የተወለዱት ሰሜን ወሎ ወልዲያ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ጎንደር በር ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ግን አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት ምስራቅ አጠቃላይ ይባል በነበረው ትምህርት ቤት ነው የተማሩት፡፡
ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በባዮሎጂ ዲፕሎማቸውን አግኝተዋል፡፡ ለአምስት ዓመታት ቦሌ እና አዲስ ከተማ ክፍለከተሞች እየተዘዋወሩ በሙያቸው አገልግለዋል። ጎን ለጎንም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በትምህርት አመራርና አስተዳደር በመማር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
ወዲያውኑ በዚያው የትምህርት መስክ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተቀጥረው ለአምስት ዓመታት አገለገሉ፡፡ በመማር ማስተማሩ ሂደትም በነበራቸው የላቀ ሚና የረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግን ከዩኒቨርሲቲው ያገኙት እኚሁ ሰው በ2008 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ወደ ተማሩበት ኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው በአማካሪነት እና የጥናትና ምርምር ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
ከዚህም ባሻገር በትምህርትና በትምህርት አመራር በግላቸው የማማከር ሥራ የሚሰሩ ሲሆን የተባበሩት አመራር የበጎ አድራጎት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን እየሰሩ ነው፤ የዛሬው እንግዳችን ረዳት ፕሮፌሰር ማዕረጉ ባይበይን፡፡ ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረጉትን ቆይታም እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜዎትን በትምህርት ጥናት ላይ ያሳለፉ ሰው እንደመሆኑ በአጠቃላይ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ በተለይም በትውልድ ቀረፃው በኩል የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮችን ያንሱልኝና ውይይታችንን እንጀምር? ረ/ፕሮፌሰር ማዕረጉ፡- እንደሚታወቀው ትምህርት የማንኛውም ሃገር የጀርባ አጥንት ነው። የእኛ ማህበረሰብ ለትምህርት ያለው አመለካከት የተለየ ቢሆንም የአደጉ ሀገሮች የበለፀጉት በትምህርት ነው።
አሁን ላይ በኢኮኖሚ በፍጥነት እያደጉ ያሉትን ቻይና እና ደቡብ ኮሪያን ብንወስድ መጀመሪያ እርምጃ የወሰዱት በትምህርት ላይ ነው፡፡ ያልተማረ ትውልድ ወይም አዕምሮ የተሰራን ሃገር ያፈርሳል እንደሚባለው ትምህርት ለአንዲት ሃገር ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ሚና ነው ያለው፡፡
ከዚህ አንፃር የእኛ ሃገር አጠቃላይ ትምህርት ስርዓት ወጣ ገባ የሚል ስትራቴጂ የሚከተል ነው። ይህም ለትምህርት ከምንሰጠው ዋጋ ይጀምራል። ለምሳሌ ስርዓተ ትምህርታችን ውጪ ተኮር ነው፡፡ ሃገር በቀል የሆነ የትምህርት ፍልስፍና የለንም፡፡ በተለይም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት ትምህርት ቤቶቻችን ይመሩ የነበረው በግብፅ ቀሳውስቶችና በህንድ መምህራን ነበር፡፡
ከንጉሱ በኋላ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ቢደረጉም ስርዓቱን ከውጭ ጣልቃገብነት ማላቀቅ አልተቻለም ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር ልንገርሽ፤ በሀገራችን ትምህርትን በተመለከተ እስከዛሬ ሦስት ወሳኝ ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡
የመጀመሪያው አፄ ኃይለስላሴ ዘመን ሊገባደድ ላይ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ ያካሄደው ጥናት ነው፡፡ ይህ ሰው በዋናነት በጥናቱ የሰጠው ምረሃሳብ ‹‹ የሃገራችሁን ሰርዶ በሃገራችሁ በሬ እረሱ ›› በሚል ኢትዮጵያ በትምህርት እንድታድግ ከፈለጋችሁ የሃገራችሁን ሰዎች አስተምሩ፤ ወደ ውጭ ልካችሁ እንዲሰለጥኑ አድርጉ የሚል ጠንካራ ምክሮችን ነው የለገሰው፡፡ ከዚሁም ጎን ለጎን የትምህርት ስርዓቱን ሃገር በቀል የማድረግ ሥራ ዋነኛ ትኩረት እንዲሰጠው ነው ያስገነዘበው፡፡
በተጨማሪም የራሳችን የትምህርት ፍልስፍና ሊኖር እንደሚገባ ነው ያስቀመጠው፡፡ ግን ደግሞ እንዳልኩሽ ንጉሱ ሊወርዱ ሲሉ የተጠና በመሆኑ አልተተገበረም፡፡ ሁለተኛው Sector review የተባለ ጥናት በደርግ ዘመን መገባደጃ ነው የተጠናው፡፡
ይህንን ጥናት እንዳውም ከመምህራን ተደብቆ የተሰራ ጥናት ከመሆኑ የተነሳ ስሙን ቀይረው secret review ወይም ሚስጢራዊው ጥናት እያሉ ነበር የሚጠሩት። ምክንያቱም መምህራኑ የማያውቁት ጥናት በመሆኑ ነው፡፡ የሚገርመው በንጉሱ ዘመን የተሰራው ጥናት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ምክረሃሳብ ነው የተሰጠው፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ፍልስፍና ፤ ሃገር በቀል የሆነ እውቀት እና ግብረገብ ይኑረው የሚል ነው፡፡
ግን ደግሞ ይኽም ተግባራዊ ሳይደረግ የመንግሥት ለውጥ መጣ፡፡ ሶስተኛውና ትልቁ ጥናት ደግሞ የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ጥናት ላይ እኔም ተሳትፌበታለሁ፡፡ ይህም ጥናት የተካሄደው የኢህዴግ መንግሥት ከመውደቂያው አፋፍ ላይ በሆነበት ጊዜ ላይ ነው የተሰራው።
በአጠቃላይ የተሰሩትን ሶስቱንም ጥናቶች ያየሽ እንደሆነ መውደቂያቸው ሲቃረብ ያከናወኑት ዋነኛ ጥናት ትምህርት ላይ ነው፡፡ ይህም ፈረንጆቹ ትምህርት የሁሉም ዘርፎች እናት መሆንዋን የሚያሳይ ነው። ግን ደግሞ አሁን ድረስ ያለው ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ስርዓተ ትምህርት የተኮረጀ ነው፡፡
አብዛኛው እኛን አይገልፀንም፡፡ ስለዚህ እኛን በማይመስልና እኛን በማይሸት ስርዓተ ትምህርት ተምሮ እንዴት ነው ትውልዱ ኢትዮጵያዊ የሚሆነው? እንደምታይው የሰው ሃገር ናፋቂ ነው የሆነው።
ሁለተኛ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ የማንነትና የፍልስፍና ማጣትም ችግር ተፈጥሯል፡፡ ለትምህርት ዋጋ የማንሰጥ ከሆነ ትልቁ ማህበረሰብ አቅጣጫውን ስቶ ነው የሚሄደው። አሁን ያለን ትውልድ ለትምህርት ደንታ የለውም። የመማር ትርጉም ገና አልገባውም፡፡ ብዙ የሆኑ ችግሮችን ከኢኮኖሚው ጋር ይዞብሽ ይመጣል፡፡
በዚህ ምክንያት ትውልዱ ትልቅ ችግር ውስጥ ነው ያለው። ይህ የሆነው ደግሞ በስርዓተ ትምህርቱ ምክንያት ነው፡፡ ስርዓተ ትምህርቱ ብቻ ሳይሆን የተተገበረበት መንገድም ጭምር ነው፡፡
በዚህ ረገድ በተለይ ስርዓተ ትምህርቱ መሬት ላይ ወርዶ የተተገበረበት መንገድ ወይም መንፈስ ትክክል ስላልነበር ነው፡፡ ለምሳሌ በንጉሱ ዘመን ለአስተማሪ የሚሰጠው ክብር በጣም ከፍ ያለ ነበር፡፡ አሁን ግን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ነው የተለወጠው፡፡ ይህንን ከራሴ ተሞክሮ አብነት አድርጌ ልጥቀስልሽ፤ ሐረርጌ በነበርኩበት ጊዜ እስከ አፋርና ሱማሌ ክልል ድረስ የመዘዋወሩ እድል ነበረኝ፡፡ ሐረርንና ድሬደዋን ጨምሮ በዞርኩባቸው አካባቢዎች በማህበረሰቡ በወጣው መመሪያ መሰረት ለጤና እና ለተለያዩ የመንግሥት ሰራተኞች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡
ይሁንና ለመምህራን የሚከራየው ቤቱን የሚከራየው ሲያጣና ባዶ ከሚሆን ተብሎ ነበር፡፡ ይህንን የምልሽ ለቀልድ ወይም ለወሬ ያህል አይደለም፤ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንጂ!፡፡
ማህበረሰቡ ለትምህርት የሰጠው ዝቅተኛ ዋጋ ነው የሚያሳየው። አንድ መምህር መከራ አይቶ እስከ ዶክትሬት ድረስ ተምሮ በእግሩ ነው የሚሄደው፡፡ ግን ደግሞ በተቃራኒው ትናንትና ትምህርቱን በዘፈቀደ እየቀረ ፤ አጥር እየዘለለ አልማርም የሚለው ትውልድ ዛሬ ላይ ባለህንፃና ባለመኪና ነው፡፡ የስልጣን ወንበር የያዘውም ይህ ትውልድ ነው፡፡
የትምህርት ስርዓቱ በተገቢው መንገድ ያለመመራቱ ይህንን ውጤት ነው ያመጣው፡፡ አሁን ሃገራችን ያጋጠማት ችግር የዚህ ውጤት ነው ባይ ነኝ፡፡ ትውልዱ ቁጥር ቆጠረ እንጂ በትምህርት ውስጥ አላለፈም፡፡ እንደምንም ብሎ ዲግሪ ይያዝ እንጂ የዲግሪው ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ አልተረዳውም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው አብዛኛው ድንጋይ ወርዋሪ የሚሆነው፡፡
ሃገር ሲያስረብሽ፣ ሲረብሽ፣ ሲሰርቅ ፤ ሲያጠፋ የሚታየው በአብዛኛው በዚህ ስርዓት ተምሯል የምንለው አካል ነው፡፡ ለዚህም ነው ትምህርት የሁሉም ማህበራዊ ፤ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ዘርፉ ምሰሶ ወይም የጀርባ አጥንት ነው የሚባለው፡፡ አሁን ላይ እንዲህ አይነት ቀውስ የገባው እኮ የሁሉ ነገር መሰረት የሆነው ትምህርት በመመታቱ ነው፡፡
በዚህ ምክንያት ትውልዱን ስደተኛ እንዲሆን አድርገነዋል፤ የተማረው የሰው ሃገር ስርዓተ ትምህርት ነው፤ የሚያስበውም የሰውን ሃገር ነው፡፡ በመሆኑምየትምህርት ፍልስፍና ዳግመኛ መቃኘት አለበት፡፡ በእርግጥ በ2009 ዓ.ም የተጠናው ጥናት ከፊተኞቹ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ የሚባል ነበር፡፡ የተሳተፉበትም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ሃገራዊ ምሁራን ናቸው፡፡
ነገር ግን ትልቁ ችግር የተፈጠረው አፈፃፀሙ ላይ ነው፡፡ አሁን በሚፈለገው መልኩ እየሄደ አይደለም፡፡ የትምህርት ስርዓቱን ወደ መሬት ለማውረድ ብዙ ጥያቄዎች ገብተውበታል፡፡ ስለዚህ እሱም ቢሆን አሁን ላይ አየር ላይ ተንሳፎ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ዶክተሩ፤ አካውንታንቱ ፤ መሃንዲሱ ፤ የህግ ባለሙያውም ሆነ ሌላው የሚገኘው በትምህርት ነው፡፡ ያንን በረሳን ቁጥር ሃገራችንን ረሳን ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ዛሬ ላይ ፎክሮ የሚበላ እንጂ ሰርቶ የሚበላ ትውልድ አልፈጠርንም፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ የትምህርት ስርዓቱ ባዶ በመሆኑ ነው፡፡ ንድፈ ሃሳብ ብቻ ስለነገርነው ክህሎት የሚባለውን ነገር ማምጣት አልተቻለም። ሥራን መፍጠር አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ጠባቂነትን አስፋፍተናል፡፡ ይህ ጠባቂነት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የትምህርት ስርዓቱ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ስርዓቱን ይመሩ የነበሩ ሰዎች ሃላፊነቱን መውሰድ አለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች ግን በደርግ ጊዜ የነበረው የትምህርት ስርዓት የተሻለ እንደነበር ያነሳሉ፡፡ እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ረ/ ፕሮፌሰር ማዕረጉ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽው፤ በደርግ ጊዜ የነበረው የትምህርት በተለይ ከጥራት አንፃር የተሻለ የሚባል ነው፡፡ ግን ደግሞ ማንኛውም ሥራ ፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡ አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ የዚያ ጊዜውም የትምህርት ስርዓት ችግሮች ነበሩበት፡፡
ይኸውም ስርዓቱ በዋናነት ጥራት ላይ ትኩረት ስለሚያደርግ በብዛት ተማሪዎችን ማፍራት ላይ ደካማ ነበር፡፡ በጣም ጥቂት ተማሪዎች ነበሩ ወደ ዩኒቨርሲቲ አልፈው የሚገቡት፡፡ የነበረው ቦታ ውስን ስለነበር ጥሩ ጭንቅላት የነበራቸውና ለሃገራቸው ብዙ ማበርከት የሚችሉ ተማሪዎች ከፍተኛ ትምህርት መግባት አይችሉም ነበር፡፡ ይህ የድሃ ልጅ ለምን ዩኒቨርሲቲ አይገባም ? የሚል ነበር አንዱ የለውጡ ምክንያት፡፡ በነገራችን ላይ ማንኛውም የፖለቲካ ጥያቄ የሚነሳው የትምህርት ተቋም ላይ ነው።
አሁን ሃገሪቱ የገባችበት ትልቁ ችግር የተጸነሰው በ1960ዎቹ ዩኒቨርሲቲዎችና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ በዚያ ጊዜ የነበረው ስርዓት ጥራትን ዋና ነገር በማድረግ ያለን ሃብት ሁሉ የሚፈሰው ለጥራት ነበር፡፡
በዚያ ምክንያት የድሃ ልጅ ተምሮ ዩኒቨርሲቲ አይገባም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ነበር ደርግ ሲወቀስ የነበረው፡፡ ወደኢህአዴጉም ስንመጣ ችግሮች ነበሩበት። ካለፈው ጋር ሲነፃፀር ክህሎት ተኮር ለማድረግ ጥረት መደረጉ የተሻለ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲስፋፉ መደረጉም በበጎ መልኩ የሚታይ ነው፡፡
ነገር ግን ትልቁ ችግር በፍልስፍና ደረጃ ሀገር በቀል የትምህርት ስርዓት አልተቀረፀም፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን ቀራፂዎቹ ራሳቸው ከየትና ለምን እንደኮረጁት በቅጡ አለማወቃቸው ነው፡፡
ልክ የሃገሪቱ የዲሞክራሲ ስርዓት ጫፍ የረገጠ እንደሆነው ሁሉ የትምህርት ስርዓቱም አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ቅኝት ነው የተቃኘው፡፡ አንዱ ክፍል ከአውሮፓ ሲወስዱ ሌላውን ከኤዢያ በማምጣት ግራ የተገባ መዳረሻውንና ግቡን ያልለየ ስርዓት ነው እንዲተገበር ያደረጉት፡፡ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ የእኛ የትምህርት ስርዓት የተመሰረተው በነጮቹ ዶላር ላይ ነው፡፡
ስለዚህ እኛን አስመስለን መውለድና ማፍራት አንችልም፡፡ ለምን ሲባል እኛ ሃብት የለንም፤ ስርዓቱ የራሱ ገቢ የሚያገኝበት ምንጭ የለውም፤ ስለዚህ ከየትም ሃገር ለምኖና ተበድሮ ነው ሃብት የሚያሰባስበው፡፡ ስለዚህ እኛ የእርዳታ ጥገኞች ነን።
በመሆኑም የሌሎችን ፍላጎት ካላስገባን በስተቀር የተሻለ ስርዓት መተግበር አንችልም። ስርዓቱ ሲቀረፅ የአሜሪካ ወይም የእንግሊዝ ፍላጎት ካልተካተተ ብድርና እርዳታን ማስተናገድ አይችሉም፡፡
ይህንን የምነግርሽ እኔ ብዙ ስርዓተ ትምህርት ቀረፀ ሥራ ላይ ተሳትፌ ካየሁት ነገር ተነስቼ ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ላንሳልሽ፤ ከፍኖተ ካርታው በኋላ አንድ ጥናት ለማጥናት አስፈላጊ ዝግጅቶች ተከናውነው ነበር፡፡
ከ22 ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ከተሰባሰቡ በኋላ እኔ እንደአጋጣሚ ቡድን መሪ ነበርኩኝ፡፡ እናም ፕሮፖዛል ( ቅድመ ጥናት) ተሰርቶ፤ ሆቴል ተይዞልን ፤ ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ፤ ቴክኒካልና ፋይናንሻል ሪፖርቱ ከተዘጋጀ በኋላ ፋይናንሱ ትምህርት ሚኒስቴር ቋት ላይ አይደለም ተባለ፡፡ በምትኩ ብሪቲሽ ካውንስል ቋት ላይ መሆኑ ተነገረን፡፡
ስለዚህ የካውንስሉ ሰዎች እኛ ያዘጋጀነው ጥናት ርዕሶቹ እንዲቀነሱና የእነሱ ፍላጎት እንዲገባ አደረጉ፡፡ እነሱ ድጋፍ ስላደረጉ ብቻ ተራ ጥናት ላይ ሳይቀር እጃቸውን ይሰዱ ነበር። አለበለዚያ ድጋፍ እንደማያደርጉልን ነው በግልፅ የነገሩን፡፡ አሁንም በጣም በሚዘገንን መልኩ ፍኖተ ካርታው ሲቀረፅም የእነሱ ፍላጎት እንዲገባ ጥረት አድርገዋል፡፡
የሚገርምሽ በፍኖተ ካርታው የግብረ ሰዶማውያን እሳቤ በዲሞክራሲ ሽፋን እዚህ ካሪኩለም ውስጥ እንዲገባ ጥረት አድርገዋል፡፡ በእኛ ሃገር የማህበረሰብ አንቂዎች ርብርብ ሳይሳካ ቀረ እንጂ እነሱ አላማቸው ብዙ ነበር፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን የእኛ የምንለው የትምህርት ፍልስፍና የለንም፡፡ ለዚህ ነው ድንግርግር ያለን፡፡ ይሄ ችግር በሁሉም ዘርፍ ነው ያለው፡፡
አሁን ፍቅራችን ተንዶ እዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ የገባነው የራሳችን የሆነ ሃገር በቀል በሆነ ፍልስፍና የማንመራ በመሆኑ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሃገር ውስጥ የሚሰሩ የእርዳታ ድርጅቶች ለእኛ አስበው የሚሰሩ እንዳይመስልሽ። እነዚህ ድርጅቶች ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ድረስ የትምህርት ተቋማትን ተከፋፍለው ይዘውታል።
ያረጀ፤ ያፈጀ፤ የነተበ ንድፈ ሃሳባቸውን ከአውሮፓ እያመጡ የእኛን ትምህርት ተቋማት ይሞሏቸዋል። እኛ አዲስ ነገር እንዳናስብ፤ ዘመኑን የሚዋጅ ሥራ እንዳንሰራ እነሱ ተጠቅመው የጣሉትን ወይም የማይሰራ ፍልስፍና አምጥተው ግራ ስንጋባ እንድንኖር ያደርጉናል፡፡
ለምሳሌ ቢ.ፒ.አር ወይም ቢ.ኤስ .ሲ የለውጥ መሳሪያዎች የሚገርሙሽ በዓለም ላይ የተተገበሩት በ1960ዎቹ አሜሪካና አውሮፓ የተተገበረ ነው፡፡ ከ70 ዓመት በኋላ ወደእኛ ሃገር ላኩት፡፡ የእኛ ሃገር የቴክኖሎጂና የፍልስፍና መውደቂያና መሞከሪያ ነው ያደረጉን፡፡
ዞሮ ዞሮ ሃገር ራሷን የሚመስል ነገር ከሌላት መፍረሷ አይቀሬ ነው፡፡ በአጠቃላይ ለዚህ ደግሞ ትምህርት ትልቅ ሚና አለው፡፡ አሁን በዚህ በ30 ዓመት ውስጥ ያየነው ትውልድ እንዳውም የመከነ ትውልድ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም በዚህ ስርዓት ተቀርፆ ነው ያለፈው፡፡
በዚህ ላይ እኔ ራሴ ያጋጠመኝን ልንገርሽ፤ ፈተና እየፈተንኩ ሳለሁ አንዷ ተማሪዬ በጣም በጠበጠችኝ፤ ቦታ ብቀይራትም አርፋ መቀመጥ አልቻለችም፡፡ ከፈተናው በኋላ ቢሮ ጠርቼ ችግሩን ብጠይቃት ‹‹ ስኮርጅ እስካለየኸኝ ድረስ፤ ብሰርቅ እንኳን ሥራ ነው›› አለችኝ፡፡ አየሽ የአንድ ሃገር መሪ ይህንን ካለ ትውልዱ ሊማር የሚችለው ይህንን ነው፡፡ በአጠቃላይ ትውልድ ይቀረፅ የነበረው በዚህ መልኩ ነበር፡፡ ስለዚህ ተቋሙንም ሆነ ትውልዱን ያበላሹት መሪዎቹ ናቸው።
እኔ ለዚያች ተማሪ መልስ መስጠት እንኳን አልቻልኩም ነበር፡፡ ትውልዱ በዚህ አስተሳሰብ ተንጋዶ በማደጉ ምክንያት በአቋራጭ መክበርን ነው የሚፈልገው፡፡ መስራት አይፈልግም፡፡ ማንነቱን ክዷል፡፡ ታላቁ ማህተመ ጋንዲ እንደሚለው ትምህርት ማለት አዕምሮን፤ ልብንና እጅን ማስተማር ነው፡፡ መልካም ነገርን የሚያስብ አዕምሮ ፤ ቀና የሆነ ልቦና እና የሚሰሩ እጆችን መፍጠር ነው፡፡ በዚህ መስፈርት አሁን የሚመረቁት ተማሪዎች ብትመዝኚ አንድም ተማሪ ላታገኚ ትቺያለሽ፡፡ ቀና ልቦና ለሃገር ያለው ተማሪ የለም፤ ከዚያ ይልቅም የእምነትና የብሔር አክራሪ የሆኑ ትውልዶችን ነው ያፈራነው፡፡
ብዙ ፅንፈኞች የተፈለፈሉት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ነው፡፡ አሁን ላይ በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚመራ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አላስተማርነውም፡፡ የሚሰሩና የሚፈጥሩ እጆች የሉትም፡፡ አንድ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ አንድ ትምህርት ቤት ላይ ስመላለስ አንድ ነገር ሰማሁ፤ የሚገርምሽ ነገር ተማሪዎቹ ራሳቸው የአይ.ሲ.ቲ ክፍሉን በጣራ ገብተው በቀን ዘርፈዋል፡፡
አንዱ ተማሪ በር ላይ ተይዞ ሲጠየቅ የመለሰው ‹‹ድርሻችን ነው›› ብሎ ነው የመለሰው፡፡ ስለዚህ ድርሻዬ ነው የሚል ትውልድ ባለበት ሃገር ላይ ሃገርን የሚያቀና ዜጋ መፍጠር እንዴት ይቻላል?፡፡ አሁን ሃገሪቱ ለገባችበት ማጥ ትልቁ ምክንያት የትምህርት ስርዓቱን በሚገባ አለመቃኘታችን ነው፡፡
አሁንም ቢሆን የተለወጠ ነገር ስለሌለ ትውልዱ አንደኛ ራሱን እንዳይሆን ዳርጎታል፤ ራስ ወዳድ ብቻ እንዲሆን አድርጎታል፤ ማንነቱን እንዲሸጥ አድርጎታል፡፡ ሁለተኛ የሰው ሃገር ናፋቂ አድርጎታል፤ በሶስተኛ ደረጃ ሰርቶ እንዳይበላ ጠባቂአድርጎታል፡፡ በተጨማሪም ሰጥቶ የመቀበል መርህ እንዳይኖረውና ስግብግብ አድርጎታል፡፡
በነገራችን ላይ ይህ ሆን ተብሎ ነው የተሰራው፡፡ ለሁሉም ዲግሪ ከመስጠት ባለፈ ተወዳዳሪ እንዳይሆን ፤ሰርቶ እንዳይበላ ነው የተደረገው፡፡ ከዚያ ይልቅም ሃሜተኛ የሆነ ትውልድ ፤ ዘራፊ የሆነ ትውልድ ወይም ደግሞ ብሔርተኛ እና ሃይማኖተኛ ሆኖ እነዚህን ተቋማት መሸጎጫ ያደረገ ብኩን ዜጋ እንዲፈጠር ተደርጓል።
ያ ለዓመታት የተሰራ ሥራ ውጤቱን አሁን እያየነው ነው የምንገኘው፡፡ አዲስ ዘመን፡- በዚህ ትምህርት ስርዓት የከፍተኛ ትምህርት ምደባው ፍላጎትንና ክህሎትን ያላማከለ መሆኑ ምን አስከትሏል ብለው ያምናሉ? ረ/ፕሮፌሰር ማዕረጉ፡- ይሄም መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ 70 በ30 የትምህርት ምደባ መሰረታዊ ዓላማው ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመገንባት ያለመ ነበር፡፡ ይሁንና ፍላጎቱና ትግበራው አልተገናኘም፡፡
አሁንም ትልቁ ችግር የሆነው በትምህርት ስርዓቱ የሃገሪቱን ታሪክና ህልውና ማፍረስ የተጀመረው ትምህርት ላይ ነው፡፡ መጀመሪያ እንደገቡ ዩኒቨርሲቲ ዳግም ሲያዋቅሩ የታሪክ ትምህርት ክፍል በትምህርት ተቋማቱ ሁሉ እንዳይሰጥ ነው ያደረጉት፡፡ አሁን ያለው ወጣት ስለኢትዮጵያ ገናና ታሪክ የሚያውቀው ነገር የለም። ሃገራቸውን እንዳያውቁ ተደርገዋል፡፡
ማህበራዊ ሳይንስ ትውልድን የማንቂያ ዘርፍ በመሆኑ በስሩ ያሉ ትምህርት ክፍሎች በሙሉ እንዲደበዝዙ ተደረገ። 70 በመቶ የሚሆነው ተማሪ በሙሉ ፍላጎቱንና ነባራዊ ሁኔታውን ባላገናዘበ ሁኔታ የተፈጥሮ ሳይንስ እንዲማር ተደረገ፡፡ ኢንዱስትሪውና መሰረተ ልማቱ በሌለበት ሁኔታ በርካታ ተማሪዎች በዘርፉ እንዲሰለጥኑ ተደረገ። በጣም የሚያሳዝነው የኬሚካል ኢንዱስትሪ በሌለበት ሃገር ብዙ ኬሚስቶች ተማሩ። ይህም ይሁን ግን ጥሩ የሆነ ቤተ-ሙከራ እንኳን የለንም፡፡
በዚህ ምክንያት ለሁለት አስርተ ዓመታት ትውልድ መከነ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የትምህርት ክፍሎችን በመዝጋታቸው አስተማሪ ማምረት አልተቻለም፡፡ ሲዘጋ ትምህርት ቤቶች ላይ ክፍተት ተፈጠረ፤ ወደ ትምህርት ቤቶች የሚገባ አስተማሪ ጠፋና ትምህርት ቤቶቹ ባዶ ሆኑ፡፡ በተቃራኒው በተፈጥሮ ሳይንስ በገፍ የሚመረቀው ተማሪ ሥራአጥ ሆነ፡፡ እንግዲህ ይህ ስርዓት ያስከተለውን ኪሳራ መገመት አያዳግትም።፡
ሳይታሰብበት የሚሰራ ሥራ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የሃገሪቱን አቅም ባከለ መልኩ ነበር ምሁራንን ማፍራት ይገባ ነበር፡፡ አቅጣጫው የት እንደሚሄድ ሳይታወቅ ፖለቲከኞቹ እያራገቡ ትውልዱ ለዚህ ሁሉ ውድቀት እንዲዳረግ ምክንያት ሆኗል።
በአይሲ ተመርቀው መሰረታዊ የሚባሉትን ሶፍትዌሮች በቅጡ የማያውቁ በርካታ ናቸው፡፡ ስለዚህ የሚደረገውና የሚፈለገው ነገር የሰማይና የምድር ያህል ዛሬም ድረስ ተራርቀው የሚታዩት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመጀመሪያ ደረጃ ሳይቀር የታሪክ ትምህርት ተዛብቶ ትውልዱ እንዲማር ስለመደረጉ ብዙዎች ቅሬታቸውን ያነሳሉ፡፡ ለመሆኑ እርሶ ይህንን ችግር አስተውለዋል? ከሆነ ምን አስከተለ ብለው ያምናሉ?
ረ/ ፕሮፌሰር ማዕረጉ፡- አስቀድሜ እንደገለጽኩት የታሪክ ጉዳይ ማንነት ነው፡፡ ታሪክ ትውልድን መቅረጫ ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ ታሪክ ነገን የምንመለከትበት ነው። በወቅቱ የነበረውን ማህበራዊ ትስስር፤ ኢኮኖሚ እድገትና ፖለቲካዊ ስርዓት የሚያሳያ መነፅር ነው፡፡ ይህችን ሃገር የማትፈለግ ለማድረግ ሲፈለግ የመጀመሪያ እርምጃ የተወሰደው ታሪክን ማዛባት ነው፡፡
ተገቢ ባልሆነና እውነታውን በሳተ መልኩ ታሪክ ተፅፎ የታሪክ ጠላት የሆነ ዜጋ ነው ያፈራነው፡፡ በአንድ ሃገር ውስጥ የተለያየ የታሪክ ትምህርት እየተሳተ እርስበርሱ የማይጋባ ህዝብ እንድንሆን ተደርገናል፡፡ ለምሳሌ የትግራይ ካሪኩለም ላይ ራስዳሽን፤ ላሊበላ ፤ ወልቃይትና ጠገዴ እንዲሁም ራያ የትግራይ አንድ ክፍል እንደሆነ አስተምረዋቸዋል፤ አሁን በዚያ የተማረ ተማሪ እንዴት አድርገሽ ነው የምትመልሽው?። በዚህ ምክንያት ታሪክ ተዛብቷል። አላስፈላጊ የሆኑ ትርክቶች እንደገና ተነስተው ሃገሪቱን ትልቅ ቀውስ ውስጥ ዳርገዋታል። አሁንም ራሱ ካሪኩለም ውስጥ የተቀረፀ ነገር አለ፡፡
ለምሳሌ የአኖሌ ሐውልት እንዲካተት ተደርጓል። በዚህ ነገር ሁሉም ባይስማማመበት እንኳን መግባባት መቻል አለብን። የመጀመሪያውን እየኮነንን አሁንም እየተሰራ ያለው በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ሐረርጌ ላይ በዳግማዊ ምኒልክ ተሰራ የተባለ ግፍ በካሪኩረሙ ተቀርፆ ተማሪዎች እንዲማሩት ተደርጓል፡፡ ይህ ጥላቻን እንጂ ፍቅርን አይደለም የሚሰብከው፡፡ አኖሌ መቼም ቢሆን ፍቅርን አይሰብክም። 500ሺ ሃደሬ በሌለበት ሃገር ላይ 500 ሺ ሃደሬ ሃረር ላይ ምኒልክ ጨፍጭፏል ተብሎ ጥላቻን ለትውልድ ለማውረስ ይሞከራል፡፡
ስለዚህ የትምህርት ስርዓታችንን የጋራ ታሪክ እንዲኖረን ፤ የጋራ ምሰሶ እንዲኖረን የማናደርገው ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁንም የምናየው የዚህ ውጤትን ነው፡፡ በነገራችን ላይ በትምህርት ስርዓት ውስጥ ብዙ ቀውሶች እንዲፈጠሩ ተደርጓል፡፡ ለዶላርና ለፈንድ ተብሎ ተማሪ እንዳይወድቅ ተደርጓል፡፡ ዝም ብሎ እንዲያልፍ ይደረጋል።
አሁን ትውልዱ ተወዛገበ ብለሽ ብትጠይቂ ሲቪክ ወይም ስነዜጋ እየተባለ የሚሰጠው ትምህርት በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ሲቪክስ ማለት ዲሞክራሲ ነው፤ ዲሞክራሲ የሚጀምረው ደግሞ ከግለሰብ እንደሆነ ያስተምራል፡፡ ትውልዱ የግለሰብ መብት መከበር አለበት ተብሎ ይማርና ከትምህርት ቤቱ ወጣ እንዳሉ ፖሊስ ግለሰብ ይዞ ሲቀጠቅጥ ያያሉ በአደባባይ ላይ፡፡ የቡድን መብትም በተመሳሳይ መንገድ ሲረገጥ ትመለከቻለሽ፡፡ ስለዚህ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ከሚማሩት ትምህርት ጋር ስለማይሄድተማሪዎች ጥያቄ መጠየቅ ጀመሩ፡፡
በ1993 ዓም እኮ ተማሪዎች የመብት ጥያቄ ጠይቀዋል፤ በ1997 ዓ.ም ላይም በተመሳሳይ ተማሪዎች ጥያቄ አንስተው ነበር ፤ ግን የተቀበላቸው ጥይትና ስናይፐር ነበር።
የሚገርምሽ በንጉሱ ጊዜ በውሃ በጭስ ነበር ተማሪዎችን ለመበተን ይሞከር የነበረው፡፡ በ1997 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ህፃናት ላይ ስናይፐር ተደቅኗል። ስለዚህ በዚህ ምክንያት ተማሪው ተስፋ ቆርጧል፡፡
ዲሞክራሲ ወይም የሲቪክ ትምህርት የሚባለው ነገር የውሸት እንደሆነ ነው የሚረዱት፡፡ ብዙዎቹ እንዳውም ‹‹ኬኩን እየነገሩን ፌክ ነው የሚሰጡን›› ነው የሚሉት። በአጠቃላይ የእኛ ሃገር የትምህርት ስርዓት በዚህ 30 ዓመት ውስጥ የምንፈልገውን ሳይሆን እያስገኘልን ያለነው የማንፈልገውን ነው እየሆንን ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህ ታዲያ እንዲያው በጥቅሉ በትምህርት ስርዓቱ ላይ የፖለቲካው ጫና ማሳደሩ ለዘርፉ ውድቀት ሆኗል ማለት እንችላለን?
ረ/ፕሮፌሰር ማዕረጉ፡- ልክ ነሽ፤ አስቀድሜም እንደገለፅኩልሽ የሃገሪቱ ምስቅልቅል የተወለደው እዚህ ጋ ነው። በደርግ ጊዜ ‹‹ትምህርት ቤቶች የደርግ አይንና ጆሮ ናቸው›› ተብለው ነበር የሚገለፁት። በኢህአዴግ ጊዜ ደግሞ ከጆሮና አይን አልፈው የልብ ትርታ ሆኑ፡፡ በየትኛው የሃገሪቱ ጥግ ያለ ትምህርት የፖለቲካ መተንፈሻ እንዲሆን ነው የተደረገው፡፡ ስለዚህ ርዕሰ መምህሩ ሲሾም የግድ ፖለቲከኛ መሆን አለበት።
መምህራኑም እንዲሁም የሚመለመሉት ለካድሬነት ነው፡፡ ስለዚህ የመማር ማስተማሩ ነፃነት እንዲጣስ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአቅምም ሆነ በአስተሳሰብ ከመምህሩ በታች የሆነ ካድሬ ያስቀምጡና እነሱ የሚፈልጉትን እንጂ ትውልዱ ወይም ሃገር የምትፈልገው ሥራ አይሰራም፡፡ በዚህ ምክንያት በተለይ ላለፉት 20 አመታት ሆን ተብሎ ትውልድ እንዲመክን ነው የተደረገው፡፡
ዛሬ ላይ ‹‹ምን አገባኝ›› ብለን ባስተማርናቸው ዶክተሮች ጨጓራችንን ታመን ስንሄድ የራስ ምታት መድሃኒት እየሰጡን ፤ ግራ እግራችን ታሞ ቀኝ እግራችን እየቆረጡ ይልኩናል፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ፖለቲካው እስከዚያ ድረስ ገብቶ ፤ አብኩቶት ያበላሸ በመሆኑ ነው፡፡
ይሄ ችግር ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ብቻ አይደለም የሚቀረው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሰርጎ የገባ ጉዳይ ነው። ዩኒቨርሲቲ ላይ የሚሾመው በመጀመሪያ ደረጃ የፖለቲካ አባል መሆን አለበት፤ ሁለተኛ ደግሞ የብሔር ተዋፅኦም ይታያል፡፡ በዚያ መልኩ ነው የሚመለመለው፡፡
ተማሪው ራሱ ገና ዩኒቨርሲቲ በገባ እለት የመጣበትን ብሔር የሚወክል የፖለቲካ ድርጅት አባል እንዲሆን የሚያደርግ ፎርም እንዲሞላ ይደረጋል። ተመርቆ ሥራ ማግኘት የሚችለው የፖለቲካ አባል ብቻ ሲሆን እንደሆነ ነግረው ያደነዝዙታል፤ በራሱ እንዳይተማመን ያደርጉታል።ይህ ደግሞ ፖለቲካውን ብቻ ሳይሆን ጎጠኝነትን ጭምር ነው የሚያስተምራቸው፡፡
አንድ ወቅት ላይ ዩኒቨርሲቲ ላሉ ተማሪዎች ከ‹‹c›› በታች እንዳይሰጥ ከበላይ አመራሮች ትዕዛዝ ተሰጥቶ መምህራን እጅግ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ በመግባት በግዴለሽነት ትውልዱ ሲመክን ቁጭ ብለው ለመመልከት ተገደው ነበር፡፡ የትም ከርሞ መጥቶ ሳያስተምር ለሁሉም ‹‹c›› ይሰጣል፡፡ እንደዛ አድርገው ነው የትምህርት ስርዓቱን የገደሉት። እኔ በነበርኩበት ሐረርጌ አካባቢ መምህራን ዋና ሥራቸውን ትተው የፖለቲካ ሥራ እያሳደዱ ነው ይኖሩ የነበሩት፡፡ አሁን ላይም ከፖለቲካ ነፃ የትምህርት ተቋም አለን ማለት አንችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ መደረጉ በራሱ ጥቅም ቢኖረውም አብሮ ይዟቸው የመጣ ችግሮች እንዳሉ ይነሳል። እርሶ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ ጥቂቶቹን ይጥቀሱልን?
ረ/ፕሮፌሰር ማዕረጉ፡- አስቀድመን እንዳል ነው ይህንንም ሃገር የማፍረሻ ዘዴ አድርገው ነው የተጠቀሙበት። በነገራችን ላይ ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም። ሰብዓዊ መብታቸው ነው፡፡ ኢህአዴግ ስላመጣው፤ ደርግ ስለነፈገው መሆን የለበትም። በተፈጥሮ የተገኘ መብት ስለሆነ ማንም ሰጪ ማንም ነፋጊ ሊሆን አይገባም፡፡
ሁሉም በራሱ ቋንቋ እንዲማር ከተደረገ ትውልዱን የሚያገናኝ ወይም የሚያግባባ ቋንቋ ሊኖር ይገባ ነበር፡፡ ያ ባለመደረጉ ነው አሁን መግባባት አቅቶን ብትንትን ያልነው። በተወለዱበት ቋንቋ መማር ሃጥያት የለውም፤ ሃጥያቱ ለሌላው ቋንቋ ጥላቻን ማስተማራቸው ነው።
ወንጀሉ ሌላውን ቋንቋ እንደተስፋፊ ወይም እንደ ጠላት አድርጎ መሳሉ ነው፡፡ አሁን ትልቁ ችግር የሃገሪቱ የቋንቋ ፖሊሲዋ ከክልል ክልል ይለያያል፡፡ አማርኛን አሁን የትም ቦታ አታገኚውም ፤ ከክልሉና ከአዲስ አበባ በስተቀር ጠፍቷል፡፡ የሚፈለገውም ይሄ ነበር፡፡ ስለዚህ አማርኛ እና አማርኛ ተናጋሪው የትም ቦታ እንዳይቀጠር አድርገውታል፡፡
የሰው እጥረት እስከሌለባቸው ድረስ በችሎታው ብቻ ተመዝኖ የሚቀጠር ሰራተኛ እየጠፋ ነው የመጣው። ቋንቋ ያለመቻሉ የሚጎዳው ግለሰቡ ሆኖ እያለ ነገር ግን በህግና በስርዓት አስገብተው የሃገሩ ባይተዋር አደረጉት፡፡
ይህም ማለት በቋንቋ አሳበው የሰውን መብት ሁሉ ነው የገደሉት፡፡ ተዘዋውሮ የመስራትንና መኖርን መብቱንም ጭምር ነው የነፈጉት። ስለዚህ ባለብዙ ቋንቋ ህዝቦች እንደመሆናችን ሁሉን በእኩል መንገድ የሚያስተናግድ ስርዓት መፈጠር አለበት፡፡ በቅንነት ከታየ ኦሮምኛ ከአማርኛ እኩል በየመስሪቤቱ ቢስተናገድ ችግር የለውም፤ ነገር ግን አንዱ ደፍጣጭ ሌላው ተደፍጣጭ ተደርጎ የሚሳልበት መንገድ ዋጋ ያስከፍለናል ባይ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በየክልሉ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሃብትና ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የትምህርት ክፍሎችን የመክፈት ፤ ተማሪዎችን የማብቃት ጉዳይ በተለይ ለኢኮኖሚው እድገት የነበረው ሚና እንዴት ይገለፃል?
ረ/ፕሮፌሰር ማዕረጉ፡- አሁን ላይ ዩኒቨርሲ ቲዎች የልህቀት ማዕከል ተብለው ተከፋፍለዋል። እስከዛሬ የነበረው ግን ይህ ስርዓት ያለመዘርጋቱ ለጥራት መጓደል አንዱ ምክንያት ሆኖ ነው የቆየው። በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ትምህርት ክፍል ሲከፈት መስፈርቱን ሲያሟላ ብቻ ነው፡፡ ጥናት ያስፈልገዋል። ማህበረሰቡ ምንድነው የሚያስፈልገው ተብሎ መለየት አለበት። ፍላጎቱና አቅርቦቱ ከተለየ በኋላ ነው ትምህርት ክፍል የሚከፈተው፡፡ የእኛ ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥራቸው ወደ 46 ከፍ እንዲል ሲደረግ በፖለቲካ ጥያቄ እንጂ ህዝቡ በሚያቀርበው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ አይደለም፡፡ እዛ አካባቢ የተሾመ ፖለቲከኛ ካለ በእሱ ወትዋችነት ተቋማት ይከፈታሉ።
የሚገርመው አዳዲስ ዩኒቨርሲቲ ሲከፈት ከሌላው በቀጥታ ተኮርጆ አንድ አይነት ስርዓት ተዘርጎቶ ነው፡፡ ስለዚህ እዛ የተከፈተበት አካባቢ ምሁራን ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ከያሉበት ተጠራርተው ሰፈራቸው ይሔዳሉ፡፡
ሁሉም ታዲያ ሰፈሩ የሚሄደው ማህበረሰቡን በቀናነት ለማገልገል ሳይሆን የራሱን ስልጣን ለማስጠበቅ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ለትምህርት ድርድር መቅረብ የማይገባቸው ጉዳዮች ሲጣሱ ይስተዋላል፡፡ አስቀድሜ ለማብራራት እንደሞከርኩት የፖለቲካ ተፅዕኖው ከታች ከተራው አስተማሪ እስከ ላይ ድረስ የተዘረጋ ስለሆነ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ተገንብቶ ሳያልቅ ትምህርት ክፍሎ ይከፈታል፡፡ የአይ.ሲ.ቲ መሰረተ ልማት ሳይሟላ ትምህርት ይጀመራል፡፡ የትምህርት ተቋማት መስፋፋት ጥሩ ቢሆንም ግን ደግሞ ያለውን አቅም ያማከለ መሆን አለበት፡፡ ይህ ባለመሆኑ የትምህርት ጥራት ድርድር ውስጥ የወደቀው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጦርነቱ የተጎዱ የትምህርት ተቋማትን ዳግመኛ ለመገንባት እየተደረገ ያለው ጥረት ምን ያህል አመርቂ ነው ብለው ያምናሉ?
ረ/ፕሮፌሰር ማዕረጉ፡- በነገራችን ላይ ይሄ ውድመት የሚመነጨው መጀመሪያ ላይ እንዳልኩሽ በ1960ዎቹ የዘውግ ወይም የብሔር ፖለቲካ ሲፀነስ ፤ ህወሓት ወደ ጫካ ሲገባ መነሻቸውም መድረሻቸውን ያደረጉት አማራ ላይ ነው። አማራውን ከምድረገፅ ለማጥፋት አልመው ነው የተነሱት።
ስለዚህ በጊዜ ሂደት ውስጥ የሃሳብ ተዘርቶ ተወልዶ አድጎ ዘንድሮ ፍሬ አፍርቷል፡፡ ምክንያቱም እነዚያ ሰዎች በ1960ዎቹ ጀምረው ይህንን ራዕይ ነድፈው፤ እቅድ አቅደው ሲሰሩ የነበሩት ሰዎች በአንድም ሆነ በሌላ ወገን ዛሬ በፌዴራል ተቋማት ውስጥ አሉ፡፡
ህወሓት መሳሪያ ይዛ ከ30 ዓመታት በላይ አማራን ስታሳድድ ነበር፡፡ ከተገፋችም በኋላ መቀሌ ገብታ ስትሰራው የነበረው ተንኮል፤ ስታሰለጥነው የነበረው ሰራዊት ጫካ ውስጥ ያወጣችውን ማኒፌስቶ እውን ለማድረግ ነው።
አማራና ኦርቶዶክስ ነው ጠላታችን ብላ ተነስታ እሱኑ ስትተገብር ቆይታ በመጨረሻ ሌላ አጋዥ ይዛ መጣች።በዚህ መሰረት በተቀናጀ መልኩ ነው የአማራ ክልል እንዲወድም የተደረገው፡፡ ብአዴን የሚባለውን አሻንጉሊት ካስቀመጠች በኋላ በዚያ ውስጥ ብዙ ተንኮሎችን ሰርታለች፤ ህዝቡ የሞተው ሞቶ ፤ ያለቀው አልቆ 2010 ዓ.ም ለውጥ እስከመጣ ድረስ ብዙ ዋጋ ተከፍሎ ነው የቆየው፡፡
ለውጡ ሲመጣም ህዝቡ ሙሉ ለሙሉ ተስፋ አድርጎ የነበረው በመንግሥት ላይ ነበር። ምክንያቱም ህዝቡ ፈሪሃ እግዚአብሔርና መንግሥት ያለው፤ ህግን ከሁሉ በላይ የሚያከብር በመሆኑ ነው።
ግን ደግሞ ባልጠበቀው መልኩ ህወሓትና ጀሌዎቿ በተቀናጀ መልኩ በድንገት አጠቃው፡፡ እንዳልኩሽ አማራ ክልል ላይ የተፈፀመ ግፍ እና ውድመት አሁን ከለውጡ በኋላ የታቀደ አይደለም፤ ከ50 ዓመታት በላይ ሲብላላ የቆየ ሴራ እንጂ!፡፡
አሁን ጊዜ ደርሶ እንደፈለጉት ክልሉን አውድመውታል። የሚገርምሽ ድሮም ቢሆን አማራ ክልል በመሰረተ ልማት ዝርጋታ እጅግ ወደኋላ የቀረ ነው፡፡ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ተቋም ባጠኑት ጥናት ጨለማው ክልል የሚል ሥያሜ ነው የሰጡት፡፡ አማራ ክልል ከአፋርና ከሱማሌ ክልል ብሶበት የጨለማው ክልል ተብሎ የተፈረጀበት ሁኔታ ነበር፡፡
አሁንም ህብረተሰቡ በላቡ መከራውን አይቶ የገነባቸው መሰረተ ልማቶች የነበረችውን ጭላንጭል ነው ያጠፉበት፤ ያወደሙበት፡፡ ስለዚህ ይህ ሁሉ ውድመት በቀላሉ ይተካል ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ነው። ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ መውደሙን የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡
ዋግምራ ዞን ሙሉ ለሙሉ ወድሟል። ሰሜንና ደቡብ ጎንደር በከፊል፤ ሰሜንና ደቡብ ወሎ ሙሉ ለሙሉ፤ሸዋ ከግማሽ በላይ ወድሟል፡፡ ይህን የምልሽ በቁሳቁስ ደረጃ የወደመውን ብቻ ነው፡፡ የተደፈሩ ህፃናት፤ እናቶች እና አዛውንቶች ስነልቦና በገንዘብ መቼውን ልትመልሺው አትችይም፡፡
የሞተ ህዝብን፤ ያዳጉት ማህበራዊ የስነልቦና ቀውስ አይደለም ለመመለስ ለመግለፅ እንኳን አዳጋች ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ እያለ የተወካዮች ምክር ቤት የመደበው አምስት ቢሊዮን ብር ከደረሰው ጉዳት ጋር ፈፅሞ የሚመጣጠን አይደለም፡፡ የወልዲያ ሆስፒታል ብቻ እንኳን አምስት ቢሊዮን ብር አይበቃውም፡፡ የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የመርሳ ቅርንጫፍ መምህራን መኖሪያቸው በመውደሙ ዳግመኛ ለመገንባት ዘጠኝ ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ነው የታወቀው፡፡
እነዚህ መምህራን አሁን ላይ ሜዳ ላይ ቀርተዋል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ መፍትሔ ነው ብዬ የማስበው ክልሉ ስትራቴጂክ እቅድ ማቀድ መቻል አለበት። የመጀመሪያው ሥራ የክልሉ መሆን መቻል አለበት፡፡ ለእኔ የፌዴራል መንግሥት ሃላፊነት የሚለው ነገር አይዋጥልኝም፡፡
በነገራችን ላይ አማራ ክልል የሰው እጥረት አላነሰውም ፤ በዓለም ላይ የተበተነው ምሁራንና ተወላጆች አሰባስቦ እንደገና ክልሉን መገንባት አለበት ብዬ ነው የማስበው፡፡
አሁን ላይ አንድ የፌዴራል ሆስፒታል አንድ የአማራ ክልል ሆስፒታልን ዳግመኛ ይገነባል ተብሎ የተጀመረው ሥራ ለጊዜው እሳት ከማጥፋት በዘለለ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላምንም፡፡ በጣም ቀላል የተባለ ጥገናዊ ለውጥ እንዲካሄድ ካልተፈለገ በስተቀር የደረሰው ጉዳት እንደ አዲስ ለመገንባት አያስችልም፡፡
ህብረተሰቡ ድሮም ጨለማ ውስጥ ነበር አሁንም በባሰ ሁኔታ ውስጥ ነው እንዲወድቅ የሚያደርገው፡፡ በአጠቃላይ የክልሉ መንግሥት፤ የሲቪክ ማህበራት እንዲሁም ዲያስፖራው አሁን ላይ እጅና ጓንት ሆኖ ያንን ክልል መልሶ ማቋቋም መቻል አለበት። በተለይም በትምህርትና በጤና ላይ አዋጭ የሆኑ ስትራቴጂክ ፕላኖች ተዘጋጅተው ዘላቂ ሥራ መሰራት መቻል አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
ይህንን ግን ለማንም የምንሰጠው ሥራ ሳይሆን ክልሉ ራሱ ሊያስተባብረው ሊመራው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው የሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጠባቂነት ለውጥ ያመጣል ብዬ ስለማላምን ነው፡፡ ሃገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ለጠባቂነት የምትመች አይደለችም፡፡ ስለዚህ የክልሉ መንግሥት ራሱ እየመራ የሚችለውን ሁሉ ማድረግ መቻል አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ረ/ፕሮፌሰር ማዕረጉ፡- እኔ በዚህ መልኩ ሃሳቤን እንድገልፅ እድሉን ስለሰጣችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 /2014