የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ቅድመ ዝግጅት ተጠናቀቀ

ስድስተኛው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችን በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት በጅማ ከተማ ለማካሄድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ። የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ትናንት በሰጠው መግለጫ እንደጠቆመው፤ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ከሰኔ 10- 19/2017 ዓ.ም የሚካሄደውን የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች የተለየ ለማድረግ ታስቧል።

መግለጫውን የሰጡት የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሀመድ እንደተናገሩት፤ “ስፖርት ለህብር ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉ ሲሆን፤ የባሕል ስፖርቶችን ጨምሮ በ26 የስፖርት ዓይነቶች ፉክክሮች ይደረጋሉ። በአጠቃላይ ከ4500 በላይ ስፖርተኞች ተሳታፊ ለመሆን በበይነ መረብ ምዝገባ ማድረጋቸው ተጠቁሟል። ውድድሩ ሀገራቸውን የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞች ማፍራት ዓላማ ያደረገ እንደሆነም ተገልጿል።

“ስፖርታዊ ጨዋነትና ወንድማማችነት የሚታይበት ጥሩ ውድድር እንዲሆን ዝግጅት ተደርጓል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ተሳታፊ ክልሎችና ከተሞችም የራሳቸውን ውድድር አድርገው ስፖርተኞቻቸውን በመምረጥ ወደ ጅማ እንደሚመጡ ተናግረዋል። ሃያ ስድስቱን የስፖርት ዓይነቶች ለማስተናገድ የመሠረተ ልማት ጉዳይ ችግር እንደማይሆን ጠቁመዋል። ለእዚህም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ስቴድየምና ሌሎች የስፖርት መሠረተ ልማቶች በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ከውድድሩ አዘጋጅ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ውድድሮችን ከሚመሩት ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የተውጣጣ ልዑክ በአካል ተገኝቶ ማረጋገጡን አብራርተዋል።

የውድድሩ መክፈቻና መዝጊያ መርሃ ግብር ከአርባ ሺ በላይ ተመልካች በሚይዘው በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስቴድየም የሚካሄድ ሲሆን፤ ከእዚህ ቀደም ከነበሩት የተለየ ለማድረግ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል። ከተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ጀምሮ በርካታ የክብር እንግዶችም ይገኛሉ ተብሏል።

መንግሥት በቂ ዝግጅት ያደረገበት 6ኛው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ ከውድድሩ ጎን ለጎን ሀገራዊ አንድነት የሚጠናከርበት የፓናል ውይይት፣ የችግኝ ተከላ፣ የልማት ሥራዎች ጉብኝት እና ማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ይካሄዳል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ከቀበሌ ጀምሮ ያሉ ስፖርተኞች ተሳታፊ የሚሆኑበት 6ኛው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ አዳዲስ የውድድር መድረክ ያላገኙ አትሌቶች የሚሳተፉበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ ቀደም ሲል በክለብና በየትኛውም ደረጃ በብሔራዊ ቡድን የተጫወተ ስፖርተኛ እንደማይሳተፍ የተጠቆመ ሲሆን፤ በአጠቃላይ የውድድሩን ጠንካራና ደካማ ጎን የሚገመግም ቡድንም ተቋቁሟል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ መንግሥት ለስፖርት ልማት ዘርፍ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በርካታ የስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታዎችን ከመገንባት ባሻገር በስፖርት ልማት ዘርፍ ላይ ያጋጠመውን ስብራት በመለየት እየሠራ ይገኛል።

ከእነዚህ ስብራቶች አንዱ ትልልቅ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ተቋርጠው መቆየታቸው ነው። በእዚህም ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ተቋርጠው የቆዩ ሀገር አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች መንግሥት በወሰደው ቁርጠኝነት በተሻለ ሁኔታ አሠራሮችን በማዘመን በአዲስ መልክ እንዲጀመሩ እየተደረገ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ለ6ኛ ጊዜ የሚካሄደው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ ከውድድር ባሻገር የወል ትርክቶች ለማህበረሰቡ የሚሰርጹበት ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከቀናት በኋላ የሚጀመረው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ ማህበራዊ አብሮነት የሚጠናከርበት፣ ስፖርታዊ ጨዋነት የሚሰፍንበት እንዲሆን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሌላው የስፖርቱ ስብራት ተብሎ የተለየው በስፖርት ዘርፍ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲሆኑ፤ ይህንን ለመፍታትም በዘርፉ የሕግ ማሕቀፎችን ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ ትኩረት ተደርጎበት እየተሠራ ይገኛል።

በባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በስፖርት ፌዴሬሽኖች የሚመራው 6ኛው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ የኦሊምፒክ መርሕን በመከተል የችቦ ቅብብሎሽ መርሃ ግብር ይካሄድበታል፡፡ በእዚህም መሠረት ከነገ ጀምሮ የኦሊምፒክ ችቦውን የያዘው ልዑክ ውድድሩ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ከተካሄደበት ሐዋሳ ከተማ መነሻውን አድርጎ የተለያዩ ከተሞችን በማቆራረጥ ወደ ጅማ የሚያቀና ይሆናል።

በቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You