎታችን ቀጥለን አገር ለመፍጠር ሮጠን ኋላ ቀርተናል። አገር የነፍስ ቦታ ናት።
ሀገር የስሜት፣ የፍላጎት፣ የህልሞች ሁሉ ቀዳሚ ናት። ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ እየሰጠን መጓዝ እንጂ በተፋለሰ ቅደም ተከተል የምንፈጥረው የጋራ ህልም የለም። ቀዳሚ ጉዳያችን አገር ናት፣ ቀዳሚ ጉዳያችን ሕዝብ ነው። አገርና ሕዝብ በኔና በእናንተ የጋራ ጥረት ጸንተው ሲቆሙ ያኔ እኛ ለአገራችን እንደለፋን አገራችን ለእኛ መልፋት ትጀምራለች። መጀመሪያ ለአገራችን እንልፋ፤ ከዛ አገራችን ለእኛ ትለፋለች። ለእኛ በመልፋት፣ ለእኛ በመድከም የምንፈጥረው አገርና ትውልድ የለም። ብሄራዊ ምክክሩ አገር በመፍጠር ረገድ የጎላ ድርሻ አለው። እንደ አገር እንደ ዜጋ የሚያስፈልገንን ማወቅ አለብን። ላለፉት ብዙ ዓመታቶች በማይጠቅሙን ነገሮች ላይ ጊዜና ጉልበታችንን ስናባክን ነበር።
አሁን የተሻለ ነገር የምናይበት፣ የበለጠ ነገር የምንሰማበት እንዲሆን ሁላችንም አእምሮና ልባችንን ማደስ ይኖርብናል። በትላንቱ ቦታ ላይ እንደ ትላንቱ የምናስብበት ጊዜ ላይ አይደለንም። አገራችን አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ልብና መንፈስ ያስፈልጋታል። ትውልዱ ፍቅርና ይቅርታ የዋጀው ነፍስና ስጋ ይፈልጋል። ሰላምና መቻቻልን መሰረት ባደረገ ህዝባዊ ምክክር አገር ልንፈጥር ዝግጅት ላይ ነን። በዚህ ብሄራዊ ምክክር ላይ እንደ ዜጋ፣ እንደ መንግሥት፣ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ከእያንዳንዳችን አገር አሻጋሪ የተቃኘ ሀሳብ ያስፈልጋል። ይሄ አገራዊ ምክክር ፍላጎቶቻችንን ገለን ለጋራ ጥቅም በጋራ የምንሰራበት ነው። አገራችንን አስቀድመን እኛ የምንከተልበት ህዝባዊ ንቅናቄ ነው።
የመታደስ ጊዜ ላይ ነን፤ የምንታደሰው ደግሞ በሀሳብ የበላይነት እንጂ የተረሱ በማስታወስ፣ የመቶ ዓመት ታሪክ በመቁጠር አይደለም። የምንታደሰው በደልን በመርሳት፣ ምህረትን በማድረግ ነው። ትላንትን የሚረሳ፣ ዛሬን የሚያወድስ ልብ ያስፈልገናል። በዚህ አገራዊ ምክክር ላይ ባህላዊ የሽምግልና ስርዓቶቻችን ዋጋ አላቸው ብዬ አምናለው። እነዚህን ባህላዊ ስርዓቶች በመመለስና በማጠናከር ያጣናቸውን አገራዊ በረከት መመለስ ይቻላል እላለው። እንዲሁም ደግሞ ከባህላዊ ስርዓት አባቶቻችንን፣ ከዘመናዊው ደግሞ በእርቅ ኮሚሽን በኩል ልምድ ያላቸውን በማከል ለአገራችን ዘላቂ ሰላም መንገድ ጠራጊ ሀሳቦችን ማዋጣት እንችላለን። ከእንግዲህ በሚያፋቅሩንና አንድ በሚያደርጉን ሀሳቦች ላይ እንጂ በሚለያዩን ጉዳዮች ላይ ጊዜአችንን ማባከን
አይኖርብንም። ከፌዴራል እስከ ክልል፣ ከዞን እስከ ወረዳ እስከ ቀበሌና መንደር በሚደርስ መልኩ ብሄራዊ ምክክሩ ለአገራዊ አንድነት ትርፍ እንዲያመጣ ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል። ብሄራዊ እርቅ ለብሄራዊ ሰላም ዋስትና ነው። ብሄራዊ ተግባቦት ለብሄራዊ አንድነት ዋልታና ማገር ነው። ያጣናቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ይሄን አገራዊ ምክክር ተከትለው እንደሚመጡ ተስፋ ከሚያደርጉት ውስጥ ነኝ። ብሄራዊ ሰላም በመግባባት የሚመጣ፣ በመደማመጥ፣ በመቻቻል የሚመጣ የአሳብ ፍሬ ነው። ብሄራዊ አንድነት ችግሮችን በመፍትሄ በማሸነፍ፣ ልዩነቶችን በመነጋገር በማጥበብ የሚመጣ የቅንጅት ውጤት ነው። ለዚህ ደግሞ የሀሳብ የበላይነት ያስፈልገናል፤ ችግሮቻችንን መርምሮ ባህላዊም ሆነ ሳይንሳዊ መፍትሄ የሚሰጥ አካሄድ ግድ ይለናል። በሂደቱም ችግሮቻችንን ሊበልጡን አይገባም። በመፍትሄ ሃሳብ ከችግሮቻችን በላይ በመሆን ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል። እስከዛሬ በመከነ ሀሳብ በችግሮቻችን ተበልጠን እንደ አገር ብዙ ዋጋ ከፍለናል። ምክክራችን ለለውጥ መሆን አለበት። መሰባሰባችን አገራችንን ሊያሻግር ይገባል። በዚህ አገራዊ ምክክር ሁላችንም ተስፋ ይናፍቀናል። አንድ አገር፣ አንድ ሕዝብ እንሻለን። ወደማንመለስበት ሩቅ የሰላም ስፍራ መምጠቅ የሁላችንም የጋራ ህልም ነው። የጠላቶቻችን መግቢያ ቀዳዳ ልዩነታችን ነው። እስከዛሬ ድረስ ፈተና የሆኑብን የውጪ ሀይሎች በልዩነታችን በኩል የገቡ ናቸው። አሁን ላይ የእኛን መለያየት እንደትልቅ በረከት ቆጥረው እኩይ ሀሳባቸውን ሊያሳኩ የሚጠብቁ ብዙ ናቸው። ውጪ ቆመው በመለያየታችን ሊያተርፉ የተዘጋጁ ብዙ ናቸው..። በህዳሴ ግድባችን፣ አሁንም በሰሜኑ ጦርነት የምዕራባውያንን የተንኮል ሀሳብ በሚገባ አይተነዋል። የልዩነቶቻችንን ቀዳዳ መድፈን አለብን። የጠላቶቻችንን መግቢያ በር መዝጋት አለብን። የልዩነቶቻችን ቀዳዳዎች የሚደፈኑት ከፍ ብዬ እንዳልኳችሁ በሀሳብ ነው። በምክክር ነው። በእርቅ ነው። ለአገራችን ስንል የጠላቶቻችንን መግቢያ ቀዳዳ መድፈን ይጠበቅብናል። ቀዳዳዎቻችንን ሳንደፍን የምናሳካው ህልም የለም።
ሊያስታርቁንና ሊያግባቡን የሚችሉ ሁሉን አቃፊ ሀሳብ ያስፈልገናል። ጠላቶቻችን መግቢያ ቀዳዳ እስኪያጡ ድረስ በአንድነትና በወንድማማችነት ተቃቅፈን መቆም ኢትዮጵያን ለመፍጠር የመጨረሻው ሀሳብ ይመስለኛል። ይሄ ሀሳብ የዚህ ትውልድ የህይወት መርህ እንዲሆን እሻለሁ። በዚህ የጋራ መርህ ውስጥ አገራችንን ወደ ፊት ማራመድ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው እላለው። እስከዛሬ የጋራ ጉዳይ አጥተን በራስ ወዳድነት ለብቻችን ነበርን፣ አገርና ህዝብን ከራስ ጉዳይ አንሰውብን በጎራ ስንቧደን ነበር ብንዘገይም እነዚያ የግለኝነት ጊዜያቶች የሚያበቁበት ጊዜ ላይ ነን። ሀሳባችን በእርቅና በምክክር የታገዘ ለጠላቶቿ የማትመች ሰላማዊ አገር መፍጠር ከሆነ፤ ሁላችንም ባለንበት ቦታ ላይ ገናና ሆነን ለመታየት የምናደርገውን የብቻና የብኩርና ሩጫ ማቆም ይኖርብናል።
በዝግታና በሰከነ አእምሮ ማየት ከቻልን ከፍላጎቶቻችን የሚቀድሙ በርካታ አገራዊ ጉዳዮች አሉን። የአገሩን ከፍታ በመሻት ሁሉም ዜጋ ከራሱ ይልቅ ለአገሩ መድከም ይኖርበታል። ከፍ ብዬ እንዳልኳችሁ የእኛ ህልውና ከአገራችን ህልውና ቀጥሎ የሚመጣ ነው። የእኛ ሰው መሆን፣ የእኛ ሉዓላዊነት ከአገር ቀጥሎ የሚሆን ነው። ከሁሉ አስቀድመን እኛን በአገር ውስጥ፣ አገርን በእኛ ውስጥ ማየት መልመድ አለብን። እርስ በርስ ከተግባባን፣ ያለፉ ታሪኮቻችንን የሚያድስ የእርቅ ተግባቦት ካለን አገር ለመፍጠር የሄድንባቸውን የብቻ ጎዳናዎች ወደ ሕዝባዊነት በመቀየር ቀጣይ እጣ ፈንታችንን መወሰን ያቅተናል ብዬ አላስብም። በዚህ እውነት ውስጥ ከተገኘን በእርቅና በውይይት የመጡ የጋራ ድሎቻችንን በጋራ የምናከብርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም እላለው። ይህ እንዲሆን ግን ቀድመው የጠላቶቻችን መግቢያ ሆኑ የልዩነት ቀዳዳዎቻችንን እንድፈን፤ የመጀመሪያ ስራችንም ስለ አገራችን ሆኖ ለአገራችን እንልፋ፤ ከዛ አገራችን ለእኛ ትለፋለች። ለዚህም ምክክራችን ለለውጥ መሆን አለበት። ይህ ነው ሰው በአገር፤ አገርም በሰው የመገለጥ ምስጢሩ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 13 /2014