አይ መርካቶ !

መርካቶ በአፍሪካ ትልቁ ክፍት ገበያ ነው:: በየዕለቱም ከፍተኛ የሆነ ግብይት የሚካሄድበት እና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚዘዋወርበት ስፍራ ነው:: መርካቶ ከአካባቢው አልፎ ለሀገሪቱም ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የማይተካ ሚና የሚጫወት ሲሆን በአካባቢው ያለው ሕጋዊም ሕገወጥ እንቅስቃሴ የሀገሪቱን አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴ በአወንታዊም ሆነ በአሉታዊ ጎኑ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው:: ለዚህም ነው ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት መርካቶን አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት ‹‹መርካቶ ላይ ብልሽት ሲኖር ለሀገርም ይተርፋል ››የሚል ምላሽ የሰጡት::

መርካቶ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚስተዋልበት በመሆኑ መንግስት ከአካባቢው ከፍተኛ የሆነ ግብር መሰብሰብ ይፈልጋል:: ሆኖም እስካሁን ባለው ሁኔታ የእንቅስቃሴውን ያህል ለመንግስት ግብር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የሚፈለገውን ያህል አይደለም:: ለዚህ ደግሞ በዋናነት በአካባቢው የሰፈነው ሕገወጥ የግብይት ስርዓት በዋነኝነት ተጠቃሽ ነው::

ለአብነትም የሽያጭ መጠንን ዝቅ በማድረግ የሚፈጸም ግብር መሰወር፤ግዢን ዝቅ በማድረግ የሽያጭ መጠን እንዲቀንስ እየተደረገ የሚፈጸም የግብር ስወራ፤ የተጨማሪ እሴት ታክስ የተለያዩ የማስከፈያ ምጣኔዎች ያለአግባብ በማቀያየር የሚፈጽም የግብር ስወራ፤ የተሰበሰበን ታክስ (VAT) ለመንግሥት አለመክፈል፤ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች በሕገወጥ መንገድ በማስገባት ሊሰበሰብ የሚገባ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማስቀረት፤ ሐሰተኛ የታክስ ተመላሽ መጠየቅ፤ በሀሰተኛ ደረሰኝ ገቢ መሰብሰብ እና የመሳሰሉት የግብር ስራዎችና ማጭበርበሮች ይከናወናሉ:: ጥናቶች እንደሚመለክቱትም እስከ 80 በመቶ የሚደርሱት በመርካቶ የሚካሄዱ ግብይቶች በሕገወጥ መንገድ የሚፈጸሙ ናቸው::

በዚህ ሒደት ውስጥ ጥቂት የሚባሉ ነጋዴዎች ሕጋዊውን የግብይት ስርዓት የሚፈጽሙ ቢሆኑም አብዛኞቹ ነጋዴዎች የግብይት ስርዓታቸውን የሚፈጽሙት በሕገወጥ መንገድ በመሆኑ መንግስት መሰብሰብ የሚገባውን ከፍተኛ ግብር በማሳጣት ላይ ይገኛሉ:: እነዚህ ተግባራት በየዓመቱ የሚፈጸሙ የግብር ማጨበርበርያ ስልቶችም ስለሆኑ እንደሀገር የተቀየሱ እቅዶች በአግባቡ ተግባራዊ እንዳይሆኑ በማድረግ አድገትን ወደ ኋላ የሚጎትቱ ናቸው::

ይህ ደግሞ ሀገርን ለድህነት ዜጎችንም ለጉስቁልና የሚዳርግ ነው:: በገቢ እጥረት ምክንያትም የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዳያልቁ፤ የትምህርት ቤት ምገባ እንዲደናቀፍ፤ የኮሪደር ልማት ስራው እንዲጓተት፤ ሕሙማን እንዳይታከሙ፤ እርጉዝ እናቶች በሕክምና ተቋማት እንዳይገላገሉ፤ ጸጥታ አካላት በአግባቡ ስራቸውን እንዳያከናውኑ እና በአጠቃላይም የተጀመረው የእድገት እና የልማት ጎዳና እንዲስተጓጎል ያደርጋል::

ስለዚህም መንግስት በመርካቶ ሕግ ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት ኅብረተሰቡ በሰፊው ሊያግዘው ይገባል:: ሀገር የሚጸናው በዜጎች ባለቤትነትና ተሳትፎ ነው:: ስለሀገራቸው የሚቆረቆሩ ዜጎች ባሉበትና በማንኛውም ጉዳይ ላይ በባለቤትነት የሚሳተፉ ዜጎች በበዙበት ሀገር ላይ ልማት ይስፋፋል፤ ሰላም ይሰፍናል፤ ብልጽግና ያብባል:: በተቃራኒው ስግብግቦች በበዙ ቁጥር ሀገር ሕገወጥነት ይስፋፋል፤ ወንጀል ይበራከታል:: ማኅበራዊ ቀውስ ይሰፍናል:: ስለዚህም ስግብግቦችን ማጋለጥና ማውገዝ እንዲሁም ለሕግ አሳልፎ መስጠት የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆን አለበት::

ማንኛውም ወንጀልና ሕገወጥ ድርጊት ከሕዝብ የተሰወረ አይደለም:: ሕዝብ የማይሰማው፤ ሕዝብ የማያየው ሁኔታና ድርጊት የለም:: ለዚህም ነው ሕዝብ ያመነበትና የተሳተፈበት ነገር ሁሉ ውጤት የሚያመጣው:: በተለይም ሕዝብና መንግስት እጅና ጓንት ሆነው የተሳተፉባቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ውጤት ማምጣታቸው፤ፍሬ ማፍራታቸው አይቀርም::

የግብይት ስርዓቱን ከሚያዛቡት ባሻገርም በተለይም በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱን ከተገቢው በላይ የሚያጦዙና ከኅብረተሰቡ ችግር ማትረፍ የሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎችን በማጋለጥና ለሕግ እንዲቀርቡ ማድረግ የሚቻለው ሕዝብ ሲተባበር ብቻ ነው:: በኅብረተሰቡ ላይ የኑሮ ጫና እየፈጠሩ የሚገኙ ሕገወጥ ነጋዴዎች በሰዓታት ልዩነት የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር በማድረግ ኅብረተሰቡን ለምሬት መዳረጋቸው የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ቢሆንም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከሕዝብ አይን ሊያመልጡ አይችሉም:: ስለሆነም ለእነዚህ ስግብግቦች ጊዜ መስጠት የበለጠ ዋጋ ያስከፍላልና ሕዝቡ ነቅቶ ሊጠብቃቸው ይገባል::

ሕገወጦች ነፍስ የሚዘሩት ምንቸገረኝነት ሲሰፍን ነው:: ሀገር የዜጎች ናትና ሕገወጥነትን አይቶ እንዳለየ ማለፍ ዜግነትን አሳልፎ መስጠትና ሕገወጥነት እንዲስፋፋ ማድረግ መፍቀድ መሆኑም መረዳት ይገባል:: በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ኃላፊዎችም ቢሆኑ ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚመጡ ጥቆማዎችን ዋጋ በመስጠት አጥፊዎች ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል::

በአጠቃላይ በምንቸገረኝነት የሚታለፉና የመንግስት ኃላፊነት ብቻ ተደርገው የሚወሰዱ ውሳኔዎች በመጨረሻ የሚጎዱት ሕዝብ ነው:: ስለዚህም ሕዝቡ በይገባኛል ስሜት በመንቀሳቀስ የሚታዩ ሕገወጥ ተግባራትንና ብልሹ አሰራሮችን ሊታገልና መስመር ሊያሲዛቸው ይገባል::

መንግስት ይፋ ያደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስርዓት ሀገሪቱ ለገባችበት የኢኮኖሚ አጣብቂኝ ሁነኛ መፍትሄ ይዞ እንደሚመጣ እሙን ቢሆንም ከወዲሁ ማሻሻያውን ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል የሚሯሯጡ ስግብግብ ነጋዴዎችን አደብ ማስያዝ ግን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል:: በእነዚህ ነጋዴዎች የተነሳ ኅብረተሰቡ የበለጠ በኑሮ ውድነቱ ወገቡ መጉበጥ የለበትም::

የእነዚህ ነጋዴዎች ስግብግብነት ታክሎበት የዋጋ ግሽበት አሁንም ትልቁ የሀገሪቱ ፈተና ነው:: በእርግጥ ከግዜ ወደ ግዜ የዋጋ ግሽበቱ መጠነኛ መረጋጋት ቢያሳይም አሁንም ትልቅ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው:: በዚህ ረገድ መንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የወሰዳቸው እርምጃዎች በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው::

ይህንን ችግር ለመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ጥረት መደረጉ፤ የገንዘብ ዝውውሩን ለመቀነስ የገንዘብ እና ፊሲካል ፖሊሲ በጥብቅ መተግበሩና ነዳጅን በመሳሰሉ ቀጥተኛ የኑሮ ውድነትን በሚያስከትሉ ሸቀጦች ላይ ድጎማ መደረጉ የኑሮ ውድነቱ አሁን ካለበት እንዳይጨምር አስተዋጽኦ ያደረጉ ቢሆንም ካለው የኅብረተሰባችን የመግዛት አቅም አንጻር በቀጣይ በርካታ ጥረቶችን በማድረግ የዋጋ ግሽበቱ ከተቻለ እንዲቀንስ ካልሆነ ባለበት እንዲቆም ማድረግ ያስፈልጋል:: በተለይም መርካቶን በመሳሰሉ አካካቢዎች እና በአጠቃላይም በንግድ ስርዓቱ ላይ ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ አስፈላጊ ነው::

ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም የሚተዳደረው በግብርና ነው:: ኢትዮጵያም ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት በሚታረስ የእርሻ መሬትና በግብርና ምርት ቀዳሚ ሀገር ናት:: ሆኖም በተቃራኒው የግብርና ምርቶችና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች እጥረት ካለባቸውና ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከሚታይባቸው ሀገራትም አንዷ ናት:: በአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣምና በተለያዩ ብልሹ አሰራሮች ምክንያት በየቀኑ እየጨመረ የሚሄደውም የሸቀጦች ዋጋ መናር በዜጋው ላይ ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን በመፍጠር ሕዝቡን ለምሬት እየዳረገው ነው::

በተለይም ኀብረተሰቡ በዕለት ተዕለት በሚጠቀ ምባቸው መሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜጎችን ሕይወት እጅግ እየተፈታተነው ይገኛል። በእህል፣ በጥራጥሬ፤ በአትክልት ምርቶች፤ በግንባታ ዕቃዎች እና በቤት ኪራይ ላይ የዋጋ ጭማሪው አሳሳቢ ሆኗል:: ነገሩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመዘገበ ያለው የምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ መሆኑ ነው:: ትራንስፖርት፣ የትምህር ቤት ክፍያና የመሳሰሉት ሲጨመሩበት የሕዝቡን ኑሮ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ እያደረገው ነው::

በየቀኑና በየሰዓቱ የሚጨምረው የሸቀጦች ዋጋ በተለይም ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ኑሮ እንደምርጊት እንዲከብደው ምክንያት ሆኗል:: መሽቶ በነጋ ቁጥር ‹‹ከገበያ ጠፍተዋል››፤‹‹ዋጋ ጨምሯል›› የሚሉት አገላለጾች ኅብረተሰቡን በሰቆቃ ውስጥ እንዲኖር እያደረጉት ነው:: ለዚህ ደግሞ የስግብግብ ነጋዴዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው::

በአሁኑ ወቅት የዋጋ ግሽበቱ 17 በመቶ አካባቢ ነው:: ይህ አሃዝ ቀደም ሲል ከነበረው 33 በመቶ አንጻር ጥሩ መሻሻል ያሳየ ቢሆንም አሁንም ግን የዝቅተኛውን ማኅበረሰብ ትከሻ ማጉበጡ አይቀሬ ነው:: አሁንም ቢሆን በአኃዝ የተቀመጠው የዋጋ ግሽበት ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር የዋጋ ግሽበቱ ምክንያት ምንድነው ብሎ በደንብ ዓይቶ መፍትሔ መስጠቱ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ነው:: የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ባለሁለት አሃዝ ነው:: በሠለጠነው ዓለም የዋጋ ግሽበት ከሁለት በመቶ ብዙም የዘለለ አይደለም:: በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ደግሞ ከአራት እስከ ስድስት በመቶ እንዳይበልጥ ጥረት ይደረጋል:: ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያም በርካታ ስራዎች እንደሚቀሩ አመላካች ነው::

ለአገሪቱ የዋጋ ግሽበት የምርት እጥረት ብቻ የሚፈጥረው አይደለም:: የዘመናዊ ግብይት ዕጦት እና የደላሎችና ሕገወጥ ነጋዴዎች መበራከት ለችግሩ መባባስ መንስዔ ናቸው:: የኢትዮጵያ ገበያ 200 እና 300 በመቶ ትርፍ የሚያዝበት ነው:: ይህ በዓለም ላይ የለም:: ይኼ አካሄድም በፖሊሲ ጭምር ታግዞ ሊስተካከል ይገባል::

የአገሪቷ ገበያ ሥርዓት ዘመናዊ ባለመሆኑ የፖሊሲ ለውጥ ያስፈልገዋል:: ሰሞኑን መንግስት ወደ ትግበራ ያስገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ስርዓትም ለዚህ ሁነኛ መፍትሄ ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል:: በሀገራችን ውስብስብና ኋላ ቀር የሆነ፣ የገበያ ስርጭት ነው ያለው:: አንዳንድ ቦታ እንዲያውም በሞኖፖል የተያዘ ይመስላል:: በተለይ ሸቀጣ ሸቀጥ ላይ ገበያው በሞኖፖል ተይዟል:: ስለዚህ ይህንን በመፍታት አዳዲስ ኩባንያዎችን በማስገባት የውድድር ሜዳውን በማስፋት ረገድ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል:: ዘርፉን ለሚቀላቀሉ የሀገር ውስጥና የውጭ አዳዲስ ኩባንያዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ከተደረገ በአንድ ቀን አዳር የተጋነነ ዋጋ በመጨመር ራሳቸውን ሚሊየነር ለማድረግ የሚጥሩት ስግብግብ ነጋዴዎች ከእንግዲህ ወዲያ ቦታ አይኖራቸውም::

ይህ አካሄድም በውድድር ዋጋ የሚቀንስበትን መንገድ በመፍጠር የኑሮ ውድነቱ እንዲረጋጋ ያደርጋል:: ቀልጣፋ የሆነ አቅርቦትና ውድድር ከተፈጠረ የዋጋ ግሽበቱን መቀነስ ይቻላል:: አዲሱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም ሁሉም ነገር በገበያ እንዲወሰን በር ስለከፈተ በጥቂት ነጋዴዎች ተይዘው የቆዩ ዘርፎችም በርካታ ተዋናዮች እንዲኖሩ በማድረግ ሸማቹ በርካታ አማራጮች እንዲኖሩት ያስችላል::

ግሽበቱን ለመቀነስ በቂ ምርት ሊኖር ይገባል ከተባለ ደግሞ ሸማቾች የሚጠቀሙባቸው ከአገር ውስጥ ሆነ ከውጭ የሚገኝ ምርት በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ከፍ ማድረግ:: ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ግሽበቱ የሚታይ ከሆነ በቂ ምርት እንዳይኖር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ሊሆን ይችላልና በቂ የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ እያስተካከሉ መሄድ:: አሁን ያለው አሠራር እየፈጠረ ያለው የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የሚቀረፀው ፖሊሲ የውጭ ኩባንያዎችንም በማስገባት እንዲረጋጋ ማድረግንም ይጠይቃል::

በአጠቃላይ ግን መርካቶን በመሳሰሉ አካባቢዎች እየተወሰደ ያለው ሕግን የማስከበር ተግባር እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት በሚፈጥሩት ላይ የሚደረገው ክትትል የታለመውን የኢኮኖሚ ሪፎርም መሬት ለማውረድ የሚያስችል በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል::

አሊሴሮ

አዲስ ዘመን ህዳር 12/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You