የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር እ. ኤ. አ. ከ2020 ጀምሮ አምስት ሺ ሜትር ሩጫ ውድድር ከዲያመንድ ሊግ ፉክክሮች እንዲወጣ ውሳኔ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡ በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ከፍተኛው ርቀትም ሦስት ሺ ሜትር ብቻ እንደሚሆንና በአጠቃላይ በወንድና በሴት 12 የውድድር ዓይነቶች ብቻ እንደሚኖሩ ከትናንት በስቲያ ኳታር ዶሃ ላይ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ይህንን ተከትሎም በርቀቱ የዓለምን የበላይነት የያዙት አፍሪካውያን ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡
የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዚዳንትና የቀድሞ የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የኦሊምፒክ አሸናፊ እንግሊዛዊው ሴባስቲያን ኮ ወደ ስልጣን ሲመጡ የረጅም ርቀት የቀድሞ ዝናና ስም ለመመለስ እንደሚሠሩ ቃል ቢገቡም አሁን ቃላቸውን አጥፈዋል፡፡ ምሥራቅ አፍሪካውያን በተለይም ኢትዮጵያና ኬንያውያን የገነኑበት የረጅም ርቀት ውድድር (አምስትና አስር ሺ ሜትር) ባለፉት ዓመታት እየተዳከመ መሄዱ ይታወሳል፡፡
በተለይም አስር ሺ ሜትር የመም ወይንም ትራክ ውድድሮች በዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ እንኳን የማይካሄዱበት አጋጣሚ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ ይህም በርካታ ምሥራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች ፊታቸውን ወደ ጎዳናና ማራቶን ውድድሮች እንዲያዞሩ ያስገድዳቸዋል፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ አምስት ሺ ሜትር ከዳይመንድ ሊግ እንዲሰረዝ መደረጉ ረጅም ርቀት ውድድሮችን እንደመቅበር ይቆጠራል፡፡
በመሆኑ አፍሪካውያንን ቅር ማሰኘቱ አልቀረም፡፡ ጀግናው አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ይህን ውሳኔ ተከትሎ ተቃውሞውን ያሰማ ሲሆን ለሮይተርስ በሰጠው ቃለመጠይቅ የአይ. ኤኤ.ኤፍ ውሳኔ ኢትዮጵያና ኬንያ በእጅጉ ተጎጂ እንደሚሆኑ አብራርተዋል፡፡ ይህ ውሳኔ በርቀቱ የነገሡትንና ባህላቸው ያደረጉትን ምሥራቅ አፍሪካውያንን በአትሌቲክስ ለማዳከም የተደረገ ፍትሐዊ ያልሆነ ውሳኔም ነው ብሎዋል፡፡
የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትጃክሰን ቱዌ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቆይታ ውሳኔው የአፍሪካ አትሌቲክስን ተጎጂ እንደሚያደርገው በመግለጽ ተቃውመ ዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለአይ.ኤኤ.ኤፍ ውሳኔውን በመቃወም በፌዴሬሽናቸው በኩል ጠንካራ ደብዳቤ እንደሚልኩ በመግለፅም ከሌሎች አፍሪካ አገራት ጋር በመሆን ውሳኔው እንዲ ቀለበስ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ አትሌቲክስን ፈታኝ ስፖርት ከሚያደርጉት ውድድሮች አንዱና ዋነኛው ረጅም ርቀት፣ ማራቶንና የአገር አቋራጭ ሩጫ ነው።
እነዚህ ውድድሮች አትሌቲክስን ፈታኝ ብቻም ሳይሆኑ ተወዳጅና ቀልብ ሳቢ ካደረጉት ምክኒያቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በእነዚህ ውድድሮች የምሥራቅ አፍሪካውያን የበላይነት እየገዘፈበት ከመጣ ጀምሮ ግን ተወዳጀነቱ እየቀነሰ የሚሰጠውም ትኩረት እያነሰ መጥቷል። ይህም ከአውራው የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮና እንዲወጡ ከምዕራባውያን በኩል ግፊት እንዲደረግ አድርጉዋል፡፡
በተለይም የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና በየሁለት ዓመቱ ራሱን ችሎ የሚካሄድ ቢሆንም በዋናው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናም ይሁን ከኦሊምፒክ ውጪ ተደርገዋል፡፡ በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር አገር አቁዋራጭ ውድድርን ወደ ኦሊምፒክ ለመመለስ እንቅስቃሴ ጀምሬያለሁ በሚልበት በዚህ ወቅት አምስት ሺ ሜትርን ከዳይመንድ ሊግ ውጪ ማድረጉ አስገራሚ ነው፡፡ የአገር አቋራጭ ሩጫ በዋናው ኦሊምፒክ መድረክ እኤአ ከ1912 እስከ 1924 በወንዶች መካከል ብቻ ተካሂዶ ነው የተቋረጠው።
ከዚህ በኋላ ግን የኦሊምፒክ መርሐግብር መሆኑ ቀርቶ የአትሌቲክስ ጉዳይ ብቻ ሆኖ ቀርቷል። ለዚህ ብዙ ምክኒያቶች በተለያዩ ጊዜዎች የሚቀርቡ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ በተካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ በርካታ አትሌቶች ውድድሩ ከብዷቸው ሲፍረከረኩና ራሳቸውን ሲስቱ ጭምር ነበር።
ይሁን እንጂ አገር አቋራጭ ሩጫ በተካሄዱባቸው ሦስት ኦሊምፒኮች የፊንላንድ አትሌቶች የበላይነት እንደነበር በታሪክ ተጽፎ ይገኛል። ከዚህ በኋላ የተፈጠረው የአትሌቲክስ ትውልድ በተለይም በረጅምና መካከለኛ ርቀቶች የአፍሪካውያን የበላይነት እየጎላየመጣበት እንደመሆኑ በአገር አቋራጭ የዓለም ቻምፒዮናዎችም ይሁን በግል አፍሪካውያን የበላይነቱን ተቆጣጥረውታል። ይህም አገር አቋራጭ ሩጫ ወደ ኦሊምፒክ እንዲመለስ የሚደረገውን ሂደት እንዳዘገየው የሚያምኑ በርካቶች ናቸው።
አፍሪካውያን ይህ ውድድር ወደ ኦሊምፒክ እንዲመለስ ብዙ ጊዜ ታግለዋል። ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፤ የመም ውድድሮችና የአገር አቋራጭ ውድድሮች ንጉሡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለና የኬንያው ታሪካዊ አትሌት ፖል ቴርጋት አገር አቋራጭ ውድድር ወደ ኦሊምፒክ እንዲመለስ ትግል ካደረጉት መካከል ይጠቀሳሉ።
በተለይም እነዚህ ሦስት ድንቅ የምሥራቅ አፍሪካ የምን ጊዜም ኮከብ አትሌቶች እኤአ 2008 ላይ ለወቅቱ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ጃኩዌስ ሮግ በአንድ ላይ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል። ይህን ሃሳብ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበርና በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የደገፉት ቢሆንም ተግባራዊ ሳይሆን ዘመናትን ተሻግሯል። ለዚህ ደግሞ ምዕራባውያኖች ተፎካካሪ መሆን ስለተሳናቸው ብቻ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡ ፡ አስር ሺ ሜትርን እያዳከሙ የመጡት ራሳቸው ምዕራባውያን ናቸው፡፡
በአምስት ሺ ሜትርም ተፎካካሪ መሆን ባለመቻላቸው ጠንካራ አትሌቶችን ከማፍራት ይልቅ ውድድሩን እንዲዳከም ማድረግ ምርጫቸው ሆኗል፡፡ ረጅም ርቀት ውድድሮች የበለጠ አፍሪካውያንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በመሆኑ የአፍሪካ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ሲ ኤኤ)፤ የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ(አኖካ)፤ የአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ግፊት ማድረግ አለባቸው ተብሎ በኦሊምፒክ መድረክ አሜሪካና ምዕራባውያን በርካታ ሜዳሊያ በመሰብሰብ የበላይነት ይዘው የሚያጠናቅቁት በአንድ ስፖርት ዓይነት ብቻ ከአስር በላይ ሜዳሊያ መሰብሰብ የሚያስችላቸው ዕድል ስላላቸው ነው።
ለዚህም በውሃ ዋና ውድድር አንድ አትሌት ብቻ ከአስር በላይ የወርቅ ሜዳሊያ የሚያፍስበት አጋጣሚ እንዳለ ማስቀመጥ ይቻላል። ምዕራባውያኑ እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ በኦሊምፒክ እንዲስፋፋና የበላይነታቸውን ይዘው እንዲዘልቁ ያገኙትን ዕድል ይጠቀማሉ። አሁንም በቀጣዩ የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ እንኳን የነሱ ፍላጎት ያለባቸው ወይንም ሜዳሊያ ያስገኝልናል ብለው ያሰቡትን ማንኛውንም እንቅስቃሴ የኦሊምፒክ ስፖርት እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ ለዚህም በቀጣዩ ኦሊምፒክ ብሬክ ዳንስ ሳይቀር እንዲካተት አድርገዋል፡፡
አፍሪካውያንም ከምዕራባውያን ጋር በኦሊምፒክ ተፎካካሪ ሆነው ለመገኘት እንደ አገር አቋራጭ ሩጫ ዓይነት ውድድሮችን ከመጠቀም ባለፈ ረጅም ርቀቶች ላይ ያንዣ በበውን አደጋ ለማስቀረት በጋራ መጋፈጥ ግድ ይላል፡፡ ከአሁኑ ካልታገሉ ግን እንደ አገር አቋራጭ ውድድር ሁሉ አስርና አምስት ሺ ሜትር ውድድሮች በቅርቡ ከየትኛውም ውድድር ላለመሰረዛቸው ማስተማመኛ አይ ኖርም፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 5/2011
በቦጋለ አበበ