አዲስ አበባ፡– የመቐለ ከተማ ውሃ አቅርቦትን ከ20 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ወደ 34 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ማሳደግ መቻሉን የከተማዋ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ቢሮ ገለጸ፡፡
የመቐሌ ከተማ አስተዳደር የውሃና ፍሳሽ ቢሮ ሥራ አስከያጅ አሸናፊ አብርሃ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ የመቐለን ከተማ የውሃ አቅርቦት ለማሳደግ ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ 38 የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ 31 ጉድጓዶች ተጠናቀው ሥራ ጀምረዋል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት በከተማዋን የንፁሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሳደግ ታቅዶ መሠራቱን አውስተው፤ የግብዓት አቅርቦት ችግሮች ቢያጋጥሙም መፍትሔ በማበጀት አመርቂ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ በውሃ አቅርቦት እና ፍላጎት ሰፊ ልዩነት መኖሩን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ለአንድ ሚሊዮን ሕዝብ 120 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ በቀን ያስፈልጋል፡፡ በከተማዋ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በቀን ከ20ሺ ሜትሪክ ኪዩብ የማይበልጥ ውሃ ሲቀርብ ቆይቷል ብለዋል፡፡
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገዙት 15 የውሃ ፓምፖች የከተማዋን የውሃ ችግር ለማቃለል ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ በቀን 45 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ለማመንጨት አቅደን አሁን ላይ ከበፊቱ ወደ 34 ሺህ ከፍ እንዲል አድርገናል ብለዋል፡፡
በከተማዋ አቅራቢያ የሚገኘው ገረብ ሰገን ግድብ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ እየተሠራ መሆኑን ገልፀው፤ በግንባታ ወቅት ያጋጠሙ የግብዓት ችግሮች ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር በጊዜያዊነት ችግሩ እየተቀረፈ ቢሆንም፤ አጠቃላይ ለከተማዋ የመጠጥ ውሃ ችግር ዘለቄታዊ መፍትሔ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በተለይ በመቐለ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ ከተሞች ሮማናት እና ማሪያም ደሐን የንፁሕ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም የከተማው ነዋሪ የውሃ ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
የአቅርቦቱ ችግር በወቅቱ እንዲቀረፍም ማኅበረሰቡ ከቢሮው ሠራተኞች ጋር በመናበብ የተሻለ ሥራ እየሠራ ይገኛል ያሉት አሸናፊ አብርሃ (ዶ/ር)፤ በተለይ የውሃ ብክነት ሲያጋጥም ኅብረተሰቡ ወደ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በመደወል መረጃ እየሰጠ በመሆኑ ከብክነት ጋር ተያይዞ ለሚፈጠረው ችግር በወቅቱ እየተቀረፈ ነው ብለዋል፡፡
የውሃ መሠረተ ልማቶች የሚያጋጥሙ ችግሮችን ፈጣን መፍትሔ ለመስጠት ጽሕፈት ቤቱ አምስት መቶ ገደማ ሠራተኞች ማሰማራቱን ገልፀው፤ በሙያው ብቁ በመሆናቸው ሥራውን ያቀላጥፋሉ ብለዋል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት 16 የውሃ ጉድጓዶች ብቻ ይሠሩ እንደነበር ጠቅሰው፤ በተያዘው ዓመት ወደ ሠላሳ አራት ከፍ ማለታቸውን እና ለቀጣይ ስምንት የውሃ ጉድጓዶች ለመቆፈር ዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል፡፡
መቐለ ትልቅና ብዙ ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ለቀጣይ ሃያ ዓመት እቅድ ተይዞ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ ከዚሁ ጎን ለጎን የአጭር ጊዜ የመፍትሔ ዕቅድ በመዘርጋት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፤
ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በማጠናከር በተለይ የገረብ ሰገን ግድብ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረግ ተመራጭ መፍትሔ ነው ብለዋል፡፡
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም