ነ ገ የሚጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛው ዙር ውድድር የተሳካ እንዲሆን የመጀመሪያ ዙር አፈጻጸምን በመገምገም፤ ክፍተቶች እንዳይደገሙ፤ እንዲሁም የነበሩ ጠንካራና በጎ ጎኖች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማስቻል የኢትዮጰያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከክለቦችና ከዳኞች ኮሚቴ ጋር ውይይት በማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እንደገለጹት፤ በአንደኛው ዙር የሊጉ ውድድር ላይ በቀረበው ሪፖርት ክፍተት መኖሩ ተገምግሟል፡፡ ለዳኞች ተገቢውን የደህንነት ሽፋን ከመስጠት አንፃር፤ አልፎ አልፎ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል፤ የዳኞች ውሳኔ መዘግየት፤ ፌዴሬሽኑ የሚያሳልፋቸው የስነምግባር እርምጃና ውሳኔዎች መዘግየት የመሳሰሉት በተደረገው ግምገማ እንደ ክፍተት ታይተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ የክለብ አሰልጣኞችና የቡድን መሪዎች ውጤት ሲጠፋባቸው ከተገቢው መንገድ ውጪ ውጤት ለማግኘት ሲሉ፤ ሜዳ ላይ የሚገኙ ደጋፊዎችንና ተጫዋቾቻቸውን ባልተገባ መልኩ በማነሳሳት ኃላፊነት የጎደለው ስራ የሚሰሩ አካላት እንዳሉም በግምገማው ታይቷል፡፡ አቶ ባህሩ እንደሚሉት፤ ችግሮቹ በሁለተኛው ዙር የፕሪሚየር ሊግ ውድድር እንዳይከሰቱ በግምገማው ላይ ክለቦች ችግሮቻቸውን እንዲያስተካክሉ አቅጣጫ ተቀምጧል። ፌዴሬሽኑም ችግሮች በሁለተኛው ዙር የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላይ የሚከሰቱ ከሆነ የማያዳግም የስነምግባር እርምጃ እንደሚወስድ ለክለቦች አሳውቋል። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማስፈን በቀጣይ አጠናክሮ የሚሰራ ይሆናል።
ስፖርታዊ ጨዋነት ችግር በአንድ ጊዜ የሚቀረፍ ስላልሆነ በሂደት እየተስተካከለ የሚሄድ በመሆኑ ኃላፊነቱ የአንድ ተቋም ወይም የክለቦች ብቻ ሳይሆን የሁሉም የስፖርት ቤተሰብ መሆኑንም ገልጿል። ኃላፊው አክለውም፤ አንዳንድ ጊዜ የስፖርታዊ ጨዋነት ክፍተት እንዳለ ሆኖ፤ ጋዜጠኞች ስለተፈጠረው ችግር ወይም ስለጉዳዩ የሚያስረዱበትና የሚዘግቡበት መንገድ የግጭት መነሻ ምክንያት ሊሆን ይችላል ካሉ በኋላ አንዳንድ ውድድሮች ገና ሳይጀመሩ ማጋጋሉና በክለቦች መካከል ካለው አንድነት ይልቅ ሊያለያዩ የሚችሉ ነጥቦች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመዝገብ ደጋፊውና ተጫዋቾች ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጭ እንዲወጡ የሚያደርጉ ሂደቶች እንደነበሩ ገልጸዋል። የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ፣ የክለብ አመራሮች፣ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ ደጋፊዎችና አጠቃላይ የስፖርት ቤተሰቡ ውድድሮች በፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲካሄዱና የሀገራችን ስፖርት አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲጓዝ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የዳኞች ብሄራዊ ኮሚቴ አንደኛ ዙር የፕሪሚየር ሊግ አፈጻጸም ምን እንደሚመስል መገምገሙን የጠቀሱት ኃላፊው፤ በዚህም ኮሚቴው በዳኝነት በኩል በታዩ ክፍተቶች ላይ በመነጋገር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት በሁለተኛው ዙር እንዳይደገሙ ለማድረግ እንዲቻል ውይይት ማድረጉን ጠቁመዋል፡ ፡ በመጀመሪያው የውድድር ዘመን በዳኝነቱ ዙሪያ የነበሩ ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ስምምነት መደረሱንም አክለዋል፡፡ አቶ ባህሩ በክለቦች በኩል አዲሱን የእግር ኳስ የዳኝነት ህግ ከማወቅ ጋር ተያይዞ ክፍተቶች እንደነበሩም ገልጸው፤ ፌዴሬሽኑ ፕሮግራሞችን አመቻችቶ ለክለብ አመራሮችና ቡድን መሪዎች ስልጠናውን እንዲያገኙ ማሳወቁንና በዚህም መሰረት ስልጠናው እንዲሰጣቸው ጥያቄ ላቀረቡ አካላት ስልጠናውን ለመስጠት ዝግጅቱን መጨረሱን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም እያንዳንዱ ክለብ ስፖርታዊ ጨዋነትን በማክበር ኃላፊነት ወስዶ ውድድሩን እንዲያካሄድ፤ እንዲሁም ስለስፖርታዊ ጨዋነትና ስለ እግርኳስ ህግ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ የሚል መመሪያ ከፌዴሬሽኑ በኩል መተላለፉን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ መሰረት ክለቦች በተግባር ትምህርቱንና ስልጠናውን እንዲሰጡ ፌዴሬሽኑ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። የሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከመጀመሪያው ዙር የተሻለ ወይም የበለጠ እንዲሆን ለማድረግ፤ የተለያዩ ተግባራት ከባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅም ቁርጠኛ አቋም መያዙንም አቶ ባህሩ ተናግረዋል። ‹‹በተደረገው ግምገማና በቀረበው ሪፖርት መሰረት የአንደኛ ዙር የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር የተሳካ ነበር። የተሻለ የውድድር ጊዜ የተመለከትንበትም ነው። ተራርቀው የነበሩ ክለቦች ተቀራርበው ውድድራቸውን ማድረግ ችለዋል። በገለልተኛ ሜዳ ውድድራቸውን ሲያደርጉ የነበሩ ክለቦች ልዩነታቸውን ወደጎን ትተው በራሳቸው ሜዳ ላይ ተጫውተዋል።
ፌዴሬሽኑም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ እነዚህ ክለቦች ችግራቸውን በውይይት በመፍታት ውድድራቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲያካሂዱ ትልቁን ሚና ተጫውቷል። የየክልሎቹ አስተዳደሮችና አመራሮችም ይህ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽ አድርገዋል። አሁንም በሁለተኛው ዙር የሊጉ ጨዋታ በክልሎች መካከል የተፈጠረው መልካም ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከፌዴሬሽኑ ጎን በመሆን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል›› በማለት አቶ ባህሩ አብራርተዋል፡፡ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ የቤት ስራው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ወይም ይህን ውድድር የሚመራው አካል ኃላፊነት ብቻ ነው ተብሎ መቆጠር የለበትም ያሉት አቶ ባህሩ፤ ስፖርታዊ ጨዋነት የሚረጋገጠው ሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ኃላፊነቱን በተገቢው ሁኔታ ሲወጣ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በክልሎች መካከል የታየው ስፖርታዊ ጨዋነት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በክለቦች መካከል የተሻለ መቀራረብ እንዲኖር የመገናኛ ብዙኃን አጀንዳ ቀርጸው ሊሰሩ ይገባል። ይህ እንዲሆን ከክለቦችና ከፌዴሬሽኑ ጋር ተቀራርበው መስራት ይጠበቅባቸዋል። ፌዴሬሽኑ በክልል ክለቦች መካከል የተፈጠረው ስፖርታዊ ጨዋነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጀመረውን ስራ አጠናክሮ በመቀጠል ከኮሚሽነሮች በተጨማሪ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች በተለያዩ የውድድር ሜዳዎች ላይ ተገኝተው ጨዋታዎችን እንዲታደሙ፣ እንዲታዘቡ የማድረጉ ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ስፖርት «ለወዳጅነት፣ ለፍቅር፣ ለአንድነት፣ ለወንድማማችነት» የሚለውን መርህ ለማስቀጠል ፌዴሬሽኑ ከየክለቡ የስራ አስፈፃሚዎችና ፕሬዚዳንቶች ጋር ውይይት በማድረግ በጎ ፉክክርን በሚፈጥር ስሜት ላይ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል። ‹‹ሊጉ ፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት ውድድሮች የሚካሄዱበት የውድድር ዘመን እንዲሆን፤ ማሸነፍ፣ መሸነፍና አቻ መውጣት የሚሉትን እግር ኳሳዊ ውጤቶች የስፖርት ቤተሰቡ መረዳት አለበት።
ጥቃቅን ነገሮችን እያነሳን በመካከላችን ያሉ ልዩነታችንን እያሰፋን ወዳልሆነ አቅጣጫ እንዳንጓዝ፤ አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ ትኩረት በማደረግ ክፍተቶቻችንን እያሟላን ውጤታማ የሆነ የእግር ኳስ ውድድር እንዲኖረን ማድረግ አለብን። የዚህ ሁሉ ውድድር ዋነኛ ግቡ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግብዓት የሚሆኑ ተጫዋቾችን ማፍራት በመሆኑ የስፖርት ቤተሰብ የበኩሉን አስተዋጽ ማድረግ ይጠበቅበታል።›› ሲሉ የሁለተኛውን የሊግ ውድድር መጀመር አስመልክተው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የኢትዮጰያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ጨዋታ ነገ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሀዋሳ ከተማ በመቀሌ ስቴዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በሚያደረጉት ጨዋታ የሚጀመር ሲሆን ሊጉ እሁድ ዕለት ቀጥሎ ወላይታ ዲቻ ከስሑል ሽረ፣ ደደቢት ከመቐለ 70 እንደርታ፣ ባህር ዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ፋሲል ከነማ ከሲዳማ ቡና፣ ጅማ አባ ጅፋር ከአዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ ሰዓት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ውድድራቸውን የሚያካሂዱ ይሆናል። መከላከያ ከደቡብ ፖሊስ በዚሁ ዕለት ከቀኑ አስር ሰዓት ግጥሚያቸውን ያካሂዳል።
ፕሪሚየር ሊጉን መቐለ 70 እንደርታ በ35 ነጥብ ሲመራ፤ ሲዳማ ቡና በ30 ነጥብ ይከተላል።ቅዱስ ጊዮርጊስ በ26፣ ፋሲል ከነማ በ25 ነጥብ ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡ ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረ እና ደደቢት ደግሞ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያሉትን የመጨረሻዎቹን ሦስት ደረጃዎች ይዘው ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011
በሶሎሞን በየነ