በዞኑ በ75 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ዘር ብዜት ሥራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፡- የዘር እጥረትን ለመቅረፍ በ75 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ዘር ብዜት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኣሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ አስታወቁ፡፡

የኣሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል የዘር ብዜት ሥራ ስለማይሠራ በዞኑ ያሉ አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር ለማግኘት ይቸገራሉ። ይህን ችግር ለመፍታትም በአሁኑ ጊዜ በዞኑ በ75 ሄክታር መሬት ላይ የተደራጁ አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር ብዜት ሥራዎችን በስፋት እየሠሩ ነው፡፡

ከዘር ብዜቱ ጎን ለጎን አርሶ አደሮች የምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ እንዲያገኙ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተው፤ በማኅበር የተደራጁ አርሶ አደሮችም ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ እያደረጉ በመሆኑ እንደ ሀገር ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ፤ ኣሪ ዞን ተስማሚ የአየር ንብረት፣ ለም አፈርና በቂ ውሃ ያለው በመሆኑ ዘላቂ የሆኑ የግብርና ሥራዎች ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ ከስንዴ በተጨማሪ የምርጥ ዘር ችግርን ለመቅረፍ ዞኑ ከአርሶ አደሮች ጋር በመወያየት በአርሶ አደሮች ማሳ በኩታ ገጠም ላይ በተለያዩ ወረዳዎች በ21 ሄክታር መሬት ላይ የበቆሎ የዘር ብዜት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ተጨማሪ የበቆሎ ዘርን ለማባዛት መንግሥት የጋራ መሬቶችን እንዲሰጣቸው እየጠየቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

እንደ ግብርና መምሪያ ኃላፊው ገለጻ፤ የዘር ብዜቱ አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር ችግር ሳይገጥማቸው የግብርና ሥራቸውን እንዲያካሂዱ ይረዳል፡፡ ዞኑ አዲስ እንደመሆኑ የተጀመሩ የግብርና ሥራዎች ተስፋ ሰጭ ናቸው፤ አርሶ አደሮችም የነበረባቸውን ችግር ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ በቀጣይ የምርጥ ዘር ብዜትን የማስፋት ሥራ በሰፊው ይሠራል፤ ሙሉ ለሙሉ የዘር ብዜት እጥረትን እንደሚፈታም ገልጸዋል።

በኣሪ ዞን የጥላ ማኑፋክቸሪንግ አክሲዮን ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አውግቸው ዘውዴ በበኩላቸው፣ በዞኑ ማኅበሩ ከሚሠራው ሥራዎች መካከል አንዱ የግብርና ሥራ ሲሆን በዋናነት ደግሞ የዘር ብዜት ሥራ ነው። በሀገራችን የዘር ወቅት ሲደርስ የዘር እጥረት ያጋጥማል፤ ይህን ችግር ለመፍታት ደግሞ ሰፊ መሬት ስለሚያስፈልግ አርሶ አደሮችን በማማከር በስንዴ፣ በበቆሎና በሌሎች ሰብሎች ላይ የኩታ ገጠም የዘር ብዜት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ማኅበሩ በዘር ብዜቱ ሂደት ውስጥ እውቀትን ለአርሶ አደሮች ማሸጋገር መቻሉን ያነሱት ሥራ አስኪያጁ፤ አርሶ አደሮች ከማኅበሩ በትራክተር አጠቃቀም፣ በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴንና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ እንዴት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት አግኝተዋል።

በኣሪ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ማኅበሩ እያካሄደ ያለውን የዘር ብዜት የጎበኙ በመሆኑ በቀጣይ የዘር ብዜት ሥራን ለማስፋት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል፡፡

ከበቆሎና ስንዴ በተጨማሪ በ200 ሄክታር መሬት ላይ ማሽላ ለማምረት ውል ገብተናል። ለግብርና ሥራው በቀን በአማካይ 62 ሰው ይሠራል፣ ይህም ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ትልቅ ነው። በጥቅሉ ሲታይ የአርሶ አደሩን ሕይወት መቀየር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ሞገስ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You