አዲስ አበባ፡- ከመኸር እርሻ 6 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል የቢራ ገብስ ምርት እንደሚጠበቅ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ገለጸ፡፡
አርሶ አደሮች የሚያመርቱትን የቢራ ገብስ ለአሰላ ብቅል ፋብሪካ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናገሩ።
በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስተባባሪነት ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ ባለሙያዎች በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የመኸር እርሻ ምርትን እየጎበኙ ነው።
በትናንት ውሎአቸው በአርሲ ዞን ሊሙ ቢልቢሎ ወረዳ በክላስተር ተደራጅተው የቢራ ገብስ የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን ማሳ ጎብኝተዋል።
መንግሥት በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በሰጠው ትኩረት የቢራ ገብስ በስፋት እየተመረተ ይገኛል።
በአርሲ ዞን የቢራ ገብስ አምራች የሆኑ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለአሰላ የብቅል ፋብሪካ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደር ግርማ ከበደ እንደሚሉት፤ ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በክላስተር በመደራጀት የቢራ ገብስ በማምረት ላይ ይገኛሉ።
በሄክታር እስከ 50 ኩንታል ምርት እያገኙ መሆኑን የገለጹት አርሶ አደሩ ምርታቸውን በቀጥታ ለፋብሪካው በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ ሀገር የቢራ ገብስን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በተደረገው ርብርብ የራሳቸውን ሚና ማበርከታቸውን ነው የገለጹት።
ከዚህ በተጨማሪ የቢራ ገብስ ምርጥ ዘር በማባዛት በሀገሪቱ ለሚገኙ አርሶ አደሮች በማሰራጨት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
የአርሲ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገና መሐመድ በዞኑ በመኸር እርሻ 177 ሺህ ሄክታር መሬት በቢራ ገብስ መሸፈኑን ገልጸዋል።
ከዚህም 6 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመው አሁን ላይ በዞኑ ቆላማ አካባቢዎች ምርት መሰብሰብ መጀመሩን አስታውቀዋል።
አርሶ አደሮቹ የገበያ ትስስር ችግር እንዳይገጥማቸው በተሠራ ሥራ ምርታቸውን በቀጥታ ለአሰላ የብቅል ፋብሪካ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከውጭ ታስገባ የነበረውን የቢራ ገብስ አሁን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ መተካት መቻሏን ገልጸዋል።
የአርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ ለሜካናይዜሽንና ክላስተር እርሻ የተሰጠው ትኩረት አመርቂ ውጤት በማስገኘት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
መንግሥት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረጉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ዕድል ፈጥሯል።
ኢትዮጵያ የቢራ ብቅልን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሏ ይታወቃል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ቡድን በአርሲ እና ባሌ ዞኖች የመኸር እርሻ አሰባሰብ እና የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን የሚጎበኙ ይሆናል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ኅዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም