የመሬት ይዞታ መረጃ አያያዝ ሥርዓታችን ኋላ ቀር በመሆኑ በዘርፉ ህገ ወጥነት እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል። ከዚህም ባሻገር መንግሥት ከመሬት ማግኘት የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አጥቷል። መረጃው በወረቀት ላይ የሚሰፍር በመሆኑም ለብክነት ፣ ለብልሹ አሠራርና ለኪራይ ሰብሳቢነት አመቺ ሆኗል። በየጊዜው በመሬት ጉዳይ ለሚነሱ የህብረተሰብ ሮሮዎችም ይህ የመረጃ አያያዝ ሥርዓታችን ኋላቀር መሆን እንደ ምክንያት ይጠቀሳል።
መንግሥት በዘርፉ የሚታዩ እንከኖችን ለማስወገድ ካዳስተር /ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን / ለመተግበር የከተማ መሬት ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 818/2006ን በማጽደቅ ወደ ሥራ ገብቷል። በዚህም መሰረት የፌዴራል መሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ቅድሚያ በተሰጣቸው ከተሞች እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀምሯል። አዲስ አበባ ፣ሃዋሳ፣ ባህርዳር፣ መቀሌ፣ አዳማ በአጠቃላይ 23 ከተሞች ህጋዊ የመሬት ይዞታ ምዝገባን ለማድረግ ወደ ሥራ ገብቷል።
ከእነዚህም አንዳንዶቹ የተዝረከረከውን የመረጃ አያያዝ ስርዓት ለማዘመን ያስችላል ተብሎ ጥቅም ላይ እንዲውል የተደረገውን ሶፍትዌር/የመረጃ ቋት/ ተጠቅመው ይዞታ የመለየት እና የባለመብትን ወሰን የማካለል ሥራ በመሥራት ለባለ መብቶች የምስክር ወረቀት መስጠት ጀምረዋል። ይህ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት በአዲስ አበባ ከተማ ተተግብሮ አበረታች ውጤት ታይቶበታል። ይሁንና በከተማዋ ካሉት በርካታ የቀበሌ ቤቶችና ውስብስብ ጉዳዮች አንጻር ሥራው በተፈለገው ፍጥነት ልክ እየሄደ እንዳልሆነ የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች ይናገራሉ።
አሁን ደግሞ በደቡብ ብሄር ቤረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተለይም በሃዋሳ ከተማ ተፈጻሚ እየሆነ ይገኛል። የቤቶች ልማትና ኮንስራክሽን ሚኒስትር አቶ ጃንጥራር አባይ ሰሞኑን በዘርፉ ሥራ ለመሰማራት የሚያስችላችውን ስልጠና ለወሰዱ 30 የደቡብ ክልል ሰልጣኞች በወንዶ ገነት ኮሌጅ ተገኝተው የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል። በክልሉ ላሉ ከተሞች በአጠቃላይ የምዝገባ ሥርዓቱን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚሆኑም ተናግረዋል። አቶ ጃንጥራር በሃዋሳ መናኽርያ ክፍለ ከተማ በመተግበር ላይያለውን ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓትንም ተመልክተዋል።
ህጋዊ ካዳስተር አንድ ባለ ይዞታ የይዞታ ባለመብት መሆኑን ብቻ ሳይሆን መብቱ ዘላቂ በሆነ መንገድ እንዲረጋገጥ የሚያስችል ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል። አገልግሎትን በፍጥነት ለማግኘት የሚያግዝ ለመንግሥትም ይሁን ለባለይዞታው የሚፈለገውን ማንኛውንም መረጃ አካቶ መያዝ የሚያስችል የመረጃ ቋት ያለው እንደሆነም ጠቅሰዋል። በወሰን ምክንያት በባለይዞታዎች መካከል የሚፈጠር አምባ ጓሮን የሚያስወግድ ፣ በግለሰቦች መካከል በሚደረገው ክርክር የሚባክነውን ገንዘብና ጊዜም የሚታደግ እንደሆነና የከተማ አስተዳደሮች የሚያስተዳድሩትን መሬት አንድ በአንድ አውቀው በተገቢ መንገድ እንዲያስተዳድሩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።
ዜጎች መብታቸው ሲከበር፤ ጥያቄያቸው ሲመለስ ማዘጋጃ ቤት መሬትን በአግባቡ ማስተዳደር ሲችል ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መረጋጋት ይፈጠራልም ብለዋል። ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓትን በመላ ሀገሪቱ በመዘርጋት የመሬት ብዝበዛንና ተያያዥ ስርቆቶችን በማስወገድ ህብረተሰቡ የሚያነሳውን የመልካም አስተዳደር ችግር በመቅረፍ በሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈንም አጋዥ እንደሆነ ተናግረዋል። የህጋዊ የመሬት ይዞታ ምዝገባ ለንብረት ዝውውርም ይሁን የባንክ ዋስትና ለማግኘት መረጃን በአጭር ጊዜ ለመስጠትና ወቅታዊና ተአማኒ ለማድረግ ይረዳል።
የከተማዋን የገቢ አቅም ለማሳደግ ፣ የኪራይ ሰብሳቢነትን ምንጭ ለማድረቅ፣ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት ፣ ቀልጣፋ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው የመሬት አስተዳደር ለማስፈን ፣ ህገ ወጥነትን ለመከላከልና የከተማዋን ፕላን ለማስጠበቅ አጋዥ ነው። የደቡብ ክልል ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ክፍሌ ገብረ ማርያም ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮችና ሮሮዎች በርካታ መሆናቸውን በመጥቀስ የከተማ መሬት በዘመናዊ አሠራር መታገዙ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እንደሚቀርፍ ታምኖ ወደሥራ ተገብቷል ብለዋል። ይህንን ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ለመተግበር የክልሉ መንግሥት የህግ ማዕቀፍ በማውጣት አበረታች እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንዳለ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በክልሉ በአምስት ከተሞች የካዳስተር ሥራ መጀመር እንደተቻለ አስረድተዋል። ያለንን የመሬት ሀብት ማወቅና በትክክል ማስተዳደር ስንችል ክልላችን ከመሬት ሀብታችን መግኘት የሚገባውን ጥቅም ወይም ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ ይችላል ብለዋል።
‹‹እስከዛሬ ባለን ተሞክሮ በተለያዩ መድረኮች ላይ ከከተማ መሬት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ገምግመናል ፣ የመፍትሔ ሃሳቦችንም አስቀምጠናል፤ ያም ሆኖ ችግሮች እምብዛም ሲቀረፉ አልታየም።›› ብለዋል አቶ ክፍሌ። አሁን በተዘረጋው ዘመናዊ አሠራር ግን ከዚህ ቀደም ሲነሱ የነበሩ ችግሮች ሁሉ መልስ ያገኛሉ ተብሎ ይታመናል። አሁን ባለው ሁኔታ ሃዋሳ ላይ የተጀመረው እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆኑ እየታየ ነው ብለዋል። ሃዋሳ ከተማ ፈጣን ዕድገት እያሳዩ ካሉ ከተሞች አንዷ በመሆኗና የኢንዱስትሪ ፓርክ መገኛም በመሆኗ ከተማዋ ዘመናዊ ከተሞች ያላቸውን አገልግሎት መያዝ እንደሚያስፈልጋት አስረድተዋል። ሥራው አዲስ እንደመሆኑ አመራሩ ሥራውን በአግባቡ የመምራት ፣ ባለሙያውም ዝግጁ ሆኖ ኃላፊነቱን የመወጣት፣ ሚዲያውም በዚህ መልክ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሥራት አለበት።
በከተሞች ላይ ያለውን የተወሳሰበ ቋጠሮ ለመፍታት ሁሉም አካል ተጋግዞ ይህን ሥራ ወደ ፊት ማስቀጠል ይኖርበታል። ይህ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ዕድገታችንን የማፋጠን አቅም የሚፈጥር የመሬት ሀብታችንን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ፣ ዘልማዳዊ አሠራርንና ጥርጣሬን የሚያስቀር እንደሆነም አስረድተዋል። በፌዴራል ደረጃ ከአዲስ አበባ በመቀጠል ይህን ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት በመተግበር ጥሩ ጅምር ያሳየችው የሃዋሳ ከተማ ነች። የሃዋሳ ከተማ ማዘጋጃቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅና የከተማ መሬት ምዝገባና መረጃ ዩኒት ኃላፊ ወይዘሪት ራሄል ዳዊት ሥራው ከመጀመሩ በፊት ለህብረተሰቡና ለአመራሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠቱ ለሥራው ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ይላሉ ።
ሃዋሳ በከተሞች ትውውቅ መድረክ ቀዳሚ መሆኗ ሲታሰብ ይህ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት በፍጥነት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተተግብሮ የከተማዋን ከፍታ በማሳደግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት ይገልጻሉ። በሃዋሳ ከተማ ሳይረጋገጥ የሚታለፍ ይዞታ አይኖርም የሚሉት ወይዘሮ ራሄል በመናኽርያ ክፍለ ከተማ የተጀመረው ዘመናዊ አሠራር አሁን ላይ በአራት ክፍለ ከተሞችምእየተተገበረ እንዳለ ጠቅሰዋል። በድንበር ማካለሉ ሂደት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው አቤቱታዎች ቢኖሩ እራሱ በመረጣቸው ታዛቢዎችና ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች ጉዳዩ ይጣራለታል ብለዋል።
አዲሱ ሶፍት ዌር በሃዋሳ ከተማ ሥራ መጀመሩ የመሬት አስተዳደር ስርዓቱን ከማዘመንና በመሬት ጉዳይ የሚከሰቱ ብልሹ አሠራሮችን ከማስወገድ አንጻር ትልቅ ሚና እንደሚጫወት የገለጹት የሥራ ኃላፊዋ የበጀት፣ የሰው ኃይልና የቁሳቁስ በተለይም የተሽከርካሪ ችግር መኖሩ ሥራውን በሚፈለገው ፍጥነት ለመሥራት ማነቆዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። በመጨረሻም ተገልጋዮች ለሥራው ትኩረት እንዲሰጡና ለአገልግሎት የሚያወጡት ገንዘብ ሳይኖር ጉዳያቸውን ተከታትለው ማስፈጸም እንዲችሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። አቶ እሸቱ ካሳሁን የመናኽርያ ክፍለ ከተማ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባል ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የሥራ ድርሻቸው የመረጣቸውን ህብረተሰብ በኃላፊነት ማገልገል ነው።
በዚህም መሰረት በአዋጅ ቁጥር 818/2006 መሰረት የባለይዞታው መሬት ልኬት መከናወኑን መከታተል ነው። እያንዳንዱ ባለይዞታ የልኬቱን ውጤት እንዲረዳ በቦርድ ላይ መለጠፉን ማረጋገጥ፣ መሬቱ ከተባለው ይበልጣል ወይም ያንሳል የሚል አቤቱታ ሲቀርብም የባለጉዳዩን ፋይል በመረከብ የማረጋገጥ ሥራ ይሠራሉ። ይዞታው አስር በመቶ የሚያንስ ወይም የሚጨምር ከሆነም በአዋጁ መሰረት እንደጉድለት ወይም እንደ ትርፍ እንደማይታይ ለግለሰቦች ያስረዳሉ።
በዚህም መሰረት በመናኽርያ ክፍለ ከተማ አቤቱታ ያቀረቡ 21 ግለሰቦችን ጉዳይ ኮሚቴው እየተመለከተ እንዳለና ከተወሰኑት ጋር መስማማት ላይ እንደተደረሰ አስረድተዋል። በአጠቃላይ ካዳስተር ተግባራዊ በሆነባቸው እንደ ሃዋሳና አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች አበረታች ውጤት እንደታየ ለመገንዘብ ተችሏል። በመሆኑም ይህን ተሞክሮ በማስፋት በመላው አገሪቱ ባሉ ከተሞች ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያ ከመሬት አስተዳደር ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ መሥራት የኖርበታል። ለዚህም የከተማ አስተዳደሮች እና ከንቲባዎች የአንበሳውን ድርሻ ሊይዙ ይገባል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 5/2011
በኢያሱ መሰለ