የመተሐራ ከተማ- የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራትን የማስጠበቅ ጉዞ

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ በትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ላይ ልዩ ትኩረት አድርጋ እየሠራች ትገኛለች። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደ ሀገር የነበሩት የትምህርት ስብራቶችና የጥራት ጉድለቶች በተለያዩ ርምጃዎች የሚታዩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ጥብቅ ቁጥጥር ያለው የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት፣ ጥራት ያለው የትምህርትና የቴክኖሎጂ ተደራሽነት፣ የመሰናዶና የከፍተኛ ትምህርት የመግቢያና የመውጫ ፈተና ደረጃን የማውጣትና የማሻሻል አሠራሮች መተግበር ደግሞ ለእዚህ እንደማሳያነት የሚጠቀሱ ናቸው።

እነዚህ ርምጃዎች እንደ ሀገር የመምህራንና የተማሪዎችን የብቃት ደረጃ ያመላከቱ ከመሆኑም በላይ ተከታታይ ጥበቅ ርምጃዎች መውሰድ እንደሚያስፈልግ ያመላከቱም ጭምር ናቸው። በተለይ እያንዳንዱ ክልል እና የከተማ አስተዳደር ከእዚህ ቀደም ከነበረው የመማር ማስተማር፣ የትምህርት ተደራሽነት እና የቴክኖሎጂ ቅንጅት ጋር የተያያዙ አዳዲስ ውጤታማ ስልቶችን መተግበር እንዳለበት ያሳዩም ነበሩ። በእዚህ ምክንያት አሁን ላይ የተሻለ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በዘርፉ ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው።

ከላይ ላነሳነው ሃሳብ ምሳሌ ከሚሆኑ ከተሞች ውስጥ አንዱ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ስር የምትገኘው የመተሐራ ከተማ ነች። በከተማዋ በሚገኙ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በአስተዳደሩ ልዩ ስልት ተነድፎ በተግባር ላይ እየዋለ ይገኛል። ይህ ስልት በልዩ መልኩ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት እና ጥራት ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑን የትምህርት ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊዎች ይናገራሉ። የዝግጅት ክፍላችንም ያሉትን ለአንባብያን እንዲህ አሰናድቶታል።

አይናለም ተፈሪ የመተሐራ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በዘንድሮው ዓመት ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚሆን ትምህርት ቤት ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት መገንባት ተችሏል። ከእዚህም በተጨማሪ ከቅድመ አንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ለሚደርሱ ተማሪዎች የምግብ ፕሮግራም ይዘጋጃል። ይሄ የምግብ ፕሮግራም አንድ ተማሪ እንዳያቋርጥ ከማገዙም ባሻገር በምግብ ምክንያት ልጆች እንዳያረፍዱ በማሰብ የሚዘጋጅ ነው። የምገባ ፕሮግራሙ ሳይቋረጥ ዓመቱን በሙሉ የሚዘጋጅም ነው።

በእዚህ የምገባ ፕሮግራም ምክንያት አምስቱንም ቀን ከሰኞ እስከ ዓርብ ውጤታማ ሆነናል። በውጤቱም ልጆቹ ምግቡን ስለሚፈልጉ አያረፍዱም፤ በጊዜ ይመጣሉ። በተለይ ጻናቶች እረፍት ሰዓት ጭምር ምግብ ይቀርብላቸዋል። ይህም ተረጋግተው እንዲማሩ እና ትኩረታቸው ትምህርት ላይ እንዲሆን አድርጓል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በተለይ ሰባት እና ስምንተኛ ክፍል ያሉትን ጎበዝ ተማሪዎችን በመለየት ስፔሻል ትምህርት ቤት በመክፈት በልዩ ሁኔታ እንዲማሩ እየተደረገ ነው። እዚህ ፕሮግራም ውስጥ ተማሪዎች ለመካተት በውጤት ከመለየት ባሻገር ልዩ ፈተና እንዲወስዱ ይደረጋል። በጣም ጎበዝና ልዩ ክህሎት ያላቸው ሲሆኑ ነው በፕሮግራሙ እንዲታቀፉ የሚደረጉት። በተጨማሪም ፕሮግራሙ ተማሪዎቹን የሚያስተምሩ መምህራን ጭምር ብቃታቸው በፈተና የሚለይበት ነው።

‹‹በዘንድሮ ዓመት እየተፈተኑ ያሉ 12ተኛ ክፍል ተማሪዎች ተለይተው በልዩ ሁኔታ ክትትል እንዲደረግባቸው አድርገናል›› ያሉት አይናለም፤ የመተሐራ ከተማ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆኑት እነዚህ 145 ተማሪዎች ምግብ፣ መኝታ እና አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን በማቅረብ ማታም ቀንም ላይብረሪ እንዲያጠኑ እና በመምህራኖቻቸው ክትትል እንዲያገኙ ስለመደረጉም ያነሳሉ። ይህንን ስልት ተግባራዊ ማድረግ የተፈለገበት ምክንያትም በ2014 እና በ2015 ዓ.ም እንደ ከተማ ዝቅተኛ ውጤት በመመዝገቡ በመሆኑ የተቀረጸ ሞዴል እንደሆነም ያስረዳሉ።

የተመረጡት ተማሪዎች እስከ ፈተናው ቀን የሚያጠኑ ሲሆን፤ በተለይ ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ክትትል ሲደረግባቸው የቆዩት ከ40 በላይ ተማሪዎች ከተማዋን እንደሚያስጠሩና ወጤታማ እንደሚሆኑ ይጠበቃል ይላሉ። ቀሪዎቹ ደግሞ ለፈተናው ሁለት ወራት ሲቀሩት ከተማሪዎቹ ጋር ተቀላቅለው እንዲማሩ ማድረግ መቻሉን ይናገራሉ።

ይህንን መንገድ መከተል ያስፈለገበትን ምክንያት ያብራሩት ኃላፊዋ፤ ካቻምና የተመዘገበውን ውጤት ለመቀልበስ እና ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው። በተጨማሪም ወደ ዩኒቨርሲቲ ሄደው ሲፈተኑ እንዳይደናገጡ፣ አድሮ መብላቱን መጠጣቱን እንዲለማመዱት ለማድረግ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። አክለውም ይህ እድል ተማሪዎች አንድ ላይ በሚሆኑበት ወቅት በጋራ ተረዳድተው ማጥናት እንዲችሉና ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላቸዋልም ይላሉ። ስልቱ ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ እና በሌሎች ጉዳዮች ሃሳባቸው እንዳይበተን ያደርጋልም ባይ ናቸው።

የተማሪዎች ምገባ በከተማዋ በአጠቃላይ አራት ሺህ 312 ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚናገሩት ኃላፊዋ፤ የምገባ ፕሮግራሙ ቀደም ብሎ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ የተጀመረ እንደነበርና ዘንድሮ ግን በተለየ ሁኔታ የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ አድርጎ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ሳይቋረጥ እንዲቀርብ የተደረገ ስለመሆኑም ያነሳሉ።

“በመተሀራ ከተማ እንደ አጠቃላይ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ስምንት ትምህርት ቤቶች አሉ” ያሉት የትምህርት ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊዋ አይናለም፤ ከአንድ እስከ ስምንት የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች አምስት መሆናቸውን ይገልጻሉ። አክለውም ከሁለተኛ ደረጃ እስከ መሰናዶ ያለውን የሚያስተምር ደግሞ (ከ9 እስከ 12) አንድ ትምህርት ቤት መኖሩን ያስረዳሉ። እነዚህ በከተማ አስተዳደሩ ስር በመንግሥት ትምህርት ቤት የሚተዳደሩ ስለመሆናቸውም ያብራራሉ። ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ የግልም የመንግሥትንም በድምሩ ሰባት ሺህ 213 ተማሪዎች በመተሐራ ከተማ ይገኛሉ ይላሉ።

በመተሐራ ከተማ መንግሥት ከሚገነባው ትምህርት ቤት እና መሠረተ ልማት ባሻገር ማህበረሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ትምህርት ቤቶች መገንባት ጀምሯል። ለእዚህ ምሳሌ የሚሆን ፕሮጀክት አሮአዲ ቀበሌ ዜሮ ሁለት ቀጣና ሦስት የሚገኘው በአንድ ወር ከ11 ቀን የተጠናቀቀው ትምህርት ቤት ነው። ይሄ ትምህርት ቤት አዲስና በ41 ቀናት ውስጥ የተጠናቀቀ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ግንባታው እንዲፋጠን ያደረገው የማህበረሰቡ ተሳትፎና ከኦሮሚያ ልማት ማህበር ጋር በመተባበር ማህበረሰቡን መገንባት የቻለ በመሆኑ ነው ይላሉ። ይህ ትምህርት ቤት “ትምህርት ቤት የሕዝብ ነው” የሚለውንም በሚገባ ያሳየ እንደሆነ ይገልጻሉም።

“የአካባቢው ነዋሪ ድንጋይ አሸዋ ጨምሮ ጉልበት ያለው በጉልበቱ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ በመተባበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሠርቶ አጠናቆታል” ያሉት ኃላፊዋ፤ ግንባታው የተጠናቀቀው ትምህርት ቤት ከ500 ያላነሰ የአካባቢውን አባወራ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል። በቀበሌው የሚገኙ የሦስት ቀጣና ነዋሪ ተማሪዎችን ማስተማር እንደሚችልም ገልጸዋል። መሰል ፕሮጀክቶች በከተማዋ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በመጀመር የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንደሚሠራም አንስተዋል። በአሮአዲ ቀበሌ የተገነባው የማህበረሰብ አቀፍ ትምህርት ቤት ከግንባታው ባሻገር የሚቀሩ ለመማር ማስተማር ሥራው የሚረዱ ቁሳቁሶችን ማሟላት ሲሆን፤ ለእዚህም ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል። በእዚህ ምክንያት ትምህርት እንዳልተጀመረበትም ተናግረዋል።

ማህበረሰቡ በእዚህ የክረምት ወራት ውስጥ ሕዝብ “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን” በማለት ለራሱ ቃል ገብቶ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ ግንባታው በሁለት ወር ውስጥ የተጠናቀቀበት ምክንያትም ኅብረተሰቡ ከፊት በመሰለፉ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ። የኅብረተሰቡ ተሳትፎ በትምህርት ቤት ግንባታ ላይ ብቻ የተገደበ አለመሆኑንም ይገልጻሉ። በምሳሌነት ሲያነሱም በተማሪዎች ምገባ ላይ እንደሚሳተፍ ያስረዳሉ። የምግብ ፕሮግራም አቅርቦት ሕዝብ ያቀርባል የሚሉት አይናለም፤ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር የሚያስፈልገውን የምግብ ግብዓት ሁሉ ሕዝቡ ያቀርባል ብለዋል። ይህንን መሰል ተሳትፎ ማድረጉ ማህበረሰቡ ልጆቹ በትምህርት የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ስለሚፈልግ ጭምር መሆኑን ይናገራሉ።

በአስተዳደሩ እና በሕዝቡ ተሳትፎ የትምህርት ተደራሽነትን፣ ጥራትን እና ልህቀትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ቢሆንም ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ ከትምህርት ሚኒስቴር እና አጋር አካላት አሁንም ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውን የሚገልጹት ኃላፊዋ፤ በተለይ በእዚህ በያዝነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ትምህርት ቤት ሁሌም ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኘ መሆን ይኖርበታል። ነገር ግን በመተሐራ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የኮምፒውተሮች እጥረት ያለበት ነው። እናም እዚህ ላይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አበክረው ይናገራሉ።

“በአንደኛ ደረጃ ላይ በጣም እጥረት አለ” የሚሉት ኃላፊዋ፤ ምክንያቱን ሲገልጹ፤ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቅድሚያ ተሰጥቶ የሚሟላ በመሆኑ ነው ብለዋል። ይሁን እንጂ ተማሪዎች ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ቤት ድረስ ከኮምፒውተር እና ከቴክኖሎጂ ጋር መገናኘት አለባቸው። ተወዳዳሪነታቸው እየጨመረ በመሄዱም ከትምህርት መስጫ መሣሪያዎቹ ጋር መገናኘት የግድ እንደሆነም ያሳስባሉ።

“በሁሉም ትምህርት ቤቶች ኮምፒውተሮችን ለማሟላት ለሚመለከተው አካል ጥያቄ በተደጋጋሚ እያቀረብን ነው” የሚሉት ኃላፊዋ አይናለም፤ በትምህርት ቤቶች የአይሲቲ መማሪያ ቦታዎች ቢኖሩም በቂ ኮምፒውተር ባለመኖሩ ምክንያት ሁሉንም ተማሪዎች መድረስ አለመቻሉን ያነሳሉ። በመሆኑም መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እንደ ከተማ የኮምፒውተር መሣሪያዎች ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጥሪ ያቀርባሉ።

በበቂ ሁኔታ መሣሪያዎቹን ማሟላት የሚቻል ከሆነ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከሚሠሩ ሌሎች ሥራዎች ጋር ተደምሮ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የሚናገሩት አይናለም፤ ዘመኑ የዲጂታል አማራጭ ይዞ በመምጣቱ ተማሪዎች በጽንሰ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር እንዲደግፉት የሚያስገድድ ነው። እናም የሚመለከተው አካል ይህንን ተገንዝቦ በትኩረት እንዲሠራበትም ጠይቀዋል። ባለፉት ዓመታት ከትምህርት ጥራት ጋር በተገናኘ ያጋጠሙ ስብራቶችን ለመፍታት በትምህርት ቤቶች የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ሊሟላ ይገባል። በመሆኑም መንግሥት ልዩ ትኩረት በማድረግ ድጋፉን ማጠናከር አለበት ብለዋል።

በከተማዋ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከሚያስችሉ ተግባራት ውስጥ አንዱ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ መለየት መሆኑን የሚያነሱት የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊዋ፤ በመተሐራ ከተማ ከትምህርት ቤቶች ደረጃ ጋር በተያያዘ በየዓመቱ በመለየት ምደባ እንደሚደረግ ገልጸዋል። በእዚህም አንደኛው፣ ሁለተኛው፣ ሦስተኛ ላይ ያሉ ትምህርት ቤቶች መለየታቸውን አንስተዋል። በተለይ በቅድመ አንደኛ ደረጃ የሚመደቡ ትምህርት ቤቶች አንደኛ ደረጃ እንዲይዙ ከማድረግ አንጻር እየተሠራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በእዚህ ውስጥ ለማለፍ የሚፈልጉ ትምህርት ቤቶች ካሉ ከክፍሎቻቸው ምቹነት ባሻገር በግቢ ውስጥ የመጫወቻና የመዝናኛ ስፍራ ሊኖራቸው እንደሚገባም ያስገነዝባሉ። ለእዚህ ደግሞ የማህበረሰቡ ድጋፍ የላቀ ስለመሆኑም ያነሳሉ። እስካሁን በነበረው ጉዞም ኅብረተሰቡ ትምህርት ቤቶች የተሟላ ደረጃ እንዲኖራቸው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በትብብር እየሠሩ ስለመሆኑም ያብራራሉ።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You