መደዳውን በሰልፍ ከቆሙት መሃል አብዛኞቹ ወጪ ወራጁን በንቃት ይቃኛሉ። ጥቂት የማይባሉት ደግሞ በጋሪ የጫኑትን ሸጠው ለመሄድ የራሳቸውን ዘዴ እየተጠቀሙ ነው። በዚህ ስፍራ እርስ በርስ ለመደማመጥ ይቸግራል። ሁሉም ከሌላው ልቆ ለመታየት የሚያሳየው ጥረት የተለየ ነው። እያንዳንዱ ገበያ ለመሳብ የሚያደርገው ጥሪ አካባቢውን በደማቅ ድምጽ ሲያውከው ያመሻል።
በዚህ ምሽት ሽንኩርትና ቲማቲም ፣ አቮካዶ፣ ሙዝና ብርቱካን ፣ ፓፓያ ፕሪምና ማንጎ በጋሪያቸው ሞልተው መቆሚያ ጥግ የሚፈልጉ ነጋዴዎች የእግረኛውን ምቾት ይነሳሉ። አብዛኞቹም አመቺ ስፍራን ለማግኘትና ቦታን ለመሻማት መሯሯጣቸው የተለመደ ነው። እንዲህ ሲሆን ደግሞ ብዙዎቹ ስለሌሎች መኖር አይጨነቁም። ያለቅጥ የጫኗቸውን ሰፋፊ የእንጨት ጋሪዎች በፍጥነት እየገፉ ወደፊት ያልፋሉ። ይኸኔ መንገዱን የሚጋሩ መንገዶች በድርጊታቸው ይበሳጫሉ። መዋከብን ከማይሹ ጥቂቶች ጋርም ክፉ ደግ ቃላትን መመላለስ የተለመደ ነው።
ቲማቲም ጭነው ከያዙት ወጣቶች መሃል ደርሰው ድንገት ቆም ያሉት አዛውንት ከየትኛው እንደሚገዙ የተቸገሩ ይመስላል። በዓይናቸው ከወዲያ ወዲህ ሲያማትሩ ያዩ ነጋዴዎች እያዋከቧቸው ነው። እሳቸው ግን ለማንም ትኩረት መስጠት አልፈለጉም። ተረጋግተው ሲቃኙ ቆይተው ወደ አንደኛው ወጣት ጋሪ ጋ ቀረቡ። ይህን ያወቀው ባለቲማቲም የያዘውን አስማምቶ ለመሸጥ ቀጭኗን የኪሎ ሚዛን አነሳ።
ሁለቱንም እጆቻቸውን ከቲማቲሙ መሃል የላኩት ሽማግሌ አይነ-አዋጅ የሆነባቸው ይመስላል። አንዱን ይዘው ሌላውን እየጣሉ ነው። አረንጓዴውን ከቀዩ፣ ብስሉን ከጥሬው እያማረጡ ቢሆንም የልባቸው አልደረሰም። ከአሁን አሁን የሚገዙትን የኪሎ መጠን ይነግሩኛል ሲል የሚጠብቀው ወጣት በትዕግስት እያያቸው ነው። ሰውዬው ዕንቁላል እንጂ ቲማቲም የሚመርጡ አይመስልም። እያንዳንዱን በጥንቃቄ በእጃቸው በማንሳት እያስተዋሉ ወደ ጋሪው ይመልሳሉ።
ከሰውዬው ቀጥለው ቲማቲሙን ለመግዛት በጋሪው ዙሪያ ከተሰባሰብነው መሃል ጥቂቶቹ በድርጊታቸው እየተናደዱ ነው። ጊዜ ከመፍጀታቸው በላይ ከነጋዴው ጋር የያዙት ጭቅጭቅ አብሽቋቸዋል። ያም ሆኖ ግን አዛውንቱ ስለማንም የተጨነቁ አይመስልም። አሁንም አንዱን ከአንዱ እያማረጡ ማንገዋለሉን ቀጥለዋል። ከዚህ ሁሉ በኋላ ግማሽ ኪሎ ብቻ እንዲሸጥላቸው የጠየቁት ሰው መጨረሻቸው ከወጣቱ ነጋዴ ጋር ባለመስማማት መለያየት ሆነ።
ግርግሩ አልፎ ገዢዎች ቀለል ማለት ሲይዙ ከባለጋሪው ወጣት ጋር ጨዋታ ጀመርን። የቲማቲም ነጋዴው አይቼው ሞላ አዲስ አበባን ከረገጠ ድፍን ሰባት ዓመታት አስቆጥሯል። የከተማን ህይወት መልመድ የጀመረው ተወልዶ ያደገባትን የቦቅላ ቀበሌ ትቶ ደብረማርቆስ በገባበት አጋጣሚ ነበር። የዛኔ እናቱን በሞት ማጣቱና በቂ መተዳደሪያ ያለማግኘቱ ቀዬውን ርቆ ለመውጣ ምክንያት ሆነው።
አይቼው ደብረማርቆስ መዋል ማደር እንደጀመረ ከአንድ ሆቴል በብርጭቆ አጣቢነት ተቀጠረ። በወቅቱ የሚከፈለው ደሞዝ በወር ሃያ ብር ብቻ ነበር። ውሎው ለመናኸሪያ ቅርብ መሆኑ ግን ሻንጣዎችን በመሸከምና እንግዶችን በማስተናገድ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ አገዘው። ይህ አጋጣሚም ከሰዎች እንዲግባባ በር ከፈተለት።
የልጅነት ጉልበቱ ከመልካም ባህሪይ ጋር ታክሎ ወዳጅ ዘመድ ቢያበዛለት አካባቢውን ፈጥኖ ለመደው። ለትንሽ ትልቁ ታዛዥ መሆኑም በቀላሉ ተወዳጅ አደረገው። ተቀጥሮ የሚሰራበት ሆቴል ባለቤት መልካምነቱ ቢስባቸው ትምህርት ቤት ልከው ቀለም ሊያስቆጥሩት ቃል ገቡ። ይህን ተስፋ ያገኘው ታዳጊም ነገን እያሰበ ዛሬን በትጋቱ ቀጠለ።
አንድ ቀን ብርጭቆዎቹን አጣጥቦ ወደ መናኸሪያ ሲያማትር ከአንድ ጎልማሳ ጋር ተገናኘ። ሰውዬው በአካባቢው አልጋ መያዝ ፈልጎ ኖሮ ከአይቼው ፈጣን ምላሽ በማግኘቱ ተደሰተ። ይህ አጋጣሚም ጓደኝነታቸውን አጎልብቶ ቅርበታቸውን አጠናከረው። ቀናትን በሆቴሉ ያሳለፈው እንግዳ አይቼውን እንደልጁ እያሻሸ ይበልጥ ቀረበው። ኑሮውን ህይወቱንና የወደፊት ተስፋውን እየጠየቀም አሳቢነቱን አሳየው። ስለማንነቱ ምንም ሳይደብቅ የተናገረው አይቼው ሰውዬው የተሻለ ህይወት እንዳለ በነገረው ጊዜ ልቡ ሸፈተ።
ጎልማሳው ከሆቴሉ በሚከፈለው ሃያ ብር ደሞዝ በእጅጉ ማዘኑን ደጋግሞ ገለጸለት። በዚህ ብቻ መኖሩ በቂ አለመሆኑን ጠቅሶም እሱ ካለበት አገር በሁለት ሺ ብር እንደሚያስቀጥረው አሳመነው። እንዲህ ብዙ ብር ሲጠራ ሰምቶ የማያውቀው አይቼው በጎልማሳው አዲስ ዜና እንቅልፍ በአይኑ አልዞርበት አለ። ባመጣው ሃሳብ ቀልቡ እንደተሳበ የተረዳው ሰው ልጁን በቀላሉ ከእጁ እንደሚያስገባ ተማምኗል። አይቼውም ቢሆን ከተባለው ቦታ ደርሶ ገንዘቡን ሲቆጥርና በአንዴ ሀብታም ሲሆን እየታየው አገሩን ለቆ ለመሄድ ተጣድፏል ።
አንድ ማለዳ እንግዳው አይቼውን በአውቶቡስ አሳፍሮ ከአካባቢው ተፈተለከ። ከቀናት ጉዞ በኋላም ወደ አንድ ጠረፍ ደርሰው ማረፊያቸውን ከዛው አደረጉ። ጥቂት ቆይቶ እንጀራ ፈላጊው ቃል የተገባለትን ስራ ለመጀመር ጥያቄ አነሳ። ይህን ያወቀው አስቀጣሪም እጁን ይዞ ወደ አንድ የእርሻ መሬት ወሰደው። ከሌላ ሰው ጋር አገናኝቶም ማጭድና ሌሎች የእርሻ መሳሪያዎች እንዲሰጡት አደረገ ።
አይቼው የተባለው ሁሉ ሀሰት መሆኑን ለማወቅ ጊዜ አልፈጀበትም። ሰወዬው በእርግጥም አታሎታል። «ይከፈልሃል» ያለው ገንዘብና እየሆነ ያለው እውነታ ፍጹም የተለያየ ነው። አሁን ስራን ብሎ መሞኘት እንደሌለበት አውቋል። በተለይ ደግሞ ልክ እንደሱ ከቀያቸው ጥለው ስራ ብለው የመጡ አብዛኞቹ በወባ ታመው መውደቃቸው በእጅጉ አስደንግጦታል።
ቀናትን በስጋት ያሳለፈው ስራ ፈላጊ በአንድ የቀን አጋጣሚ አካባቢውን ጥሎ አዲስ አበባ ገባ። በስፍራው ሲደርስ ያጋጠመው ግርግርና የሰው ብዛት ቢያደናግረውም ተግባቢነቱ አግዞት ከብዙዎች ፈጥኖ ተላመደ። ውሎ ሲያድር ደግሞ የባዕድ ዘመዶችን አገኘ። ከእነሱ ተጠግቶ ቀናትን እንዳስቆጠረም በቀን ስራ ውሎ ራሱን ለማስተዳደር በህንጻ ግንባታ የቀን ስራ ተቀጥሮ ስራ ጀመረ ።ድንጋይ መሸከም፣ አሸዋና ሲሚንቶ ማቡካት፣ የግንበኛና የአናጺ ረዳት፣ መሆንን ለመደ።ይህ ሁሉ ድካምም አቅምና ጉልበቱን ፈተነው።
ዛሬ አይቼው በዕድሜው በስሏል። በልምድ ጎልብቷል። ይህ መሆኑ ደግሞ ህይወቱን ለመለወጥ ቆም ብሎ ማሰብ እንዳለበት እየጠቆመው ነው። አሁን በጀመረው ውሎ መግፋት እንደማይኖርበት ሲገባው ሌሎች አማራጮችን ያስባል። የልጅነት ህልሙ ሰርቶና ተምሮ ህይወቱን መለወጥ ነው። አግኝቶና ከብሮ ሌሎችን ማገዝ ነው። ይህ ደግሞ ከአካባቢው ጥሎ እንዲወጣ ያደረገው እውነታ ነውና ሁሌም ቢሆን ያስበዋል።
አንድ ቀን ስራ ውሎ ሲመለስ አንድ ሰው በድንገት አገኘው። ይህ ሰው ጥሩ ባህርይና የተለየ መግባባት ነበረው። ስለህይወት፣ ስለስራና ኑሮ ሲያጫወተው ቆይቶ አሁን ካለበት በተሻለ ዘበኝነት ሊያስቀጥረው እንደሚችል ነገረው። የቀን ስራ ውሎ ያደከመው አይቼው ይህን ሲሰማ ውስጡ ነቃ፣ የተነገረው ደሞዝና የስራ ባህርይ ማረከው። ከቅጥሩ በፊት ግን በግለሰቡ የተነገረው ማሳሰቢያ አስገራሚ ነበር።
ሰውዬው ለእሱ እንደነገረው ዘበኛ ትፈልጋለች የተባለችው ሴት የምትቀጥረው ሰው ምንም ዓይነት ገንዘብ እንዲኖረው አትፈልግም።ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ ተቀጣሪው በመሳሪያ መግጠምና መፍታት ተፈትሾና ተመዝኖ መግባት ይኖርበታል። ይህን የተረዳው አይቼው ሰውዬውን ተጠራጠረው። ከዚህ ቀደም እንደሆነውም መታለል እንዳማይኖርበት አመነ። ወዲያውም ሰባት ብር ብቻ እንዳለው ነግሮ ሌላውን በሱሪው ሰፍቶ ደበቀ። ሰወዬው አስከትሎት ጉዞ እንደጀመሩ ግን መንገድ አሳብሮ ከጥቅጥቅ ጫካ አስገባው። የተባለውን ስፍራ የሀሰት መሆኑን የገባው ወጣት ለዝርፊያ መታሰቡ ቢገባው በሩጫ ፈጥኖ እግሬ አውጭኝ ሲል አመለጠ ።
ከዚህ በኋላ አይቼው ከጊዜና አጋጣሚዎች ብዙ ተማረ። በዕድሜ መብሰሉም የስራ አይነቶችን እንዲለይ ምክንያት ሆነው። አሁን ወጣቱ ማለዳ ከአትክልት ተራ የሚገዛውን አትክልትና ፍራፍሬ በወቅቱ ዋጋ እየሸጠ ራሱን ያስተዳድራል።አብሮት ያደገው ተግባቢነትና ትዕግስትም ክፉውን በበጎ እንዲመልስ እያገዘው ነው። አንዳንዴ ደንብ አስከባሪዎች የያዘውን ይበትኑበታል። የአንዳንድ ደንበኞች ባህርይም ከአቅሙ በላይ ይሆንበታል።
በክፉና ደግ መንገዶች የተመላለሰው ወጣት ግን ሁሉንም እንደየአመጣጡ መመለስን ያውቅበታል። ሁሌም ባይሆን አንዳንዴ ለገበያ ያመጣው እንዳሰበው ላይሸጥለት ይችላል።ይሄኔ ከገዛው በታች ከስሮ ይሸጣል። አንዳንዴ ደግሞ እንደሙዝ ያሉቱ ውለው አያድሩለትም። ይህ ሁሉ ግን ለብርቱው ወጣት ምንም ሆኖ አያውቅም። ወቅት ያፈራቸውን እየመረጠ ለገበያ ያቀርባል። ነገን በተሻለ ያስባልና ከባዕድ ዘመዶቹ ተጠግቶ ለኮንዶሙኒየም ቤት ይቆጥባል። ከቀን ውሎው የተረፈውንም ባንክ ማስቀመጥን ለምዷል። የቀን ወጪውን ሸፍኖም እስካሁን ከ20 ብር በላይ መቆጠብ ችሏል፡፡
ባለጋሪው አይቼው ከሁሉም በላይ ድህነትን ለመበቀል ያለው ስሜት የተለየ ነው። ትናንት ተቀጥሮ የሰራበትን ህንጻ ነገ ደግሞ በራሱ ወዝና ጉልበት መገንባትን ይሻል። እንደሌሎች ባለሀብቶች ለመሆንም የዛሬው ብርታቱ ጠንካራ ዋስትና እንደሚሆነው ሲናገር በእርግጠኝነት ነው።