ወይዘሮ አሚና ሽኩር ከ1975 ዓ.ም እስከ 1985 ዓ.ም ለተከታታይ 12 አመታት ለኢትዮጵያ ዕህል ንግድ ድርጅት የቦሊቦል ክለብ ተጫዋችና የክለቡ አምበል ነበሩ። ለኢትዮጵያ የሴቶች የቦሊቦል ብሄራዊ ቡድን ከምስረታው ጊዜ ከ 1978 ዓ.ም ጀምሮ ጨዋታ እስከ አቆሙበት 1985 ዓ.ም ድረስ የብሄራዊ ቡድኑ አምበልና ተጫዋች ነበሩ። ብሄራዊ ቡድኑንም ለሁለት አመት በምክትልና በዋና አሰልጣኝነት መምራት ችለዋል። አሁን ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ቦሊቦል ፌዴሬሽን የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ እና የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች የቦሊቦል ስፖርት ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የሴቶች የቦሊቦል ስፖርት በአሁኑ ጊዜ በምን ሁኔታ እንደሚገኝና የእርሳቸው የተጫዋችነትና የአሰልጣኝነት ዘመን ምን እንደሚመስል ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አዲስ ዘመን:- የቦሊቦል ተጫዋች እንዴት ሊሆኑ ቻሉ?
ወይዘሮ አሚና:- በደርግ ጊዜ በነበረው ስርዓት ታዳጊ ስፖርተኞችን ለመመልመል በቀበሌ፣ በወረዳና በትምህርት ቤቶች ደረጃ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ነበር። እኔም ተክለ ሰወነቴ ለቦሊቦል ስፖርት አመች ስለነበር በቀበሌ ደረጃ ተመልምዬ ስፖርቱን ጀመርኩ። በዚህም ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ብሄራዊ ቡድን የቡድን አምበልና ኮከብ ተጫዋች ለመሆን በቅቻለሁ፡፡
አዲስ ዘመን:- በተጫዋችነት ዘመንዎ ያስመዘገቡትን ውጤቶች ቢነግሩኝ ወይዘሮ አሚና:- በተጫዋችነት ዘመኔ 25 የወርቅ፣ ሰባት የብርና ስምንት የነሀስ በአጠቃላይ 40 ሜዳሊያዎችን አግኝቻለሁ። ሶስት ዋንጫዎችንም ተሸልሜያለሁ። የብሄራዊ ቡድኑ ኮከብ ተጫዋችና አምበል በመሆኔ በ1981 ዓ.ም ሰሜን ኮሪያ ፕዮንግያንግ ላይ በተካሄደው የአለም የወጣቶች ስፖርት ፌስቲቫል ላይ በክብር እንግድነት ተጋብዤ በቦታው ተገኝቼ ነበር። በፌስቲቫሉ ላይ ከሌሎች ሀገር ከተውጣጡ ተጫዋቾች ጋር አፍሪካን ወክዬ የመጫወት እድሉን በማግኘቴ፤ በውድድሩ የተጫወትኩበት ቡድን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል። እኔም የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሆኜ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልሜያለሁ። በዚህም የሀገሬን ሰንደቅ አላማ በአለም መድረክ ላይ ከፍ አድርጌ በማውለብለብ ለሀገሬ ኩራት፤ ለኔ ደግሞ ታሪክ መስራት ችያለሁ። ከዚህ በተጨማሪ ኬንያ ላይ ተደርጎ በነበረው የመላው አፍሪካ የቦሊቦል ጨዋታ ጥሎ ማለፍ ውድድር ላይ ኮከብ ተጫዋች ተብዬ ተሸልሜያለሁ። ከ1976 ዓ.ም እስከ 1980 ዓ.ም ድረስ ከኢትዮጵያ ዕህል ንግድ ድርጅት የቦሊቦል ክለብ ጋር ለተከታታይ አራት አመት በአራት የውድድር አይነቶች አራት ዋንጫዎችን ማንሳት ችያለሁ። በዚህም ክለቡን በአምበልነት እየመራሁ የተለያዩ ዋንጫዎችን እንዲያነሳ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቻለሁ። ከክለቡ ጋርም በርካታ ዋንጫዎችን የኮከብ ተጫዋችነት ክብርንም ለተከታታይ አመታት ማሳካት ችያለሁ። በ 1980 ዓ.ም በጨዋታ ላይ እያለሁ ጉልበቴ ላይ በደረሰብኝ ጉዳት ለክለቤ ተሰልፌ አልተጫወትኩም ነበር። በዚህም ክለቤ ከአምስት አመት በኋላ የመጀመሪያውን ሽንፈት አስተናግዷል። ክለቤም ከአምስት አመት በኋላ ሽንፈትን ሲያስተናግድ በወቅቱ ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ‹‹የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት የቦሊቦል ክለብ በሰማኒያ አመተ ምህረት ለመጀመሪያ ጊዜ ሰማንያቸውን ቀደዱ›› ብሎ ዘግቦት ነበር። በክለብ ደረጃ ስናሸንፍበት የነበረው መንገድ በጣም ታሪካዊ ሲሆን፤ ለብሄራዊ ቡድኑ ተሰልፌ በመጫወት ብሄራዊ ቡድናችን በመላ አፍሪካ በቦሊቦል ውድድር ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘን በማጠናቀቅ ትልቅ ውጤት አስመዝግበን ነበር፡፡
አዲስ ዘመን:- ራስዎን ከተጫዋችነት አለም መቼ አገለሉ? ወደ አሰልጣኝነትስ እንዴት መጡ?
ወይዘሮ አሚና:- በ1985 ዓ.ም የመላው አፍሪካ የማጣሪያ ጨዋታን ወደ ናይጄሪያ ሂደን ለመጫወት በአዲስ አበባ ስቴዲየም ልምምድ በማድረግ ላይ እያለሁ፤ ወድቄ ቅንጭላቴ ላይ በደረሰብኝ ጉዳት ከተጫዋችነት አለም ልገለል ችያለሁ። በጉዳቱ ለሶስት ወር ያክል ማየት ተስኖኝም ነበር። በሀገር ውስጥ ህክምናዬን ስከታተል ቆይቼ ከአቅም በላይ ስለሆነባቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ በማቅናት ህክምና ተከታትዬ አራት ጊዜ ከፍተኛ ቀዶ ጥገና ከተሰራልኝ በኋላ ጤንነቴ ተመልሶልኛል፡፡ ተጫዋች በነበርኩበት ወቅት የአሰልጣኝነት ኮርሶችን ወስጄ ስለነበር፤ በአለም አቀፍ ደረጃ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት አለኝ። በመሆኑም ጤንነቴ ከተሻሻለ በኋላ ብሄራዊ ቡድኑን በምክትልና በዋና አሰልጣኝነት ይዤ ሰርቻለሁ። በአሰልጣኝነቴ የተሻለ አፈጻጸም በማሳየቴ በ1995 ዓ.ም ከኩባዊው አሰልጣኝ ዋና አሰልጣኝነቱን ተረክቤ ብሄራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት መርቻለሁ። በዘመኔም ብሄራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ይዤ በ1996 ዓ.ም ለመላ አፍሪካ ውድድር ወደ ግብጽ ተጉዤ ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቄያለሁ። እንዲሁም የተጫዋችነት ዘመኔን ባሳለፍኩበት የኢትዮጵያ ዕህል ንግድ ድርጅት የቦሊቦል ክለብ በረዳት አሰልጣኝነትና በዋና አሰልጣኝነት ለረጅም አመት ሰርቻለሁ።
አዲስ ዘመን:- የኢትዮጵያ ወርቃማ የሴቶች የቦሊቦል ዘመን የሚባለው መቼ ነበር?
ወይዘሮ አሚና:- ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1981 ዓ.ም ወርቃማው የኢትዮጵያ የሴቶች የቦሊቦል ዘመን ነበር። ምክንያቱም በዚያን ጊዜ 16 የሴቶች የቦሊቦል ክለቦች የነበሩ ሲሆን፤ ስምንቱ በ‹‹ሀ›› እና ስምንቱ በ ‹‹ለ›› ምድብ ተከፍለው የጋለ ውድድር ያደርጋሉ። በክለቦቹ መካከል የነበረው የውድድር መንፈስም በጣም ጠንካራ በጨዋታውም ኳስ መሬት እንዳትነካና ላለመሸነፍ ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግበት ስለነበር በእኔ እይታ ይህ ወቅት ወርቃማው የቦሊቦል ዘመን ነው።
አዲስ ዘመን:- በእርስዎ የተጫዋችነት ዘመን ስፖርቱ የነበረው ጥንካሬ እንዴት ይገለጻል?
ወይዘሮ አሚና:- ተተኪ ስፖርተኛ እንዲወጣ በቀበሌና በትምህርት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራ ነበር። በዚያን ጊዜ በየነበረው ስርዓት አንድ ክለብ አምስት የስፖርት አይነት መያዝ ግዴታው ስለነበር ክለቦች በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ውድድሮችን ያደርጋሉ፡፡ በሁሉም የስፖርት አይነቶች ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ። በመሆኑም በወቅቱ የቦሊቦል ስፖርት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጠው ስለነበር ጠንካራ ውድድሮች ነበሩ፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩ ስፖርተኞችም ለስፖርቱ ከፍተኛ ፍቅር ነበራቸው ለገንዘብ ሳይሆን ለማልያቸው የሚጫወቱ ነበሩ።
አዲስ ዘመን:- የሀገራችን የሴቶች የቦሊቦል ስፖርት አሁን ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል?
ወይዘሮ አሚና:- ቦሊቦል በአለም አቀፍ ደረጃ ከእግር ኳስ ስፖርት ቀጥሎ ተወዳጅ ነው። ነገርግን የሀገራችን የሴቶች የባሊቦል ስፖርት ሞቷል በሚባል ደረጃ ላይ ነው። ምክንያቱም የሴቶች የቦሊቦል ክለብ ሶስት ብቻ ናቸው ያሉት። በክለቦች መካከል ምንም አይነት ፉክክር ካለመኖሩም በላይ ውድድሮች በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ እየተካሄዱ አይደለም። በአጠቃላይ አሁን ላይ ስፖርቱ ትኩረት ተነፍጎታል።
አዲስ ዘመን:- መንስኤው ምንድን ነው?
ወይዘሮ አሚና:- አሁን ላይ ያለው ስርዓት ነፃ ገበያ በመሆኑ አንድን ክለብ ወይም ድርጅት ይህን የስፖርት አይነት ያዝ ብለህ አታስገድደውም። ገበያው ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ነው፤ በመሆኑ ክለቦችና ድርጅቶች ጥቅም በሚያገኙበት የስፖርት አይነት ላይ መስራት ይፈልጋሉ። በቀበሌና በትምህርት ቤቶች ላይ ተተኪ ስፖርተኞች እንዲኖሩ ሲሰሩ የነበሩ ስራዎች ቀርተዋል በሚባል ደረጃ ላይ ናቸው። የስፖርት ጽህፈት ቤቶች አደረጃጀታቸው ሙያና ሙያተኛ የተገናኙበት አይደለም። በመሆኑም ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ የስፖርት ጽህፈት ቤት ፈጻሚዎች ከሙያው ጋር የማይገናኙ ናቸው፡፡ በዚህም ስፖርቱ ላይ የተሻለ ውጤት ማምጣት አልተቻለም። የስፖርተኞች መፍለቂያቸው ትምህርት ቤቶች ሆኖ እያለ፤ ትምህርት ቤቶች ላይ ያለው ባለሙያ በተግባር አስደግፎ ስፖርቱን ለማስተማር ብቁ ባለመሆናቸው ልጆቹን በስፖርታዊ ክህሎት ቀርጾ ለማሳደግ ይቸገራሉ፡ ፡ በአጠቃላይ የአመለካከት ችግር መኖሩ፣ ለስፖርቱ ትኩረት አለመሰጠቱና ምንም ስራ ሳይሰራ ከታች እየተሰራ ነው እየተባለ የውሸት ሪፖርት እየተቀረበ ስፖርቱ እንዳያድግ ሆኗል።
አዲስ ዘመን:- መፍትሄው ምን ሊሆን ይችላል?
ወይዘሮ አሚና:- የስፖርት ጽህፈት ቤት አደረጃጀት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራትና ከላይ እስከታች ተፈትሾ የተዘረጉ መዋቅሮች በስፖርት ሙያተኛ ሊመራ ይገባል። የስፖርተኞች መፍለቂያቸው ትምህርት ቤቶችና ቀበሌዎች በመሆኑ እነዚህ ቦታዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል። ትምህርት ቤቶች የስፖርቱን ጽንሰ ሀሳብ በተግባር ሰርቶ የሚያሰራ መምህር ሊኖራቸው ይገባል። ከላይ ያለ አካል ከታች የሚመጡ ሪፖርቶችንና የሚሰሩ ስራዎችን ወደታች ወርዶ በአካል በመፈተሽና ክትትል በማድረግ የውሸት ሪፖርት እንዲቆም ማድረግ ይገባል። በአጠቃላይ ለማህበረሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ቢሰራና አመለካከቱ ቢቀየር ስፖርቱ ወደ ነበረበት ክብሩና ታሪኩ ሊመለስ ይችላል። የመንግስትና የግል ድርጅቶች የተለያዩ ክለቦችን ቢይዙና ለስፖርቱ ድጋፍ ቢያደርጉ እድገት የማይመጣበት ምክንያት የለም። መንግስትም ስፖርቱ እንዲያድግ ከፈለገ ባሉት የስፖርት ጽህፈት ቤቶች መዋቅሮች ሙያተኛና ሙያን ሊያገናኝ ይገባል። ይህ ካልሆነ የሀገራችን የቦሊቦል ስፖርት ሊያድግ አይችልም።
አዲስ ዘመን:- ስፖርቱ እንዲያድግ የኢትዮጰያ ቦሊቦል ፌዴሬሽን በተጨባጭ ምን ምን ተግባራቶችን እያከናወነ ነው?
ወይዘሮ አሚና:- የፌዴራል ፖሊስ የቦሊቦል ክለብ ሲፈርስ ልጆቹ እንዳይበተኑ ፌዴሬሽኑ ከአቶ ጌታ ዘሩ ጋር በግል በመነጋገር በእርሳቸው ስር እንዲሆኑ አድርገናል። እርሳቸውም ለስፖርቱ ከፍተኛ ፍቅር ስላላቸው ልጆቹን በግላቸው ድጋፍ እያደረጉ በማሰልጠን ላይ ናቸው። ለእርሳቸው ከፍተኛ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል። ሌላው ደግሞ የውሃ ስራዎች የቦሊቦል ክለብ ፈርሶ ነበር። ሆኖም ድርጅቱ ክለቡን እንዲይዝ በመነጋገር እንደገና እንዲቋቋም ተደርጓል። የተለያዩ ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶችን በማፈላለግ ስፖርቱ የሚደገፍበት መንገድ እያመቻቸን እንገኛለን፡፡ ለአብነትም ሀበሻ ሲሚንቶ የቦሊቦል ስፖርትን የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ስፖንሰር አድርጎልናል። በአጠቃላይ ፌዴሬሽኑ ስፖርቱ እንዲያድግ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ሲሆን፤ አሁን ላይ ባለሙያው እያንቀላፋ በመሆኑ ከእንቅልፉ ነቅቶ ስፖርቱን ለማሳደግ ከፌዴሬሽኑ ጎን እንዲቆም ያስፈልጋል። ፌዴሬሽኑም ስፖርቱን ለማሳደግ የተሻለ ሀሳብ፣ ክህሎትና እውቀት አለኝ ብሎ ለሚመጣ ለማንኛውም ሙያተኛና ስፖርቱን መደገፍ ለሚፈልግ ዜጋ በሩ ክፍት ነው። ስለዚህ ፌዴሬሽኑ ብቻውን ምንም ለውጥ ሊያመጣ ስለማይችል ሙያተኛውና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ማህበረሰቡ ለስፖርቱ እድገት ሲሉ ከፌዴሬሽኑ ጎን ሊቆሙ ይገባል።
አዲስ ዘመን:- ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፡
ወሮ አሚና:- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011
በሶሎሞን በየነ