ሰው በማህበራዊ መስተጋብሩ ካጎለበታቸው እሴቶቹ ውስጥ አንዱ ተዛዝኖና ተሳስቦ መኖር ነው። መረዳዳት፣ አንዱ አንዱን መደገፍ፣ መተጋገዝ የበጎነት መገለጫዎች ናቸው።
በጎነት ከመልካም ሰዎች ልብ የሚፈልቅ ቅን አስተሳሰብና ተግባር በመሆኑ የሀሴት ማህደር ነው ልንለው እንችላለን። በጎ የተደረገላቸውንም፤ በጎ ያደረጉትንም ሰዎች ደስተኞች ያደርጋቸዋል፤ ለነፍስም ለስጋም እፎይታን ይጣል። ከአያት ከቅድመ አያቶቻችን ከወረስናቸው ኢትዮጵያዊ ጸጋዎቻችን አንዱ ይኸው መልካም አሳቢነት ነው።
አባቶቻችን ስለመልካምነት፣ ስለደግነት፣ ስለበጎነት፣ ስለቅንነት በምሳሌያዊ ንግግራቸው ሳይቀር አስተምረውናል። ‹‹ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፤ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም›› ብለው ሰብእናችንን ሞርደውታል። የዛሬው ‹‹የሀገርኛ›› አምድ ዝግጅታችን በበጎ አድራጎት ሥራ የተሰማሩ ወጣቶችን ተሞክሮ ያስቃኘናል።
ወጣቶቹ ከውስጣቸው ፈንቅሎ የወጣውን ሰውን የመርዳት ፍላጎት ከሌሎች የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከቀሰሙት ልምድ ጋር አጣምረው ወደ ተግባር የገቡ ናቸው። ‹‹ሀገር ፍቅር በጎ አድራጎት ድርጅት››ን መስርተው ደካሞችን፣ የአዕምሮ ህሙማንንና ጠያቂ የሌላቸውን የአካባቢያቸውን ነዋሪዎች መርዳት ከጀመሩ አምስት ዓመታትን አስቆጥረዋል።
ከድርጅቱ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወጣት ተስፋዬ አለማየሁ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል።
ተስፋዬና ጓደኞቹ በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ መሳተፍ የጀመሩት ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ነው። የዛሬውን ‹‹ሀገር ፍቅር በጎ አድራጎት ድርጅት›› ከመመስረታቸው በፊት ‹‹ሀ›› ብለው በድርጅት ውስጥ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት በስለእናት የሕፃናት መርጃ ማህበር እና በጌርጌሴኖን የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ነው።
ይሁን እንጂ ከዚያ በፊትም ቢሆን በየመንደራቸው ለተቸገሩ ሰዎች ቀድሞ በመድረስ ሰብአዊ ተግባራትን ይፈጽሙ ነበር። ጓደኛሞቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጡ በአጋጣሚ ተዋውቀው የራሳቸውን ማህበር ለማቋቋም የበቁ ቅን ልቦና ብቻ ያሰባሰባቸው ናቸው።
ወጣቶቹ ስለእናት የሕፃናት መርጃ ማህበር በየወሩ በሚያዘጋጀው የቡና ጠጡ መርሃ ግብር ላይ መገኘት ከጀመሩ ወዲህ ነው ግንኙነታቸው እየተጠናከረ የመጣው። የሥራ ክፍፍል እያደረጉ ያላቸውን ትርፍ ጊዜ በሙሉ ሕፃናቱን በመንከባከብ ያሳልፉ ነበር። በማዕከሉ ከሚረዱት ሕፃናት አንዳንዶቹ የአካል ጉዳትና የአእምሮ ህመም ያለባቸው ስለሆኑ ወጣቶቹ እንደየ ሕፃናቱ ችግር እየቀረቡ ይረዷቸዋል።
አንዳንዶቹም ወላጅ አልባ በመሆናቸው እንደ አባት እና እናት፣ እንደ እህትና ወንድም ፍቅር የሚሰጣቸው ሰው ያስፈልጋቸው ስለነበር ወጣቶቹ አዘውትረው ወደ ማዕከሉ በመሄድ ቤተሰባዊ ስሜት ያሳድሩባቸዋል።
ሕፃናቱን እያቀፉና እየደባበሱ በማጫወት ደስ እንዲላቸው ያደርጉ ነበር፤ ከዚህም ጎን ለጎን ስፖንሰሮችን በማፈላለግና ሌሎች የጉልበት ሥራዎችንም በመሥራት ጭምር ለድርጅቱ እገዛ ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ።
ወጣቶቹ በሰፈራቸው በሚገኘው ስለእናት የሕፃናት መርጃ ማህበር ብቻ ተወስነው አልተቀመጡም። ከላፍቶ ክፍለ ከተማ ወደ ጉለሌ ርቀው በመሄድ በበጌርጌሴኖን የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የተጠለሉ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አቅመ ደካሞች እየሄዱ ይጠይቁ ነበር። ልክ እንደሕፃናቱ ሁሉ ለእነርሱም እንክብካቤ ያደርጉላቸው ነበር።
ከዚያ በኋላ ግን ባገኙት ልምድ መሠረት በአካባቢያቸው የሚገኙ አቅመ ደካሞችን ለመርዳት ተስማምተው ይደራጃሉ። ማህበራቸው ሕጋዊ ስላልነበረ በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የማህበሩ አባላት ከኪሳቸው እና ከቅርብ ጓደኞቻቸው ገንዘብ ያሰባስባሉ።
በተጨማሪም ሽሮ፣ በርበሬ፣ ሽንኩርት የመሳሰሉ አስቤዛዎችን በማሰባሰብ እጅ እያዩ ለሚኖሩትና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የአካባቢያቸው ሰዎች ለአመት በዓል የምሳ ግብዣ እያደረጉ ደስ ብሏቸው እንዲውሉ ያደርጋሉ።
ለተወሰኑ ጊዜያት በዚህ መልክ የምሳ መርሀግብሮችን እያከናወኑ ጎን ለጎን የረዥም ጊዜ እቅዳቸውን ለማሳካት እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ።
የማህበሩ አባላት ብዛት እስከ ሰላሳ የሚደርስ ነው። አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ስለሆኑ ሥራቸውን የሚያከናውኑት በትርፍ ጊዜያቸው ነው። ቅንነት ያሰባሰባቸው እነዚህ ወጣቶች ሃሳባቸውን እውን ለማድረግ ሳይታክቱ ይሠሩ እንደነበር ተስፋዬ ይናገራል።
እናም ወደ አዲስ አበባ በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በመሄድ በጉዳዩ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ይመክራሉ። ጽሕፈት ቤቱም የያዙትን የተቀደሰ ዓላማ በመደገፍ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቢሮ እንዲያገኙና ቀበሌው እንዲተባበራቸው የድጋፍ ደብዳቤ ይጽፍላቸዋል።
እነርሱ ግን ቤት እስኪሰጣቸው ድረስ ቁጭ ብለው መጠበቅ አልፈለጉም። ለጊዜው የተሰጣቸውን እውቅና ተጠቅመው በተለይም ጀሞና አካባቢው በሚገኙ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ቤት ለቤት በመዟዟር ገንዘብ፣ ምግብ፣ አልባሳት በማሰባሰብ ለችግረኞች ድጋፍ ያደርጉ ጀመር።
አባላቱ ማህበሩን ወደ ድርጅት ለማሳደግ ከፌዴራል ሲቪክ ማህበራት ማደራጃ ባለሥልጣን ፈቃድ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው በመጨረሻም ይሳካላቸዋል። ‹‹ሀገር ፍቅር በጎ አድራጎት ድርጅት›› ሕጋዊ ፈቃድ ያገኛል።
በድርጅት መዋቅር መሠረት መሥራቾችና ድርጅቱን ሊመሩ የሚችሉ አካላት እንዲሁም የቦርድ አባላት ተቋቁመው ድርጅቱ ህልውናውን ያረጋግጣል።
ፍቃዱን ካገኙ በኋላ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ጽሕፈት ቤት በተሰጠቻቸው ትንሽ ቦታ ላይ የራሳቸው አንድ ቢሮና አንድ ዕቃ ማስቀመጫ ቤት በመሥራት አቅማቸውን ያጠናክራሉ። በቋሚነት ድጋፍ የሚያደርግላቸው አካል ባያገኙም በራሳቸው ጥረት ሀብት የማሰባሰብ ሥራ እየሠሩ ለበርካታ ችግረኞች መድረስ ይችላሉ።
ቁጥራቸው ሃያ የሚሆን አቅመ ደካሞችና ህሙማንን በድርጅቱ ውስጥ አቅፈው መርዳት ይጀምራሉ። ድርጅቱ በየወሩ ከሚያደርገው የአስቤዛ ድጋፍ በተጨማሪ አባላቱ ተራ አውጥተው በየሳምንቱ ቤት ለቤት እየሄዱ ቤታቸውን በማጽዳት፣ ልብሳቸውንና ሰውነታቸውን በማጠብ፣ ቡና በማፍላት ይንከባከቧቸዋል።
ተረጂዎችን እየተንከባከቡ እግረመንገዳቸውን ቋሚ ስፖንሰሮችንም የማፈላለግ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ይሯሯጣሉ። በጊዜያዊነት የሚያገኙትን ሀብት እያሰባሰቡ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለተረጂዎቻቸው እንደሚያደርሱ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ወጣት ተስፋዬ ተናግሯል።
አሁን ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር አብዛኛው ሰው ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጠ በመሆኑ እርዳታ የሚጠብቅ ነው የሚለው ተስፋዬ፤ ድርጅቱ በዋናነት አቅመ ደካሞችንና ረዳት የሌላቸውን እየለየ ይረዳል ብሏል።
ተረጂዎቹ የሚለዩት የአካባቢው ነዋሪዎች በሚሰጡት መረጃና የድርጅቱ አባላት በሚያደርጉት የማጣራት ሥራ የተረጋገጠ ሲሆን ነው። ድርጅቱ በቋሚነት ከሚረዳቸው ሃያ ሰዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ማረፊያ ቤት እንኳ በማጣት መንገድ ዳር ሸራ ወጥረው የሚኖሩ፤ አንዳንዶችም ተጀምረው በተቋረጡ ሕንፃዎች ስር የሚኖሩ ናቸው። በቀበሌ ቤት ውስጥ የሚኖሩትም ቢሆኑ ቤታቸው በላያቸው ላይ ሊፈርስ የተቃረበ ነው።
ተስፋዬ ለማሳያነት ስለአንዳንድ ሰዎች አሳዛኝ ሕይወት እንዲህ ይናገራል። ‹‹አንዲት አዛውንት ድንገት በገጠማቸው የጤና መታወክ ፓራላይዝድ ሆነው አልጋ ላይ ቀርተዋል። ገንዘብ ቢያገኙ እንኳን ሰርቶ መብላት የሚያስችል አቅም የላቸውም።
የምትንከባከባቸው አንድ ልጃቸው ነበረች፤ እርሷም በድንገት ታማ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች። እየመጣ የሚጠይቃቸውም ሆነ አጠገባቸው ሆኖ የሚረዳቸው ዘመድ አዝማድ የለም። ለነፍሳቸው ያሉ የአካባቢው ሰዎች በሚያደርጉላቸው ድጋፍ የሚኖሩ ናቸው። ቤታቸው የሚጠግነው አጥቶ በላያቸው ላይ ፈራርሷል።
ድርጅቱ ቤት የመጠገን አቅም ባይኖረውም የቀበሌው መስተዳድር ችግሩን ተረድቶ ቤታቸውን እንዲጠግንላቸው መረጃ የመስጠትና ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ የማደረግ ሥራዎችን ሠርቷል። ከዚህ ባሻገር ቀበሌው አቅም ካላቸው በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመጻጻፍ የዊልቸር ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል።
የድርጅቱ አባላት ተራ በተራ ወደ እኚህ እናት ቤት በመሄድ በዊልቸር የሚደርጉትን እንቅስቃሴ ያግዟቸዋል። ያም ብቻ ሳይሆን ልብሳቸውን በማጠብ፣ ቤታቸውን በማጽዳት፣ ምግብ በማብሰል፣ ቡና በማፍላት በተለየ መልክ ይረዷቸዋል።
ተስፋዬ አንድ የአዕምሮ ህመም ያለባቸው እናት በድርጅቱ ሲረዱ የነበረበትን ሁኔታም እንዲህ አስታውሷል። ‹‹ሴትዮዋ ሁልጊዜ ቤት ዘግተው የሚቀመጡ ናቸው። ማንም ሰው አይቀርባቸውም፤ የአካባቢው ሰዎችም ሆኑ ድርጅቱ የሚያደርጉላቸውን የምግብ ድጋፍ በራፋቸው ላይ ነው የሚያስቀምጡላቸው።
የአዕምሮ ታማሚዋ እናት ሲርባቸው ብቻ ቤታቸውን ከፍተው በመውጣት ምግቡን ይዘው ይገባሉ። የሴትዮዋ የጤና ሁኔታ እየከፋ ሲመጣ ድርጅቱ ከፖሊስ ጋር በመተባበር ወደ አማኑኤል የአእምሮ ህሙማን ሆስፒታል አስወስዷቸው ክትትል እንዲደረግላቸው አድርጓል።
ታማሚዋ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከዚህ ዓለም በሕይወት ሲለዩ ድርጅቱ ከተቀማጭ በጀቱ እስከ ሰባት ሺ ብር ወጪ አድርጎ የቀብር ሥነሥርዓታቸውን አስፈጽሟል›› ይላል ተስፋዬ።
በልብ ህመም የሚሰቃይ አንድ ሕፃን ልጅ ሕክምናውን በአገር ውስጥ ማድረግ እንደማይችል ውጭ አገር ለመታከም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚስፈልገው ለቤተሰቦቹ ተነግሯቸው በተጨነቁ ጊዜ ድርጅቱ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በማዘጋጀት ከፍተኛ እገዛ አድርጎለታል። የሕፃኑን ችግር ለለጋሽ ድርጅቶችና ለባለሀብቶች በማሳወቅ ድርጅቱ የተቻለውን ሁሉ ሲያደርግለት እንደነበር ሥራ አስኪያጁ ገልጿል።
ሕፃኑ ዛሬ በጣሊያን አገር ሕክምናውን በመከታተል ላይ ይገኛል። በጉሮሮ መጥበብ ምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል ምግብ መብላት ያልቻለ ታዳጊን ደርጅቱ እርዳታ በማሰባሰብ 20 ሺ ብር ወጪ ሸፍኖለት እንዲታከም አድርጎታል።
አሁን ድኖ ምግብ መመገብ መቻሉን ተስፋዬ ነግሮናል። ከዚህም ባሻገር ኮቪድ አስራ ዘጠኝ በተከሰተ ጊዜ ከአርቲስት ያሬድ ሹመቴ ጋር በመተባበር ሰማኒያ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች ድርጅቱ የአስቤዛ ድጋፍ አድርጓል። ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እጅ የማስታጠብና ኅብረተሰቡ እራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲሠሩ እንደነበር አስታውሷል።
አንዳንድ ተረጂዎች መንቀሳቀሻ ገንዘብ ቢያገኙ ሠርተው የመኖር ፍላጎት አላቸው የሚለው ወጣት ተስፋዬ፤ ሁለት እናቶች ስንደዶ መግዣ ተሰጥቷቸው እንደ ሰፌድ፣ ሌማት የመሳሰሉ የእደ ጥበብ ውጤቶችን እየሠሩ እራሳቸውን የመርዳት ሙከራ ላይ መሆናቸውን ተናግሯል። የሀገር ፍቅር በጎ አድራጎት ድርጅት የተመሠረተበትን አምስተኛ ዓመት መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ለማክበር በዝግጅት ላይ መገኘቱን ተስፋዬ ገልጾልናል።
ከመንግሥት አካላትና ከአርቲስቶች የክብር እንግዶችን በመጋበዝ ቋሚ ስፖንሰሮችን ለማፈላለግ አጋጣሚውን እንደሚጠቀሙበት ተናግሯል። በዕለቱ አምስት አመት የተሠሩ ሥራዎች በዶክመንተሪ ፊልሞች የሚቀርቡ መሆናቸውንም ገልጿል።
ድርጅቱ እስከ አሁን አቅመ ደካሞችን በምግብ ለመደገፍ የግለሰብ እና የድርጅት በሮችን እያንኳኳ የሚያገኛትን ገንዘብ እንደ ማካሮኒ፣ ፓስታ፣ ሩዝ፣ ዘይት የመሳሰሉትን ለዕለት የሚደርሱ አስቤዛዎች እየገዛ ያድላቸዋል።
ወደ ፊት ግን ድጋፍ የሚስፈልጋቸውን የኅብረትሰብ ክፍሎች በአንድ ቦታ አሰባስቦ የመረዳት እቅድ እንዳለው የገለጸው ሥራ አስኪያጁ ለዚህም ሰፋ ያለ ቦታ እንደሚስፈልጋቸው ተናግሯል። የሚመለከተው አካል ቦታ ቢሰጣቸው የለጋሾችን ቁጥር በማሳደግና ቋሚ ስፖንሰሮችን በማፈላለግ ለበርካታ ችግረኞች ተደራሽ መሆን እንደሚቻል ተስፋዬ ተናግሯል። ለዚህም የመንግሥት ትብብር ያስፈልገናል ብሏል።
‹‹በጎነት ለራስ ነው›› የሚለው ተስፋዬ፣ ወጣቶች በየአካባቢያቸው ያሉ አቅመደካሞችን በተለያየ መንገድ ሊረዷቸው ይገባል ይላል።
እገዛ ለማድረግ መደራጀት የግድ አይደለም ያለው ተስፋዬ ዜብራ መሻገር የሚቸገሩትን አቅመ ደካሞች በማሻገር፣ ውሃ መቅዳት ለማይችሉት በመቅዳትና በመላላክ ማገዝ ይቻላል ብሏል። ከተቻለ ግን ወጣቶች በየአካባቢው እንዲህ ዓይነት ማህበራትን እያደራጁ የተቸገሩ ወገኖችን የመርዳት ልምድ ቢያዳብሩ በሚሠሩት መልካም ነገር የህሊና ርካታ እያገኙ የብዙዎችን ችግር መቅረፍ ይችላሉ ብሏል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 /2014