ከሰማንያ በመቶ መላይ የሀገራችን ህዝብ በገጠር የሚኖር እንደመሆኑ የሥራ አጡም ቁጥር የሚበዛው በዚሁ አካባቢ ነው። እንደ ግብርና ሚኒስቴር መረጃ በገጠር በየዓመቱ ከ700 ሺ በላይ አዳዲስ ሥራ ፈላጊዎች ሥራ አጡን ይቀላቀላሉ። የኢትዮጵያ ዕድገት ጥናት ኢንስቲትዩሺን እ.አ.አ በ2016 ባደረገው ጥናት በገጠር ከሚኖረው ህዝብ 63 በመቶ ወጣት ነው። ከዚህም ውስጥ 78 በመቶ የሚሆኑት የቤተሰቦቻቸውን መሬት እያረሱ የሚኖሩ ሲሆን የተቀሩት የሠዎችን መሬት የእኩል እያረሱ ህይወታቸውን የሚገፉ ናቸው ብሏል። ጥናቱ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ጥቂት ወራት በመሥራት አብላጫውን የበጋ ወራት ያለሥራ እንደሚያሳልፉ አስታውቋል።
የግብርና ሚኒስቴር የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራን እንዲያስተዳድር ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልዕኮ ወስዶ ወደ ሥራ ከገባ ከ2008 ዓ.ም ወዲህ በገጠር ሥራ ፈላጊዎችን በተለይም ወጣቶችን ወደ ሥራ በማስገባት በአካባቢያቸው ባሉ ጸጋዎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል እንቅስቃሴ አድርጓል። በግብርና ሚኒስቴር የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ በቀለ እንደሚያስረዱት ከህዝብ ቁጥር ማሻቀብ ጋር በተያያዘ በየጊዜው እያደገ የሚሄደውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ መንግሥት የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመንደፍ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። የገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ መርሐ ግብር በገጠር የሚገኙ ወጣቶች ከመንግሥት ሥራ ጠባቂነት ተላቀው የራሳቸውን ሥራ በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ የተዘረጋ አዲስ አሠራር ነው:፡
ይህ ፕሮግራም ተግባራዊ ከተደረገ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች መንግሥት ያመቻቸላቸውን የብድር፣ የቦታና የስልጠና ድጋፎች ተጠቅመው በእርሻ፣ በእንስሳት ማድለብ፣ በንግድና በመሳሰሉት ሥራዎች በመሰማራት አበረታች ውጤቶችን አስመዝግበዋል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ በገጠር አራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች በተለይም ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እስከ አሁን ወደ ሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሚደርሱት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይሁንና በየዓመቱ በገጠር እየጨመረ ከሚመጣው የሥራ አጥ ቁጥር አንጻር አጥጋቢ ሥራ ተሠርቷል ማለት አያስደፍርም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምክር ቤቱ በ2011 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ወጣቶች ሥራ ፈላጊዎችን እንደሚቀላቀሉ በመጥቀስ ከእነዚህም መንግሥት አንድ ሚሊዮን ለሚሆኑት ብቻ ሥራ እንደሚያስይዝ መግለጻቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም በሀገሪቱ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የሥራ አጡን ቁጥር መቀነስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ የግብርና አስተዋጽዖ ከፍ ያለ ቦታ እንዳለው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በመቀጠልም ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠውና በይበልጥም የዝናብ ጥገኛ ከመሆን የመስኖ ልማት ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ መግለጻቸው ይታወሳል። መንግሥት በግብርናው ዘርፍ የያዘው አቅጣጫ በገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ መርሐ ግብርን በመተግበር የወጣቱን ዕውቀትና አቅም ጥቅም ላይ በማዋል ኢኮኖሚያዊ ዕድገታችንን ከማስቀጠል አንጻር የሚጫወተው ሚና ቀላል እንዳልሆነ በዘርፉ ያሉ ምሁራን ይገልፃሉ።
አቶ ስለሺ በገጠር የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተቋማቸው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንዳለ ይገልጻሉ። አስከ አሁንም ማሳያ የሚሆኑ መልካም ተሞክሮዎች እንዳሉ ጠቅሰው ዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መነደፋቸውን አስታውሰዋል።
በገጠር የተማሩ ወጣቶች ቁጥር እየበዛ መምጣቱ ዓለም አቀፍ የግብርና አስተሳሰቦችንና አሠራሮችን በቀላሉ ተቀብሎ ተግባራዊ በማደረግ ግብርናውን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል። የተለያዩ አማራጮችንም እንዲከተሉ ዕድል ይሰጣል። አቶ ስለሺ እንደሚያስረዱት መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ ያለው የገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ በሚፈለገው ልክ ውጤታማ መሆን ያልተቻለው ከቀበሌ እስከ ሚኒስቴር መስሪያቤት ተቀናጅቶ የመሥራት ችግር በመኖሩና በቂ የሆነ የብድር ፣ የመሬት እና የተለያዩ ግብዓቶች ባለመቅረባቸው እንደሆነ ያስረዳሉ። ሀገራችን እየተከተለች ያለው ግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪው እንዲሸጋገርም የግብርናውን አቅም ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። በመሆኑም መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት በገጠር እየባከነ ያለውን እውቀትና የሠው ኃይል ወደ ሥራ ለማስገባት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ይገልጻሉ።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር ሚልኬሳ ዋቅጂራ ግብርናው ለወጣቱ፤ ወጣቱም ለግብርናው አስፈላጊ ነው ይላሉ። የግብርናው ዘርፍ የሥራ አጥነትን ቁጥር በመቀነስ የመጀመሪያው እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር ሚልኬሳ ጃፓን ወደ ኢንዱስትሪ ከመግባቷ በፊት ያደገችው በእርሻ እንደሆነና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራትም የሰው ኃይል ፣ የመሬትና የውሃ ሀብት ይዘው የእርሻን ዕድገት ሳያረጋግጡ ሌላ ዕድገት መጠበቅ እንደማይቻላቸው አስረድተዋል። እርሻ በኢኮኖሚ ውስጥ ከአምስት ስድስት ጊዜ በላይ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። እርሻ በመስክ ሥራ፣በትራንስፖርት፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በሱፐር ማርኬት ፣ በችርቻሮ ወዘተ የሚያልፍ እንደመሆኑ ብዙ የሰው ኃይልን ያሳትፋል ይላሉ።
በመሆኑም ግብርናን ማስፋፋት የገጠር ወጣቶችን ቀጥታ ተጠቃሚነት ማረጋገጡ ብቻ ሳይሆን በተዘዋዋሪ የከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራንም እንደሚያግዝ መገንዘብ ያስፈልጋል። ሰፋፊ መሬት ባለበት መስኖን ተጠቅሞ ማምረት የመሬት እጥረት ባለበትም ከብቶችን ማደለብ፣ ዶሮን ማርባት፣ ንብ ማነብ፣ በአጭር ጊዜ ጥቅም የሚሰጡ እንደእንጉዳይ ዓይነት ተክሎችን በመትከል መጠቀም እንደሚቻል ተናግረዋል። በሀገራችን ባለው ልምድ መንግሥትና ምሁራን ያላቸው ቅርበት የላላ ነው ያሉት ዶክተር ሚልኬሳ ዩኒቨርሲቲዎች በያሉበት አካባቢ የማህበረሰቡን ችግር ለይተው መፍትሔ በማቅረብ መንግሥትን መርዳት ይኖርባቸዋል ብለዋል። የውጭ ባለሀብቶችም በግብርና ሥራ ተሰማርተው ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን የሰላም ሁኔታ አስተማማኝነቱ መረጋገጥ አለበት ሲሉ ጠቁመዋል። ሰዎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የመሥራት ዋስትና ሲኖራቸው በአንድ ቦታ የተከማቸው የሠው ሐይል ሰፋፊ መሬት ወዳለበት ቦታ ሄዶ የመሥራት ዕድል ይፈጠርለታል።
ሥራ ሲፈጠር ሰው እራሱ ይንቀሳቀሳል የሰላሙም ሁኔታ ይሰክናል ብለዋል። የመስኖ ሥራ መስፋፋት በገጠር ወጣቶች ያለሥራ የሚያባክኑትን የበጋ ወራት ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፤ ምርትና ምርታማነትን ከማሰደግ በተጨማሪም የሚገኘውን ተረፈ ምርት ለእንስሳት መኖ እንዲውል በማድረግ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ያስችላል። ግብርናው በሁሉም መልክ ቢጠናከር ኢንዱስትሪውን በመመገብ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ዘለቄታ ያለው እንዲሆን ያስችላል።
ወጣቱ የአካባቢውን ጸጋዎች ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር የሚያስችል ሥርዓት ስላልተዘረጋለት ከገጠር ወደ ከተማ በመኮብለልበከተማ የሥራ አጥ ቁጥር እንዲበራከትና መጨናነቅም እንዲፈጠር ከማድረጉም ባሻገር ወደ ውጭ ሀገር በመሰደድም ለተለያዩ አደጋዎች እንዲጋለጥ ምክንያት ሆኗል። አሁን መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት በተጨባጭ መሬት ላይ የሚያርፍ ከሆነ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊፈቱ ይችላሉ። በጥቅሉ ሲታይ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የሥራ አጥ ቁጥር በተለይ ደግሞ በገጠሩ የአገራችን ክፍል የሚስተዋለው የሥራ አጥ ቁጥር ከፍተኛውን አሃዝ የያዙት ወጣቶች ናቸው።
በመሆኑም በየዓመቱ 700 ሺ የገጠር ወጣት ሥራ አጡን ይቀላቀላል ሲባል በገጠር ያለው ዋናው የሥራ ዕድል ፈጠራ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግለው የግብርናው ዘርፍ በሚገባ አልተሠራበትም ማለት ነው። እዚህ ላይ በየዓመቱ የምንፈጥረው የሥራ ዕድል ደግሞ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ወጣቱ ገጠሩን ትቶ ወደ ከተማ ለመሰደድ ይገደዳል። እዚህ ላይ ትልቅ ችግር ሆኖ የሚነሳው ይህ ሰፊ ቁጥር ያለው ወጣት ሥራ አጥቶ ከገጠር ወደ ከተማ በሚንከራተትበት ወቅት በከተሞች የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጫናው ቀላል የሚባል አይደለም። ለዚህ ነው ሁል ጊዜም ቢሆን መንግሥታት የሁልጊዜ አጀንዳቸው ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚሆነው፤ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ላይ የሚሠራው ሥራ ሁለንተናዊ ለውጥ በማምጣጥ ሚናው የላቀ ነው።
ስለሆነም አሁን ያለው የሥራ ዕድል ፈጠራ ሂደታችን አዝጋሚ ነው ብቻ ሳይሆን ትኩረትም የተነፈገ ይመስላል። ወጣቱ ሥራ አጥ ሆኖ ለከተሞች በተለይ ደግሞ ለአላስፈላጊ ብጥብጥና ሁከት የሚጠቀሙት ይህን ሐይል በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል። ይህን የልማት ሐይል ለልማት አለመጠቀም ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢኮኖሚውንም ሆነ ፖለቲካውን ክፉኛ እንደሚጎዳው ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የተሰወረ ሀቅ አይደለም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 5/2011
በኢያሱ መሰለ