ኢትዮጵያ በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እየሠራች ነው

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዘርፍ የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀትንና በነዳጅ ጋዝ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ የሚያስችል ፖሊሲ ቀርጻ እየተገበረች መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ያዘጋጀው በአረንጓዴ ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ላይ ያተኮረ ኢትዮ-ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን እና ሲምፖዚየም በሁዋጃን ኢንዱስትሪ ዞን ትናንት ተከፍቷል።

አፈጉባዔው በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ ሀገሪቱ የአረንጓዴ እምቅ ኃይልን በመጠቀም በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረትና ለረጅም ጊዜ ሀገራዊ ብልፅግናን የሚደግፉ ጠንካራ የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎችን እውን በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

ኢትዮ- ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ኤግዚቢሽን እና  ሲምፖዚየምም ዘላቂ፣ ጠንካራና የበለፀገ ማኅበረሰብን ለመፍጠር እና ያለንን እምቅ የአረንጓዴ ኃይል እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ማሳያ ነው፡፡ በተጨማሪም ዓለም በዘርፉ የደረሰበትን ደረጃና ከፊታችን የሚጠብቀንን ትልቅ ሥራ የሚያመላክት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሀገራችን የተሟላ ለውጥ ለማምጣት፣ እድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ እና የሕዝብን ኑሮ ደረጃ በደረጃ ለማሻሻል በሚደረገው ርብርብ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይሁን እንጂ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ያላቸው ተጨማሪ ትግል የሚፈልጉ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የከተሞች መጨናነቅንና የመሳሰሉ ተግዳሮቶች አሉ። እነዚህን ችግሮች ለማሸነፍ በሚደረጉ ጥረቶችም አዳዲስ ፈጠራዎችና መልካም ዕድሎች እየተስተዋሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ኢኮኖሚን ለማሳደግና እምቅ ሀብትን ለመጠቀም ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ሀገራት በካርቦን ምንጭ ላይ ከተመሠረተው የትራንስፖርት አገልግሎት ምትክ በኤሌክትሪክና በሌሎችም ታዳሽ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገልግሎት በማስገባት ላይ ናቸው ያሉት አቶ ታገሰ፤ በኢትዮጵያም በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፍ የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀትንና በነዳጅ ጋዝ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማምረትና የመገጣጠም ሥራን በማበረታታት እንዲሁም ለዚህ አገልግሎት የሚውሉ መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የሚያስችል ፖሊሲ ቀርፃ ተግባራዊ እያደረገች ናት ብለዋል።

ዘላቂነት ያለው የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል ታዳሽ ኃይል የማዕዘን ድንጋይ በመሆኑ ለስኬቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል።

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት፣ ዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አረንጓዴ ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ ከታለሙ እንቅስቃሴዎች አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ እምቅ የታዳሽ ኃይል ያላት ሀገር መሆኗን አስታውሰው፤ ይህን ዕድል በመጠቀም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፈር ቀዳጅ ለመሆንና የትራንስፖርት መልክዓ-ምድሯን በማሻሻል ላይ ትገኛለች። የ10 ዓመት የትራንስፖርት እቅድም ለሞተር አልባ የትራንስፖርት ስትራቴጂዎች፣ ለሕዝብ ትራንስፖርት ፖሊሲዎችና ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ ይሰጣል ብለዋል።

ለዚህም አስፈላጊውን መሠረተ ልማት ማሟላትና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ዝግጅቱ አረንጓዴ ትራንስፖርትና መሠረተ ልማቶች አምራቾችን፣ የኢንዱስትሪ መሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን እና ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት የትብብር ዕድሎችን ለመፍጠር፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመለወጥ እና ለአረንጓዴ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ ቀልጣፋ የትራንስፖርት ዘርፍ አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን የማሳደግ ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል።

ኤግዚቢሽኑ እና ሲምፖዚየሙ እስከ ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ ታውቋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ኅዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You