የኢትዮጵያውያን ኦሊምፒክ!

በታላቁ የዓለማችን የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ መርሕና ፅንሰ ሀሳብ መሠረት የሚካሄደው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተቋርጦ ቆይቷል። ይህ የኢትዮጵያውያን ኦሊምፒክ ሊባል የሚችል ትልቅ ሀገር አቀፍ የስፖርት መድረክ ከነዚህ ዓመታት በኋላ ወደ ውድድር ተመልሶ ዛሬ ለስድስተኛ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት በጅማ ይጀመራል።

ለተከታታይ አስር ቀናት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታድየምና ሌሎች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በሚካሄደው ውድድር ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በሃያ ስድስት የስፖርት አይነቶች ተፎካካሪ እንደሚሆኑበት የመድረኩ አዘጋጅ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ ጠቁሟል። ቀደም ባሉት የውድድር መድረኮች ፉክክር የሚደረግባቸው ስፖርቶች ብዛት ከአስራ ሰባት የዘለለ አልነበረም። ዘንድሮ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ውድድር ላይ የተካተተውን የባህል ስፖርት ጨምሮ ሌሎች በርካታ ስፖርቶች ፉክክር የሚደረግባቸው ሆነዋል።

በዚህ የኢትዮጵያውያን ኦሊምፒክ በሆነ መድረክ ከ4500 በላይ ስፖርተኞች ተሳታፊ ይሆናሉ። ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅ ሲሆን፣ ውድድሮች በብሔራዊ የስፖርት ፌዴሬሽኖች የሚመሩ ናቸው። መላው ኢትዮጵያ ጨዋታ የኦሊምፒክ መርሕን በመከተል የችቦ ቅብብሎሽ መርሐ ግብር ይካሄድበታል። በዚህም መሠረት ከቀናት በፊት የኦሊምፒክ ችቦውን የያዘው ልዑክ ውድድሩ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ከተካሄደበት ሐዋሳ ከተማ መነሻውን አድርጎ የተለያዩ ከተሞችን በማቆራረጥ ዛሬ ጅማ ይደርሳል። በዚህም አርባ ሺ ተመልካች በሚይዘው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ስቴድየም በሚኖረው ልዩ የመክፈቻ መርሐ ግብር ደማቅ አቀባበል ተደርጎለት 6ኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች በይፋ የሚጀመር ይሆናል። ከተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ጀምሮ በርካታ የክብር እንግዶችም ይገኛሉ ተብሏል።

መላው ኢትዮጵያ ጨዋታ ከውድድሩ ጎን ለጎን ሀገራዊ አንድነት የሚጠናከርበት የፓናል ውይይት፣ የችግኝ ተከላ፣ የልማት ሥራዎች ጉብኝት እና ማኅበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚካሄድበትም ይሆናል። ከውድድር ባሻገር የወል ትርክቶች ለማኅበረሰቡ የሚሰርፁበት መድረክ ጭምር ይሆናል ተብሏል። ማኅበራዊ አብሮነት የሚጠናከርበት፣ ስፖርታዊ ጨዋነት የሚሰፍንበት እንዲሆን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውም ተጠቁሟል።

በተለያዩ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ያልቻሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ከስፖርቱ ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የቻለው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች፣ ኢትዮጵያን በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረክ ወክለው ውጤታማ የሆኑ ስፖርተኞችን ማፍራት ችሏል። የረጅም ርቀት ኮከቡ አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ካፈራቸው ዓለም አቀፍ ኮከቦች አንዱ ሲሆን፣ በብስክሌት ስፖርት ደግሞ ሐድነት አስመላሽ ተጠቃሽ ናት። በዘንድሮው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታም ከዚህ ቀደም በክለብና በየትኛውም ደረጃ በብሔራዊ ቡድን የተጫወተ ስፖርተኛ እንደማይሳተፍ ታውቋል።

ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ ቆይቷል። ውድድሩ 1999 ላይ ሲጀመር አዲስ አበባ ከተማ አስተናጋጅ እንደነበረች ይታወሳል። ቀደም ሲል የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች የኦሊምፒክ ፍልስፍናን መሠረት በማድረግ የተቀረፀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በየአራት ዓመቱ ይካሄዳል ተብሎ የታሰበ ስለነበር ሁለተኛው ውድድር ከአራት ዓመት በኋላ 2002 ላይ ተካሂዷል። ዳግም ማስተናገድ የቻለችውም አዲስ አበባ ነበረች።

መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ የተካሄደው ሦስተኛውና በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት 2004 ዓ.ም ላይ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስቴድየም የተከናወነው ነበር። ከአዳማ በኋላ 2006 ዓ.ም ላይ አራተኛውን ውድድር ያስተናገደው አማራ ክልል ሲሆን በወቅቱ አዲስ በነበረው በባሕርዳር ስቴድየም ተከናውኗል። አምስተኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ደግሞ በደቡብ ብሔርና ብሔረሰቦች ክልል አስተናጋጅነት በሐዋሳ ስቴድየም 2008 ዓ.ም ላይ ተካሂዷል። ከሐዋሳ በኋላ ግን ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሳይካሄድ ቆይቶ ዳግም ዛሬ ሲጀመር ጅማን መዳረሻው አድርጓል። በቡናና እንጨት ምርቶቿ የምትታወቀው የአባ ጂፋር ሀገር ይህን መሰል ታላቅ ውድድር ስታስተናግድም በታሪኳ የመጀመሪያ ይሆናል።

በቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You