የዓለም ትልቁ ውድድር በየአራት ዓመቱ ከሚያካሂደው ኦሊምፒክ ባሻገር፤ ተጨማሪ ውድድሮችንም እንደሚያካሂድ ይታወቃል። የፓራሊምፒክ፣ የወጣቶች፣ «ስፔሻል» ኦሊምፒክ፣… ይጠቀሳሉ። በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ የሚካሄደውም በኢትዮጵያ ብዙም ዕውቅና የሌለው የስፔሻል ኦሊምፒክ ነው። ይህ ኦሊምፒክ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ስፖርተኞች የሚያሳትፍ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ እንደምትሆን የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን በድረ ገጹ አስታውቋል። በዓለም ላይ ከ200 ሚሊዮን ህዝብ በላይ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ቢኖሩም፤ በተለይ በታዳጊ ሃገሮች የተገለሉና ለከፋ ኑሮ ተጋላጭ የሆኑ ናቸው።
በዚህም ምክንየት የተለያዩ ዕድሎችን እንደማያገኙ ይታወቃል፤ በዚህም በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ለማሳተፍ በሚል ኦሊምፒኩ መካሄድ ጀምሯል። እአአ በ1968 በጆን ኦፍ ኬነዲ ቤተሰቦች በአሜሪካ ሲመሰረት፤ የመጀመሪያው ውድድርም በቺካጎ ነው የተካሄደው፡፡ ላለፉት 50 ዓመታት ውድድር በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ እአአ ከ2003 ጀምሮ ከአሜሪካ ባሻገር ሌሎች ሃገራትም እየተፈራረቁ ያስተናግዱታል። ዛሬ የሚጀመረውን ውድድርም አውስትራሊያ፣ ጀርመን እና ደቡብ አፍሪካን ያሸነፈችው የዩናይትድ አረብ ኤሜሬትሷ አቡ ዳቢ ታስተናግደዋለች። በውድድሩ ላይ ከ190 ሃገራት የተወጣጡ 7 ሺ 500 አትሌቶች በ24 ስፖርቶች የሚፎካከሩ ይሆናል።
ለውድድሩ ዘጠኝ ስታዲየሞች የተዘጋጁ ሲሆን፤ የዛሬው የመክፈቻ ስነ-ስርዓትም በዛይድ ስፖርት ሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል። የዛሬ ሳምንት የሚደረገው የመዝጊያ መርሐ ግብርም በዚሁ ስታዲየም ሲካሄድ፤ ባንዲራውም እአአ የ2021 ተረኛ አዘጋጅ ሃገር የሆነችው ስዊድን ትረከባለች። ለመጀመሪያ ጊዜ በመካከለኛዋ ምሥራቅ አገር የሚደረገው ውድድር ላይ፤ ከአትሌቶች ባሻገር 2 ሺ 500 አሰልጣኞችና የቡድን ልዑክ፣ ከ4ሺ በላይ የክብር እንግዶች ይገኛሉ።
ከክብር እንግዶቹ መካከልም ዲዲየር ድሮግባ እና ሮማሪዮን የመሳሰሉ የእግር ኳስ ከዋክብቶች እንደሚገኙ ይጠበቃል። ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ ደግሞ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ይከታተሉታል። ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የምትሳተፍ ሲሆን፤ በሁለት ወንድና ሁለት ሴት በድምሩ በአራት አትሌቶች ትወከላለች። በወንዶች በኩል አትሌት ብሩክ ፈለቀ እና አትሌት ሚሊዮን ያደታ፤ በሴቶች ደግሞ አትሌት ትግስት ኡጋሳ እና አትሌት መዓዛ ኤልያስ በውድድሩ እንደሚሳተፉም መረጃው ይጠቁማል። በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍ ሪካ 14 ሃገሮች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፉ ይሆናል። ይህ ስፖርታዊ ኩነትም ከስፖርታዊ ውድድር ባሻገር አካታች ማህበረሰብን ለመፍ ጠር የሚደረግ እንቅስቃሴም ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 5/2011
በብርሃን ፈይሳ