ዳግም ከበደ ኢትዮጵያውያኖች ስንፍናን የምንተችበት ጠንካራ አገላለፆች አሉን። ስንፍናን ብቻ ሳይሆን ከተግባር ወሬ የሚቀድመውንም እንዲሁ ሸንቆጥ አድርገን መስመር እንዲይዝ ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ ማህበራዊ ሂሶችን በተለያዩ መልእክት የማስተላለፊያ ዘዴዎች እንጠቀማለን። ይሄ የሺህ ዘመናት አገረ መንግሥት ያላት ኢትዮጵያን ያስረከቡን አያት ቅድመ አያቶቻችን፣ ከስርዓት የሚያፈነግጡትን ለመሞረድ የሚጠቀሙበት መንገድ ነው። ድሮ ድሮ ነገሥታት “እረኛ ምን አለ” ብለው ጆሯቸውን ይሰጡ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው። የሚያስተዳድሩት ሕዝብ ምን እንዳስከፋው ምን እንዳሳዘነው ከእረኛው ግጥምና ዜማ ውስጥ መረዳት ስለሚችሉና አመራራቸውን በዚያው ልክ ለማስተካከል ስለሚረዳቸው ነው።
ታዲያ ብልሆቹ አያቶቻችን ደበሎውን ለብሶ ከቁሩ ጋር እየተጋፋ ከብት የሚጠብቀውን “ብላቴና” የሚያወጣውን ቃል አንዳች ሳይጠራጠሩ “የሚገዙትን ሕዝብ ፍላጎት” ከአመራር ስርዓታቸው ቅኝት ጋር ያጣጥሙት ነበር። ይህ ብልሃታቸው ዘመናት ለዘለቀችው ኢትዮጵያ ታላቅ መሰረትና “የአመራር ጥበብ” ነበር። ዛሬስ? ዛሬማ እድሜ ለታላላቅ የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤቶች ምስጋና ይግባውና መንግሥት የሕዝቡን እሮሮ የሚያዳምጥበት፣ የጎደለውን የሚለይበት፣ እራሱን እንዲያርም የሚያስችለው አያሌ መረጃዎችን በገፍ የሚያገኝበት መንገዶች በየአቅጣጫው ተዘርግተዋል።
“ታዲያ አሁን የጠፋው ምንድነው?” አትሉም?፤ አሁን የጠፋውማ ብልህ መሪና የሕዝብን ቁስል እንደራሱ የሚሰማው የአስተዳደር ስርዓት ነው። እስቲ ይህን ነገር በቀጣይ አርፍተ ነገሮች ውስጥ በቅርብ ግዜ ብቻ የተከሰተውን የኑሮ ውድነትና ሕዝብ ላይ እየተከሰተ የመጣውን የምጣኔ ሃብት ጫና እንደ ምሳሌ አንስተን ለመመልከት እንሞክር። መንግሥት የአገርን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብን ደህንነትና ሌሎች ህግ የማስከበር ተግባራትን የመከወን የሞግዚትነት ድርሻ ከመያዙም በላይ፤ የገበያ ስርዓቱን የመቆጣጠርና ህገወጥነት እንዳይስፋፋ የመከተታል ተግባርና ኃላፊነት አለበት። በመሆኑም ሕዝብ በራሱ መስራት ባለመቻሉ ምክንያት ቆጥሮ የሰጠውን ኃላፊነት የመወጣት ግዴታም ጭምር አለበት። ከሰሞኑ በአገራችን ኢትዮጵያ ከምግብ ሸቀጦች አንፃር ሰፊ ግርግሮችና ከፍተኛ የዋጋ ንረት ያስከተለ ችግር ተከስቷል። በተለይ በዘይትና በዳቦ
ሸቀጦች ላይ የተስተዋለው የዋጋ ንረት ሃይ ባይ አጥቶ አሁንም ድረስ ማህበረሰቡ እያንገላታ ይገኛል። ይህን እሮሮም ሕዝቡ በተለያዩ አማራጮች ይመራኛል ላለው አካል እያደረሰ ቢገኝም “እረኛ ምን አለ የሚል” ሰሚ ግን በፍጥነት እያገኘ አይመስልም። ከእዚያ ይልቅ የግል ክብሬ ተነክቷል በሚል “ከጋዜጠኞችና ማህበራዊ አንቂዎች ጋር” ግብግብ ውስጥ መግባትና ትልቁን የማህበረሰብ ምስል መዘንጋት አስተውለናል። ይህ ብቻ ሳይሆን ህገወጥ ነጋዴዎችንና የገበያ ስርዓቱን ስር ነቀል በሆነ መንገድ ችግሮችን እንዲፈቱ አድርጎ ከማስተካከል ይልቅ ትናንሽ ህግ አስከበርን የሚሉ ዜናዎች ላይ በማተኮር ላይ ተጠምዶ መቆየትም በአስተዳደር ስርዓት ውስጥ የሚገኙ አመራሮች ላይ ተመልክተናል።
ይህን ጉዳይ ከእጅ መጠቋቆምና “ከራስ የሥልጣን ክብር” በዘለለ ለመመልከት ሞክረን የአብዛኛውን የኢትዮጵያ ችግር ከስር መሰረቱ የሚፈቱ ችግሮች ላይ አተኩረን ልንፈታቸው ይገባል። “ከስር መሰረቱ” የሚለውን ሃረግ እስቲ ከሰሞኑ የዘይትና የዳቦ ዋጋ መናር እና ምጣኔ ሃብታዊ ጫናዎች አንፃር እንመልከተው። መንግሥትም እንደ ቀደሙት እረኞች ቆጥሮን ያዳምጠንና የሕዝብን ችግር በቅን ልቦና ለማቃለል ይሞክር። ከቅርብ ግዜያት ወዲህ የማህበረሰቡን መሰረታዊ የሸቀጥ ፍላጎት የሚሞሉ ትላልቅ የፕሮጀክት ግንባታዎችን ተመልክተናል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የዘይትና የዳቦ ፋብሪካዎች ይገኙበታል። የኤሌክትሪክ ሃይል አመንጪ ጣቢያዎችንም እንዲሁ። መንግሥትና ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችም ጭምር ከባለሃብቶች ጋር ሆነው አስቀድመው የተስፋ ዳቦ መግበውን ነበር።
የፕሮጀክቶቹን ታላላቅነትና ሊፈቱት የሚችሉትን ችግር ገና አጣጥመንና ደስታችንን ገልፀን ሳንጨርስ ዘይትና ዳቦ ጣሪያ ነክተው ቁስላችን ያመረቅዙት ገቡ። አንዳንድ የፕሮጀክቶቹ ማነቆዎች ቢገቡንም እንኳን መንግሥት ከሰጠን ተስፋ አንፃር ግን ዛሬ ላይ የተመለከትነውን የዋጋ ንረት ባላየነው ነበር። እንዲያም ሆኖ ግን “የማይቆነጥጡት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል” ሆኖ አንዳንድ አመራሮች ከሕዝቡ ቁስል ይልቅ የራሳቸው ክብርና ጎጥ በልጦባቸው ችግሩን ለመሸሽና በተለያዩ ሰበብ አስባቦች ለማድበስበስ ሲሞክሩ አስተውለናል። ይሄ ለማናችንም አይጠቅምም። ዜጎች ወደውና ፈቅደው የዘረጉት አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ማናቸውም ግለሰቦችም ሆኑ ባለስልጣኖች 24/7 ሰዓት ቀንና ሌሊት ነቅተው የሕዝቡን ችግር ለማቃለል መስራት ይጠበቅባቸዋል። ከሁሉ በላይ ግን የሕዝቡን እጅግ ፈታኝ ችግሮች ጆሮ ሰጥተው ማዳመጥ እና የሚደርስባቸውን ትችቶችና የምክረ ሃሳብ መልዕክቶች ዛሬም ከግብርናው ጫንቃ ያልተላቀቀው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፤ ከኋላ ቀር አስተራረስና በዝናብ ላይ ከተመሰረተው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ያለውን ድህነትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፈታኝ ሆኗል።
ይህ ደግሞ ግብርናው በአንድ በኩል ከድህነት ለመውጣት፤ በሌላ በኩል ኢኮኖሚውን ትራንስፎርም ለማድረግ የተሰጠውን ግብ እንዳያሳካ አድርጎት ቆይቷል። ይህን ከመቀየር አንጻር እንደ ሃገር የድህነት ምጣኔን ወደ ሰባት በመቶ መቀነስን፤ ዝቅተኛ የምርታማነት መነሻዎች ታሳቢ በማድረግም ከ2013 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት ኢኮኖሚውን በአማካይ በየዓመቱ በ10 በመቶ እንዲያድግ የማድረግ የአስር ዓመት ግብ ተይዟል። የአገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማረጋገጥ ደግሞ በአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ዘመን የግብርና ዘርፍ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የሚኖረው ድርሻ በ2012 በጀት ዓመት ከነበረው 32 ነጥብ ሰባት በመቶ ድርሻ በ2022 በጀት ዓመት ወደ 22 በመቶ እንዲቀንስ፤ ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት በአማካይ በየዓመቱ የ1ነጥብ6 በመቶ አስተዋጽዖ እንዲኖረው ማድረግ እንደሚገባም ታምኖበታል።
ይሄን ተገንዝቦ ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሰ ያለው ገዢው ፓርቲ ብልጽግናም፤ ግብርናውን ለምግብ ዋስትና፣ ለድህነት ቅነሳ እና ለኢኮኖሚ ሽግግሩ እምርታ የማይተካ ሚናውን ሊወጣ በሚያስችለው አግባብ እንዲጓዝ እየሰራ ስለመሆኑ በርካታ ውጤቶች መታየት ጀምረዋል። ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት የማላቀቅ የመስኖ ልማት ሥራዎች፤ በቴክኖሎጂ የመደገፍና የኩታ ገጠም ግብርና ጅማሮዎች፣ እንዲሁም የምርታማነት ዕድገት ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ መሄድ ለለውጡ እንደ አብነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው። ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአማራ ክልል ተገኝተው ያደረጉት ምልከታና፤ ምልከታቸውን ተከትሎ፣ “ግብርና የሀገራችን የኢኮኖሚ መሠረት ሆኖ ቆይቷል። የስንዴ አቅርቦት በዓለም አቀፍ ሁነቶች ጫና እየደረሰበት የግብርና ልማት ሥራው የምግብ ዋስትናንና ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን እውን የሚያደርግ ይሁን! በቀናነት መቀበል ይኖርባቸዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ መሰረታዊ የኑሮ ሸቀጦችን በተመለከተ ይፋ የሚደረጉና የሚመረቁ ፕሮጀክቶች በትክክልም ፍላጎቶችን በቋሚነት የሚያሟሉ መሆናቸውን ማረጋገጥና የሚገጥማቸውን እክሎች መቅረፍ ያስፈልጋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በመረጃ ማሰራጫዎች “ከሰማይ ዳቦና ወተት ሊዘንብ ነው” ብለን ለሕዝባችን ነግረነው በነጋታው አህያ የማይሸከመው የዋጋ ንረት ከተከሰተ ከማስተዛዘብ አልፎ አብሮ የማያዛልቅ ይሆናል።
ምክንያቱም ዜጎች ከሌሎች ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፍላጎቶቻቸው በላይ የሚያስቀድሙት ህልውናቸውን እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል። በሌላው ዓለም ላይ ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ብዙ መዘዞች ይደመጣሉ። መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና ደርሶ ለዚህ ቀጥተኛ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ሥልጣናቸውን እስከማስረከብና መልቀቅ ይደርሳሉ። ለምሳሌ ሰሞኑን ዳቦ ላይ ጭማሪ በመታየቱ የሱዳን ዜጎች አደባባይ ወጥተው መንግሥታቸውን እስከመቃወም ደርሰዋል። ምክንያቱም “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” ነውና። ይህን መሰል ጉዳይ እንደምሳሌ ለማንሳት የፈለግነው ያለምክንያት አይደለም “የማይቆነጥጡት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል” የሚለውን አባባል ከሰሞኑ ስላስተዋልን ጭምር ነው። አንዳንድ አገራቶች እኛ አገር ወድቀው እንኳን ጎንበስ ብለን ለማንሳት ብዙ የአዕምሮ ግብግብ ውስጥ የምንገባባቸው “አስር ሳንቲምና ሀምስት ሳንቲም” ጨመረብን ብለው አብዮት ያስነሳሉ። እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ጨዋ ማህበረሰብ ነው ያለን።
አይደለም 10 ሳንቲም 500 መቶና ስድስት መቶ ብር በዘይት ላይ ሲጨምር እናቶቻችን “ዋናው አገር ሰላም ይሁን በተልባም ቢሆን እንበላለን›› የሚሉ እጅግ የሚደንቅ ስብእና ያላቸው ናቸው። ታዲያ ይህን ማህበረሰብ ጎንበስ ቀና ብለው ቢያገለግሉት ምን ይጎድልባቸው ይሆን። ለዚህ ነው መንግሥት ህገወጥ ነጋዴዎችና ከለላ የሚሆኑ አመራሮች ላይ እንዲጨክን የምንጠይቀው። በዚህ ምክንያት ነው ትልልቅ ፋብሪካዎች ለሕዝብ ይፋ ሲደረጉ ከፕሮፓጋንዳና የፖለቲካ ትርፍ በዘለለ ዘላቂ የችግር መፍቻ መንገዶች መሆናቸው እንዲረጋገጥ የምንጠይቀው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ሕዝብ በተለያዩ መንገዶች ለመንግሥት የሚያደርሳቸው “ህብረሰባዊ ትችቶች” ቁብ ሊሰጣቸው ይገባል። ሕዝብ የቀለደ ይምሰል እንጂ የውስጡንና ብሶቱን ሊሰማኝም ይገባል ላለው ለመረጠው መንግሥት አድርሷል። በዚህ ቁስሉ ላይ እንጨት የሚሰድዱ ካሉ አንድ ሊባሉ ይገባል የሚለው የዛሬው ማሰሪያ መልክት እንዲሆን እንፈልጋለን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13 /2014