በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአስተዳደር አመቺ እንዲሆኑ ታስበው ከተቋቋሙ 11 ክፍለ ከተሞች መካከል የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አንዱ ነው። ክፍለ ከተሞች ለማኅበረሰቡ የአገልግሎት ተደራሽነትና የማስተዳደር አቅምን በማጎልበት ለነዋሪዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ አገልግሎት እንዲሰጡ ታስበው የተቋቋሙ ናቸው።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የማስፋፊያ እና የኢንቨስትመንት ስፍራ እንደመሆኑ መጠን በክፍለ ከተማው አሁን ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ምን እንደሚመስል፤ በክፍለ ከተማው ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በምን መልኩ እየተፈቱ እንደሆነ፤ ክፍለ ከተማው የይዞታ ማረጋገጫ አገልግሎት አሰጣጥ ምን እንደሚመስል፤ እንዲሁም በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚነሱ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ምን እየሰራ እንደሆነ ከክፍለ ከተማው የዋና ስራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፈ አቶ መሃመድ አሕመድ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን:- በክፍለ ከተማው በስሩ ከሚገኙ ወረዳዎች ጋር በመናበብ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ ምን ሰርታችኋል?
አቶ መሃመድ:- በክፍለ ከተማው 12 ወረዳዎች እና 504 ብሎኮች ይገኛሉ። እነዚህን ወረዳዎች በሚያስፈልገው ልክ ለማስተዳደር ከወረዳዎች ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው። ይህ ማለት በልማት፣ በጸጥታ፣ በመልካም አስተዳደር በጋራ እንሰራለን። የአመራሩን አቅም በማሳደግ ማኅበረሰብን ማገልገል የሚችል አመራር ከመፍጠር አኳያ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። በተለይም ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በክፍለ ከተማው ከሚገኙ 447 ለሚሆኑ አመራሮች የአቅም ማሳደጊያ ስልጠና ተሰጥቷል። በዚህም ትክክለኛውን አመራር በትክክለኛ ቦታ በማስቀመጥ ትልቅ ውጤት ተገኝቷል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚከሰቱት ብቁ የሆነ አስተዳደር ሲጠፋ ነው። አንድ አመራር ሕዝብ ሲያገለግል በማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ብቃት ሊኖረው ይገባል። ሲባል ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማ ያሉ አመራሮች ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት ብቃታቸው ይጠናል። ቀጥሎም በብቃታቸው ላይ ተጨማሪ የማብቃት ስራ ይከናወናል። ከዚህ በኋላ የሰዎችን አቅም ባገናዘበ መልኩ ምደባ ይደረጋል። በዚህም የማኅበረሰባችን ትልቁ ችግር የሆነውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ ይሰራል።
የጸጥታ ችግር እንዳያጋጥም አመራሩ ከሕዝቡ ጋር በቅንጅት እና በትብብር እየሰራ ነው። በዓላት ያለምንም ኮሽታ እንዲከበር የአመራሩ ሚና ከፍተኛ ነው። ይህ የሆነው አመራርና ሕዝብ ላይ በመሰራቱ ነው። በተጨማሪም የኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት የስራ እንቅስቃሴ ሰላማዊ እንዲሆን ሰላምን የማጽናት ስራ ሰርተናል።
ከለውጡ በፊት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ብዙ የልማት ስራዎች ባለመሰራታቸው፤ ከፍተኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ነበር። ነገር ግን የለውጡ መንግስት ከመጣ በኋላ ብዙ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል። በክፍለ ከተማው የተሰራው መንገድ ከለውጡ በፊት አልነበረም። መንገዱ ባለመኖሩ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠረና ኅብረተሰቡን ለቅሬታ የዳረገ ነበር። አሁን ላይ ከፌደራል እስከ ከተማ አስተዳደሩ ድረስ ያሉ ተቋማት በቅንጅት እና በመተባበር በርካታ የልማት ስራዎች እያከናወኑ ነው።
በክፍለ ከተማችን በርካታ ሀገር አቀፍ ድርጅቶች የሚገኙበት ነው። ለምሳሌ በአፍሪካ ደረጃ 10 ሺ ሴቶች ማሰልጠን የሚችል የሴቶች የልሕቀት ማዕከል እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወገኖች የሚስተናገዱበት የዐይነ ስውራን ትምህርት ቤት የሚገኘው በክፍለ ከተማችን ነው። በተጨማሪም ኦቪድ ሪል ስቴትን ጨምሮ በርካታ የቤት አልሚዎች የሚገኙት በዚህ ክፍለ ከተማ ነው።
ማኅበረሰቡ የልማት ተጠቃሚነት እና የመልም አስተዳደር ችግር እንዲፈታለት ይፈልጋል። በክፍለ ከተማው ያሉ አርሶ አደሮች እንደ ትናንቱ አርሶ ወደ ቤቱ መግባት ብቻ አይፈልግም። እርሻውን በዘመናዊ ትራክተር ማረስ እና ወደ ኢንዱስትሪ ማደግን ይሻል። ከዚህ አኳያ አንዳንድ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ። ችግሩን ለመፍታት በክፍለ ከተማ ደረጃ የተቋቋመ ጽህፈት ቤት አለ። ከዚህ ጽህፈት ቤት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሌሎች ተቋማት አሉ። የሕዝቡን የመልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምን እንደሆነ በየጊዜው እየተገመገመ አቅጣጫ እየተቀመጠ ይሰራል።
አዲስ ዘመን፡- በክፍለ ከተማው ከሚታዩ ችግሮች አንዱ በአየር ካርታ ለሚታዩ ቤቶች መብት ከመፍጠር አንጻር ያለው ችግር መሆኑ ይነሳል። ችግሮችን ለመቅረፍ ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ መሀመድ፡– በክፍለ ከተማ ከሚከናወኑ ዐብይ ተግባራት መካከል 45 በመቶ የሚሆነው የመልካም አስተዳደር ስራ ነው። በክፍለ ከተማ ደረጃ የመንገድ ይግባልን ጥያቄ ይነሳል። የ1988፣ 1997 እና በ2003 ዓ.ም አየር ካርታ ላይ ያሉ ሰዎች የመብት ይፈጠርልን ጥያቄ ያነሳሉ። ከዚህ በመነሳት የ1988፣ 1997 የአየር ካርታ ላይ የሚታዩ ቤቶችን የምናስተናግድበት አግባብ አለ።
ነገር ግን በ2003 ዓ.ም የአየር ካርታ ላይ የሚታዩ ቤቶች መመሪያ ስለማይፈቅድ ላይስተናገዱ ይችላሉ። ወደፊት መመሪያው ጸድቆ ሲመጣ የሚስተናገዱበት አግባብ ይፈጠራል። አሁንም ከመብት ጋር ተያይዞ የሚስተዋል የመልካም አስተዳደር ችግር አለ። ይህ የሆነው ያልተስተካከሉ አሰራሮች ስላሉ ነው። ከተማ አስተዳደሩ ችግሩን በባለቤትነት ይዞ ለመፍትሄው እየሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፤- ከማኅበር ቤቶች ጋር ተያይዞ በክፍለ ከተማው የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመፍታት ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ መሃመድ፡– የማኅበር ቤቶች አካባቢ የኦዲት ስራ እየተሰራ በመሆኑ አሁን ላይ ኅብረተሰቡ አገልግሎት እያገኘ አይደለም። በክፍለ ከተማው 901 ማኅበራት አሉ። ከነዚህ ማኅበራት ውስጥ 217 የሚሆኑት ኮሚቴ ተዋቅሮ አገልግሎት እየተሰጡ ነው። ከዚያ ውጭ ያሉት ግን ኦዲት ተደርጎ ስላልተጠናቀቀ አገልግሎት አያገኙም።
ከማኅበር ቤቶች ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የብልሹ አሰራር አለ። ሌቦች፣ ሰነዶችን አመሳስለው የሚሰሩ እና የሕዝብና የመንግስን ሀብት በማይሆን መንገድ የዘረፉ ብዙ አካላት አሉ። ያንን ለማጥራት እንዲሁም አስተዳደሩ ትክክለኛ የሕዝብ ሀብት ለሕዝብ መዋል አለበት የሚል አቋም ስላለው፤ ከጉዳዩ ክብደት አንጻር ችግሩን ለመቅረፍ ደግሞ ጊዜ ይወስዳል። በመሆኑም አሁን ላይ ከማኅበር ቤቶች ጋር ተያይዞ አገልግሎት አላገኘሁም ብሎ ቅሬታ የሚያቀርብ ሰው መኖሩ አይቀረም።
የክፍለ ከተማው አስተዳደር ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ውይይት በማድረግ በ901ዱ ማኅበር ላይ ያለው ችግር እና ክፍተት ምን እንደሆነ እንዲለይ ተደርጓል። ምን መሆን አለበት የሚለው የውሳኔ ሀሳብም ቀርቧል። ለዚህ አማራጭ የውሳኔ ሀሳብ የሚመለከተው አካል በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ክፍለ ከተማ ፈተና የሆነባችሁ ችግር ምንድ ነው?
አቶ መሃመድ፡- ሰነድ አልባ ባለይዞታዎች የክፍለ ከተማው ዐብይ ፈተናዎች ናቸው። ማስተናገድ የምንችለው 1988 እና 1997 የአየር ካርታ የሚታዩ ቤቶችን ነው። ከዚያ በኋላ ያሉትን ግን የተስተካከለ መመሪያ ተዘጋጅቶ በሚመለከተው አካል ጸድቆ ሊሰራበት የሚችል መመሪያ አልወረደም። በዚህ የተነሳ የሚመጡ ጥያቄዎችን መመለስ ባለመቻላችን አሁን ላይ ጉዳዩ ለክፍለ ከተማው ትልቅ ፈተና ሆኗል። ይህ ደግሞ ማኅበረሰቡ ቤት ውስጥ እየኖረ ካርታ ማግኘት አንዳይችል አድርጎታል። ካርታ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ግንባታ መገንባት ስለማይችሉ ለመኖር ፈተና ሆኖባቸዋል።
ከለውጡ በፊት ክፍለ ከተማው ከልማት ወደኋላ የቀረ ነበር። ከለውጡ ወዲህ ግን ክፍለ ከተማው ትኩረት ስለተሰጠው ብዙ የልማት ስራዎች እየተሰሩ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም የሚነሱ የልማት ጥቄዎች አሉ። እነሱን ጥቄዎች ለመመለስ እየተሰራ ነው። ለምሳሌ በክፍለ ከተማችን ወረዳ አንድ፣ ዘጠኝ እና 13 የጤና ጣቢያ ይገንባልን ጥያቄ አንስተዋል።
ለዚህ ጥያቄ ቶሎ ምላሽ ያለመስጠት፤ በታቀደለት ጊዜ ከመገንባት አንጻር ትልቅ የልማት ችግር መሆኑ ተለይቷል። በመሆኑ ይህን ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ እገዛ እያደረገ ነው። በማኅበር ቤቶች በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይኖራሉ። ከ600 በላይ ማኅበራት ዋናው ችግራቸው አገልግሎት አናገኝም የሚል ነው።
ማኅበረሰቡ ግንባታ መገንባት፤ መሸጥ መለወጥ ይፈልጋል። እኛ ደግሞ ኦዲት እያደረግን ስለሆነ አገልግሎት መስጠት አልተጀመረም። የኦዲት ስራው በጣም ውስብስብ ነው። በሕይወት የሌሉ ሰዎችን ጭምር እንዳሉ አድርጎ የማቅረብ ሁኔታ ስላለ ለማጥራና ኦዲት ለማድረግ አስቸጋሪ ነው።
በክፍለ ከተማው ሰፊ ቁጥር የሚይዙ አቅመ ደካሞች ስላሉ ለመኖሪያ የሚሆን የቀበሌ ቤት ይጠይቃሉ። ለምሳሌ ተመዝግበው ቤት እዲያገኙ በካቢኔ የተወሰነላቸው ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች አሉ። ነገር ግን ያለው አቅመ ደካማ ቁጥር እና የቀበሌ ቤት መመጣጠን ባለመቻሉ ትልቅ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኗል።
ችግሩን ለመፍታት ምድር ቤት ብቻ የነበራቸውን ቤቶች በማፍረስ እስከ ጂ+5 ድረስ በመገንባት የቤት ችግርን ለመቅረፍ እየሰራን ነው። ለምሳሌ በወረዳ 3 በባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ ተገንብቶ የተጠናቀቀ ቤት አለ። ይህ ቤት ቀደም ብሎ የምድር ቤት ብቻ ያለው ነበር። አሁን ላይ ወደ ፎቅ በመቀየር በቦታው የተወሰኑ ሰዎችን ይይዝ የነበረው ቦታ በርካታ ሰዎች እንዲኖሩበት ማድረግ ተችሏል።
በዚህ ቦታ በነበረው ምድር ቤት በፊት የነበሩት 16 አባወራዎች ሲሆኑ አሁን ላይ ቤቱ 56 አባወራዎችን መያዝ ችሏል። ስለዚህ በዚህ መንገድ በመገንባት በርከት ያሉ ሰዎችን የቤት ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ ነው። ይሁን እንጂ አቅርቦቱና ፍላጎቱ መመጣጠን ባለመቻሉ ችግሩ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል።
ሌላው በክፍለ ከተማው ያለው ችግር ደግሞ ከአርሶ አደሮች የሚነሳ ነው። ክፍለ ከተማው አርሶ አደር በብዛት የሚገኝበት ነው። ስለሆነም መሬታቸው ለልማት ይፈለጋል። በዚህ ወቅት አርሶ አደሩ እኔ ለምን በቦታው አላለማም የሚል ጥያቄ ያነሳል። አንድ አርሶ አደር ቦታው እንዴት ማልማት ይችላል የሚለው በከተማ ደረጃ አሰራርና መመሪያ ተበጅቶለት በራሱ ቦታ ላይ ማሟላት ያለበትን መስፈርት አሟልቶ ማልማት የሚያስችል አሰራር ተበጅቷል።
አዲስ ዘመን፡- በክፍለ ከተማው ሰዎች የራሳቸው ንብረት ከተሽከርካሪ ለማውረድ በተደራጁ ወጣቶች ማስፈራሪያ እና ዛቻ እየደረሰባቸው ነው። በግዴታም ንብረታቸውን ያወርዳሉ፤ ለጸጥታ ኃይሎች ሲያመለክቱም መፍትሄ አያገኙም። ክፍለ ከተማው ይህንን አይነቱን ችግር ማስቀረት ለምን ተሳነው?
አቶ መሀመድ፡– ጫኝና አውራጅ በሚል የተቋቋሙ ማኅበራት በአንድ አይሱዙ ከ10 እስከ 15 ሺ ብር ድረስ የማይገባው ይጠይቁ ነበር። ቤተሰብ እና የራሱ ሰው ያለው ነዋሪም ንብረቱን በራሱ ማስወረድም አይችልም ነበር። ይህንንም በተመለከተ ቅሬታዎች ቀርበውልን ማኅበራቱን አፍርሰናል።
አሁን ላይ ሰዎች ንብረታቸውን በፈቀዱት ሰው እንዲያስጭኑ እና እንዲያወርዱ ማድረግ ችለናል። ለሰላም እና ጸጥታ ሰራተኞች የውይይት መድረክ ፈጥረን ተወያይተንበታል። በክፍለ ከተማው ያሉ ብሎኮች ሁሉም የራሳቸው አመራሮች ስላሏቸው ለሁሉም ስልጠና ሰጥተናል። ይሄ ሲባል ግን በግለሰብ ደረጃ ሾልከው ይሄንን ሕገ ወጥ ተግባር የሚያደርጉ አይኖሩም ማለት አንችልም። ጉዳዩ በአንድ ጊዜ ተሰርቶ የሚያልቅ ሥራ ባለመሆኑ ክትትል ይፈልጋል። እንደዚህ አይነት ተግባራትን የሚፈጽሙ ሰዎች ሲኖሩ ግን የጸጥታ ኃላፊዎች ኃላፊነቱን እንዲወስዱ መግባባት ላይ ደርሰናል። በዚህም የመጣ ለውጥ አለ።
ለምሳሌ በቅርብ ግዜ በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ቤታቸው ፈርሶባቸው ወደ ክፍለ ከተማው የመጡ ከአንድ ሺ በላይ አባወራዎች አሉ። የእነሱ እቃዎች በነዋሪው እገዛ እንዲወርድ አድርገናል። ለውጦች አሉ፤ ነገር ግን አሁንም ጥቆማዎች ከመጡ ወርደን የምናጠራበት አሰራር አለን።
አዲስ ዘመን፡- በክፍለ ከተማው ሲሰሩ የነበሩ የባጃጅ ሹፌሮች ስራ በመከልከላቸው ዘርፍ ቀይረው ከባድ መኪኖችን እንዲጠብቁ መደረጉ ይታወሳል። ነገር ግን መኪና የሚያሳድሩት በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግቢ ውስጥ በመሆኑ ንዝረት መፈጠሩን ነዋሪዎች አመልክተው ነበር። ስራውን የሚሰሩት ወጣቶች በነዋሪዎች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ስላደረሱባቸው ስጋት ውስጥ እንዳሉ ቅሬታ አቅርበዋል። በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?
አቶ መሃመድ፡- ከባጃጆች ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባጃጆች ለከተማዋ አይመጥኑም የሚል አቋም አለው። ስርቆት የሚፈጸሙት እና ሴቶች የሚደፈሩት በሁለት እግር እና በሶስት እግር ባጃጆች ነው። የትራፊክ አደጋዎችም እንዲከሰቱ ምክንያት ነበሩ። ታርጋ የሚያገኙት ከክልሎች ሲሆን ወንጀል ፈጽመው ሲያመልጡ እነሱን ማግኘት አስቸጋሪ ከመሆኑ ባሻገር ታሪፉንም እንደፈለጉ ይጨምሩ ነበር።
የአፍሪካ መዲና በሆነችው ከተማ ባጃጆች አይመጥኑም። ነገር ግን በአንድ ጊዜ አይጠፉም። ጉዳዩ በሚመለከተው አካል ተጠንቶ ሲቀርብ እና በሕጋዊ መንገድ እንዲመዘገቡ ሲደረግ ፈቃደኞች አልነበሩም። ፈቃደኞች ሆነው የተመዘገቡትን በውስጥ ለውስጥ መንገዶች እንዲሰሩ አድርገናል።
አሽከርካሪዎቹ 200 እና 300 በመሆን እየተደራጁ መንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር ይሞክሩ ነበር። ነገር ግን አወያይተን ዘርፍ እንዲቀይሩ አድርገናል። በስራ እድል ፈጠራም ስራ እንዲያኙ ተደርጓል። ዓላማችን ግን ባጃጆች ከተማዋን ስለማይመጥኑ ከስራው ውጭ ማድረግ ነው። ዘርፍ እንቀይራለን ላሉ ብድር ተመቻችቶ ስራ አስጀምረናቸዋል። ይሄንን አላደርግም ወደ ዘረፋ እገባለሁ ካሉ ግን የሕግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ኃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ነዋሪው ቅሬታውን ለማቅረብ ወረዳዎች ቅርብ ናቸው። በዚህም ከእነሱ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል? ክፍለ ከተማውስ እንዴት ይመራቸዋል? በምን መልኩስ ይቆጣጠራቸዋል?
አቶ መሃመድ፡– ከወረዳዎች ጋር በየቀኑ እንገናኛለን። የወረዳ ስራ አስፈጻሚዎች ከክፍለ ከተማው ስራ አስፈጻሚ ጋር በየቀኑ የሚገናኙበት አሰራር አለ። በየሳምንቱ ቅዳሜ በመገናኘት ስራዎች ይገመገማሉ። ከዚያ ውጭ በየዘርፉ ያሉ አመራሮች በየ15 ቀኑ ተገናኝተው ስራዎችን ይመዝናሉ። ከአንድ ወረዳ ላይ በተለያዩ ዘርፎች ቅሬታ ሲኖር እርምጃዎችን እንወስዳለን። በ2017 ዓ.ም በተደጋጋሚ ቅሬታ የቀረበባቸው ስድስት የወረዳ ስራ አስፈጻሚዎችን አንስተናል። ከ12 የፓርቲ ኃላፊዎችም 10 የሚሆኑትን ከኃላፊነት አንስተናል።
ከጸጥታ ጋር በተያያዘም የክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሚመሩት፤ የክፍለ ከተማው የፖሊስ መምሪያ፤ የሴኩሪቲና ደህንነት፤ ሰላም እና ጸጥታ የደንብ ማስከበር ያሉበት የጸጥታ ምክር ቤት አለ። ችግሮች ሲኖሩ በቶሎ እርምጃዎችን ይወሰዳል። በየግዜው በመገናኘት ጥቆማዎችም ሲደርሱን ኮሚቴ አዋቅረን በመላክ ጉዳዩ እንዲታይ እናደርጋለን።
ይህንን እናደርጋለን ስንል ምንም አይነት ችግሮች የሉም እያልን ግን አይደለም። ክፍተቶች ይኖራሉ። ችግሩ እንዲቀረፍ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ክትትል እና ቁጥጥር እናደርጋለን። ከጸጥታ ጋርም በተያያዘ ሁሉም ተመሳሳይ አቋም አላቸው ማለት አይቻልም። ሰዎች ስለሆንን የተለያየ ሀሳብ ይኖረናል። ይሄንን ግን በሂደት እያስተካከልን እንሄዳለን።
አዲስ ዘመን፡- በኮሪደር ልማት ምክንያት ወደ ክፍለ ከተማው ለመጡ ነዋሪዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ምን አይነት ሥራዎችን ሰርታችኋል?
አቶ መሃመድ፡– ወረዳ አምስት ላይ ተገጣጣሚ ቤቶች ተሰርተዋል። በከተማ ደረጃ የተሰሩ አምስት ሺ የሚሆኑ ቤቶች የተገነቡት በእኛ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነው። ገላን እና ቂሊንጦ ኮንዶሚኒየም ውስጥ የገቡ የልማት ተነሺዎችም አሉ። ከሞቀ ሰፈራቸው ስለወጡ ለተነሺዎች መንግስት የተለየ አቅጣጫ አስቀምጦ በልዩ ሁኔታ እንዲስተናገዱ አድርገናል። የሸማቾች አገልግሎትን እና የሲቪል መታወቂያ አገልግሎት በቅርባቸው እንዲያገኙ አድርገናል።
መንገድ፤ መብራት፤ የጸጥታ ጉዳይ በጥብቅ ዲስፕሊን እንዲመራ ተደርጓል። የከነማ ፋርማሲ አገልግሎት፤ ባሶች እና የሰንበት ገበያዎች ገንብተዋል። ኅብረተሰቡን የማስተዋወቅ ስራም ሰርተናል። ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ አቅጣጫ አስቀምጠው በገላን ጉራ አካባቢ በ17 ቀን ውስጥ ጂ+4 እና ጂ+ 2 ትምህርት ቤቶች ተገንብቶ አልቆ ጣራ እየተመታ ነው። በዚህም የልማት ተነሺዎቹም ደስተኛ መሆናቸውን ማወቅ ችለናል።
አዲስ ዘመን፡- አርሶ አደር የሚበዛበት ክፍለ ከተማ ስለሆነ መሬት ወረራ እንዳይፈጸም ምን እየተሰራ ነው?
አቶ መሃመድ፡- ወረራ አለ የሚል ግምገማ የለንም። አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ላይ ብዙ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው። ከመንገዶች መገንባት እና መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ ብዙ ፍላጎቶች ወደ ከተማው እየመጡ ነው። ደላሎች ፊታቸውን ወደዚህ ያዞረበት ሁኔታ አለ። ይሄንን ለመከላከል ግን ለእያንዳንዱ አርሶ አደር ካርታ ወጥቶለታል። እራሱ እንዲያለማ እየደገፍነው ነው።
ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ከዚህ ነጻ ነን ማለት አንችልም። አንድ ቦታ ላይ በርካታ ካርታዎች የማውጣት አካሄድ አለ። በ2015 ዓ.ም እንደዚህ አይነት ወረራዎች ስለነበሩ እርምጃ ወስደንባቸዋል። ‹‹ኦቨር ላፕ›› ያደረጉ ካርታዎች እንዲመክኑ ተደርገዋል። መሬት ባንክ የገቡ ቦታዎችንም ታፔላ አቁመንባቸዋል። እያንዳንዱን መሬት ተፈራርመን ለደንብ ማስከበር ሰጥተናል። መሬቱ ለሌላ ልማት ሲፈለግ ተቀናሽ እናደርጋለን።
ያለ ትዛዝም መሬቱን አያስረክብም። ችግሮች ሲኖሩ ሕዝቡ ጥቆማ ይሰጠናል። ስለዚህ በክፍለ ከተማው የመሬት ወረራ እንደችግር የሚነሳበት ደረጃ ላይ አይደለም። አሁን ላይ ከመሬት ወረራ ተያይዞ አደጋ የተፈጠረበት ሁኔታ የለም ።
አዲስ ዘመን፡- ለረጅም ግዜ ታጥረው የቆዩ መሬቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ መሃመድ፡- የኢንቨስትመንት ፈቃድ እኛ አንሰጥም። ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ፈቃድ ወስደው ነው። በሊዝም መሬት የሚወስዱ ካሉ ግዜ ይሰጣቸዋል። ከተማ አስተዳደሩ ቡድኖችን አዋቅሮ ስራ መጀመር አለመጀመራቸውን ያጣራል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ግን ለኢንቨስተሮች የከተማ ካቢኔ እንዲለሙ ወስኖላቸው ቦታውን ሊረከቡ ሲመጡ አርሶ አደሮች ፍርድ ቤት ይሄዱና እግድ ያመጣሉ። አርሶ አደሮቹ እራሴ አለማለሁ ይላሉ። ነገር ግን አስቀድመው ያስገቡት ፕሮፖዛል የለም፤ ለወደፊት እያሰብኩ ነው የሚል ሀሳ ይሰጣሉ።
አንዳንዶቹ ደግሞ አቅም የላቸውም። ሌሎች ሰዎች ከጀርባቸው ይሆኑና “እኔ አመቻችልሃለሁ” ቦታውን አትልቀቅ ይሏቸዋል። ፊት ለፊት የሚመጣው ግን አርሶአደሩ ነው። ከጀርባ ያሉትን ሰዎች አናገኛቸውም። ከዚያም ወደ ክስ ይሄዳሉ። እግድ ሲወጣባቸው አንድ ዓመት እና ከዛ በላይ የፍርድ ሂደቱ ስለሚቆይ ቦታዎቹ በነበሩበት ሁኔታ ይቆያሉ።
ሕጉ የሚለው መሬቱ ለልማት ተፈልጎ፤ በካቢኔ ውሳኔ ቦታው ለልማት ሲተላለፍ ለአርሶ አደሩ የካሳ ክፍያ ይሰጣል። ነገር ግን አልቀበልም የሚል ከሆነ ገንዘቡ በዝግ አካውንት ገቢ እንዲደረግ ይደረጋል። የፍርድ ሂደቱ ሲያልቅ እንዲሰጠው ይደረጋል። ይግባኝ እየተጠየቀባቸው እስከፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድረስ የሚሄዱ ጉዳዮች አሉ። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ቦታዎች ላይ መጓተቶች ይኖራሉ። ከዚያ ውጭ ያሉ ቦታዎች ላይ ግን ከተማ አስተዳደሩ ክትትል እና ቁጥጥር እያደረገ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፡- ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች ጥያቄያቸው ከምን የመነጨ ነው? የካሳ ክፍያ ተመኑስ ምን ያህል ነው?
አቶ መሃመድ፡– ከካሳ ጋር የተያያዙትን ጉዳዮች በተለያየ መንገድ ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛው ከ2012 ዓ.ም በፊት ካሳ የተከፈላቸው አሉ። በፊት ካሳው ሲከፈላቸው በካሬ የታሰበው ክፍያ ዝቅተኛ ነበር። አንድም መሬት ጾም ማደር የለበትም ተብሎ ካሳ ተከፍሏቸው ተመልሰው እንዲያርሱ ተደርጓል።
አሁን በካቢኔው ውሳኔ ተሰጥቶበት ቦታው ለልማት ሲፈለግ “እያረስኩት ነው ልጆቼን የማበላው የለም” ብለው ጥያቄ ይዘው ይመጣሉ። ይሄንን ቅሬታ ለመፍታትም የከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ተገንዝቦ የልዩነት ካሳ እንዲከፈላቸው አሰራር ተፈጥሯል። በፊት ከ40 እስከ 80 ብር በካሬ እንዲከፈላቸው ለተደረጉ ሰዎች አሁን ማሻሻያ አድርገን አንድ የጤፍ ማሳ የነበረበት የካሳ ክፍያው በካሬ 235 ብር እንዲሆን አድርገናል። ስለዚህ አሁን በተከፈለው ክፍያ እና አሁን ባለው ተመን መካከል ያለውን ልዩነት ተከፍሏቸው እንዲነሱ ይደረጋል።
መሬት ላይ ብዙ ግዜ ሪፎርም ይሰራል። በሪፎርሞችም መሃል የማስነሳት ሂደቱ በመሃል ይቆማል። አሁን ላይ የተሻሻለ ነገር አለ። አርሶ አደሩ በራሱ መሬት ላይ ማልማት ይችላል። ነገር ግን ማልማት የሚችለው ካቢኔው ሲወስንለት ነው። ይሄ ሂደት ግን ግዜ ይወስዳል። በዚህ መሃል አርሶ አደሩ መሄድ ያለበትን የአሰራር ሂደት መከተል አይፈልግም። ዛሬም እዚሁ ከተማ ላይ እርሻ እያረሱ መኖር ይፈልጋሉ። ይሄ ደግሞ አይበረታታም። አሁን የተሻሻሉ መመሪያዎች ስላሉ በዚያ መሰረት እየተስተናገዱ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በከተማ ግብርና ዙሪያ በክፍለ ከተማው ምን ተሰርቷል? ብድር እና ድጋፍ ሲያገኙ ለተገቢው ዓላማ መዋሉን ቁጥጥር ታርጋላችሁ?
አቶ መሃድ፡– በዚህ ዙሪያ ከፍተኛ ስራ እየሰራን ነው። ነዋሪው በራሱ ይዞታ ላይ ከብቶችና ዶሮዎችን ማከናወን ይችላል። በዚህም ብዙ ነዋሪ ተጠቃሚ ሆነዋል። በሀገር ደረጃ ልምድ የተወሰደው ከእኛ ክፍለ ከተማ ነው። በክፍለ ከተማችን ከሶስት ሺህ እስከ አምስት ሺ ዶሮ ያላቸው አርሶ አደሮችንም መፍጠር ችለናል። የተቀናጀ የከተማ ግብርና ላይ ሰፊ ስራ ሰርተናል። ብዙዎችም ሕይወታቸውን ለውጠዋል። በክፍለ ከተማችን የልሕቀት ማዕከልም በመኖሩ ስልጠናዎች ይሰጣሉ።
ነገር ግን መድከም የማይፈልጉ እና ለድጋፍ ተብለው የሚደረጉላቸውን ድጋፎች ለሌላ ዓላማ የሚያውሉ የሚሸጡም እንዳሉ ደርሰንበታል። የማስተካከያ እርምጃዎችን ወስደናል። ግንዛቤ የመፍጠር ስራም እየሰራን ነው። የዚህን አይነቱን ችግር ለመቅረፍ ግን ጊዜ ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ከሸገር ሲቲ ጋር በተያያዘ የወሰን ማካለል ችግሮች እና ቅሬታዎች ተነስተው ነበር። ችግሮቹን በምን መልኩ ፈታችሁ?
አቶ መሃመድ፡– ከወሰን ማካለል ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ነገር ይታወቃል። ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር ቡድን ተዋቅሮ እስከ ታች ድረስ የተለያዩ ንዑሳን አደረጃጀቶች ያሉት ኮሚቴ ተደራጅቶ የወሰን ማካለሉ ሥራ ተሰርቷል። ስለዚህ ወደ ተግባር ከመገባቱ በፊት ከማኅበረሰቡ ጋር ሰፋፊ ውይይቶች ተካሂደዋል። ለረጅም ጊዜ ከወሰን ጋር ተያይዞ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች ይታወቃሉ። ጥያቄዎቹ በአሰራር ባለመፈታታቸው ለሕገ ወጥነት መንገድ ሲከፍቱ ነበር።
የሸገር ሲቲ ወሰኑም ለአስተዳደር እንዲያመች የተደረገ እንጂ የልማቱን ሥራ በጋራ እየሰራን ነው። ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ጭምር በመነጋር በጋራ እየተሰራ ነው። አቃቂና ልደታ፤ ንፋስ ስልክ እንደሚባለው ለአስተዳደር የተደራጀ እንጂ ሌላ ልዩነት የሚፈጥር አይደለም። ስለዚህ አሁን ላይ በሸገር ሲቲ እና በአቃቂ መካከል ችግር ሆኖ የተነሳ ጥያቄም የለም።
ፋይል ከማዘዋወር በተያያዘ የሚነሳ ቅሬታ ነበር፤ ለከንቲባ ቢሮ ድብዳቤ በመጻፍ ፋይል ከመለዋወጥ አንጻር ያለው ክፍተት እንዲሞላ ተደርጓል። የሸገርን ውሃ፤ መብራትና መሰል መሰረተ ልማቶችን አዲስ አበባ እያሟላ ነው። ስለዚህ እንደ ችግር ሆኖ የሚነሳ የጎላ ነገር ሳይሆን ጥቃቅን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፡- ክፍለ ከተማው የአዲስ አበባ መውጫ ላይ እንደመሆኑ ከሸገር ከተማ አስተዳደር እና ከሌሎች ክፍለ ከተሞች ጋር በመተባበር ሰላምና ጸጥታ ችግሮች እንዳያጋጥም በምን መልኩ እየሰራችሁ ነው?
አቶ መሃመድ፡– ከሸገር ከተማ አስተዳደር ጋር የጋራ ግብረኃይል አለን፤ በጋራ በመሆንም ስራዎችን እየሰራን ነው። ችግሮችም ሲያጋጥሙ በጋራ በመሆን እንፈታለን። እሬቻ ላይም ይሄንኑ አሳይተናል። የእኛ ‹‹የሰላም ሰራዊት›. እና የእነሱ ‹‹ጋቸና ሲርና›› ጋር በልዩ ሁኔታ ተናበን እንሰራለን። ሌቦችም ከሸገር ሲቲ ሸሽተው እዚህ ሲመጡ በቁጥጥር ስር በማዋል አሳልፈን እንሰጣለን። እነሱም በተመሳሳይ ይሄንኑ ያደርጋሉ። የወጣቶች እና የሴቶች የጋራ መድረክ ስላለ ስለሰላም በስፋት ስለሚሰራ እስካሁን ያጋጠመን ችግር ግን የለም።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ጊዜ እናመሰግናለን።
አቶ መሃመድ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
በሞገስ ተስፋና መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም