ፈጣን፣ በእጅጉ ቀልጣፋ፣ ርቀት የማይገድበው፣ ረቂቅና የማይታሰበውን የሚከወንበት ዘመን ላይ እንገኛለን። ከሁሉም ነገር በላይ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉ እጅን በአፍ በሚያስጭን ተዓምራዊ እድገት ላይ ነው ።
ሁሉም ነገር ቀላል እየሆነ የማይታሰበው ነገር ሁሉ በፍጥነት የሚተገበርበት ግዜ። ሉላዊነት ምድራችንን በመዳፋችን ውስጥ ጨብጠን እንድንይዛት እድሉን ሰጥቶናል። መረጃ በበይነ መረብ በማይክሮ ሰከንድ ፍጥነት እደጃፋችን ላይ እየደረሰ ይገኛል።ረቂቃኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ግዜን ይቆጥቡልናል፤ ውስብስብ ችግሮችንም ይፈቱልናል።
በጥቅሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችን የሰው ልጅ የእውቀት ውጤት በፈጠራቸው ሳይንሳዊ ግኝቶች መፍትሄ አግኝተዋል፤ እያገኙም ነው። ስልጣኔን ለማረጋገጥ በአገራት መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ውስጥ የሚፈጠር ጦርነት የአራተኛው ትውልድ የዲጂታል ቴክኖሎጂ “የሳይበር ዋርና” ረቂቅ የባይሎጂካልና የቴክኖሎጂ ጦር መሳሪያዎችን የሚያካትት ሆኗል። ድሮ ድሮ ከዘመናት በፊት የሰው ልጅ ሉዓላዊ ድንበሩንና ማንነቱን የሚከላከለው በጦርና ጋሻ፣ በሹል ድንጋይና ሌሎች ምድራዊ ቁሳቁሶች ነበር።
ያ ዘመን አሁን ከታሪክ መዝገብነት ያለፈ ሌላ ትርጉም የለውም። ዓለም በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በበይነ መረብ፣ በኢኮኖሚ ቀጣናዊ ትስስር በጠንካራ የፋይናንስ ተቋማት የተሳሰረ ሆኗል። የአንዱ አህጉርም ሆነ አገር ህልውና በቴክኖሎጂና ዘመኑ በፈጠረው ዲጂታል ሥርዓት የተሳሰረ ሆኗል።
ከዚህ ስርዓት ውስጥ በጉልበትም ይሁን በኢፍትሃዊነት ዝንፍ ማለት የሚያስከፍለው ዋጋ የትየለሌ ነው። በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምድ ላይ ይህንን ርእሰ ጉዳይ ለማንሳት የወደድነው ያለ ምክንያት አይደለም።
ይልቁኑ የአዲሱ ዓለም የዲጂታል ቴክኖሎጂ ስርዓትና ከእርሱ ጋር ተያይዞ በወቅታዊነት የምናየው የምዕራቡ ዓለም አለመግባባቶችን መቃኘት ስለወደድን ነው። ይህን ጉዳይ በዚህ አምድ ላይ ማንሳታችን እኛ ኢትዮጵያውያን የምድራችንን የዘመኑን የውድድር ዓለም እንድንረዳና ራሳችንን ከዚህ እውነታ ጋር አጣጥመን አገራችን፣ ሉዓላዊነታችንንና ማንነታችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል።
በተለይ ጠንካራ አገር በመገንባት ህልውናችንን ወደፊት ሊፈታተኑ የሚችሉ ጉዳዮችን አስቀድመን እንድንዘጋጅ ስለሚረዳን ጭምር ነው። ለመሆኑ “የዲጂታሉ ዓለም ሥርዓት” እና “የሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ” ከሉዓላዊነት፣ ከጦርነት፣ ከኢኮኖሚና ጥቅል የፋይናንስ ማዕቀቦች ጋር ምን ያገናኘዋል? አገራት በግንባር ከሚደረግ የህልውናና የፍትሃዊነት ጦርነት ውጪ በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚያደርጉት ፍጭትስ ምን ይመስላል? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲያስችለን ከሁለት ሳምንት በፊት ተጀምሮ የዓለምን ትኩረት በያዘው የሩሲያና ዩክሬን ግጭት ውስጥ ለማየት እንሞክራለን።
በተለይ አሜሪካና አውሮፓውያን ሩሲያ ላይ እስከ አምስት ሺህ የሚደርሱ የተለያዩ ከቴክኖሎጂ፣ ከሳይበር፣ ከባንክና መሰል የዓለም የንግድና የግንኙነት ሥርዓት ላይ የጣሉትን ማዕቀቦች ይዘት ለአስረጂነት በሚጠቅም መልኩ በጥቂቱ እንዳስሳለን። በቅድሚያ ግን “የባንክ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓትና የሩሲያ ከስዊፍት ቴክኖሎጂ መገለል ሌላኛው የጦርነት ጎን” የሚለውን ጉዳይ እንመልከት።
ስዊፍት የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ምንድን ነው
በመግቢያችን ላይ “ዓለም በእጃችን መዳፍ ውስጥ ትገኛለች” በማለት የተለያዩ አመክንዮችን ለመጠቃቀስ የሞከርነው እንዲያው በግብታዊነት ተነስተን ሳይሆን በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ተመርኩዘን ነው። ለዚህ ጥያቄ ነጠላ ምላሽ እንዲሆነን ርቀት የማይገድበው፣ እምነትን የማያጎድልና ጥርጣሬን የሚያስወግድ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓትን እንመልከትና ብዙም ሳንቆይ ወደ ዋናው ርእሰ ጉዳያችን እንመለስ። ይህ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ስዊፍት (Worldwide Interbank Financial Telecommunication) ይባላል። ለመሆኑ እንዴትና በምን አይነት ሁኔታ ይሰራ ይሆን? በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ላይስ ምን አይነት የዲጂታል ጦርነት መሳሪያ ሊሆን ቻለ? ብለን መጠየቃችን አይቀርም።
ስዊፍት በዓለም ላይ ያሉ የፋይናንስ ተቋማትና ባንኮች ድንበር ሳይገድባቸው ለደንበኞቻቸው ገንዘብ የሚላላኩበት መንገድ ነው። ለምሳሌ ያክል በአሜሪካ ውስጥ ነዋሪነቱን ያደረገ አንድ ግለሰብ በህንድ አገር ለምትገኝ አንድ ወዳጁ ገንዘብ ለመላክ ፍላጎት ቢኖረው “እንዴት እልከዋለው” የሚል ስጋት አያድርበትም። የሁለቱ አገራት ባንኮችም የግዴታ በተለያዩ ሉዓላዊ አገር ውስጥ መሆናቸው እክል አይፈጥርባቸውም። ምክንያቱ ደግሞ በዓለም ላይ ከ11 ሺህ በላይ ያሉ ባንኮች በስምምነት የዘረጉት የስዊፍት የገንዘብ ዝውውር ቴክኖሎጂ በመኖሩ ምክንያት ነው።
ታዲያ በአሜሪካ የሚገኘው ግለሰብ በአቅራቢያው ያለ ባንክ በመሄድ ገንዘቡን ሲልክ ባንኩ ደግሞ በህንድ አገር ለሚገኘው ሌላኛው ባንክ በስዊፍት ቴክኖሎጂ አማካኝነት ዝርዝር የገንዘብ ሰነዱን በመላክ የግለሰቡ ወዳጅ የተላከላትን ገንዘብ እንድትቀበል ያደርጋል።
ይሄ የገንዘብ ዝውውር ቴክኖሎጂ ታዲያ ኑሮን እያሳመረ አላስፈላጊ ውጣ ውረዶችን በእጅጉ የቀነሰ፣ ግዜንና ስጋትን ያስቀረ ዓለምን በፈጣን የልውውጥ መድረክ እንድትመራ ያስቻለ ነው።
የስዊፍት ባለቤትና ተቆጣጣሪ ማነው?
ስዊፍት የተጀመረው አንድ ተቋም ሥርዓቱን ዘርግቶ የባንኮች የገንዘብ ዝውውር ሥርዓትን በብቸኝነት ጠቅልሎ እንዳይዝ ባቀዱ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ባንኮች አማካይነት ነው።
ሥርዓቱን ከሁለት ሺህ የሚልቁ ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት በጋራ ባለቤትነት ይዘውታል። ይህ የስዊፍት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት በቤልጂየም ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር የሚደረግበት ሲሆን የአሜሪካ ፌዴራል ግምጃ ቤት እና የእንግሊዝ ባንክን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ ዋና ዋና ማዕከላዊ ባንኮችም በቁጥጥሩ ይሳተፋሉ።
ስዊፍት በአባል አገራት መካከል ደኅንነቱ የተጠበቀ ዓለም አቀፍ ንግድ እንዲኖር የሚረዳ ሲሆን ግጭቶች ሲኖሩ ለማንም እንዳይወግን ይጠበቃል። ሆኖም ከዚህ መርኅ በተቃራኒ ኢራን በኒውክሌር መርሃ ግብሯ ላይ በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 ከስዊፍት ታገደች። በዚህም ምክንያት ወደ ውጭ ከምትልከው የነዳጅ ሽያጭ ገቢዋ ግማሹን ያጣች ሲሆን 30 በመቶ የውጭ ንግዷንም አጥታለች። ስዊፍት ግን ማዕቀቡ እንዲጣል ምንም አይነት ተጽዕኖ እንዳላደረገ እና ውሳኔው በመንግሥታቱ ላይ የተመሰረተ ነው ብሏል።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትና የስዊፍት ማዕቀብ መዘዙ
ከአስራ ዘጠኝ ቀን በላይ ያስቆጠረው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት እስካሁን እልባት አላገኘም። ሁለቱም ወገኖች ድርድሮችን ለማድረግና በጠረጴዛ ዙሪያ ለመወያየት ቢሞክሩም አሁንም ግን የጦርነት ስጋቱ በእጅጉ ጨምሯል።
ከሰባ ዓመት በኋላ ታይቶ የማይታወቅ ጦርነት ነው በተባለለት በዚህ ውጊያ ላይ ዓለም አይኖቹን እንደተከለ ነው። አወዛጋቢዋ አገር አሜሪካና አውሮፓ ሩሲያ የዩክሬንን ሉዓላዊነት ጥሳ ወረራ ፈፅማለች በሚል በሞስኮ ላይ የማዕቀብ ናዳ እያዥጎደጎዱ ይገኛሉ።
ሩሲያ ግን ለዚህ ድርጊት ‘ጆሮ ዳባ’ ብላ የኪዮቭን ሰማይና ምድር በሚሳኤልና በብረት ለበስ ታንኮች እያረሰቻቸው ትገኛለች። ከተጣሉት ማዕቀቦች መካከል በሩሲያ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት፣ ባንኮችና በአለም ላይ ያሉ የንግድ ድርጅቶችና ባለሃብቶቿ የስዊፍት የገንዘብ ዝውውር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማገድ ይገኝበታል።
ይህ ቴክኖሎጂ ሩሲያ እያካሄደች ያለችውን ጦርነትእንድታቆም ጫና ለመፍጠር የተደረገ ግፊት አንደኛው አካል ነው። በዚህ እቀባ ላይ በየትኛውም አገር የሚገኝ የሩሲያ ዜጋም ሆነ ሌላ ግለሰብ ገንዘብ ስዊፍት የባንክ ሥርዓትን ተጠቅሞ እንዳይልክ፣ እንዲሁም ከሩሲያ ወደሌላኛው የዓለም ክፍል ክፍያም ሆነ የበይነ መረብ ንግድ ላይ እንዳይሳተፍ የሚያደርግ ነው።
በዚህ እቀባ የሩሲያ የፋይናንስ ተቋማት መሽመድመዳቸው የማይቀር ቢሆንም ለዘመናት የገነባችው ሃያልነት በቀላሉ የሚገረስሰው ግን አይሆንም። ይህ ማለት ልዩ ልዩ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓቶችን ዘመኑ በሚፈቅደው የፈጠራ ክህሎት ለመዘርጋትና ከዚህ ጫና ለመውጣት ሞስኮን ለመሰሉ አገራት የሚከብድ ሆኖ አይታይም።
የማህበራዊ ቴክኖሎጂ እቀባ
በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ታንኮች፣ ሚሳኤሎች ረቂቅ የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም አያሌ ወታደሮች ብቻ ሳይሆኑ የዲጂታሉ ዓለም በጦርነቱ አንድ እየሆነ ይገኛል። እነ አሜሪካና ሌሎች የአውሮፓ አገራት ዩክሬንን ለመከላከል በኔቶ በኩል ጦር የማዝመት እቅድ የለንም እያሉ ቢናገሩም “በዲጂታል ጦርነት” ላይ ግን ቀጥተኛ ተሳታፊ እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።
ይህን ለማለት የሚያስችለው ደግሞ ሉላዊነት የፈጠረውን ድንበር ተሻጋሪ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሩሲያውያንና ዜጎቿን ከቀሪው ዓለም እንዳይተሳሰሩ እያሳደሩ የሚገኙት ጫና ነው። እንደ ምሳሌ ለማንሳት ብንሞክር የሩሲያ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በአውሮፓና በሌሎች አገራት እንዳይሰራጭ የጃሚንግ ቴክኖሎጂ ሰለባ እንዲሆንና የሩሲያን ፕሮፓጋንዳ የማኮላሸት ትግበራ እየተካሄደበት እንደሆነ ማየት ይቻላል።
እቀባው በዚህ ብቻ ሳይወሰን የተለያዩ ግዙፍ የማህበራዊ ድረ-ገጽ አንቀሳቃሽ ኩባንያዎች በዚህ “ኢ-ፍትሃዊ” ነው ብለው በፈረጁት ጦርነት ላይ በዲጂታል ጦርንት አማካኝነት ሞስኮን እየወጉ ይገኛሉ። ለምሳሌ ያክል ስሙን በቅርቡ የቀየረው “ሜታ” የፌስቡክ ካምፓኒ የሩሲያ የፕሮፓጋንዳ ቻናሎችን አቅቧል። በተቃራኒው ሩሲያ ላይ የጥላቻ ንግግር የሚሰነዝሩ ግለሰቦች ልዩ ፈቃድ መስጠቱ አስገራሚው የሳይበር ጦርነት አካል ሆኗል።
እንግዲህ እነዚህ ሁላ ማዕቀቦች ሩሲያን በማሽመድመድ ከጀመረችው አላማ ያሰናክሏት ይሆን? የሚለውን ወደፊት የምናየው ቢሆንም የአሜሪካና የአውሮፓውያን ጣልቃ ገብነት ግን ምን ያህል እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየን ይመስለኛል።
እንግዲህ በዚህ አለም አንድ እየሆነች በመጣችበት ዘመን የትኛውም አገርም ሆነ ሕዝብ ተነጥሎ ሊኖር እንደማይችል ግልጽ ነው። በመሆኑም ዘመኑ የሚዋጀውን እየከወኑ ከአለም ጋር አብሮ መጓዝ የሚጠበቅ ይሆናል። በዚህ መገፋፋት መተነኳኮልና የጥቅም ሽኩቻ በበዛበት የውድድር ጉዞ ተሸናፊ ሆኖ ላለመገኘት አገራት ቢያንስ በሁለት ተያያዥ ነገሮች ጠንካራ ሆነው ሊገኙ ይገባል። የመጀመሪያው ነገር በዚህ የተወሳሳበና ፈጣን ለውጥ በሚከሰትበት ዘመን ከቴክኖሎጂ ጋር መራመድ ነው።
በዚህ ግዜ ከቴክኖሎጂ የሚርቅ እንኳን አገር ይቅርና አንድ ግለሰብም ቢሆን እጁን ወደ ቀደሙት መዘርጋቱ የግድ ነው። በመሆኑም ከገንዘብ ዝውውር የመከላከያ አቅምን እስከማጎልበት ድረስ ወቅቱ ወደደረሰበት የቴክኖጂ አቅም መጠጋት አገርን ከዘመኑ ወረራ ለመታደግ አስፈላጊ መንገድ ነው። ሁለተኛው ነገር በየጉዳዩ ሰበብ እየፈለጉ ጣልቃ ለሚገቡት አሜሪካና ግበረ-አበሮቿ በር ላለመክፈት ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት ነው።
በዚህ ዘመን ደግሞ ያለ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ አቅምን ለማጎልበት መሞከር ህልም ሳይሆን ቅዠት ነው። በመሆኑም አቅም በፈቀደ መልኩ ከምንም በላይ ቅድሚያ በመስጠት ትኩረትንም ጥረትንም ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴክኖሊጂ ግኝቶችን ወደ አገር ማስገባት ላይ ሊሆን ይገባል መልዕክቴ ነው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 /2014