ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚያ ሰሞን “ድርቅ በተፈጥሮ ቢመጣም ረሃብ ግን የስንፍናችን ውጤት ነው፤ ” በሚል ርዕስ ወቅታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል። ሆኖም ዘንድሮም ሆነ ካችአምና አልያም ከዚያ በፊት የገጠሙን ርሃቦች በስንፍና ብቻ የመጡ አይደሉም። ድርቅ በገጠመን ቁጥር የሚያጋጥመን ርሃብም ሆነ የምንገኝበት ኋላቀርነትና የከፋ ድህነት ምንጭ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለማንበራችን እና አገራዊ ዘላቂ ተቋማትን ባለመገንባታችን የመጣ ነው። ዜጎች በነጻነት የሚሳተፉበትና የእኔ የሚሉት መንግሥት ቢኖራቸው ለፈጠራና ለሥራ ስለሚተጉ እድገትና ብልጽግና ይመጣ ነበር።
መንግሥትም ተጠያቂነት እንዳለበት ስለሚረዳ ትክክለኛ የልማት ፖሊሲ በመቅረጽ ለተግባራዊነቱ ሌት ተቀን ይተጋ ነበር። የመሬት ፖሊሲያችንን በአብነት ማንሳት ይቻላል። መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው ስለሚል፤ አርሶ አደሩ የባለቤትነት ስሜት ስለማይሰማው መሬቱን በሚፈለገው ደረጃ ይንከባከባል ወይም ያለማል ተብሎ አይጠበቅም። እንዲህ ያሉ ፖሊሲዎች በልማቱ ላይ ያላቸው አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለ ሆኖ አዲስ አተያይና የተወሰኑ ማሻሻያዎች ደግሞ ምን ያህል ተስፋ የሚጣልበት ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ በኩታ ገጠም ግብርና እና በቆላ ስንዴ ልማት የተገኙ ውጤቶች ጥሩ ማሳያ ናቸው።
በቀጣይ ግብርናውን ሜካናይዝድ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችና አረንጓዴ አሻራው ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ምርትንና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ያሻሽላል። አንድም መሬት ጦም ማደር የለበትም በሚል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችና የከተማ ግብርና ሲስፋፋ ደግሞ ሊመጣ የሚችለውን ለውጥ ማሰብ ነው። ሌላው ይቅርና እነዚህ የልማት ቅኝቶች ቢያንስ በሕወሓት/ኢህአዴግ ወይም በደርግ አገዛዝ ቢታሰቡ ኖሮ ዛሬ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ርሃብ አንገብጋቢ አጀንዳ ባልሆነ።
የእነ ዳረን አኪሞግሉ እና ጄምስ ሮቢንሰንን ፤ “WHY NATIONS FAIL” መጽሐፍ ፤ ለአገራት ኋላቀርነትና ድህነት ዋናው ምክንያት ፤ አካታች የፖለቲካ ሥርዓትና አሳታፊ የኢኮኖሚ ልማት አለመቅረጽ ነው የሚለው ሙግት ውሃ የሚያነሳው ለዚህ ነው። የገጠመን ርሃብ ከስንፍናችን በላይ ነው የምለው ለዚህ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወቅታዊ መልዕክትም የመጣንበትን ስሁት የፖሊሲ መንገድ የሚያሳይና ይሄን ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።
“በድርቅ ምክንያት እየተሰቃዩ የሚገኙ የሶማሌና የቦረና አርብቶ አደር ወገኖቻችን አፋጣኝ እርዳታችንን ይሻሉ፤” ካሉ በኋላ፣ በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ከብቶች በመኖና በውሃ እጥረት እየረገፉ መሆኑን ገልጸዋል:: የተከሰተው ድርቅ ረሃብን ማስከተሉን በመልዕክታቸው ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ በረሃቡ ምክንያት ሕፃናትና አረጋውያንን ሕይወታቸውን እያጡ መሆኑን ተናግረዋል:: “ክረምቱ እስኪደርስላቸው እንጠብቅ ከተባለ ብዙ ወገኖቻችንን እናጣለን፤” በማለት፣ ለድርቅና ለረሃብ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ከሚደረገው ርብርብ ባሻገር አፋጣኝ ምላሽ ለሚሹ ወገኖች ዕርዳታ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል::
በሶማሌ ክልልም በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞንም በአካል ለማየት ሙከራ አድርገናል። በሁለት መንገድ ነው ችግሩን ልንፈታ እየሞከርን ያለነው። አንደኛው ከአጭር ጊዜ አንፃር የዕለት ደራሽ ምግብ ለማድረስ ሙከራ ተደርጓል። 750 ሺ ገደማ ኩንታል እህል ተልኳል። ወደ 259 የውሃ ቦቴዎች በቦታው ተገኝተው እየሰሩ ናቸው። የከብት መኖ ተልኳል። ኒውትሪሽን ለሕፃናት እንዲሁም ክትባቶች ተሰጥተዋል።
በዚህም ምክንያት ሰው አልሞተብንም። በነገራችን ላይ ርሃብ እኮ ሁሉም አገር አለ። የኢትዮጵያ የተለየ እንዳይመስላችሁ። ችግሩ ሰው ሲራብ አገሪቱ አብልታ ከሞት ትታደጋለች ወይስ አትታደግም? ነው ዋናው ጥያቄ። ከዛ አንፃር ሰው አልሞተብንም ፤ ይሄን እንደ ጥሩ ነገር እናያለን። ከከብቶች አንጻር ትልቅ ጉዳት ደርሷል። አርብቶ አደሩን መደገፍና መልሶ እንዲቋቋም ማድረግ ያስፈልጋል። ከረጅም ጊዜ አንፃር ሁለት ሥራ ይኖራል። አንደኛው ውሃ ማኔጅመንት ነው። ውሃ … ውሃ… ውሃ የኢትዮጵያ መፍትሔ እሱ ነው ብለዋል።
ሁለተኛው ከብቶቻቸውን የሚሸጡበት የገበያ ትስስር መፍጠር ነው ፤ ለዛ ምቹ መንገድ እየተፈጠረ ከሄደ አርብቶ አደር አካባቢዎች ቦረናም ሶማሌም በእርግጠኝነት ለሰው ይተርፋሉ። ምርጥ መሬት አላቸው ፤ ሰው አላቸው። ችግሩ ውሃ አድርሰን ቅድም እንዳነሳሁት እያረሱ ከብቶቻቸውንም በተለመደው መንገድ እያራቡ ከሁለቱም እየተጠቀሙ አንዱ ሲጎዳ በአንዱ እንዲጠቀሙ አለማድረጋችን ላይ ነው። እሱን እየፈታን እንሄዳለን። በኔ እምነት በሚቀጥለው ዓመታት አሁን በጀመርነው መልኩ መስራት ከቀጠልን ይሄ ጉዳይ መልክ ይይዛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ በማለት ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት ፣ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በጊዜ ደርሰው እርዳታ በማድረጋቸው የሰውን ሕይወት መታደግ ቢችሉም የአርብቶ አደሩ የሕይወትና የኖሩ መሠረት የሆኑ እንስሳት ማለቃቸው በምንም ሊተመን የማይችል ጉዳት አድርሷል። እንስሳቱን ለምን በጊዜ ከእልቂት መታደግ አልተቻለም የሚለው ጥያቄ ግን በደንብ ሊፈተሽ ይገባል። የአርብቶ አደሩ የህልውና መሠረት የሆኑ የቤት እንስሳቱን ማትረፍ ለምን አልተቻለም። ጉዳቱንስ ከዚህ በላይ ለምን ለመቀነስ አልተቻለም። እነዚህ ጥያቄዎች ለቀጣይ መማሪያ እንዲሆኑ በደንብ ሊፈተሹ ይገባል። በጊዜ ያልሰራናቸው የቤት ሥራዎች እንዳሉ ቁልጭ አርጎ ያሳያል። አርብቶ አደሩ ለዘመናት ተረስቶ እንደኖረም ያረጋግጣል። የቅርብ ክትትል ማነስ ፤ የውሃና የመኖ ችግር ፤ ዘርፉን ከኋላቀርነት አለማላቀቅ ፤ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አሰራራችን ዘመናዊ አለመሆንና አበክሮ አለመዘጋጀት ለዛሬው አሳፋሪ ችግር ዳርጎናል። ሀ ብለን መማር ስላልቻልን በገጠመን መከራ ልንማር ይገባል።
የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ፣ ከሰሞኑ ለሚዲያ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም ከሰባት እስከ አምስት ዓመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ይከሰት የነበረው ድርቅ አሁን ድግግሞሹ እያጠረ መሆኑን ገልጸው ፤ ይህም ከዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጋር እንደሚያያዝ አስረድተዋል:: ዳይሬክተሩ ኮሚሽኑ ከሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚያገኘውን መረጃ ለክልሎች እንደሚሰጥ በመግለጽ ፤ የቅድመ መከላከል ሥራውን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሚያከናውኑት ክልሎቹ ራሳቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል:: ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር የሚነፃፀር “በጣም ዘመናዊ” የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት እንደሌለው የተናገሩት አቶ ደበበ ፤ ድርቁ ከደረሰ በኋላ ግን ኮሚሽኑ በሁለቱም ክልሎች የተጠየቀውን የምግብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።
አገራችን በታሪኳ አስከፊ ቸነፈር ፣ ድርቅና ርሃብ መልሶ መላልሶ ጎሳስሟታል:: ከክፉ ቀን ጀምረን ፣ በ1966 ዓ.ም ፣ በ1977 ዓ.ም ፣ በ1987 ዓ.ም ፣ በ1997 ዓ.ም ፣ ወዘተረፈ ተከስቶ የነበረን ድርቅና ርሃብ በአብነት ማውሳት ይቻላል:: ይህ በየአስር ዓመቱ ይከሰት የነበር ድርቅ ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የድርቁ ድግግሞሽ ወደ ሰባት ዓመታት ፤ በማስከተል በየአምስት ዓመቱ ይከሰት የነበር ቢሆንም አሁን አሁን በየዓመቱ የሚከሰት ሆኗል። ስለሆነም በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ውስጥ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች በድርቁ መጎዳታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) መረጃ ያመለክታል::
እንደ ኦቻ መረጃ በሶማሌ አሥር ዞኖች ፣ በኦሮሚያ ስምንት ዞኖች ፣ በደቡብ ሰባት ዞኖች ፣ እንዲሁም በአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አንድ ዞን በድምሩ 26 ዞኖች የከፋ ድርቅ አጋጥሟቸዋል:: አበው በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ በ2009 ዓ.ም ከተከሰተው የከፋ ድርቅ በቅጡ ያላገገሙት እነዚህ አካባቢዎች አሁንም ለከፋ ድርቅ መጋለጣቸውን ያመላከተው የኦቻ ሪፖርት ፤ ቀጣዩ የዝናብ ወቅት በቂ እርጥበት እንደማያገኙ መተንበዩ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል:: በዚህ ላይ በአማራና በአፋር ክልሎች በሕወሓት ወረራ የተነሳ ከ11 ሚሊዮን በላይ የዕለት ደራሽ እርዳታ ፈላጊ መኖራቸው ችግሩን የከፋ ያደርገዋል። በዚህ የራሽያና የዩክሬን ጦርነት የዋጋ ግሽበቱንና የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ይገኛል።
ወደ ድርቁ ስንመለስ ፤ የቦረና ዞን እንደ ሌሎቹ ቆላማ አካባቢዎች ሁሉ ዝናብ የሚያገኘው ከመስከረም አጋማሽ እስከ ታኅሳስ ወራት በሚቆየው የበጋ ወቅትና ከየካቲት እስከ ግንቦት ባሉት አራት ወራት በሚቆየው የበልግ ወቅት ነው:: የበጋ ወቅት ለአካባቢው ሁለተኛ የዝናብ ወቅት ሲሆን ፣ የበልግ ወቅት ደግሞ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የዝናብ ድርሻ የሚገኝበት ዋነኛ የዝናብ ጊዜ ነው:: እንግዲህ ይህ የበልግ ዝናብ ነው በቂ እንደማይሆን የተሰጋው። እንዲሁም 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሕዝብ የያዘው የቦረና ዞን ባለፉት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች እርጥበት አላገኘም:: በዞኑ የሚገኙት 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ከብቶችም በዝናብ የሚያገኙትን ውሃና ግጦሽ ማግኘት ተስኗቸዋል::
ስድስት ወራት ያስቆጠረው የቦረና ዞን ድርቅ እስካሁን ዋጋቸው 7 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ከ500 ሺህ በላይ ከብቶችን ገድሏል:: ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑ የዞኑ ነዋሪዎችም ለውሃ እጥረት መጋለጣቸውን የአማርኛው ሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል። ከየካቲት አጋማሽ እስከ ግንቦት ወር ድረስ በሚቆየው የበልግ ወቅት ዝናብ የሚዘገይና ከመደበኛው በታች ይሆናል የሚል ትንበያ በመኖሩ ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስጠንቅቋል::
የ2014 ዓ.ም የበልግ ወቅት አገባቡ የዘገየ በመሆኑ ፣ የካቲትና መጋቢት ወራት እንደማይዘንብ ፣ በሚያዝያና በግንቦት ወራት ደግሞ የዝናብ መጠኑ ከመደበኛው በታች እንደሚሆን ትንበያው ማሳየቱን ፣ በኢንስቲትዩቱ የረዥም ጊዜ የአየር ፀባይ ትንበያ ቡድን አስተባባሪ አቶ በቃሉ ታመነ ለሪፖርተር ተናግረዋል:: እንደ አስተባባሪው ገለጻ ምንም እንኳን በሚያዝያና በግንቦት ወራት ከመደበኛው ጋር ተቀራራቢ ዝናብ ቢኖርም ፣ በየካቲትና መጋቢት ወራት ዝናብ ስለማይኖር አካባቢዎቹ ካለፈው ዓመት አንስቶ ዝናብ ባለማግኘታቸው የተከሰተው ድርቅ ይቀጥላል የሚል ስጋት ፈጥሯል ::
ከየካቲት እስከ ግንቦት ባሉት አራት ወራት የሚቆየው የበልግ ወቅት የሶማሌ፣ የኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ለሚካተቱበት የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የዝናብ ድርሻ የሚገኝበት ዋነኛ የዝናብ ጊዜ ነው:: እንደ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ሪፖርት በ2013 ዓ.ም በነበረው የበልግ ወቅት የበልግ አብቃይ በሆኑት አካባቢዎች ዝናቡ ዘግይቶ በመድረሱ ፣ በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ ከተስተዋለው አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ በስተቀር ፣ በብዙ ቦታዎች በአብዛኛው ደረቃማ የአየር ሁኔታ ተስተውሏል::
እነዚህ አካባቢዎች የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ ስላልሆኑ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ከመስከረም አጋማሽ እስከ ታኅሳስ ወራት የሚቆየው የበጋ ወቅት ነው:: ባለፈው የበጋ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ባሌ ፣ አርሲ ፣ ጉጂና ቦረና ዞኖች ፤ እንዲሁም የሶማሌ ክልል ደቡባዊ አጋማሽ ክፍል ያገኙት የዝናብ መጠን ማግኘት ከነበረባቸው በታች ነው::
በዚህም ምክንያት በሁለቱ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ ቀጥሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአርብቶ አደሮች እንስሳት ሲሞቱ ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ዕርዳታ ጠባቂ ሆነዋል:: ነገር ግን አሁን እየገባ ያለውና ለደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ዋነኛ የዝናብ ጊዜ የሆነው የበልግ ወቅት በሁለት ወራት ዘግይቶ ከገባ በኋላ ፤ ከመደበኛ በታች ዝናብ እንደሚያገኙ ትንበያ ተቀምጧል::
በትንበያው መሠረት በኦሮሚያ ክልል ማዕከላዊ ክፍል በመጀመሪያዎቹ የበልግ ወራት አነስተኛ ዝናብ ሲያገኝ የቦረና፣ የጉጂና የባሌ ቆላማ ዞኖችደግሞ መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ ያገኛሉ:: በሶማሌ ክልልም በተመሳሳይ የሊበን፣ የአፍዴር፣ የሻብሌ፣ የቆራሄ፣ የዶሎና የኖጎበ ዞኖች በአመዛኙ መደበኛና ከመበደኛ በታች ዝናብ አግኝተው የፋፈንና የሲቲ ዞኖች ደግሞ ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ ያገኛሉ የሚል ትንበያ ተቀምጧል:: ዝቅተኛ የሆነው የዝናብ መጠን የደቡብና የሲዳማ ክልሎችንም እንደሚመለከት ተገልጿል::
የአየር ፀባይ ትንበያ ቡድን አስተባባሪው አቶ በቃሉ ትንበያውን ዋቢ በማድረግ ሁለቱ ክልሎች በ2013 ዓ.ም በልግና ባለፈው በጋ ማግኘት የሚጠበቅባቸውን የዝናብ መጠን እንዳላገኙ አስታውሰው ፤ አሁንም የሚመጣው በልግ አገባቡ ስለሚዘገይና ከመደበኛው በታች የሆነ የዝናብ መጠን ስለሚያስተናግድ ድርቁ እንደሚቀጥል አስረድተዋል:: በበልግ አጋማሽ ላይ ከመደበኛው በታች ቢዘንብም እንኳን በቂ አይሆንም ። ዝናቡ በሚዘገይባቸው ሁለት ወራት ላይ ማግኘት የሚገባቸውን ስለማያገኙ የውሃ እጥረቱን ያባብሰዋል።
በተጨማሪም በበልጉ ወቅት የደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ቆላማ የአገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ ሙቀት እንደሚኖር ፤ ይህ ሙቀት ከዝናብ እጥረትና መቆራረጥ ጋር በመዳመር ከዕፅዋትና ከአካባቢው የሚኖረውን ትነት እንደሚያባብሰው ተጠቁሟል:: እንዲሁም የዝናብ እጥረት በሚጠበቅባቸው አካባቢዎች የእርጥበት መቆራረጥና የሙቀት መፈራረቅ መኖሩ ለፀረ ሰብል ተባይና በሽታ መከሰት አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተሰግቷል።
ከዚህ የርሃብና የድርቅ አዙሪት ሰብረን ለመውጣት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታችንን ተቋማዊ ማድረግ፤ ብልሹ አሰራርና ሙስናን መታገል ፤ ዜጋውን የአገሩ ባለቤት ማድረግና ግብርናችንን ሜካናይዝድ ማድረግ የተጀመሩ የኩታ ገጠምና የቆላ ስንዴ ልማቶችን ማስፋት ፤ የአነስተኛና የከፍተኛ መስኖ ሥራዎችን ማከናወንና ያለንን የውሃ ሀብት ይበልጥ አልምተን መጠቀም ይጠበቅብናል ።
አገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር ! አሜን::
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2014