አዲስ አበባ፡- በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የስፖርት አመራርነት፣ ዳኝነትና አሠልጣኝነት የሴቶች ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ ተጠቆመ፡፡ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የሴቶች ቀንን የፓናል ውይይት በማካሄድ ተከብሯል፡፡ በመድረኩ አገራቸውን በክብር ያስጠሩ ጀግና ሴት ስፖርተኞች ተዘክረዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ111 ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ የሴቶች ቀን፤ ‹‹እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ›› በሚል መሪ ሃሳብ ሴቶችን በማበረታታትና ለሌሎች ተምሳሌት የሆኑ ሴቶችን በመዘከር ተከብሯል፡፡ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትርም በዓሉን የፓናል ውይይት በማዘጋጀት ያከበረ ሲሆን፤ ‹‹የኢትዮጵያ ሴቶች በአድዋ የጦር ሜዳ ውሎ እና እንድምታው፤ እቴጌ ጣይቱ እንደ ማሳያ!›› በሚል በታሪክ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸውን ሴቶች የተዘከሩበት ጽሁፍ ቀርቧል፡፡ በተመሳሳይ የአገራቸውን ባንዲራ በዓለም አደባባይ በማውለብለብ ጀግንነታቸውን ያስመሰከሩ ጀግና ሴት አትሌቶችም በመድረኩ ተዘክረዋል፡፡
በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የትምህርት፣ ሥልጠና እና ውድድር ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ አማረ ‹‹የኢትዮጵያ ሴቶች በስፖርት›› በሚል ርዕስ ዳሰሳዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ በዚህም ስፖርት ለሴቶች ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡ ይኸውም በኢፌዴሪ የስፖርት ፖሊሲ ሴቶች በሚማሩበት፣ በሚሰሩበትና በሚኖሩበት አካባቢ በስፖርት ቀጥተኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡ ሴቶች በስፖርቱ በአመራርነት፣ በባለሙያነትና በስፖርተኝነት እየተሳፉ ናቸው፡፡
በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የስፖርት አመራርነትም አስቀድሞ የነበረው 30 ከመቶ የሆነው የሴቶች ተሳትፎ ወደ 50 ከመቶ ሊያድግ ችሏል፡፡ ይሁንና ከ26 የስፖርት ማሕበራት መካከል የጾታ ተዋጽኦውን በትክክል ተግባራዊ ያደረገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ብቻ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ የስፖርት ፌዴሬሽኖች አመራርነትም የኢትዮጵያ አሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና የምስራቅ አፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ አባል ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ እና የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል የሆኑት ወይዘሮ ዳግማዊት ብርሃኔ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እንደ አሰልጣኝነት እና ዳኝነት ባሉ የስፖርት ሙያዎችም በተመሳሳይ የሴቶች ተሳትፎ እስከ ዓለም አቀፍ እያደገ ያለ መሆኑም በመድረኩ ተመላክቷል፡፡ በስፖርተኝነትም በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች የአገራቸውን ስም በድል እንዲነሳ ያደረጉ እንዲሁም በጥቁር ስፖርተኞች ታሪክ ፈር ቀዳጅ በመሆንና ተጽእኖ በመፍጠር ረገድ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ስፖርተኞች መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2014