የወንበሩ ምቾት ሳይቀመጡ የሚገምቱት ነው። አንድ ቀን ቁጭ ብዬበት ዘላለም ቆሜ ልኑር የሚያስብል ዓይነት። ከጋዜጠኞች የቀረ ያለ አይመስልም። በግርምት ቆሜ ዙሪያውን አየሁ። ከዳንኤል ታደሰ እና አለም ቸርነት ጋር ዓይን ለዐይን ተገጣጠምን፤ ገረመኝ። በአይናቸው ጠርተው፤ በፈገግታ እያዩኝ ካጠገባቸው እንድቀመጥ ጋበዙኝ።
በአዳማ ከተማ በምግብ ዋስትና ራስን ስለመቻል ሥልጠና እየተሰጠ ነው። ሠልጣኞቹ በትክክልም ራሳቸውን በምግብ የቻሉ ይመስላሉ። መድረኩ ላይ በከረባት የታነቀ አንድ ጎልማሳ፤ ያዘጋጀውን የቁጥር መረጃ በፕሮጀክተር እያሳየ፤ ባለፉት አመታት በተሰሩ ሥራዎች በግብርናው ዘርፍ የተገኘውን ውጤት አመርቂነት ይገልፃል። አገሪቱ ራሷን በመመገብ ረገድ መሻሻሏን፤ ከአምና የነበረውን ከዘንደሮው ተመሳሳይ ወቅት ጋር በማነፃፀር በዘንድሮው ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዜጎችን መመገብ እንደቻለች ይሰብካል።
በርካቶች ከልክ በላይ ስለሚበሉ በቁንጣን እየተሰቃዩ መሆኑን ያስረዳል። ሀገሪቱን ራሷን ከመመገብ አልፋ፤ የእህል ምርቶችን ወደ ውጪ መላክ ስለመጀመሯ ይደሰኩራል። ያላደጉትም ፣ የማያድጉትም ከኢትዮጵያ መውሰድ ስላለባቸው ተሞክሮ ይዘላብዳል። ሠልጣኞቹ፣ አንዳንዶቹ ማስታወሻ እየያዙ፤ አንዳንዶቹ በገዛ ሃሳብና ጭንቀታቸው እንደተያዙ ያደምጡታል።
አብዛኞቹ ደግሞ ያደመጡት ይምሰሉ እንጂ ፌስ ቡክ ላይ ተጠምደዋል። እለቱ የሥልጠናው መጠናቀቂያ ነው። ለሠልጣኞችም የክፍያ ቀን ነው። የምመጣበትን አታውቁምና ነቅታችሁ ጠብቁ እንደተባለው ሁሉ ዛሬ ሠልጣኙ ሁሉ ንቁ ሆኗል፤ አሰፍስፏል። ላለፉት ሦስት ቀናት ዝም ጭጭ ብሎ የነበረው ሠልጣኝ ዛሬ አፉ ተከፍቷል።
ጠይቆ የማያውቀውን ሁሉ ይጠይቃል። ድንገት አንድ ድምፅ ጆሮዬ ውስጥ ገባ። የማውቀው መሰለኝ። ለማረጋገጥ ግን ድፍረቱን አጣሁ። እንደምንም እራሴን አደፋፍሬ ቀስስስ… ብዬ ዞርኩኝ። አየሁት። አዎ ራሱ ነው። አሌክስ ነው። ከአንድ የአዳራሹ ማዕዘን የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ ቁጭ ብሏል።
ሥልጠናው የገባው ይመስላል። ከአሰልጣኙ አፍ እየነጠቀ ሰማያዊ ማስታወሻው ላይ ይሞነጫጭራል። እስከማዋራው ቸኮልኩኝ። የዕረፍት ሰዓቱ አላደርስ አለኝ። ተቁነጠነኩ። የማደርገው ሳጣ ፌስ ቡክ ከፈትኩ። አሌክስ ቀጥታ መስመር ላይ ነው። ጊዜ አላባከንኩም። ‹‹አሌክስ፣ ገብቶሃል?›› ፈገግ ብሎ ‹‹አዎ በጣም›› ሲል መለሰልኝ እንዲያብራራልኝ ጠየኩት።
በሥልጠና መሃል ዕረፍት ሰዓት ላይ የዘርፉን እድገት በተጨባጭ ማስረጃ ብትንትን አድርጎ እንደሚተነትንልኝ ቃል ገባልኝ። መጽሐፉ እንኳን ‹‹ያመነ ይድናል›› አይደል የሚለው፤ እንዳንተ የአገሩን ተጨባጭ ሁኔታ የሚረዳ ሰው እኮ ነው የሚያስፈልገው!›› ልለው ፈልጌ ተውኩት። ብዙም ሳንቆይ የሻይ ዕረፍት የሚል ትዕዛዝ ተላለፈ። አብዛኞቹ ሠልጣኞች ቁርስ በልተው እንዳልመጡ በሚያሳብቅ መልኩ ተሽቀዳድመው ወጡ። ከተዘጋጀው ቁርስ በተወሰነ ርቀት ላይ ትርሲትና አሰፋን አየሁዋቸው። ውሏቸው አንድ ላይ ነው። ወሬያቸውም አንድ ዓይነት፤ ሁሌም ቢሆን እድገትና ልማት ነው።
ጠጋ ብዬ ማዳመጥ ጀመርኩ። ወሬያቸው መሃል መዲናዋ ላይ ሲገነባ ስለተመለከቱት ህንፃ ነው። የአገሪቱ ልማት ከሚጠበቀው በላይ እየተጓዘ እንደሆነና ህንጻዎቹ ወደ ሰማይ እተመነደጉ ፈጣሪ በቃህ ብሎ ካላስቆመና እንደ ባቢሎን ዘመን ቋንቋችንን ካልደበላለቀው ከፍታውን የሚያስቆም ሃይል እንደሌለ በተመስጦ ያወራሉ። አርሶ አደሮች ከግብርናው ሥራ ጎን ለጎን ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በመደረጉ፣ አንዳንዶቹ የማዳበሪያ ብድርና የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ደብዳቤን ሳይቀር በእንግሊዘኛ ቋንቋ አሳምረው ፅፈው መጠየቅ መጀመራቸውን ይነጋገራሉ። ሥልጠናው ላይ የሰሙትን የግብርናው ዘርፍ ሁለት አሃዝ እድገት እየደገሙ ለማን እንደሆነ ባላውቅም አድናቆት እና ምስጋና ያዥጉደጉዳሉ። በዚህ መሃል ድንገት እዮብ መጣ። እዮብ አገሩን የተሻለ ለማድረግ ራሱን የሚሰጥ ሰው ነው።
ለአገሩ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ፣ አቃተኝ፣ በዛብኝ አይልም። ቋንቋ አጠቃቀሙ፣በሳቢነቱ፣ በበሳልነቱ አይታማም። ለሁሉ ፈጣን ነው። ላመነበት ይጮሃል። ሃሳቡን በጩኸት ማስረዳት ይቀናዋል። በአስተሳሰብ የተለየውን ጭምር ያከብራል።የሚመስሉትን ይወዳል። የማይመስሉትን ይጠላል።
ጥለውት እንዳይሄዱ፣ የያዘውን ጥሎ አይከተልም። ቅደሙ ሲል እንጂ ልቅደም ሲል አይስተዋልም። ከኋላ ሆኖ ከፊት እንደሆነ ያስባል። ባመነበት መንገድ ሌሎችን ለመከተል አይደክመውም። ያልተሄደበት መንገድ ያስፈራዋል።
ጭንቅ ጭንቅ ይለዋል። የገባውን ላልገባቸው ለማስረዳት ደከመኝ አይልም። የፊቱን ገፅታ ለተመለከተው በስልጠናው፣ በካድሬዎቹ ዳሰሳና በሚሰማው ተበሳጭቷል። እነርሱም ቢሆን መጣባቸው እንጂ ከእርሱ ጋር መታየት አይፈልጉም። ተከራክረው እንደማያሳምኑት ጠንቅቀው ያውቃሉ። ብዙውን ጊዜ ሰው ሳይቀና አገር አይቀናም ብሎ ይሟገታቸዋል። አንድ ለአምስት፣ ቢፒአር፣ ካይዘን ምናምን ሲሉት አይሰማም። ‹‹የአንድ ሰሞን ሙቀት ናቸው››ይላቸዋል።
ትርሲትና አሰፋ እንዳልተመለከቱት ሆነው ሙገሳቸውን ቀጥለዋል። ድንገት ‹‹ከበሬ እርሻ ያልወጣ ግብርና ይዘን፣ ባዶ ጉራ……. ከንቱ ሪፖርት›› የሚል የእዮብ ድምፅ ተሰማ። ካድሬዎቹ ፊታቸው ቀላ። ዝም እንዳይሉ በኋላ ሊገመገሙ ሆነ። ይህን ያሰበው አሰፋ መጪውን በመፍራት ሥልጠናው ላይ የሰማውን ቃል በቃል ይደግም ጀምረ። ካድሬ አሰፋ የተለየ ሰው ነው። ከእርሱ ሃሳብ ጋር ልክክ ብሎ ካልገጠመለትና በአስተሳሰብ ኩርባው ስር ካልተሽከረከረ ሃሳብህን ለማዳመጥ ቀርቶ ለመስማት ይጎመዝዘዋል። የሌሎች ለየት ያለ ሃሳብ ይጎፈንነዋል። ሁሌም « ልክ ነህ» ብሎ ለማዳመጥ አይዘጋጅም።
ቀናተኛ ነው። ሃሳብህን ሌሎች ከገዙት ለቀናት ያህል ለንቦጩን አይሰበስብም። «እንቆቅልህ» ስትለው «ምን አውቅልህ» ሳይሆን «እኔ አውቅልህ!» ይልሃል። የሚፈልገውን ማፅደቅ ብቻ ሳይሆን፣ የማይፈልገውን መንቀል ተግባሩ ነው። ‹‹ከበሬ እርሻ ያልወጣ ግብርና ይዘን፣ ባዶ ጉራ……. ከንቱ ሪፖርት›› አለ እዮብ በድጋሚ ክርክሩ ጦፎ ድምጻቸው ጎልቶ መሰማት ጀመረ።
በዚህ መሃል ‹‹እዮብ ……….እዮብ›› የሚል የሴት ድምፅ ተሰማ። ተናኜ ነበረች። ቆንጂዬ ናት። ቆንጆ መረዳት ግን የላትም። እስከማውቀው ተናኜ እዮብን በጣም ትወደዋለች። ታዝንለታች። ባመነበት መንገድ የሚጓዘው ጉዞ ያስፈራታል። በፍየሎች ዘመን በግ መሆኑ ያሰጋታል።
ፊቷ ፍም መስሏል። እዮብ ከማን ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ አውቃለች። ትንቅንቁ አላስደሰታትም። እኔ ወደ ቆምኩበት ሥፋራ ጠጋ ብላ በቁጣ ጠራችው። አልቆየም። ሰከንዶች ሳታባክን ስሜቷን በሚያሳብቅ መልኩ፤ ‹‹አንተ ሰው ቢያንስ ለልጅህ አስብ እንጂ አባት የሌላት ልጅ ማሳደግ ትፈልጋለህ፤ ቆይ ለምንድነው እማታስበው? ቤተሰብህስ… ›› ስትል ተማጸነችው።
‹‹እውነት በተካደበት፣ ቅጥፈት በነገሰበት አገር ውስጥ የወለድኳት ልጄ፣‹ምን ብለህ እንዲህ አይነት ሥርዓት ውስጥ ወለድከኝ› ብትለኝ መልሴ ምንድነው?›› ሲል መለሰ። ‹‹ግድ የለም እባክህን ዝም በል፣ ሁሉንም ተወው›› አለችው።
ይሕን ጊዜ ፊቱ ተለዋወጠ፤ ‹‹ስንቶች በረሃብ ቸነፈር እየታረዙ እንዲህ ቀልድ ሲነገር እንዴት አትሞግት፤ ዝም ብለህ ቁጭ በል ትይኛለሽ?›› አላት። እንዳማታሸንፈው ታውቃለችና እጁን ይዛ እያካለበች ፊት ለፊት ወደሚታየው አዳራሽ አስገባችው። እዮብ ከእይታችን እንደተሰወረ አፍታም ሳይቆይ ትርሲት ዝምታዋን ሰበረች። ‹‹እንዴት ከፀረ ልማቶች ጋር ክርክር ትገጥማለህ? በል ሂስህን አውርድ አሰፋ ›› ስትል ወቀሳ አቀረበች። አሰፋ ደነገጠ። ላብ አጠመቀው።
ይገባበት ጉድጋድ አጣ። ይሁንና መፍትሄ ላይ ማተኮር እንዳለበት ፈጥኖ ተረዳ፤ እንዲህም አለ። አዎን ልክ ነሽ ‹‹ሂሴን ማውረድ አለብኝ፤ ፀረ ልማቶችን አይነ ውሃቸውን አይቼ ማወቅ ነበረብኝ፤ የአዕምሮዬ ምህዳር የጠበበ ነው፤ ድርጅቴን በእጅጉ አሳዝኛዋለሁ።›› እያለ እንባ እንባ እያለው ሂሱን አወረደ። እጁን እጇ ላይ አስቀምጦ ዳግም እንዲህ አይነት ስህተት እንደማይሰራ እና ጭራሹን እንደማይለመደው በድርጅቱ ስም ማለ።
ይህ ሥነ ሥርዓት እየተፈፀመ አሌክስን ተመለከትኩት። ጠጋ ብዬ። ‹‹እንዴት ነው ሥልጠናው ገብቶሃል? ›› ስል ጠየኩት። ፈገግ ብሎ ‹‹ባክህ አልገባኝም፣ ለአበሉ ስል እኮ ነው፣ መምጣቴ›› አለ ቅድም እኮ እድገቱን በታትነህ ልታስረዳኝ …… አላስጨረሰኝም። ጥሎኝ ሄደ። ምክንያቱን ባላውቅም ተከተልኩት።
ልደርስበት ስቃረብ፤ ‹‹አሌክስ አሌክስ አንተ አሌክስ›› የሚል ጥሪ ተሰማ። ትርሲት ነበረች። አሌክስ ድምፁን አውቆታል። ‹‹እንዴት ነህ ሥልጠናው እንዴት ነው፣ ግልፅ ያልሆነልህ ነገር አለ›› አለች ትርሲት ‹‹ በፍጹም ሁሉም ግልፅ ነው፣ ሥልጠናውም በጣም ጥሩ ነው›› እንደዚህ አይነት ሥልጠና በየጊዜው ሊዘጋጅ ይገባል ሲል›› መለሰ። የማስመሰል ከፍታው ከማስገረምም በላይ አቅለሸለሸኝ።
የሰማሁትን ባለማመን በንዴት ጥፍሬን ስበላ ቆየሁ። እግዜር መቼ ነው ከእንዲህ አይነት ሰው ጋር የሚያፋታኝ ስል አማረርኩ፤ ፈራሁ፤ ተበሳጨ፤ አዘንኩ። ከሥፍራው ለመጥፋት ተመኘሁ። ደግሞ ብገመገምስ ብዬ ሃሳቤን ተውኩት። ሥልጠናው ወደ መጠናቀቁ ደርሷል። አሠልጣኙ የማጠቃለያ ንግግሩን አሰማ። «የዛሬ ሥልጠናችንን በዚህ ጨርሰናል። ጥሩ ጊዜ እንዳሳለፍን በእጅጉ ተስፋ አደርጋለሁ። እርግጠኛም ነኝ።
የሥልጠናችን ቆንጆ መዝጊያ እንዲሆንም፤ የእራት ግብዣ አዘጋጅተናል። መልካም እራት ይሁንላቸሁ›› አለ። አዳራሹን ደማቅ ጭብጨባ ሞላው። ለሦስት ወር የሚሆን እራት የቀን አበል የወሰዱት ሠልጣኞችም የመጨረሻውን እራት ባይሆንም የእለቱን ሥልጠና እራት ወደ ተዘጋጀበት ሥፍራ እርስ በርስ እየተገፋፉ መውጣት ጀመሩ። ከእለታት ሌላ ቀን። ሃይለኛ ዝናብ ይዘንባል። አስፋልት ዳር ያለች አነስተኛ ዳስ ውስጥ አንድ አባት ይታያል።
የምትንቀጠቀጥ የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ አጠገቡ ቁጭ ብላለች። የልጅቷ ጥርሶች ይንቀጫቀጫሉ። የተቀዳደደው አዳፋ ብርድልብስ በስብሷል። ምግብ ከቀመሰ ሁለት ቀን ያለፈው ይመስላል። ተዳክሟል። በደከመ ድምፅ ያቃስታል።
የደረቀ እንባ አሻራውን ጉንጮቹ ላይ ይታያል። ጠጋ ብዬ ተመለከትኩት። አዎ እርሱ ነው። ከአንድ አመት በፊት በሀና ማርያም የማያፈስ ቤት የነበረው እዮብ ነው። ሳግ ተናነቀኝ። እንባዬ ወረደ። አውቆኛል። በሚቁለጨለጩ አይኖቹና ሀዘን በተሸከመ ድምፁ ሰላምታ ሰጠኝ።
ከደሳሳዋ ጎጆው ውስጥ ሆነን መጨዋወት ጀመርን። ይህ ሁሉ ስቃይ የደረሰበት ከዛ ሥልጠና በኋላ መሆኑን አወጋኝ። ከሥልጠናው መልስ በፓርቲው የጥላቻ መዝገብ ጎልተው የተፃፉት ‹‹ፀረ ልማት፣ፀረ ሰላም» የሚል ታርጋ እንደተለጠፈበትና ለዓመታት የኖረበት ቤት «ሕገ-ወጥ ነው» ተብሎ እንደፈረሰበት አረዳኝ። ከተቀመጥኩበት አሻግሬ እያየሁ አስባለሁ። በረዶ የቀላቀለው ወጨፎ ወደ ውስጥ መዝለቅ ሲጀምር የእዮብ ስቃይ እየተጋባብኝ መጣ።
ለደቂቃዎች ጭውውውው አለብኝ። በወቅቱ እዮብ እውነት ነበረው። የግብርናው ዘርፍ እድገት በሚመለከት የተሰጠው ሥልጠና ሁለት ሳምንት እንኳን ሳይሞላው የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት /ፋኦ/ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን መቻል ቀርቶ ዜጎቻችን በቀን ሦስት ጊዜ መመገብ እንደቸገራት የሚያረጋጋጥ ሪፖርት ይፋ አደረገ። እዮብ እውነት እንደነበር በቂ ማረጋገጫን የሰጠ ነበር።
እውነት ላትሸነፍ፤ ሁሉም ሊያልፍና ሁሉም ሊጠፋ በውሸት ሪፖርትና በካድሬዎች ጭፍን ድጋፍ እዮብ ባልሰራው ሃጥያት የመስዋዕት በግ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ አንገበገበኝ።
የማደርገውን አሳጣኝ። ስንቱ በውሸት ሪፖርት ሕይወቱ እንደተበላሸ ማሰብ ጀመርኩ። በዚህ ስሜት ውስጥ እያለሁ አንድ ሙዚቃ በአቅራቢያው ከሚገኝ መጠጥ ቤት ተከፈተ። ሙዚቃው የቴድሮስ ካሳሁን ነው። እንዲህ ይላል። ታላቅና ታናሽ ምላስና ሰንበር ጉራ ብቻ ያስገምታል ስጋ ሞቶ ለሚቀበር ጉራ ብቻ ወርቅ የዘጋ ሳጥን ቁልፍ የሌለው መፍቻ ጉራ ብቻ ምን ያደርጋል ወድቆ አለሁ ማለት ብቻ…………. ጉራ ብቻ
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 /2014