የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማምጣት ሁለንተናዊ ጥረት በሚደረግበት በዚህ ጊዜ በተለይም የአገር በቀሎቹ ተሳትፎ እጅግ የሚፈለግ ነው። ኢንዱስትሪዎቹ ወደ ስራ ከመግባታቸውም በተጨማሪ አንዱ ሌላውን እየደገፈ ሲሄድ የሚፈለገው ውጤት ሊመጣ ይችላል። የስታርችና ሙጫ አምራች ናቸው፤ በዓመት እስከ 1 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ወጪን እያስቀሩ ነው፤ ከስታርችችና ሙጫ በተጨማሪ ማርቭል እንዲሁም አቢሲኒያ ቮድካን በማምረት ወደ ኮንስትራክሽን ዘርፉም ለመቀላቀል መንገድ ላይ ናቸው ያስካይ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ።
የኢንዱስትሪው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ይትባረክ እንደሚሉት ኢንዱስትሪው በተለይም የውጭ ምንዛሪን በማስቀረትና ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን አላምዶ በማሰራጨት በኩልም ሰፊ ተግባርን እያከናወነ ነው። እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ በተለይም እንደ አገር የሚያስፈልግን ኢንዱስትሪን ማቆም ብቻ ሳይሆን ጥራት ያላቸው ምርቶች ተመርተው በአገር ውስጥና በውጭ አገር ገበያ ተፈላጊ ያደርጋቸዋል፡፡
በዚህም የስካይ ለሚያመርታቸው ምርቶች ጥራት ከፍተኛ ትኩረት ከመስጠቱም ባሻገር የምርምርና ስርጸት ክፍልን (ዲፓርትመንት) በማቋቋም በየጊዜው ገበያው የሚፈልገውን ጥራት በማምጣት እንዲሁም የወደፊቱን በማሰብ ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስም እየሰራ ነው። «አገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን ለመደገፍ የሚደረግ ጥረት አለ፡፡ ሆኖም እንደ ሀይል አቅርቦት የመሰረተ ልማት ችግሮች አንዳንዴም የአገር ውስጥ ግብዓቶችን እንኳን በበቂ ሁኔታ አለማግኘት ከፍተኛ ችግር ነው፤ እነዚህ እንዳሉ ሆነው የአገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ችግር ከውጭ ከሚገቡት ጋር ተወዳዳሪ መሆን አለመቻል ነው፤ ይህ የሆነው ደግሞ መንግስት ለውጪዎቹ ባለ ኢንዱስትሪዎች ድጎማን ያዳርጋል ፤ ይህ ደግሞ ምርታቸውን በጥራትናበብዛት እንዲያመርቱ እድል ፈጥሯል። በመሆኑም ለአገር በቀል ኢንዱስትሪዎች የሚሰጠው ድጋፍና ማበረታታቻ መጨመር ይኖርበታል» በማለት ዋና ስራ አስኪያጁ ሀሳባቸውን ይሰጣሉ።
ዶክተር ሙላት አበጋዝ በጥራት፣ በኢንስፔክሽንና በሰርቲፊኬሽን የኢንዱስትሪ ዘርፉን በአማካሪነት የሚያገለግሉ ሲሆኑ፤ በሰጡት ሀሳብም የኢንዱስትሪው እድገት በሚጠበቀው ልክ እየሄደ አይደለም፤ ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ቢቻልም ዋና ዋናዎቹ ግን ብዙ ጥሬ እቃዎች ከውጭ የሚገቡ መሆኑና በአገር ውስጥ የሚመረቱትም አመርቂ አለመሆን ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ላይ ያለው የማወቅ የመረዳትና በስራ የመተርጎም ክፍተት፣ ኢንዱስትሪው ግዙፍ ገንዘብን (ካፒታልን) የሚጠይቅ በመሆኑ ከራስ አመንጭቶም ሆነ ከመንግስት ብድር ወስዶ በዘርፉ አለመሰማራት፣ የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ አለማግኘት ለዘርፉ አለመጠናከር ማነቆ መሆናቸውና በአገሪቱ ያለው የሀይል አቅርቦትመቆራረጥ ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ነው ያብራሩት።
አገሪቱ አሁን ላይ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፉ ለመሸጋገር ሰፊ ስራዎችን እየሰራች ቢሆንም ኢንዱስትሪው በሚፈለገው ልክ ተጉዟል ለማለት አይቻልም፡፡ ይህንን ዘርፍ በተሻለ ሁኔታ ለማጠናከርና በአገር ግንባታ ላይ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ለማድረግ ከባለሀብቱና ከመንግስት እንዲሁም ከሌሎች ብዙ ስራ ያስፈልጋል ይላሉ። ከባለሀብቱ የሚጠበቀው ተስማሚ ቴክኖሎጂ መርጦ የሰው ሀይሉን አደራጅቶና አብቅቶ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን እውቀት ይዞ መገኘት ሲሆን ፤ መንግስትም የውጭ ምንዛሪና የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግርን ፈትቶ የገበያ ትስስርን አጠናክሮ እንደ ማሽነሪና ሌሎች ኢንዱስትሪዎችን ሊያቆሙ የሚችሉ ግብዓቶች በወቅቱ እንዲገኙ ማድረግና የሀይል አቅርቦቱ እንዳይቆራረጥ በማድረጉ በኩል ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ይጠቅሳሉ።
በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ፖሊሲባለሙያው አቶ ደስታ ላምቤቦ በበኩላቸው በአገራችን ኢንዱስትሪያላይዜሽን በጣም ገና ከመሆኑ የተነሳ የአገር ውስጥ ባለሀብቱ ወደ ዘርፉ በሚፈለገው ልክ እንዳልተቀላቀለ ያስረዳሉ። መንግስት በተለይም በአገር ውስጥ የማይመረቱ የኢንዱስትሪ ምርቶችና ግብዓቶች እንዲመረቱ የተመረቱ ምርቶች ደግሞ በዋናነት ወደ ውጭ ተልከው ምንዛሪን እንዲያመጡ፤ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን በማበረታታት ላይ ነው፤ ምክንያቱም የፖሊሲ አቅጣጫው የሚያዘው በመሆኑ ነው ይላሉ አቶ ደስታ ። በሌላ በኩልም ፖሊሲው ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችና ግብዓቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ አቅጣጫ ከማስቀመጡም በላይ የማትጊያ ወይም ማበረታቻ ስርዓትንም ዘርግቷል፤ ይህ ግን አንዴ ተከናውኖ የሚያበቃ ባለመሆኑ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች እየገቡ አዳዲስ ምርቶችንም እያመረቱ ስለሚቀጥሉ የፖሊሲ ማሻሻያውም በየጊዜው እየተከናወነስለመሆኑ ደግሞ ይናገራሉ።
«አሁን ባለው ሁኔታ ኢንዱስትሪው በአገር ኢኮኖሚ ላይ ያለው ድርሻ በጣም አነስተኛ ነው፤ መንግስት ይህንን የማሳደግ አቅጣጫ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው ፤ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስም የተለያዩ ኢንስቲትዩቶች ተቋቁመው አገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን በማበረታታት፣ ተኪ ምርቶችን እንዲያመርቱ አስፈላጊውን ሁሉ በማመቻቸት ላይ ናቸው » እንደ አቶ ደስታ ገለጻ። ይህም ቢሆን ግን አሁንም ኢንዱስትሪው ገና ብዙ ርቀት መጓዝ አልቻለም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥም ለውጥ ያመጣል ተብሎ አይጠበቀም፤ ከሁሉም በፊት ግን የባለሀብቱም ሆነ የሌላው ማህበረሰብ አስተሳሰብ መቀየር አለበት፤ ይህም ሲባል በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ከማናናቅና ላለመጠቀም ፍላጎት ከማሳየት መውጣት ያስፈልጋል፤ ኢንዱስትሪዎቹም በጥራትና ዋጋ ላይ ከፍተኛ ትኩረት አደርገው መስራትና ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረብ ይኖርባቸዋል ይላሉ አቶ ደስታ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011
በእፀገነት አክሊሉ