‹‹እኔ ሁሌም የማየው ነገ አለኝ›› – ወይዘሮ ደጅይጥኑ አለነ

ብዙዎች በባህላዊ እውቀቶች ዙሪያ በሚሠሯቸው የምርምር ተግባራት ያውቋቸዋል። ዛሬ ጭምር ለሀገር እንዲተርፍ የሚያስችል ሰፊ ፕሮጀክት ይዘው እየሠሩ ይገኛሉ። ይህም ‹‹መድኃኒታማ ዕፅዋትን ማበልፀግ›› የሚል ነው። እውቀቱ እንዲሰነድ፣ ዕፅዋቱ እንዲጠበቁና ወደ ተግባር እንዲቀየሩ የሚያደርግ ሲሆን፣ ምርምሩ የራሳቸው ቢሆንም በኦፊሰር እንዲመራ ሆኖ ብዙዎች ተሳትፈውበት ሀገር እንድትጠቀምበት እየተሠራበት ያለ ነው።

ወይዘሮ ደጅይጥኑ አለነ ከሁለተኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ በመሆናቸው ሀገር የምትጠቀምበትን በሚገባ ለይተው ይሠራሉ። በተለይም ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ላይ በሚያስተምሩበትና በሚመራመሩበት ወቅት ትልልቅ የሚባሉ እስከ ዘጠኝ የሚደርሱ ምርምሮችን ለሀገር ያበረከቱ ናቸው። ይህ በቃኝ ሳይሉም አሁን ላይ ሕዝባቸውን ወክለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን የተለያዩ ቦታዎች ላይ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።

ዋና ሥራቸው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሆነው የሚያገለግሉበት ሲሆን፣ በተጨማሪነት ሴቶች በምርምርና መሰል መንገዶች መሳተፍ በብዙ መልኩ ያስጨንቃቸዋልና በምክር ቤቱ የሴቶች ኮከስ ፈንድ አፈላላጊ ሆነው የሚሠሩበት ነው። ሌላው በምክር ቤቱ የሚሠሩ ፕሮጀክቶችና የምርምር ሥራዎች ላይም የሚሳተፉበት ነው።

በእነዚህ ተግባራቶቻቸው የመረጣቸውን ማኅበረሰብ በብዙ መልኩ አግዘዋል። ለአብነት ውሃ የማያገኘውን ውሃ እንዲያገኝ፣ በጨለማ ውስጥ ይቆይ የነበረውን ማኅበረሰብ መብራት እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ብርሃናማው መንገድ እንዲቀላቀሉ ያደረጉ ናቸው። ጦርነቱ ባይገድባቸው ኖሮ ደግሞ ከዚህም የላቀ ሕልም ነበራቸው።

ደጅ ጠናሁ

ተወልደው ያደጉት ደቡብ ጎንደር ድባና ሴፍ-አጥራ በሚባል ቦታ ነው። ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ሲሆኑ ተቀማጥለው ያደጉ ናቸው። በዚያው ልክ እንደማንኛውም ልጅ የውጪ ሥራ ሳይቀር እየሠሩ ነው ያደጉት። በተለይም የአረምና የአጨዳ እንዲሁም መሬቱ በሚጎለጎልበት ጊዜ የእርሳቸው ድርሻ ከፍተኛ ነበር። ከቤተሰቡ ጋር ወጥተው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ፍጥነታቸው ደግሞ ከሁሉም የተሻለ በመሆኑ የቤት ውስጥ ሥራ እንኳን ቢኖር ለዚህኛው ቅድሚያ እንዲሰጡ ይደረጋሉ። በተጨማሪም የእነርሱ ሥራ ካለቀ በኋላ የአካባቢውን ሰው እስከማገዝ ይደርሳሉ።

ወይዘሮ ደጅይጥኑን ቤተሰቦቻቸው ሲወልዷቸው ስድስት ዓመት ሙሉ ቆይተው ነው። በዚህም ‹‹እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁ እርሱም ዘንበል አለልኝ›› እንዲል መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያቸው በብዙ ልመና እና ደጅ ጥናት ስለሰጣቸው ‹‹ደጅይጥኑ›› የሚል ስምን አውጥተውላቸዋል። በዚህም እርሳቸው ሳይቀሩ በስማቸው ይደሰታሉ። ምክንያቱም ደጅ መጥናት ያለውን ምላሽ በቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆን በራሳቸውም ዘወትር ያዩታልና።

የእንግዳችን በቤተሰብ የመወደድ ልኬታቸው መልከ ብዙ ነው። አባት ልጃቸው ትንሽ ከተማረች በኋላ የተሻለ ኑሮ ሊያኖራትና ሕይወቷ በደስታ የተሞላ እንዲሆን ይሻሉና እንድታገባ ምኞታቸው ነው። እናት ደግሞ እርሳቸው ያለፉበት ውጣ ውረድ አለመማር በእርሷ ላይ እንዲሆን ስለማይፈልጉ ልዩ ትኩረቷ ትምህርቷ ብቻ እንዲሆን ይፈልጋሉ። በዚህም ቤት ውስጥ ሳይቀር ብዙ ሥራ እንድትሠራ አይፈቅዱላትም። ይልቁንም ቁርስ ምሳና እራት አልጋዋ ላይ ተቀምጣ እንድትበላ ያቀብሏታል። ወንድምና እህቶቿም ቢሆኑ ለእርሷ የተሻለ ዕድልን ብቻ ነው የሚፈልጉት። እናም በምታደርጋቸው ማንኛውም እንቅስቃሴዎች ይደግፏታል፣ ነገዋንም ያመላክቷታል።

ባለታሪካችን በልጅነታቸው ለማያውቁት ሰው ታጭተው ነበር። ይህም ተግባር በአካባቢው ቋንቋ ‹‹ግጥግጥ›› በሚባለው ሥርዓት ውስጥ ያለፉበት ነው። ግጥግጥ ማለት ልጅህን ለልጄ የተባባሉት ቤተሰቦች በየተራ ድግስ እየደገሡ የሚጠራሩበትና ጮማ ቁርጡን፤ ጠላ ጠጁን በሠፊው በማዘጋጀት ቤተሰብ ለቤተሰብ እየተገናኙ የሚገባበዙበት የድግስ ሥርዓት ነው። እናም ተወዳጅዋን ደጅይጥኑን ገና ጨቅላ ሳለች አዝለው በመሄድ ለባሏ ቤተሰቦች ቃል ገብተው በግጥግጥ ተጋምደው ተመልሰው ነበር። ነገር ግን የግጥግጡ ሥርዓትና ሕግ በአባት ልጅ ወዳድነት እንዲፈርስ ሆኗል።

በባህሉ መሠረት ቃልን ማፍረስ የሚያስጠይቅ ቢሆንም በእነርሱ ዘንድ ግን ምንም ዓይነት ቅጣትና መሰል አለመግባባቶች አልነበሩም። ይልቁንም በስምምነት የተፈጸመ ነው። ምክንያቱም እንግዳችን በትምህርታቸው ውጤታማና የቤተሰቡን ስም አስጠሪ በመሆናቸው፣ ከወንዶቹ የላቀ ውጤት በየጊዜው በማስመዝገባቸው ማግባት እንደሌለባቸው አመኑ። ከዚያም መላ ዘየዱና ‹ልጃችሁ ካልተማረ በስተቀር የእኔን ልጅ ማግባት አይችልም› ሲል መለሱ። ባል የሚሆነው ቤተሰብ ይህንን ሃሳብ ከመቀበል በቀር ምንም አማራጭ እንደሌላቸው ሲረዱ ያለምንም ማቅማማት በሃሳቡ ተስማሙ። ጋብቻውም ተሰረዘ። ይህ ደግሞ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ወይዘሮ ደጅይጥኑም ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ሆኑ።

በፈተና የነጠረው ትምህርት

ባለታሪካችን በልጅነታቸው መሆን የሚፈልጉት መምህር ነው። ያ ካልተሳካላቸው ደግሞ ኢንጅነር የመሆን ፍላጎት ነበራቸው። በዚህም ፍላጎታቸው እውን ይሆን ዘንድ በብዙ ታግለዋል። ያላሳለፉት ውጣውረድም የለም። አንዱና ዋነኛው የማኅበረሰቡ ጫና ነበር። ማኅበረሰቡ ያልተማረ ሰው ስለሚበዛበት ለሴት ልጅ የሚሰጠው ግምት በእጅጉ ያነሰ ነው። ‹‹ሴት ልጅ ተምራ የት ልትደርስ ነው›› የሚል አስተሳሰብ ጎልቶ ይወጣል። ትንሽ የተማረው ደግሞ ‹‹ሴት ልጅ እዚህ ድረስ ከተማረች በቂ ነው›› የሚል አመለካከት አለው። ከስንት አንድ ነው እስከመጨረሻው ተምራ ሀገሯን ማገልገል ትችላለች ብሎ የሚያስበው። በዚህም ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ብዙ መሰናክሎች አልፈው ነው። ይህንን መቋቋም ያቃታቸው ሴቶችም ትምህርታቸውን እስከ ማቋረጥ ይደርሳሉ፡፡ እንግዳችንም ይኸው ጉዳይ ነው የገጠማቸው፡፡

ባለታሪካችን የትምህርት ጉዟቸው በአካባቢው ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን በቤተሰባቸው ጣልቃ ገብነት ጭምር ይፈተን እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህም ከእናት ወገን የሚመጡ ጫናዎች ነበሩ። እናታቸው በእርሳቸው የትምህርት ጉዳይ አይደራደሩም። የእርሳቸውን የነገ ዕጣ ፋንታ እንደ ቀደመ የራሳቸው የጨለማ ጉዞ ማድረግ አይፈልጉም። እናም ‹‹እኔ በልጄ ተስፋና ሕልም አለኝ›› ሲሉ ዘወትር ትምህርታቸው ላይ ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን ያበሳጫቸው ነበርና እነርሱ ምክር በሚሉት ሃሳብ ‹‹ልጅቷን ቆሞ ቀር ልታደርጊያት ነወይ፣ ትምህርት ትምህርት ስትይ እንዳታዋርዳችሁ›› እና መሰል ነገሮች ይሏቸው እንደነበር ይናገራሉ።

‹‹እናቴ በእኔ መቼም ቢሆን ተስፋ አትቆርጥም። እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ወጃ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስማር ጉዞው አንድ ሰዓት የሚፈጅ ስለሆነ ቀድማ በመነሳት ስንቅ ትቋጥርልኛለች›› የሚሉት ባለታሪካችን፣ አባታቸውም ብዙ ጫና እንደማያሳርፉባቸው እንዲያውም ማታ ላይ ለጥናት በሚል ኩራዝ እንደሚለኩሱላቸው፣ ጠዋት ለትምህርት ሲሄዱ ወንዶች እንዳይተናኮሷቸው በማለት በሌሊት ወጥተው እንደሚሸኙዋቸውና አንዳንድ ማንበብ የከበዳቸውን ነገር ጭምር በተማሩት ልክ እንደሚያግዟቸው ያስረዳሉ።

ወይዘሮ ደጅይጥኑ ከቤተሰቦቻቸው የሚደረግላቸው ድጋፍ በእጅጉ የጠነከረ በመሆኑ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለው የትምህርት አቀባበላቸው የደረጃ ተማሪ ሲያደርጋቸው የቆየ ነው። ሁለተኛ መውጣትን በፍጹም አያውቁትም። ከሁሉም ክፍል ጭምር አንደኛ በመውጣት ነው ጊዜያቸውን ያሳለፉት። ከዚያም ባሻገር ደብል በማለፍ በሁለት ዓመት ውስጥ ነው አራተኛ ክፍል የደረሱት። አምስተኛ ስድስተኛ ክፍልንም ቢሆን በጥሩ ውጤታማነት ነው የተማሩት። እንዲያውም አብዛኞቹ ሴት ጓደኞቻቸው ከአራተኛ ክፍል ስላቋረጡ አርባ ደቂቃ ሙሉ ከወንዶች ጋር ተፎካክረው እየሄዱ ነው ትምህርታቸውን በሰይፋጥራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ያጠናቀቁት።

ይህ ጉብዝናቸው ግን ከሰባተኛ ክፍል በኋላ አልቀጠለም። ምክንያቱም ቤተሰቡ ላይ የሚደርሰው ጫና ሲበረታ ለትምህርት በሚል ወደ አክስታቸው ጋር ወረታ ተላኩ። በእዚህ ቤት ቤተሰቡ በጣም ሀብታም ስለሆነ የማይመጣ ሰው የለም። በዚህም ለሰዎቹ የሚሆን ምግብ ማዘጋጀት ግድ ይላል። ይህ ደግሞ እንግዳችንን ከትምህርት ይልቅ ሥራ ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋቸዋል። ከዚያም የሚብሰው ደግሞ እነዚህ ቤተሰቦች ያልተማሩ በመሆናቸው የማንበብን ጥቅም አይረዱምና እርሳቸው ላይ ጫና ያሳርፉባቸዋል።

ከትምህርት ቤት መጥተው ላይብራሪም ሆነ ከጓደኞቻቸው ጋር ለማንበብ እና እውቀትና ክህሎታቸውን ለማሻሻል አይፈቀድላቸውም። በዚህም ቅድመ አንደኛ ደረጃ የነበረቸው የትምህርት ውጤት መቀጠል አልቻለም። ደረጃቸው ቀንሷል። በዚህ ሁኔታ ዓመታት አልፈው 12ኛ ክፍልን ቢያጠናቅቁም ያሰቡት ላይ መድረስ ግን አልቻሉም። በቀጥታ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ሕልማቸው በአጭሩ ተቀጨ፡፡ ውጤታቸው በግል ከፍለው ለዲግሪና ዲፕሎማ መማር ቢፈልጉም ተከራይተው መማር አይፈቀድላቸውምና ከአንዱ ወደ አንዱ ቤት ተዘዋውረው የትናንቱን ኑሮ እንዲኖሩ የሚያስገድዳቸው ሁኔታ እንዲገጥማቸው ሆኗል።

በትምህርታቸው ተስፋ ቆርጠው የማያውቁት ባለታሪካችን፤ በግል እየከፈሉ ዲፕሎማቸውን በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ መማር ችለዋል። ትናንትን ዛሬም ላለመድገምም ከሚኖሩበት ቤት ወጥተው ተከራይተው መማሩን ጀምረዋል። ይህ ውሳኔያቸው ብቻ መኖር ያለመዱት በመሆኑ ፍራቻ ቢፈጥርባቸውም በትምህርታቸው ግን ውጤታማ አድርጓቸዋል፡፡

ብዙም የትምህርት ግንዛቤው በሌለው ቤት ውስጥ ማደግ በርካታ ፈተናዎች አሉት የሚሉት ባለታሪካችን፣ ተከራይተው ሲማሩ ያላሳለፉት ችግር አልነበረም። አንዱ ደግሞ ገንዘብ ማጣት ነበር። ቤተሰቡ ምንም ሳያንሰው የእርሳቸውን የትምህርት ወጪ ከመሸፈን ባለፈ ምን ያስፈልጋታል ብሎ የሚልከው ተጨማሪ ገንዘብ የለም። እህል ሰፍሮ መስጠት እንጂ ገንዘብ መላክን እንደ ትልቅ ነገር አድርጎ ይወስደዋል። እህሉንም ጭምር ትዝ ብሎት የሚልክ አልነበረም። በዚህም ፆም የሚያድሩባቸው ጊዜያት እንደነበሩ አይረሱትም።

ሌላው ፆታዊ ትንኮሳ ሲሆን፣ አብረዋቸው ከአደጉት ሰዎች ሳይቀር ይህ አስተሳሰብ ይንፀባረቃል። በተለይም ገንዘብ አጥሯቸው ሲጠይቋቸው የሚያሳዩት ፊትና ያላቸው አመለካከት በእጅጉ የሚያናድድ ነበር። ግን ዓላማን ከግብ ለማድረስ የግድ መስዋዕትነትን የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉና እነዚህና መሰል ችግሮቻቸውን ተጋፍጠው በምትኖራቸው የእረፍት ጊዜ ተጨማሪ ሥራዎችን በመሥራት ጭምር ያንን የፈተና ጊዜ አልፈውታል። ትምህርታቸውንም ለማጠናቀቅ ችለዋል።

‹‹ከፍ ስንል ከፍታው በራሱ ችግሮችን ይፈታል። ጫናዎችም ይቀንሳሉ። አክባሪያችንንም እናበራክታለን›› የሚሉት እንግዳችን፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሲጀምሩ ከላይ የነበሩት ፈተናዎቻቸው በእጅጉ እንደቀነሱ ያነሳሉ። በተለይም ‹‹አትማሪ›› የሚለው አስተሳሰብ ከሁሉም ዘንድ ርቆ በምትኩ እንደእርሷ ሁኑ የሚለው ልምድ መሆኑን ያወሳሉ።

እርሳቸው ዲግሪያቸውን በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ እንደበፊቱ ታላቃቸውን ገንዘብ ላክልኝ ብለው አይለምኑም፣ እናትና አባታቸውንም ቀለብ ስፈሩልኝ፣ የክፍያ ገንዘብ ላኩልኝ እያሉ አይጨቃጨቁም። መንግሥት በራሱ ወጪ ዕድል ሰጥቷቸዋል። እርሳቸውም በሚከፈላቸው ደመወዝ ሌሎች ወጪዎቻቸውን መሸፈን ችለዋል። ይህ ደግሞ ነፃነት ያለው ተማሪ አድርጓቸዋልና ጥሩ ውጤት አምጥተው እንዲመረቁ ዕድል ሰጥቷቸዋል።

የመጀመሪያ ዲግሪ ውጤታቸው ደግሞ ለቀጣዩ ትምህርትም አነሳስቷቸዋል። በዚህም እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲን ሳይለቁና የትምህርት መስካቸውን የተለየ ሳያደርጉ አጠናቀዋል። ይህ ክፍያቸው ደግሞ የፈለጉትን የልጅነት ሕልማቸውን እንዲኖሩት አግዟቸዋል። እናታቸውን አኩርተው፣ አባታቸውን አስደስተው ዛሬ ላይ በአካባቢያቸው ጭምር ተደማጭ ለመሆን በቅተዋል። ለብዙ ሴቶችም አርዓያ ሆነዋል።

የሥራ ሀሁ

እንግዳችን ሥራቸውን አሀዱ ያሉት ለትውልድ ቀያቸው በሚቀርበው ጎንደር ውስጥ ባለው ብሉናይል ኮሌጅ ውስጥ ነው። ለዓመት ያህልም አገልግለውበታል። ሆኖም በእነርሱ አካባቢ ያለው ቅርንጫፍ በቂ ተማሪ ባለማግኘቱ የተነሳ እንዲዘጋ ሆነ። የዚህ ጊዜ ወይዘሮ ደጅይጥኑ ወደ ደቡብ ጎንደር ደራ ወረዳ አንበሳሜ የተሰኘ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተሸጋገሩ። በዚያም የተወሰኑ ዓመታት ቆዩ።

ባለታሪካችን ብዙ ጊዜ ትምህርት ቤት ላይ ሲመደቡ ራቅ ያለና መኪና እንደ ልብ የማይገኝበት አካባቢ ነበር የሚደርሳቸው። ሙያውን ስለሚወዱት ግን መቼም ከፍቷቸው አያውቅም። ይልቁንም በአይሱዙ ከሰው ላይ ሰው ተደራርቦ እየተረጋገጡ ሳይቀር ተጭነው ጥሩ ዜጋን ለማፍራት ይጣጣራሉ፡፡ ተተኪ ትውልድን የማፍራቱ ጉዳይ ግዴታቸው እንደሆነም አምነው የቻሉትን ያደርጋሉ። በዚህም ብዙዎች ያመሰግኗቸዋል።

ወይዘሮ ደጅይጥኑ በኮሌጁና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ካስተማሩ በኋላ በጋብቻ ምክንያት ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲን እንዲቀላቀሉ ሆነዋል። ይህ ግን ዝም ብሎ የተሰጣቸው ሳይሆን በብዙ ውድድርና ትግል ነው። እንዲያውም ሲያስታውሱት ሴት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ውድድሩን መሳተፍ አትችይም ተብለው ነበር። ወደ ክስ ከገቡ በኋላ ደግሞ ሌላ ሰበብ ተፈጠረባቸው። ይህም ከዚህ በፊት ምርምሮችን ያደረገ ሰው ነው የምንቀጥረው የሚል ነበር። ሆኖም አይበገሬዋ እንግዳችን ‹‹ማስታወቂያው ሲወጣ ይህንን አይልም፣ በሲቪል ሰርቪስ ሕግ መሠረት እኛን የማይጋብዝበት ምክንያትም የለም የሥራ ልምዴም ቀጥተኛ ነው›› ሲሉ ሙግታቸውን ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ድረስ በማቅረብ አጠናከሩ።

እስከመጨረሻው ድረስ በመታገላቸውም የዩኒቨርሲቲው የምርምር ክፍሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ፈተናውን እንዲፈትናቸው ተደርጎ ከሁሉም በልጠው አለፉ። ያሰቡት ደረጃንም ተቆናጠጡ። ግን በዚህ ሁኔታ መግባታቸውና ወንዶቹ ያሰቡትን ሰው አለማስገባታቸው ስላናደዳቸው የተለያዩ ጫናዎችን ያደርጉባቸው ነበር። ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን ሠርተው እንኳን የሚያቀርባቸው ወንድ እንዲሆን ይደረጋል። ይህ ካልተሳካ ደግሞ ሀሳቡ ይወሰድና በሌላ ወንድ ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ ይሆናል።

ይህና መሰል ጫናቸው በጣም የሚያበሳጫቸው እንግዳችን፣ አንድ ቀን ግን ይህ አይሆንም አሉ። ሥራቸውን ራሳቸው ማቅረብ እንዳለባቸው ተሟገቱ። ለዚያም በበቂ ሁኔታ ሌት ተቀን ተዘጋጁ። ዕድል ቀናቸውና መድረኩ ከምንጊዜውም የተለየ ሆነ። ወንድ ምርምር አቅራቢዎች ተረስተው የእርሳቸው ስም ገነነ። የእርሳቸው ምርምርም መነጋገሪያ ሆነ። እስከ ፕሮጀክት እንዲቀየርም ሀሳብ ቀረበበት። እንዲህ ዓይነት ሃሳብ የያዙ ተመራማሪዎችን ወደፊት አምጡ የሚል አቅጣጫም እስከመቀመጥ ደረሰ። ይህ ደግሞ ለእርሳቸው ተስፋ መለምለም የበለጠ ዕድል ሰጠ።

ምርምራቸው የብዙዎችን ሕይወት የሚዳስስና ሀገርን ከአለችበት ደረጃ አንድ ርምጃ የሚያራምድ ነበር። ምክንያቱም ሀገራችን በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሀብቷ የተሻለች ነችና እርሱን የሚቃኝ ነው። ባህላዊ ግን ጥበብ የተመላበትን እውቀት ወደ ተግባር የሚቀይር፣ ዕፅዋቶቻችንን የሚጠብቅና ተፈጥሯዊ የሆኑ መድኃኒቶች የሚያበልፅግና ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ የሚያስችል ነው።

አሁን ወደ ፕሮጀክትነት የተቀየረው ያጠኑት የምርምር ሥራቸው ‹‹መድኃኒታማ ዕፅዋትን ማበልፀግ›› የሚል ሲሆን፣ ፕሮጀክቱን ወደ መሬት ለማውረድና እየተሠራበት እንዲቀጥል ለማድረግ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር የፈጀ የፕሮጀክት ቀረፃ ሂደት ጠይቋል። በዚህ ውስጥ ባህልና ሀገር በቀል እውቀቶችን በማጣመር ወደ ዘመናዊ የመድኃኒት አጠቃቀም ሥራ መቀየር ነው። ይህ ደግሞ በተለይ እንደ እነ ቻይና፣ ኮሪያና ሕንድን ምን ያህል እንደጠቀማቸው ተናጋሪ አያሻንም። ስለሆነም በቂ የተፈጥሮ ሀብትና እምቅ የእውቀት አቅም ያለባት ሀገር ብትሠራበት አትጠቀምም ማለት ሞኝነት ነውና እርሳቸውም ይህንን በማድረግ በኩል አሻራቸውን አሳርፈዋል።

እንግዳችን በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ውስጥ ከማስተማር ባሻገር በምርምሩ ዘርፍ ሙሉ የሚባሉና የዳሰሳ ጥናቶችን ጨምሮ ምርምሮችን ከዘጠኝ በላይ አድርገዋል። ሦስት የሚሆኑ የሥልጠና ማንዋሎችንም አዘጋጅተዋል። ይህንን ሥራቸውን ሲያከናውኑ ደግሞ ከጀማሪ ተመራማሪነት እስከ የባሕል ጥናትና ምርምር አስተባባሪነት በመድረስ ነው።

እንግዳችን ዩኒቨርሲቲው ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ ቢቀጥሉም የመጣላቸው አማራጭ በቀላሉ የሚተውት አልሆነላቸውም። ሰዎች የበለጠ እንዳከበሯቸው ስለተሰማቸውም እምቢ ማለት አልቻሉም። ምክንያቱም የአካባቢያቸው ሰዎች እርሳቸውን የሚያዩበት ዓይን የተለየ ነው። በሙያቸው፣ በሥራቸውና በውጤታማነታቸው ይኮሩባቸዋል። የልጆቻቸው አርዓያ እንደሆኑም ይነግሯቸዋል። እናም የሰጧቸውን ዕድል አሻፈረኝ ማለት አልደፈሩም። ስለዚህም ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ለምርጫው ውድድሩ ወደ ትውልድ ቀያቸው አቀኑ። አሸንፈውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ተቀላቀሉ።

በዚህም ለአካባቢያቸው ለውጥ በብዙ ደከሙ። ውጤታማ ለውጦችንም አመጡ። ዋና ዋና ናቸው የሚባሉትም የውሃና መብራት ጉዳይ ናቸው። እነርሱን በተቻላቸው መጠን መፍትሔ እንዲኖራቸው አስችለዋል። ከዚያም በተጨማሪ በአካባቢያቸው ከእነርሱ አልፈው የሚፈሱ ሁለት ትልልቅ ወንዞች ጥቅም ላይ እንዲውሉና የዜጎችን የመልማትና በልማት የመጠቀም ዕድል ለማስፋት ፕሮጀክት ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነበር። ሆኖም አካባቢው ላይ በተፈጠረ ግጭት የተነሳ ያሰቡት ሳይሳካ ቀረ። ግን ተስፋ እንዳላቸው ይናገራሉ። ሰላም ከመጣ ራሳቸው ሰላሙ በቶሎ መረጋገጥ ካልቻለ ደግሞ ቀጣዩ ትውልድ እንደሚጨርሰው ያምናሉ።

ደጅይጥኑ ዛሬ

እንግዳችን አሁን የተለያዩ ምርምሮችን ያደርጋሉ። በተለያዩ ጉዳዮች ላይም ጥናቶችን ያቀርባሉ። ካቀረቡት ውስጥም በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ዙሪያ የሴቶችን ሚና የሚያሳየው አንዱ ነው፡፡ ይህም “በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሴቶች አካታችነትና እኩልነት በኮሪዶር ፕሮጀክት ልማቱ ላይ ምን ይመስላል የሚል ነበር”

ባለታሪካችንም በዘርፉ ላይ በርከት ያሉ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ አስተማሪ የሆኑ ጥናቶችን በማቅረብ ይሳተፋሉ። በምክር ቤት ውስጥም በቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑበትን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተሰጣቸውን በአግባቡ በማከናወንም ያገለግላሉ። ከዚያም ባሻገር ከምክር ቤቱ ሳይወጡ የሴቶች ኮከስ በሚገባ እንዲጠናከር ይሠራሉ። በተለይም የምክር ቤት አባላት የሆኑ ሴቶች አቅማቸው እንዲገነባና በምክር ቤቱ በሚወጡ አዎጆች ሕጎችና ፖሊሲዎች ላይ እንዲሳተፉ፤ ተጠቃሚነትና ተሳታፊ እንዲሆኑ ድጋፍ (ፈንድ) የማፈላለጉን ሥራ ከሌሎች የዘርፉ ሰዎች ጋር ያከናውናሉ፡፡ በርካታ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙም ያደርጋሉ፤ አድርገዋልም። በተጨማሪም በቋሚ ኮሚቴው ውስጥ የክትትልና ቁጥጥር ተግባርን፤ የልማት ድርጅቶችን እቅድ አፈፃፀም ይገመግማሉ፡፡ ገንቢና የሪፎርም ሐሳቦችን ያቀርባሉ።

የሕይወት ፍልስፍና

ባለታሪካችን አንድ አቋም አላቸው። ሰዎች በእውነትና በእውቀት ነገሮችን ማከናወን አለባቸው በሚለው። በዚህም ሁሌም ሥራቸውን የሚመዝኑት ከዚህ አንጻር ነው። እውነት ካለ ሥራችን ቀና መስመር ይይዛል። ነጋችን ብሩህ ይሆናል። መንገዶቻችን መሰናክሎች ቢኖሩባቸው እንኳን ስኬታችን ላይ ከመድረስ አይገድቡንም። ትውልድ በእኛ ጥላ እንዲራመድ ይሆንበታል። ሀገርም አሸናፊና አዳጊ ትሆናለች ብለው ያምናሉ።

እውቀትንም የሚተነትኑት ከዚህ አኳያ ነው። እውቀት ያለው ትውልድ አለቃውን ይቀንሳል፣ ሀገሩን ያበለፅጋል፣ ከዓለም እኩል መራመድ ይችላል። ተወዳድሮም ማሸነፍ ይሆንለታል። በስኬቱ ሌሎች እንዲሻገሩም ያደርጋል ብለው ያስባሉ።

‹‹እኔ ሁሌም የማየው ነገ አለኝ›› የሚሉት እንግዳችን፣ ሀገርን የሚመለከቱበት ጉዳይ የተለየ ነው። በተለይም የተማረው ኃይል ያድርግ የሚሉት ጉዳይ እጅጉን ይረቃል። በተሰጠን ችሎታና ፀጋ ልክ ካልተጠቀምንና ነገን ብሩህ ማድረግ ካቃተን ተጠያቂነታችን በትውልድ ብቻ አለያም በሀገር ደረጃ ብቻ የሚያበቃ አይደለም ብለው ያስባሉ። ተጠያቂነታችን ከሞትን በኋላም የሚቀጥል ነው የሚል አቋም አላቸው፡፡ ምክንያቱም ሥራ እንጂ ድሎት በፈጣሪ ዘንድ አይጠየቅም። ሥራ እንጂ ድክመትም በእርሱ ዘንድ አይታይም። እናም ነጋችን በሰማይም በምድርም ያማረ እንዲሆን ትውልዱ ላይ መሥራት ይጠበቅብናል። የተሰጠንን መክሊት ለፍሬ ማብቃት ይኖርብናል ይላሉ።

መክሊታችንን ስንጠቀምበትም ደግሞ ሀገራችንን ከፍ በሚያደርግ መልኩ ሊሆን ይገባል። ይህም የሚታየው ተተኪ ትውልድን ከማፍራት አንጻር፣ ከባህልና እሴት እንዲሁም ከተፈጥሮ ጥበቃ አንጻር ቢሆን የተሻለ ነው። ይህንን ስናደርግ ደግሞ ተሻጋሪና ሰውኛ እሳቤ ያለው ዜጋን እንፈጥራለን። ታማኝና አስተዋይ እንዲሁም በሥነምግባር የታነጸ ትውልድን እናበራክታለን። ሀገሩንም ፈጣሪውንም የሚወድ ለነገ አልሞ የሚሠራ ዜጋንም እናፈራለን የሚል አቋምም አላቸው።

ፍራቻን የታደገው ትዳር

እንግዳችን ባለቤታቸውን ያገኙዋቸው በአጋጣሚ ነው። ብዙ ጊዜያቸውን በትምህርት ሲያሳልፉ ‹‹ላግባሽ›› የሚል ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ያንን ለማድረግ ዝግጁ አልነበሩም። ይልቁንም ይህንን ጥያቄ ያቀረበን ወንድ በተለያየ መልኩ ከሥራቸው ያርቁታል። ቀረቤታቸውንም ይገድባሉ። በዚያ ላይ ፊታቸው የማይፈታ ዓይነት ሴት በመሆናቸው ደፍሮ እንኳን የሚጠይቃቸው ከስንት አንድ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ቀን የብቻ ሕይወታቸውን የሚያጠፋ ሀሳብ ከውስጣቸው መነጨ። ይህም ብቻቸውን መኖሩን እንዲያከትም የሚያደርግ ነው፡፡ የሆነ ሰው መጥቶ የሆነ ነገር ቢያደርገኝስ፣ ብታመምስና መሰል ነገሮች እያሉ አዕምሯቸውን የሚበጠብጠውን ጥያቄ በቃህ የሚል ነው። ይህም ማግባት አለብኝ የሚለው ሲሆን፣ ለዚህም ዕድል የሚያመቻቹ ተግባራትን ወደ ማከናወኑ ገቡ፡፡ አንዱ ወንዶችን የሚያርቁ ባሕሪያቶቻቸውን መቀነስ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ትዳራቸው የተባረከ ይሆን ዘንድ ወደ አምላካቸው መማጸን ነበር።

ይህ ምቹ ነገራቸው ደግሞ ለፈላጊዎቻቸው ቀና መንገድን አመላከተ። የዛሬውን የሁለቱን ልጆቻቸውን አባት ዮሴፍ (ዶ/ር)ን አገናኛቸውም፡፡ ይህ ሲሆንም ዕድሜያቸው 20 ቤትን ያልተሻገር በመሆኑ ብዙ ነገሮችን አመቻችቶላቸዋል። ከልጆቻቸውም ሆነ ከባለቤታቸው ጋር በቀላሉ እንዲግባቡ አድርጓቸዋልም።

የእንግዳችን ቤት ዛሬ በብዙ ነገር ሙሉ ነው። በተለይ በባለቤታቸው በኩል የሚደረግላቸው እንክብካቤ ሁሌም ደስተኛ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ነው። ሴት ነሽና ቀድመሽ ገባሽም አልገባሽም ቤቱን መምራት ያለብሽ አንቺ ነሽ አይባሉም። ርቀሽ መሄድ አትችይም ልጆቹን ማን ይጠብቃል የሚል ነገርም አይገጥማቸውም። በአጠቃላይ በጎዶሏቸው እየገባ የፈለጉትን እያደረገ ይጠብቃቸዋል። በተሰማሩበት ሥራ ውጤታማ እንዲሆኑም ይደግፋቸዋል። እናም ስለእርሱ ሲናገሩ ‹‹ምርኩዜ ነው›› ይላሉ።

መልዕክት

የሰው ልጅ አንዱ ለመስጠት አንዱ ለመቀበል ይፈጠራል፤ ከዚህ አንጻር ደግሞ ምሑራን የተለዩና የሚሰጡት ነገር ያላቸው ሰዎች ይመስሉኛል። እናም ስጦታቸውን መጀመር ያለባቸው ለትውልዱ የተሻለውን ሁሉ መርጦ ከመስጠት ነው፡፡ በመቀጠል ሀገራቸው ላይ ዐሻራቸውን ማሳረፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ሀገራቸው ከእነርሱ የምትፈልገው ብዙ ለዋጭ ሃሳቦችን ነው። ነገዋን እንዲያበሩላት ትሻለች። ከዚህ አንጻር ምን ያህሎቻችን እየሠራን ነው ከተባለ ምላሹ ለእያንዳንዳችን ይሁን? ይላሉ።

አክለውም የተማረው ኃይል ሀገርን ከሚሰብር ይልቅ መጠገኑ ላይ መረባረብ አለበት። በተለይም አሁን በሚታዩ ግጭቶች ዙሪያ መፍትሔ የሚያበጅ እንጂ ችግሩ እንዲባባስ የሚተጋ ሊሆን አይገባም። እርሱ ነቃ ብሎ ሀገሩን ቀና ማድረግ አለበት። ለዋጭ አጀንዳዎችን በየጊዜው መሰንዘር አለበት፡፡ ሀገር ውጤታማ በምትሆንበት የሥራ መስክ ላይ አተኩሮ ለለውጧ መሥራት ይኖርበታል ሲሉም የመጀመሪያ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።

ሌላው ያሉት ነገር ከውጪ የሚመጡ አጋዥ ድርጅቶችን መንግሥት በሚገባ ሊያያቸው ይገባል ነው። ድርጅቶቹ የራሳቸውን አጀንዳ ደብቀው በትንንሽ ነገር እኛን እንዲያሳስቱ መፍቀድ የለበትም። ድርጅቶቹ ድጋፍ ልስጥ ብለው ጥያቄ ሲያቀርቡ ቀድሞ አጀንዳ መስጠት የእኛ ጉዳይ መሆን ይገባዋል። እነርሱ በአሰቡት አጀንዳ ላይ ሳይሆን እኛ በሰጠናቸው ሃሳብ ላይ እንዲሠሩ መደላደልን መፍጠር ይጠበቅብናል ሲሉም ይመክራሉ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You