በኢትዮጵያ ዝናብ በሚጠበቅባቸው ወራት ምንም ዓይነት ዝናብ ማግኘት ባለመቻሉ ድርቅ አጋጥሟል። ብዙ አርብቶ አደሮች ኑሯቸውን የሚመሩባቸውን ከብቶቻቸውን አጥተዋል።
የተረፉትም ቢሆኑ ክፉኛ ተጎድተው ለችግር መዳረጋቸው ሲገለፅ ቆይቷል። በኦሮሚያ ክልል በቦረና እና በሌሎችም ዞኖች፣ በሶማሌ በዘጠኝ ዞኖች እንዲሁም በሌሎችም የአርብቶ አደር አካባቢዎች የመጣው ድርቅ ከእንስሳት አልፎ ወደ ሰው እንዳይሻገር አስግቷል።
ለድርቁ መንስኤ የዝናብ እጥረት ነው ቢባልም በተቃራኒው ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ቅርብ ርቀቶች ወንዞች አሉ።
ከብቶቹ እንዳይጎዱ እና እስከ ሞት እንዳይደርሱ ወንዞቹን መጠቀም የሚቻልበትን ሁኔታ እና አስቀድሞ ድርቅ ከመከሰቱ በፊት መከላከል ስለሚቻልበት መንገድ በሚመለከት የፌዴራል ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንን አነጋግረን ቀድሞ መሥራት የነበረበት ግብርና ሚኒስቴር ነው የሚል ምላሽ ሰጥቶን ለንባብ አብቅተነዋል።
በመቀጠል ወደ ግብርና ሚኒስቴር ያቀናን ሲሆን፤ የብዙ እንስሳትን ሕይወት ማጥፋቱን ጠቅሰን በኢትዮጵያ ዝናብ መቅረቱን አስመልክቶ ቀድሞ መረጃ የለም ወይ? ወንዞችን ለምን መጠቀም አይቻልም? አርብቶ አደሩ ለከፋ ጉዳት ከመጋለጡ በፊት ከብቶቹ ለገበያ የሚቀርቡበትም ሆነ ታርደው የሚበሉበት ሁኔታ ለምን አይመቻችም? በሚሉ እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ይመለከታቸዋል የተባሉትን በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ዶክተር ዮሐንስ ግርማን አነጋግረን እንዲህ አቅርበንላችኋል።
አዲስ ዘመን፡- የግብርና ሚኒስቴር ድርቁን በተመለከተ የሚሠራውን ሥራ በቅድሚያ ይግለፁልኝና ምላሾትን ከዚህ ይጀምሩልን?
ዶክተር ዮሐንስ፡- በእርግጥ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ ነው። ድርቁ ከጀመረ ስድስት ወራት አልፈውታል።
መጀመሪያ ድርቅ ውስጥ እንደገባን 77 ሺህ እስር የእንስሳት መኖ በአስቸኳይ ድርቁ ወደ ጀመረባቸው አካባቢዎች እንዲጓጓዙ ተደርጓል። ወደ ቦረና ዞን፣ ወደ ሶማሌ ክልልም በግዢ ቀርቧል። እንስሳቱ በጣም ሲጎዱ በሳር ብቻ መቋቋም አይችሉም። ሌሎች የተመጣጠኑ ምግቦችን ይፈልጋሉ።
ስለዚህ ሳር ከማቅረብ በተጨማሪ ከድርቁ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ በሽታዎችን ለመከላከል እና የእንስሳት አቅምን ለመገንባት መድኃኒቶች እና ሌሎችም ቫይታሚኖች በግዢ ማቅረብ ተችሏል። ከቦረና እና ከሶማሌ ባሻገር በደቡብ ኦሮሚያም በባሌ እና በጉጂ የእንስሳት መኖ ለማቅረብ ጥረት ተደርጓል።
አልፎ ተርፎ በአካል ያሉ ችግሮችን ተገኝቶ በመለየት ወረዳዎች እና ከዞኖች ጋር እንዲሁም ከክልሎች እና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በማሰባሰብ እና በማነጋገር የት ላይ ምን መደረግ እንዳለበት ለይቶ የጋራ እገዛ ማድረግ ተችሏል።
አሁንም በዚሁ መልክ እየሠራን ነው። ሣር እና መኖ እናቅርብ ሲባልም የመኖ እጥረት እንዳይኖር አንዳንድ ቦታዎች ወደ ሰሜን ኦሞ ዳሰነች አካባቢ በ30 እና በ35 ቀን የሚደርሱ የተሻሻሉ የእንስሳት መኖዎችን በማልማት እንዲያመርቱ እና እንዲጠቀሙ ተደርጓል።
የተለያዩ ባለሞያዎችን በመላክ እና ሌሎችም እገዛ ለማድረግ የሚያመቹ የእንስሳት መኖን የመሳሰሉ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች እንዲቀርቡ ተደርጓል። በአጠቃላይም የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ጉዳይን በየጊዜው በመከታተል ሪፖርት በማቅረብ ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- በ2009 ዓ.ም ተከስቶ የነበረው ድርቅ የከፋ ጉዳት አስከትሎ ማለፉ የሚታወስ ነው። የዘንድሮ ድርቅ ጉዳቱ ምን ያህል ነው?
ዶክተር ዮሐንስ፡- እውነቱን ለመናገር ጉዳቱ የአሁኑም በጣም ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም ሁለቱም የዝናብ ወቅቶች ቀርተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ቢኖርም ለውጡ ዝናብ አጠር በሆኑ በተለይ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል። አሁን ሁለቱም የዝናብ ወቅቶች መቅረታቸው ማለትም ዋና የዘር ወቅት የሚባለው ከመጋቢት እስከ ግንቦት መዝነብ የነበረበት ዝናብ ባለመዝነቡ እና ከዚያም በኋላ በድጋሚ በተጨማሪነት ከመስከረም እስከ ኅዳር መዝነብ የነበረበትም አለመዝነቡ ድርቅ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።
አዲስ ዘመን፡- ለምን ቀድሞ መከላከል አልተቻለም?
ዶክተር ዮሐንስ፡- የመጀመሪያው ዝናብ ሲቀር እንደማስጠንቀቂያ ታይቶ መሠራት የነበረባቸው ሥራዎች ሊሠሩ ይገባ ነበር። የመጀመሪያው መኖ በግዢም ሆነ በተለያዩ መንገዶች የማከማቸት ሥራ ሊሠራ ይገባ ነበር።
ያሉትን በማቆየት የመስከረም ዝናብ ሊቀር ይችላል ብሎ በማሰብ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን እንስሳት በመቀነስ ወደ ገበያ እንዲገቡ በማድረግ አርብቶ አደሩ እንስሳውን ቶሎ እንዲሸጥ፤ ባለሀብቶችም እንስሳውን ቶሎ እንዲገዙ እና ከአርብቶ አደሩም ሆነ ከአርሶ አደሩ እጅ ብዙ እንስሳት እንዲወጡ ማድረግ ይገባ ነበር።
አርብቶ አደሩ በውስን ውሃ ሲጠቀም የውሃው ማነስ ተፅዕኖ አሳድሮ እንዲህ ዓይነት ጉዳት ከመምጣቱ በፊት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች መሠራት ይችሉ ነበር። ነገር ግን አጠቃላይ አገራችን ከነበረችባቸው ብዙ ችግሮች አንፃር እና ዘንድሮ ድርቁ በጣም በመጠንከሩ እንስሳቱ በሙሉ አርሶ አደሩ እጅ ውስጥ እንዳሉ ወደ ዋናው ድርቅ ለመግባት ተገደናል።
መጀመሪያ ከበጋ ድርቅ መጥተን ከመጋቢት እስከ ግንቦት ያለው ዝናብ ቀረ። ውስን የነበረው የመኖ ሀብት እየተመናመነ መጣ። ጭራሽ መስከረም ሲደርስ ወደ ድርቅ ተገባ። ስለዚህ አርሶ አደሩ በኪሱ ምንም የለም። ቢያንስ 10 በመቶ የሚሆነውን የመኖ ዋጋ እንኳ ለመክፈል ዝግጁ አልነበረም።
በዚህ ሳቢያ ከፍተኛ ችግር ደረሰ። አጠቃላይ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጠረ። ስለዚህ በአጠቃላይ መንግሥት ወደ መኖ፣ ውሃ እና አጠቃላይ አስፈላጊ ዕርዳታዎች ወደ መሥጠት ገባ። ያም ቢሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ከብቶች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሞቱ።
አዲስ ዘመን፡- ለምን ቀድሞ አውቆ ተዘጋጅቶ ጉዳቱን እንዴት መቀነስ አልተቻለም?
ዶክተር ዮሐንስ፡- የተለመደ የራሳችን አሠራር አለ። ክልሎች ታች ያለውን ነገር እያዩ ዳሰሳ ያደርጋሉ። በሜትሮሎጂ ጥቆማም ሆነ ከሜትሮሎጂም ውጪ የራሳቸውን አካባቢ ይቃኛሉ።
አንድ የዝናብ ወቅት ላይ ዝናብ ሲቀር ወይም ዘንቦም ሲያጥር ምክረ ሃሳብ ይሠጣሉ። ክልሎች የራሳቸውን ድጋፍ ካደረጉ በኋላ ከአቅማቸው በላይ ሆኖ መቆጣጠር ሲያቅታቸው ወደ ፌዴራል ጥያቄ ያቀርባሉ። ከዚያ በፊት ግን ወዲያው ለሚያጋጥም ችግር ክልሎች ራሳቸው ጉዳዩን ይዘው ያስተዳድሩታል። አሁን ግን ችግሩን አስቀድሞ መከላከል ያልተቻለበት ዋነኛው ምክንያት ምናልባት ድርቁ ከመስፋቱ በፊት ክልሎች ራሳቸው በቀጥታ ከፌዴራል ጋር በፍጥነት አለመገናኘታቸው የፈጠረው ችግር ሊሆን ይችላል። መዘግየት መፈጠሩ እና የመረጃ ክፍተት እንጂ የመጀመሪያው ዝናብ ሲቀር ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ይታወቃል።
አዲስ ዘመን፡- በሶማሌ ክልል በዘጠኝ ዞኖች፤ በኦሮሚያ ክልልም የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የከፋ ድርቅ አለ። ይህ ድርቅ በዚህ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ለምን ቀድሞ አልተሠራም በማለት ለአደጋ ሥጋት እና ዝግጁነት ኮሚሽን ጥያቄ ስናቀርብ ምላሻቸው ይሔንን ቀድሞ መሥራት የነበረበት ግብርና ሚኒስቴር ነው ብለዋል።ሸበሌን፣ ዳዋን፣ አዋሽን እና ሌሎችም ወንዞች በቅርብ ርቀት እያሉ ከብቶች በውሃ ጥም እና በድርቅ ማለቃቸው ለምንድን ነው? በትክክል ቀድሞ መሥራት ያለበት ማን ነው?
ዶክተር ዮሐንስ፡- ትክክል ነው።በዘላቂነት መፈታት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ምናልባት ለእንደዚህ ዓይነት ችግር እንዳንጋለጥ ሊያደርጉ የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራት አለባቸው። በተለይ ገናሌን እና ዳዋን የመሳሰሉትን ወንዞች ውሃቸውን ተጠቅሞ በመስኖ መኖ በማልማት እንስሳቱን መታደግ ይቻላል።
መኖን በማምረት ለሌሎችም ለመሸጥ አያስቸግርም፤ ሰብሎችንም በማምረት ውሃውን በተለያየ መንገድ መጠቀም ይቻላል። ነገር ግን በአጠቃላይ አርብቶ አደሩ አካባቢ ያለው ችግር የአሁን አይደለም።
የረዥም ዘመናት ችግር ነው። የፖሊሲ ችግር ነበር። በአገር ደረጃ አርብቶ አደር አካባቢ ሥነምህዳርን ታሳቢ ያደረገ የተለየ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ለአርብቶ አደሩ ተለይቶ መውጣት ነበረበት።
ከዚህ በፊት የተለየ ፖሊሲ ተቀርፆ ኢንቨስት ተደርጎበት አልታየም። በተቻለ መጠን አርብቶ አደሩን በተመለከተ የተወሰኑ ስትራቴጂዎች አሉ። ነገር ግን በአገር ደረጃ በፖሊሲ እና በስትራቴጂ ተደግፎ በሚጠቅም መልኩ ኢንቨስት አልተደረገም።ስለዚህ በአጠቃላይ በአገር ደረጃ ትኩረት አላገኘም።
በአገር ደረጃ አርብቶ አደር በከፍታ አካባቢ እንዳለ ነዋሪ አይቶ በቂ ዝናብ እንደማያገኝ ተረድቶ ለእርሱ የሚመቸውን አሠራር ከመዘርጋት ይልቅ ለምን ሰብል አታመርቱም? ብሎ ማሰብ አለ። ይህ በአገር ደረጃ የሚስተዋል ክፍተት ነው።
በአጠቃላይ አርብቶ አደሩን በሚመለከት በአገሪቱ የፖሊሲ እና የአቅጣጫ ችግር ነበር። ነገር ግን በአዲሱ መንግሥት ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ አገር አቀፍ የአርብቶ አደር ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ተቀርፆዋል። በተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ ሁለት ዓመት አካባቢ ሆነውታል።
የአርብቶ አደሩን ሕይወት፣ የከርሰ ምድር ውሃን እና የአርሶ አደሩን መኖ ለማልማት እንዲሁም ለሰው እና ለእንስሳት ውሃ የሚቀርብበት ሁኔታን ያመቻቻል።
አርብቶ አደሩ የሀብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረግ ሥራዎች፣ መኖን ማልማት ብቻ ሳይሆን ጤናን መጠበቅ፣ ገበያ እና የገበያ መሠረተ ልማቶችን ማመቻቸት፣ የእንስሳት ዝርያን የማሻሻል፣ ተደራጅቶ የተለያዩ ግብአቶችን እና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ ተደራጅቶ እንስሳቱን መሸጥ፣ የአርብቶ አደሮች አቅማቸውን የማሳደግ እና ድጋፍ እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ስትራቴጂ ተነድፏል። በተለይ አርብቶ አደሩ የፋይናንስ አቅርቦት አልነበረውም።
ስለዚህ በአዲሱ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ብድር ሊያገኙ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚያመቻች ነው። ነገር ግን ፖሊሲ ብቻ በቂ አይደለም። የተቀረፀውን ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በደንብ አደራጅቶ መሬት ላይ ማውረድ እና ገንዘብ መድቦ ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል።
የአርብቶ አደሩን ፖሊሲ በአርብቶ አደሩ ስነምህዳር እናበአርብቶ አደሩ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ሀብቱን ማሳደግ እና ማስፋት በሚቻልበት መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል። በዚያ መሠረት ፖሊሲውን ማስተግበር ይገባል። ኢንቨስትመንትም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- በትክክል ቅድመ ትንበያ ሲኖር ድርቅ ሊመጣ እንደሚችል እርግጠኛ መሆን ላይ ከተደረሰ የጉጂ ከብቶች ለምን ሲዳማ ሔደው አይተርፉም ? አርብቶ አደሮች ለምን ሸጠው አይጠቀሙም? ከብቶቹ ታርደው ለምን አይበሉም?
ዶክተር ዮሐንስ፡- ከብቶቹን ወደ ረዥም ርቀት እና ወደ ሌሎች ቦታዎች መውሰድ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ሁልጊዜ ድርቅ ሲመጣ መፍትሔ የመፈለግ ሥራ ቢሠራም ብዙ ለውጥ ማምጣት አይቻልም። ዋናው ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ላይ ትኩረት መሥጠት ያስፈልጋል።
በዘላቂነት ለውጥ በሚያመጣ ጉዳይ ላይ ስንል የገበያ መሠረተ ልማት እና የገበያ ትስስር ወሳኝ ነው። አንዱ ለምሳሌ እዚያው አርብቶ አደሩ አካባቢ ቄራዎች እንዲኖሩ ወይም እነርሱ ከብቶቻቸውን ወደ ቄራዎች መላክ ቢቻል መልካም ነው።
ስራቴጂክ በሆነ መልኩ በየቦታው የእንስሳት ገበያ የሚኖርበት ሁኔታ ቢመቻች ዘላቂ መፍትሔ የሚመጣ ይመስለኛል።
አርብቶ አደሩ ተደራጅቶ እንስሳውን በአንድ በረት ለዓመታት ከሚያቆይ ጥሩ ስጋ እንዲኖራቸው አድርጎ በወሳኝ ጊዜ ላይ ቢሸጣቸው አትራፊ መሆን ይችላል። ለዚያ ቶሎ የገበያ ትስስር መፍጠር ቢኖር እና በየሦስት ወሩ ጥሩ መኖ እና ውሃ እያቀረቡ ቶሎ ቶሎ መሸጥ ቢቻል ዓለም አቀፋዊ በሆነ የዓየር ለውጥ ድርቅ እንኳ ቢመጣ አርብቶ አደሩ ቀጥታ የመንግሥትን ሀብት ከመጠቀም ሊላቀቅ ይችላል።
ከዚህ በኋም ድርቅ ይመጣል፤ ይሔዳል። ዋናው ጉዳይ አርብቶ አደሩ ራሱ ድርቅን መቋቋም እንዲችል ማድረግ ነው። ምክንያቱም ሁኔታዎች ከተመቻቹ ገንዘብ አለው። የኑሮ ደረጃው ይሻሻላል።
ከብቶች አርብቶ መጠቀምን እንደአንድ ቢዝነስ ይመለከተዋል። እግረመንገዱን አደጋን የመቋቋም አቅም ይፈጥራል። ሁሌም የመንግሥት ዕርዳታን ከመጠበቅ ይላቀቃል።
አዲስ ዘመን፡- ይሔን እንዴት ማድረግ ይቻላል? በየአካባቢው ቄራዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አለ?
ዶክተር ዮሐንስ፡- በእርግጥ በቦረና አካባቢም በአንዳንድ ራቅ ባሉ አካባቢዎች እዚህም መሃል ከተማ ላይ ላሉት ቄራዎች ግንኙነት ፈጥሮ ሊሠራ የሚችልበት ሁኔታ አለ።
ነገር ግን ቄራዎቹ በቅርበት ቢኖሩ አርብቶ አደሮቹ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበት ዕድል ይኖር ነበር። ነገር ግን ከተጀማመሩ ነገሮች ውጪ በስፋት የተሔደበት ሁኔታ የለም።
ለእዚህ ግብዓት እና ቴክኖሎጂ መኖር አለበት። በተጨማሪ አርብቶ አደሩ ተደራጅቶ የተለያየ ብድር እና ቴክኖሎጂዎችን ማግኘት እና ገበያ መር መሆን አለበት። አርብቶ አደሩ ራሱ ‹‹እንደዚህ አድርጌ ሸጬ አገኛለሁ›› ብሎ ማሰብ እና ማልማት አለበት። አሁን ሰው ማረድ እና መብላት ሲፈልግ ብቻ እየገዛቸው ነው። ነገር ግን እነርሱ ራሳቸው ለገበያ ብለው መሥራት አለባቸው።
ያ ሲሆን የአስተሳሰብ ለውጥ ሲመጣ ችግሩ ይቀረፋል። ስለዚህ በአገር ደረጃ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ይገባል። ነገር ግን መረሳት የሌለበት ለእዚህ ጉዳይ እዚም እዚያም የተሠሩ ነገሮች አሉ። በሁሉም በኩል የተሞከሩ ነገሮች አሉ።
በአገር ደረጃ የፖሊሲ ቁርጠኛነት እና ትኩረት ያስፈልጋል። ለማድረግ ፈቃደኝነቱ ካለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። የአገር ሀብት የሆነውን የእንስሳት ምርት ለመታደግ መኖ ማምረት ቀርቶ፤ የቆላ ስንዴ እንኳ ብለን ደረቁን መሬት አለስልሰን ከከርሰ ምድር ውሃ እያወጣን በመስኖ እያመረትን ነው።
ስለዚህ ጎን ለጎን መኖ እንድናመርት ገበሬው አደልቦ በየሦስት ወሩ ከስጋ አቀነባባሪዎች ጋር የገበያ ትስስር ተፈጥሮለት ዋናውን ገበያ እንዲያገኝ ቢደረግ መልካም ነው። ነገር ግን ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል። የእንስሳት ሀብት ጉዳይ በአንድ ቀን ተሠርቶ የሚያልቅ አይደለም።ጊዜን ይጠይቃል።ከዚያ በኋላ ጥቅሙ ይታያል።
ይህ ለአገርም ትልቅ ከፍተኛ ትርጉም አለው። ምክንያቱም እንደሚታቀው ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ መጠን ያለው የቁም እንስሳት ሀብት አለን። ያንን በትክክል መጠቀም ብንችል በአባወራ ደረጃ ያለው የኢኮኖሚ ጠቀሜታም ከፍተኛ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- አርብቶ አደሩ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስበት በኢኮኖሚ ራሱን እንዲችል ማን ምን ዓይነት ሥራ ይመለከተዋል? ተጠያቂ አካልን ለመለየት ምን መሠራት አለበት ይላሉ?
ዶክተር ዮሐንስ፡- እውነቱን ለመናገር የእንስሳት ጉዳይን ግብርና ሚኒስቴር ብቻውን ሠርቶ የሚችለው አይደለም። የብዙ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ይጠይቃል። ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም የኤክስቴንሽን ሥራ ያስፈልጋል።
የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እና ስልጠናዎች፣ ግብአቶችን እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ በተጨማሪ ማሰራጨት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም የቆላማ እና መስኖ አካባቢ ሚኒስቴር አንድ ውሃ ገብ በሆነ ቦታ ላይ መንጥሮ ለመስኖ እንዲሆን እንደሚያደርገው ሁሉ፤ ግብርና ሚኒስቴርም መዝግቦ ለመኖም ሆነ ለሰው እህል የሚሆን ሰብል ማምረት መቻል አለበት።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የመስኖ ሥራዎችን ውሃ ገብ በሆኑ አካባቢዎች ላይ እያመቻቸ ነው። እዚህ ላይ ተቀናጅቶ መሥራት አስፈላጊ ነው። እውነቱን ለመናገር አሁን ተቀናጅቶ መሥራት ተጀምሯል። ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየሠሩ ነው።
የተጀማመሩ ነገሮች በመኖራቸው ወደፊት በስፋት ከተሠራበት ጥሩ የሚሆን እና ለውጥ የሚመጣ ይመስለኛል። ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ሀብት የማሰባሰብ ሥራዎችም ሆኑ በተለይ የፋይናንስ ሥራዎች መሳተፋቸው በጣም አስፈላጊ ነው። የኢትዮጵያ አርሶ አደር ተንቀሳቃሽ ሀብት አለው።
ያም እንስሳቱ ብቻ ናቸው። በብሔራዊ ባንክ የተንቀሳቃሽ ሀብትን ለማስያዝ አሁን አዋጅ እና ደንብ ወጥቶ ስትራቴጂም ተነድፏል። ምናልባት አርብቶ አደራችን ያለውን ሀብት አስይዞ ያለውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሀብቱን ለማስፋት እና እንስሳቱን ለማልማት እና የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት የገንዘብ ብድር ያገኛል። ነገር ግን እዚህ ላይም የሌሎችም ተቋማት ተሳትፎ አስፈላጊ ነው።
የመንግሥት ፖሊሲውን የማስፈፀም ቁርጠኝነት እና የክልሎች የዞን እና የወረዳ አመራሮች ተሳትፎ በጣም አስፈላጊ ነው። የብዙ አካላትን ሚና የሚጠይቅ ነው። ዋናው መመለስ ያለበት ድርቅ ሲመጣ ብቻ ምላሽ መሥጠት አይደለም። በዘላቂነት አርብቶ አደሩ እንዴት አደጋውን መቋቋም ይችላል የሚለው ነው። አደጋ ሲመጣ ምን ያህል መቋቋም እንችላለን? የሚለው ላይ መሥራት አለበት። ደግሞም ይቻላል። ምክንያቱም ብዙ ዕድሎች አሉ።
እነርሱን ካሰፋን እና ካጠናከርን ለውጥ ማምጣት ይቻላል። የሚከብድ ነገር አይደለም። ድርቅ ወደ ርሃብ የሚቀየርበት ሁኔታም አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ዮሐንስ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 /2014