በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት መገናኛ ብዙሃን ለሀገር ግንባታ ባላቸው ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ በቀረቡት መነሻ ጽሑፎች ቀድሞ በነበረው ስርዓት መገናኛ ብዙሃን በነፃነት እንዳይናገሩ ተሸብበው መቆየታቸውንና መንግሥትን የሚደግፉና የሚቃወሙ በሚል በሁለት ጎራ እንዲሰለፉ መድረጉም በወቅቱ ተነስቷል። አሁን ሃሳብን በነፃነት ለመግለጽ ምህዳሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሰፋበት ወቅት ቢሆንም የመገናኛ ብዙሃንን አሠራር የሚመለከት ግልጽ ህግ አለመኖሩ ኃላፊነት ለጎደላቸው ተግባራት በር መክፈቱም ይጠቀሳል።
በሌላ በኩልም የግልም ሆኑ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ጥቃቅን ነገሮችን በማሰብ ላይ ሳይሆን ዘላቂ ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽን መብት በአግባቡ ተጠቅመው ዘገባዎቻቸውን ሐላፊነት በተሞላበት መንገድ ማሰራጨት እንዳላባቸውም በወይይት መድረኩ ላይ ተነስቷል።
ያነጋገርናቸው ምሁራንም በሃሳቡ ይስማማሉ። በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል መኮንን መገናኛ ብዙሃን መንግሥትን የሚቆጣጠርና አቅጣጫን የሚያሳይ በመሆኑ አራተኛው መንግሥት እያልን ነው የምንጠራው፤ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታውም የሚወጣው ሚና ትልቅ ከመሆኑ አንጻርም በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚያውና በማህበራዊ ሽግግሮች ላይ ትልቅ ተጽህኖ አለው ይላሉ። ፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ኢትዮጵያ ከመቶ ዓመት ያልተሻገረ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ ያላት ብትሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለይም ከ1960ዎቹ ጀምሮ የተለያዩ ሐላፊነቶቹን ከመወጣቱም በላይ ከ1983 እስከ 1987 ዓ.ም ባሉት ዓመታት በተለይ የህትመት መገናኛ ብዙሃን እጅግ በጣም የተስፋፉበት፣ ብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች የታተሙበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከፌዴራሊዝም መጀመር በኋላ ያሉትን ሚዲያዎች በሁለት ከፍለን ብናያቸው መልካም ነው ያሉት የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አንዳንዶቹ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩባችውና ፍጭትየሚካሄድባቸው ለሀገር የሚጠቅም አጀንዳ የሚቀመጥባቸው ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ ልማታዊ በሚል ስም የመንግሥት አፍ ብቻ ሆነው የተለያዩ እይታዎቸን ሳያንጸባርቁ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውም ሚናቸውን ሳይወጡ የቀሩ መሆናቸውን ይናገራሉ። አሁን ከለውጡ በኋላም ቢሆን የተለመደ አሠራራቸው ውስጥ ነው ያሉት፤ ምክንያቱም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ መንግሥትን ከማገልገል ውጪ የተለያዩ ሃሳቦችን በማቅረብ ረገድ ክፍተቶች አሉባቸው። እንዲያውም ወደ ነፈሰበት የማዝመም ባህሪ ይታይባቸዋል ብለዋል።
ወቅቱ የግል የህትመትና የብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ቁጥር ያደገበት ነው፤ ነገር ግን ወደ አንድ ጎን ያደላ ሥራ ከመሥራት ባሻገር አገርን የሚገነባ ብሎም መገናኛ ብዙሃኑ ሦስተኛ መንሥግትነታቸውን የሚያሳይ ሥራ እየሠሩ አይደሉም ፤ በመሆኑም ስለብሄር ፣ስለ ቋንቋና ስለ ጎጥ የሚሰብክ መገናኛ ብዙሃንን በማቋቋም ሀገር መገንባት አይቻልም። መገናኛ ብዙሃን አሁንም ከዚህ ቀደም ሲፈሱበት በነበረው ቦይ ከመፍሰስ መቆጠብ አለባቸው ይላሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ አሁን ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ ያለው ማህበራዊ ሚዲያው ነው የሚሉት የፖለቲካ ምሁሩ ከመደበኛው መገናኛ ብዙሃን ይልቅ የማህበራዊ ሚዲያው ተጽዕኖ እየጎላ መምጣቱንና በማህበራዊ ድረ ገጽ በተጻፈ ጽሑፍ ሰዎች ይሾማሉ ይሻራሉ።
ምናልባትም ማለት የሚቻለው ማህበራዊ ሚዲያው ለሀገር ግንባታ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ አለመሆኑን ነው። የፖለቲካ ምሁሩ እንደሚሉት መገናኛ ብዙሃን በዕውቀትና በብቃት መመራት በፖለቲካውም በኢኮኖሚወም እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሊያስተነትኑ የሚያስቀምጡትን ጋዜጠኛ የእውቀት ልክ ማወቅና በሚችለው ልክ እንዲሠራ ማድረግ መገናኛ ብዙሃኑን ከችግር የሚያወጣ ግንባር ቀደም መፍትሔ መሆኑን ይናገራሉ። ጠባብ በመሆን የተወሰኑ ቡድኖችን ፍላጎት ከማስጠበቅ ይልቅ ሀገራዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ ሌላው ትኩረት ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ተናግረው ለምሳሌ ሲ.ኤን.ኤንን ብንመለከት ብዙውን ጊዜ የአንድ ፓርቲ አጀንዳን ነው ይዞ የሚንቀሳቀሰው።
ነገር ግን ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች የዴሞክራት ነው፤ የሪፐብሊካን እያሉ በአሜሪካን ጥቅም ላይ አይደራደሩም። በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንደሀገር የሚያስቡ በእውቀት ላይ የተመሰረቱ ቢሆኑ መልካም ነው። « መገናኛ ብዙሃንን መስርቶ ወደ ሥራ ለመግባት ከፍተኛ በጀት ይፈልጋል። እኛ ሀገር ደግሞ ገና ትላልቅ ድርጅቶችን የማቆሙ ባህል ገና ከመሆኑ የተነሳ ግለሰቦች ናቸው የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን እያቆሙና እየመሩ ያሉት። እነዚህ ግለሰቦች ደግሞ ቆመንለታል የሚሉት አንድ ቡድን ያላቸውና የገቢ ምንጫቸውም ይህ ቡድን ነው። ይህን የገቢ ምንጭ ያለማቋረጥ ለማግኘትም አሁን ባለው ሁኔታ የግድ አንድ ጠላት ይፈጥራሉ። ከዚያም እከሌ የእኔ ጠላት ነው እያሉ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ገንዘቡን ያገኛሉ። እንዲህ ያሉ መገናኛ ብዙሃን እንደ ሀገር በህዝቦች መካከል መለያየትን ከመስበክ ያለፈ ሚና አይኖራቸውም» ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃን የሁሉም ዓይነት ፍላጎቶች ልሳን ነው መሆን ያለባቸው። ስለዚህ ገቢ የሚያገኙበትን የተለያየ ስልት ቢቀይሱ መንግሥትም በተሻለ መንገድ እንዲሠሩ ህጎችን ቢያሻሽልና መሰል ሥራዎች ቢሠሩ አሁን ያለውን ለውጥ ወደ ተሻለ ነገር የማሻገር አቅማቸው ከፍተኛ ይሆናል እንደ ፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ገለጻ። ብሮድካስት ባለስልጣን ከዛሬ አንድና ሁለት ዓመት በፊት አሳሪ ህጎችን በማውጣት ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን አፍኖ ቆይቷል፤ ለውጥ ሲመጣ መጀመሪያ ነፃ ማድረግ የሚገባው መገናኛ ብዙሃኑን ነው። ታስረው የነበሩትን መገናኛ ብዙሃን መልቀቁ ሐጢያት ባይሆንም መንግሥት ግን እስከመቼ ነው መገናኛ ብዙሃኑን ፈትቶ እንደለቀቀ የሚቆየው ? የተለቀቁት መገናኛ ብዙሃንስ እስከምን ድረስ ነው የሚሄዱት ? የሚሉ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለባቸው። የማህበራዊ ድረ ገጽ ወታደሮች ቁጭ ብለው የሚጽፉትን የህትመትና የብሮድካስት መገናኛ ብዙሃኑ ወስደው ያስተጋባሉ። ሁኔታው በዚህ መልኩ ከቀጠለ ሀገር ይፈርሳል። ይህ ደግሞ እንደ አገር ይዞን የሚጠፋ በመሆኑ ብሮድካስት ባለስልጣንም ሆነ መንግሥት ህግና ስርዓት ሊያበጅለት ይገባል።
የብሮድካስት ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብረሃ ከዚህ ቀደም መገናኛ ብዙሃኖቹ በበጎ ነገሮች ላይ ብቻ ማተኮር፣ የሚፈጠሩ ክፍተቶችንና ህጸጾችን ያለመንካት፣ የአንድ አቅጣጫ ሃሳብን የመጨረሻ አድርጎ የመውሰድና የሃሳብ ልዩነትና ተቃርኖ ለሀገር ዕድገት አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት ያለመጓዝ ችግር እንደነበረባቸው ይገልጻሉ። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ብሮድካስት ባለስልጣን በአዋጅ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት በህዝብ ባለቤትነት የሚተዳደሩ (የመንግሥት) የምንላቸው፤ በግለሰቦች የሚቋቋሙ (የግል ወይም የንግድ)ና በህዝብ ተደራጅተው ህዝብ የሚመራቸውና ህዝብ የመረጃ ምንጭ ለሚሆንባቸው የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ፍቃድ ሰጥቷል።
እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ትላንት ከነበረባቸው የአንድ ወገን መረጃን የማሰራጨት ችግር ተላቅቀው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማሳየት ጥረት እያደረጉም መሆኑን ይናገራሉ። ነገር ግን መገናኛ ብዙሃኑ ሚዛናዊ መረጃ ከማቅረብ፤ በህዝቦች መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር ከማስቻል ፤ የህዝቦች ትልቁ እሴት የሆነው ሰላም እንዲጠበቅ፣ ሀገሪቱ የምትመራበት ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት እንዲከበር ከማድረግ አንጻር አሁንም ክፍተቶች አሉ ይላሉ። የማንኛውም መገናኛ ብዙሃን ሥራ ማስተማር፣ ማዝናናትና ማሳወቅ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ስለዚህ የህዝብን ሰላም፣ መቻቻልና አብሮነት እንዲሁም የሀገርን ሰላምና አንድነት መሰረት አድርገው መሥራት ያለባቸው ቢሆንም ይህን በማድረግ በኩል ችግሮች አሉ።
«መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት የሚገኝ ትርፍን አስበው ከተንቀሳቀሱ ስህተት ነው። እንዲህ ካለ ተግባር የሚገኝ ምንም ዓይነት ጥቅም ስለማይኖር ሀገርንና ህዝብን እናገለግላለን ተብሎ በተቋቋመ ሚዲያና በተወሰደ ፍቃድም ህዝብን ማናከስ ትርፉ መተላለቅ ከመሆኑም በላይ ከዚህ የሚያተርፍ ተቋም አለ ብለን አናምንም» ይላሉ ዳይሬክተሩ። ብሮድካስት ባለስልጣን በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ፕሮግራሞች ላይ ክትትል በማድረግ የማስተካከያ እና የአቅም ገንባታ ሥራዎችን የሚሠራው በሁለት መንገድ በሚያገኘው መረጃዎች ላይ በመመስረት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አንዱ አድማጭ ተመልካቾች በሚተላለፉ ፕሮግራሞች ላይ የሚያቀርቧቸው ቅሬታና ጥቆማዎች ሲሆን፤ ሌላው የባለስልጣኑ ባለሙያዎች በክትትልና (ሞኒተሪንግ) በመስክ ምልከታ መሆኑን ገልጸዋል።
«ከእውቀትና ከአስተሳሰብ የክህሎት ችግር በመነጨ በህዝቦች መካከል መጠራጠርንና ቅሬታን የሚፈጥሩ ጉዳዮች እየተዘገቡ ነው። የትኛውም መገናኛ ብዙሃን ፍጹም አይደለም። በሥራ ላይ ስህተት ሊያጋጥም ይችላል። ሆነ ተብሎ የሚሠሩ ከሆነ ግን መስመር እንዲይዙ የሚወሰድ ዕርምጃ እንዳለ ሆኖ፤ መነሻቸው የዕውቀት ወይም የክህሎት ክፍተት ከሆነ ለመገናኛ ብዙሃንና የሚዲያ ባለሙያዎች ስልጠናዎችንና የአቅም ማጎልበቻ መድረኮች ይፈጠራሉ» እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ። አቶ ገብረጊዮርጊስ አብረሃ ሚዲያዎችን ለመቆጣጠርና ለመደገፍ በ1999 ዓ.ም ስለወጣው የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ሲናገሩ “አሁን በሥራ ላይ ያለው የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ብቸኛ የብሮድካስት ሚዲያ በነበረበት ጊዜ የወጣ አዋጅ ነው።
ነገር ግን አሁን በተለምዶ የመንግሥት የሚባሉ በህዝብ ባለቤትነት የሚመሩ ከ10 በላይ የራዲዮና ዘጠኝ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሉ። ምንም የግል ብሮድካስት አገልግሎት ካልነበረበት ወቅት በመውጣት አሁን አሥራ ሁለት የግል ሬዲዮና አስራ ስምንት የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተከፍተዋል። በተጨማሪም አርባ ስምንት የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። ስለዚህ ነባሩ የብሮድካስት አዋጅ እነዚህን ሁሉ ለማስተዳደር አመቺ ስላልሆነ ከእነዚህ ዕድገቶች ጋር መጣጣም አለበት” ብለዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011
በየትናየት ፈሩ