አዲስ አበባ፡- የአካባቢና ማኅበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ ረቂቅ አዋጅ ወቅቱ የደረሰበትን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጦች ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑ ተገለጸ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ እና ቆላማ አካባቢና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ይፋዊ የሕዝብ ውይይት አካሂዷል።
በኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ሕግና ደረጃዎች ኃላፊ አቶ ወንደሰን ታደሰ ስለ ረቂቅ አዋጁ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ የአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ረቂቅ አዋጅ ወቅቱ የደረሰበትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሌሎች ለውጦች ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው።
በሥራ ላይ ያለው አዋጅ አሁን በተደረሰበት የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት ጋር የተመጣጠነ የልማት እንቅስቃሴዎች በሰዎችና በአካባቢ ላይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ የሚያይ እንዳልሆነ ገልጸው፤ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት የሚያደርግ በመሆኑ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የቀድሞው አዋጅ ያልዳሰሳቸውን ጉዳዮች በማካተት አዲሱ ረቂቅ አዋጅ የአካባቢያዊ ተፅዕኖ ግምገማ አዋጅ በሚል መዘጋጀቱን አውስተው፤ ይህም ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በሚሆኑበት ወቅት በአካባቢና በማኅበረሰቡ ላይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ በአግባቡ የመገምገም አቅም እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።
የይሁንታ ፈቃድ ሳያገኙ ፕሮጀክቶችን በሚጀምሩ አካላት ላይ ከ500 ሺህ በማያንስ እንዲሁም ከ10 ሚሊዮን በማይበልጥ ብር ቅጣት እንደሚጣል በረቂቅ አዋጁ መቀመጡንም ገልጸዋል።
ባለ ፕሮጀክቶች በየሁለት ዓመቱ የአካባቢና ተፅዕኖ ግምገማ ማድረግ እንደሚገባቸውና የይሁንታ ፈቃዳቸውን በየዓመቱ ማደስ እንደሚጠበቅባቸው በረቂቅ አዋጁ ተጠቅሷል።
በረቂቅ አዋጁ ይሁንታ ፈቃድ ያገኙ የፕሮጀክት ባለቤቶች በየሦስት ዓመቱ የአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖ አጠባበቅ ዕቅዶችን ለባለሥልጣኑ ሊያቀርቡ እንደሚገባም ተመልክቷል ብለዋል ።
ፕሮጀክቶች ላይ የሚደረገው ክትትል ክልሎችን የሚያካትት እንዲሆን በረቂቅ አዋጁ ቢቀመጥ እንዲሁም የይሁንታ ፈቃድ ሳያገኙ ኘሮጀክቶችን በሚጀምሩ አካላት ላይ የሚጣለው ቅጣት የተጋነነ ነው የሚሉ ሃሳቦች በውይይቱ ተነስተዋል።
ፕሮጀክቶች በየሁለት ዓመት ኦዲት መደረጋቸውና የይሁንታ ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ በየዓመቱ እንዲያድሱ መደረጉ በተለይ በርከት ያሉ ፕሮጀክቶች የሚያከናውኑ ተቋማት ላይ የሥራ መጓተት ሊፈጥር ይችላልም ተብሏል።
ለተነሱት ሃሳቦች መልስ የሰጡት የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዳይሬክተር ለሊሴ ለሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ የኅብረተሰቡ ችግር ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ነው። ረቂቅ አዋጁ አሁን እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶችን ብቻ ሳይሆን ሥራ ላይ ያሉና ከሕግ ውጪ የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን የሚገመግም ነው ብለዋል።
የአካባቢ ኤዲት በየሁለት ዓመቱ እንዲካሄድ መደረጉ ፕሮጀክቶች ምን ላይ እንዳሉ ለማወቅ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በሁለት ዓመት ብቻ የተገደበም ሳይሆን ባለሥልጣኑ በማንኛውም ጊዜ ድንገተኛ የኦዲት ሥራ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
ቅጣትን በተመለከተ የቅጣቱ አይነት እንደ ፕሮጀክቱ አይነት የሚወሰን ይሆናል። ቅጣቱ የትኛውም ፕሮጀክት ያለ ይሁንታ ፈቃድ ወደ ሥራ እንዳይገባ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም