መሐል ፒያሳ ከምትገኝ አንዲት ካፌ ውስጥ በቅርቡ ከአሜሪካ ከመጣች አንድ የአክስቴ ልጅ ጋር ተቀምጫለሁ:: ከአክስቴ ልጅ ጋር በእድሜ እኩዮችና የልብ ጓደኛሞች ነን። ባህር ማዶ እንደማደጓ የአገራችንን ቋንቋ ያልረሳች፣ ወግና ባህሏን ያልሳተች ሙሉ ኢትዮጵያዊት ናት::
ከእርሷ ጋር ከሚያለያየን ይልቅ የሚያግባባን ይበዛል። የሙዚቃ ምርጫችን ግን ከምንለያይባቸው ጥቂት ነገሮች መካከል አንዱና ዋንኛው ነው። እኔ ሰከን ረጋ ያሉና ቆየት ያሉ አገርኛ ዘፈኖችን ስመርጥ እርሷ ግን ፈጣን ሆይ ሆይታ የበዛባቸው ዘመን አመጣሽ ሙዚቃዎች ይበልጥ ይስባታል።
ከተቀመጥንበት ካፌው ሰሜን አቅጣጫ ከተሰቀለ ስፒከር
‹‹ሰርካለም እንዲያው ደህና ደህና (3 ጊዜ)
ጀማመርነው እንጂ መች ዘለቅነው ገና፣
ሳብዬ ይሁን ደህና ደህና (3 ጊዜ))
ፍቅሩን አይንፈገን ሰላምና ጤና…›› የሚል ቆየት ያለ ሙዚቃ ይንቆረቆራል:: እኔም በትዝታ የኋሊት ተጉዤ በተመስጦ አብሬ ማንጎራጎር ጀምርኩ::
የአክስቴ ልጅ በአግራሞት ውስጥ ሆኖ ድንገት፣ ‹‹ለስንት ሰው ነው ግን የሚዘፍነው?›› ስትል አቋረጠችኝ። የተለመደ ጭቅጭቃችን ነው ብዬ በዝምታ ላልፋት እየፈለግኩ ግን ደግሞ ወዲያው ‹‹እንዴት፣ ለምን ልትይ ቻልሽ?›› ብዬ ጠየኳት።
‹‹መጀመሪያ ላይ ሰርካለም ብሎ ሲደግመው ደግሞ ሳብዬ ይላል እኮ›› አለችኝ። ድጋሚ ሰማሁት። ቃል በቃል ሸምድጄ ስንት አመት ስዘፍነው የኖርኩት ዘፈን ውስጥ ልብ ያላልኩትን ነገር ስላሳየችኝ ከመገረም ባለፈ ለእርሷም ሆነ ለራሴ የምሰጠው ምላሽ አልነበረኝም:: በዝምታ ውስጥ ሆኜ ደቂቃዎች አሳለፍኩ::
የአክስቴ ልጅ መጸዳጃ ቤት መሄድ እንደምትፈልግ በሚያሳብቅ መልኩ ‹‹መጣሁ ብላ›› ድንገት ተነስታ ሄደች:: እኔም ሙዚቃና ሙዚቀኛውን እያሰብኩ በመሃል በመጠኗ የሱሪዬን የኋላ ኪስ የምትስተካከል ማስታወሻ ደብተሬ ትዝ አለችኝ::
በዚህች ማስታወሻዬ ላይ የምሰማቸውን አስገራሚ አንዳንዴም አስቂኝ ሃሳቦች እሞነጫጭርባታለሁ:: በድንገት ብልጭ ብለው አፍታ ሳይቆዩ ድርግም የሚሉ ሃሳቦችን እንዳመቸኝና እንደተመቸኝም አሰፍርበታለሁ። ማስታወሻዬ በገፅ ብዛትና በመጠኗ አነስተኛ ትምሰል እንጂ በርካታ አነጋጋሪና አሳሳቢ ማህበራዊና ባህላዊ ህፀፆቻችንን በአጭሩና በትዝብት መልኩ ከትባለች::
የአክስቴ ልጅ ከሄደችበት እስከትመጣ ማስታወሻዬን ገልበጥ ገልበጥ እያደረኩኝ ስቃኝ፣ የቻይናው ሕዝባዊ ሪፐብሊክ መስራች የሆነውን ማኦ ‹‹አራቱን አሮጌዎች አስወግድ›› በሚል መርህ አሮጌ ባህል፣ አሮጌ ልማድ፣ አሮጌ ወግና አሮጌ አስተሳሰቦችን እናስተካክላለን ስለማለቱ የሚያትት ፅሁፍ አገኘሁ::
እሳቤውን ለምን እና እንዴት እያልኩ ሳስብ ድንገት ስኩለርን ተመለከትኩት:: ስኩለር ትክክለኛ ስሙ አይደለም:: ይሕን ስም የሰጠሁት ከዝነኛው እንግሊዛዊ ደራሲ ከጆርጅ ኦርዌል የእንስሳት አብዩት “Animal Farm” መፅሃፍ አንድ ገፀ ባህሪ ጋር በሁሉ ተግባር ስለሚመሳሰልብኝ ነው::
የእንስሳት አብዮት ጆርጅ ኦርዌል በሩሲያ አብዮት ውስጥ የታዘበውንና አብዮቱ በሕዝብ ላይ ያስከተለውን የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሕይወት ድቀት ምፀታዊ /ሳቲሪካል/ በሆነ አቀራረብ ያጋለጠበት ስራ ነው። ስኩለር የተሰኘው ገፀ ባህሪ ደግሞ ኦርዌል ከቀረፃቸው እጅግ ውስብስና አስገራሚ ገፀ ባህሪያት መካከል አንዱ ሆኖ ይገኛል። ስኩለር ‘ድንጋይ ዳቦ ነው’ ብሎ የማሳመን ችሎታ ነበረው። ፈጣን ተናጋሪና እጅግ ጮሌ ሲሆን የሌሎችን ሀሳብ (ለመልካም ግብ ሳይሆን ለማደናገሪያ ወይም እውነትን ለማድበስበሻ) የማስለወጥ ሀይሉ ከአነጋገር ስልቱ ጋር ተዳምሮ ወደር የማይገኝለት ‹‹አጭበርባሪ›› ፖለቲከኛ አድርጎታል።
በርካታ ፀሀፍት ስኩለርን ከሶቪየት ህብረቱ የስታሊን ፕሮፓጋንዲስት ሞሎቶቭ፤ አንዳንዶቹም ከኮሚኒስት ፖርቲው አፈ-ልሳን ‘ፕራቭዳ’ እና እንዲሁም ከናዚ ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ ክፍል ሃላፊ ጆሴፍ ጎብልስ ጋር አነፃፅረው አቅርበውታል።
የእኔና ስኩለር ትውውቃችን ከአመታት በፊት እሰራበት በነበረ አንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ነው:: ስኩለር ከአመታት በፊት ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረ አካራሪ ብሔርተኛ ካድሬ ነበር:: በእኔ የመረዳት ምጣኔ ልኬት ስኩለር ተናግሮ የሚኖር፣ ግን ደግሞ የተናገረውን የማይኖር፣ ተግባሩና ምኞቱ የተራራቀ ሰው ነው::
ጨቅላነቱን እየሸሸ ትልቅ ለመባል የሚሟሟት የወንበር እድሜ የሚቀሽብ ሽምግልናውን ለመሸሽ እድሜን የሚቀንስ ባለ ሁለት ዓመት፣ ባለ ሁለት እድሜ ነው። በትግል ወቅት ግራ ጭኑ ላይ በመመታቱ ሲራመድ ወደ አንድ አቅጣጫ ጎንበስ ቀና እንደሚል ከርቀት ይለያል።
የአፍሪካ መቀመጫ የሆነችን አዲስ አበባን የተዋወቃት ታንክ ላይ ተንጋሎ በነተበ ቁምጣ ሲጃራውን እያቦነነ ነው። ከመሰልና መሳዮቹ ጋር ‹‹አስቀይሞኛል›› ከሚለው የደርግ አገዛዝ ነፃ ወጥቶ አዲስ አበባ ከገባ ሁለት አስርት ዓመታተን ቢሻገርም እርሱ ያው እንደ ትላንቱ ነበር:: አለባበሱን ቢቀይርም፤ አስተሳሰቡ አልተቀየረም። ጠመንጃውን አልጣለም። በሃይል ማሰቡን አላቆመም። ቁጡ ባህሪው አብሮት ነበር::
በእርግጥ ባህሪው ከአብዛኞቹ የትግል አጋሮቹ ጋር በፅኑ ይመሳሰላል። አክራሪ ብሔርተኛው ስኩለርም ደርግን ለማባረር በተኮስው የጥይትና መሬት በወደቀ የቀልሃ ቁጥር ብዛት ከሌላው ብሔር የተሻለ ማግኘት አለብኝ የሚል እምነት ተከታይ ነው።
ለሁለት አስርት ዓመታት አንግቦት ከተጓዘው አንዳንዶች ከዚህም ወላጁን ስለማያውቅ «ዲቃለው» ብለው ከሚጠሩት አብዮታዊ የዲሞክራሲ ፍልስፍና ውጭ ሌላው ሁሉ ትክክል አይመሰልውም። በሚያስደነግጥ፣ በሚያሳስብና በሚያስተዛዝብ መጠን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቀኖና የታፈነ ነው።
እስከማውቀው በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የስኩለር ስራና የስራ ድርሻ ከምንምና ከማንም በላይ የሚያፈቅረውን ፓርቲ እድሜ ለማስቀጠል አብዮታዊ ዲሞክራሲን በግድ መጥመቅና ፓርቲን ከማንኛውም አደጋ ተግቶ መጠበቅ ነበር:: እርሱም ቢሆን ከዚህ ስራው ሌላው የሚመርጠውም ሆነ የሚሰራው አልነበረም::
ባይገርምም ስኩለር አልተማረም። አለማወቁን አልተለየውም። ከድንቁርና ነፃ አልወጣም። የማሰብ ከፍታው በጣም ቅርብ ነው። የአዕምሮ ልቀቱ የላላ ነው። አለማወቁን በቃላት ይለውሳቸዋል። ሲናገር ሃሳቡ ግዝፈት የለውም። ትንሽ ነው። ብዙ ያወራል። አያዳምጥም። ሲጠየቅ ከሚሰጣቸው መልሶች መካከል አብዛኞቹ እውቀት ሳይሆን ሙቀት የሚሰጡ እንደነበሩም መቼም አልረሳውም::
በጎጥ በረት ውስጥ መፈልፈሉና የጎሳ ጡጦ ጠብቶ ማደጉም ለክፋቱ ሁሉ ምንጭ ነው። ከመረዳዳትና ከመተባበር ባህል ጋር አይተዋወቅም። መልካምነት ምን ማለት እንደሆነ አያውቅም። ከደግነት ይልቅ ክፋት ምርጫው ነው። ሰው ደስ ሲለው ምቾት አይሰማውም። ፍቅር አያውቅም። ራስ ወዳድነቱ ግዙፍ ነው። ሃላፊነት አይስማውም። ቡድን ማደራጀት ይወዳል። ከማዳን ለመቅበር ይቸኩላል።
ስኩለር ከሁሉም በላይ ስብሰባ እንደሚወድ ትዝ ይለኛል:: ስብስባ የሚጀምረው በአስቸኳይ ለችግሩ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል በሚል ነው። ይሁንና የስብስባው አጀንዳና ችግሩ ምን እንደሆነ እንኳን በቅጡ ሳናውቅ ስብሰባችን ይበተን እንደነበር አስታውሳለሁ::
በኢትዮጵያ እኩልነት ዴሞክራሲ ነፃነትና ፍትህ እንዲሰፍን፣ ለውጡ እንዲመጣ ፍላጎት የለውም። ለውጥ እውን እንዳይሆን የሚችለውን ሁሉ ያዋጣል:: ሕዝብ እንዲናገር እንዲጠይቅ አይፈልግም። በዚህ መንገድ ብዙ ስብስባዎችን መርቷል።
የጀመረውን ሃሳብ አሊያም ስራ መጨረስ አይችልም። ሊኖረው ቢገባም ራሱን የመውቀስ ባህል የለውም። ሁልጊዜ ትክክል መሆን ስለሚፈልግ ስህተትን መቀበል እሬት እሬት የሚለው፤ ስህተትን መቀበል ቀርቶ ከነአካቴው ስህተቱ የማይታየው፥ ስህተትን ከመቀበል ይልቅ ወደ ሌሎች ለማላከክ የሚሽቀዳደም ሰው ነው።
ስኩለር በቂ ገንዘብ ነበረው። መሃል አዲስ አበባ ላይ የኢንቨስትመንትም ባይሆን የመኖሪያ ቦታ ተሰጥቶታል። በረሃ እያለ አስቦት የማያውቀውን ጥሩ ቤት ገንብቷል። አንዳንዶችም ‹‹መንግስት የደሃውን ማህበረሰብ የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግር ለማቃለል ባስጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ተጠቃሚ ነው፣ ሰንጋ ተራ በመባል በሚታወቀው አካባቢም፣ የአርባ ስልሳ የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ ደርሶቷል፣ የቤቱን ዋጋም ከፍሎ ጨርሷል እያሉ›› ያሙታል:: በርካቶችም ይህን ነዋይ ጥሮ ግሮ ሳይሆን የብሔር ካርዱን እያወጣ ጊዜ በሰጠው ሃይልና ጉልበቱ ተጠቅሞ እንዳፈራው ሲናገሩ በተደጋጋሚ አድምጫለሁ::
በእርግጥም አካራሪ ብሔርተኛው ሰው ትላንት የሌላን ሰው መብትና ጥቅም በመደፍጠጥ የራሱን ሕይወት በምቾት ማማ ላይ ለመስቀል ሲል የሌሎችን አውርዷል:: የሌሎችን ሕይወት አፍርሶ የራሱን ገንብቷል:: ዛሬ ላይ ግን ነገሮች ተለውጠዋል::
ምክንያቱ ግራ ቢገባኝም እኛ ካለንበት ካፌ ፊት ለፊት አንድ ጥግ ድንጋይ ላይ ኩርምት ብሎ ቁጭ ያለውን ሰው በዛሬ መነጽር ትኩር ብዬ ስመለከተው የተመቸው አይመስልም:: ስኳር ይሁን ደም ግፊት ባላውቅም ፊቱ አባብጧል:: አይኖቹ ደፍርሰዋል:: የፊቱ መጥቆር ከሰል ፊቱ ላይ ደርድሮ የሚሸጥ አስመስሎታል።
መቀመጫውን ያገኘው የምረጡኝ ቅስቅሳ አድርጎ አሊያም ተወዳድሮ አይደለም። ያስቀመጠው ጊዜው ነው። በዚህች ወንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ አላፊ አግዳሚ መንገደኞችን ይገላምጣል:: ሁኔታው በልጅነቴ ፣‹‹ተቸግሬ የማስቸግራችሁ›› በማለት ሲማፀን የማውቀውን የሰፈራችን ችግረኛ አስታወሰኝ::
ትላንት ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር የነበረው ስኩለር ዛሬ ላይ በእጅጉ ተቸግሮ፣ እያስቸገረ ነው:: የሰራው ግፍ በዚህ መልክ አደባባይ አውጥቶታል:: ያስታውስ፣ አያስታውሰኝ እርግጠኛ መሆን ባልችልም በዚህ ሁኔታው ስመለከተው ይበልጥ ስነልቦናው ይጎዳል ብዬ በማሰብ ፣ አይኖቼን ወደ ትንሿ ማስታወሻዬ ደቀንኩ::
ዳንኤል ፍራይድ የተባለው ዕውቅ የአሜሪካን ዲፕሎማትና ፖለቲከኛ ስለ አክራሪ ብሔርተኝነት ሲገልጽ ‹‹ብሔርተኝነት እንደ ርካሽ መጠጥ ነው። በመጀመሪያ ሰካራም ያደርግሃል፣ ከዚያም ለጥቆ ያሳውርሃል፣ ከዚያም ይገድልሃል‹‹ Nationalism is like cheap alcohol. First it makes you drunk, then it makes you blind, and then it kills you›› ማለቱ የተናገረው ንግግር በማስታወሻዬ ግርጌ ሰፍሮ ተመለከትኩ:: የስኩለር መጨረሻ ይህን ዳንኤል ፍራይድ እሳቤ በተጨባጭ አረጋገጠለኝ::
አዎን አክራሪ ብሔርተኛ ግድግዳው እንደዘመመ፣ ጣራው እንደተቀደደ፣ ማገሩ እንደላላ ደሳሳ ጎጆ ነው:: የጊዜ ጉዳይ እንጂ ጎጆው መፍረሱ አይቀርም:: በወቅቱ ገዢ መንግስት የሰጠውን ከክፋት ስራው የመዳን እድል ያልተጠቀመበት ስኩለር መጨረሻው መፍረስ ሆኗል::
የሰው ልጅ በማታው ሕይወቱ፣ በጠዋትና በቀን ውሎው ስራው ብድራቱንና ደመወዙን እንደየስራው ሲቀበል በዓይናችን በብረቱ ተመልክተናል፣ እየተመለከትንም ነው::ፈረንሳዊው ፈላስፋ አልበርት ካሙስ፡-‹‹የመጨረሻውን የፍርድ ቀን አትጠብቅ:: እዚሁ በምድራችን ላይ በየቀኑ እየተፈፀመ ነውና፣ Don’t wait for the last judgment – It takes place every day›› የምትል ድንቅ አባባል አለችው:: አዎን ስኩለር በአድሏዊነትና በዘረኝነት ተሸብቦ ራስወዳድነት በወለደው ክፋቱ በሰራው ክፉ ተግባር ፍርዱ ሰማይ ሳይደርስ እዚሁ መሬት ላይ እየተፈፀመ ነው::
ፈረንሳዊው የሂሳብ ሊቅ፣ የፈጠራ ባለሙያና ፈላስፋ የነበረው ብሌዝ ፓስካል፣‹‹ሰው የተፈጠረው ለማሰብ ነው››፤ ይለናል:: እርግጥ ነው ሰው ማሰብ እንጂ አለማሰብን አይችልም::አለማሰብ ራሱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ማሰብ ይኖርበታል::
በዘመን ሂደት ያልተቀየረ አስተሳሰብና ያልተፈታ ችግር፤ በዘመን ሂደት የችግር ካንሠር ይሆናል::አዎ! አንዳንድ ቁስልን ገና በእንጭጭነቱ ማከም እየተቻለ ውሎ ያድርና ቁስሉ አመርቅዞ ወደካንሰር ይለወጣል:: ወደካንሰር ያደገን ቁስል ማዳን አይቻልም:: ዳፋው ሁልጊዜም በቁስሉ ህመም ሲሰቃዩ መኖር ብቻ ነው::
ለእኔ አክራሪ ብሔርተኝነት ማስታገሻ እንጂ መፈወሻ መድሐኒት የለውም:: ይህን ማድረግም ከብልህ ሰው የሚጠበቅ አዋቂነት ነው:: ቢቻል ሕመሙ እንዳይከሰት ቀድሞ መጠንቀቅ ይገባል:: አሁን ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ላይ የምናስተውላቸው አገር ለማፍረስ የሚታትሩ፣ እኛ ካልመራነው፣ ካልበላነው የሚሉ አክራሪ ብሔርተኞችም ከሕመማቸው በቶሎ እንዲሽሩ ማድረግ የግድ ነው::
በስኩለር ያየሁትን የአክራሪ ብሔርተኝነት አስከፊና አሳዛኝ መጨረሻ እያብሰለሰልኩ የአክስቴ ልጅ ከሄደችበት ተመልሳ አጠገቤ መቀመጧን ልብ አላልኩም::
‹‹እህሳ ሙዚቀኛው ለምን ለሁለት ሰው ዘፈነ? መልስልን የሚለው ጥያቄዋ ከነበርኩበት ሃሳብ አወጣኝ::
ግን እንዴት በአንድ ጊዜ ለሁለት ሰው ዘፈነ?
ለእኔ መልስ የሌለው ጥያቄ ነበር::
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2014