ምሁራን እደንደሚናገሩት ሕዝብን እናስተዳደራለን የሚሉ አካላት ፍትሃዊነትን ያስቀደሙ ፤ ሥነ ምግባራቸውም በሚመሩት ሕዝብ ሃይማኖት እና ባህል የተገራ መሆን አለበት። ፍትሃዊነትን ያስቀደሙ ሥነ ምግባራቸው በአግባቡ የተገራ መሪዎች ደግሞ ሁልጊዜም የሌሎችን ስሜት መጋራት የሚችል ስብዕናን የተላበሱ ፤ ለተጎዱ እና ለታመሙ እንዲሁም በእድሜ ለገፉ የሚራሩ፤ የማሕበረሰብን ፍላጎት የሚያስቀደሙ ናቸው::
አሁን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ከዚህ ነገር ጋር ፈጽሞ የተጣረሰ ነው:: ከሰሞኑ የትግራይ ተወላጆች ወደ ጎረቤት አገር ኤርትራ እንዲሁም ወደ አጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎች በከፍተኛ ቁጥር እየተሰደዱ መሆናቸውን እየተነገረ ነው።
በአንጻሩ ደግሞ የትግራይን ሕዝብ እወክለዋለው እያለ እየማለ እና እየተገዘተ የኖረው ቀንደኛው የትግራይ ሕዝብ ጠላት የሽብር ቡድን አሁን ላይ እራሱን የትግራይ መንግሥት እያለ እየጠራ ይገኛል:: የሽብር ቡድኑ ማንን ይዞ ነው ራሱን የትግራይ መንግሥት እያለ የሚጠራው? በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች የትውልድ ቀያቸውን በመተው የሽብር ቡድኑ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር እንወዳይገናኙ አድርጎ የቆለፈበትን አደገኛ ቁልፍ ሰብረው ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች እንዲሁም ወደ ወንድም የኤርትራ ሕዝብ እየተመሙ ነው::
የትግራይ ሕዝብ ወደ አዋሳኝ አካባቢዎች በከፍተኛ ቁጥር እየተሰደደ ባለበት ወቅት የሽብር ቡድኑ እራሱን የትግራይ መንግሥት ማለቱ ቡድኑ በየትኛውም ዓለም የሌለ ጉድ ፍጥረት መሆኑን ሁነኛ ማሳያ ነው ።
ሕወሓት እራሱን የትግራይ መንግሥት ነኝ ካለ ስለምን በአፋር በኩል የእርዳታ መንገድ አልተከፈተልኝም ብሎ በጭፍኑ ለሚደግፉት ለእነ አሜሪካ መሰል አገራት ይጮሃል? መንግሥት እኮ መንግሥት የሚያስብለው እወክልሃለሁ የሚለውን ሕዝቡን በሁለንተናዊ መልኩ ሊደግፍ ሲችል ነው::
ሕወሓት ግን በአንድ በኩል እኔ የትግሬ መንግሥት ነኝ ይላል:: በሌላ በኩል ደግሞ ወደማስተዳድረው ክልል እርዳታ እንዳይገባ ተከልክለናል ይላል:: ሲጀምር የየትኛው አገር መንግሥት ነው ዜጎቹን በዱቄት እና ፓስታ እርዳታ ላይ በተመሰረተ ኢኮኖሚ አገሩን የሚያስተዳድር? እራሱን መንግሥት ብሎ የሚጠራ ነገር ግን አስተዳድረዋለሁ፤ እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ እና አገር በፓስታ እና በዱቄት እርዳታ ላይ በተመሰረተ ኢኮኖሚ ሊያስተዳድር የሚፈልግ ብቸኛው የዓለማችን ጉድ ፍጥረት ሕወሓት ብቻ ነው::
የሽብር ቡድኑ የትግራይ ሕዝብ በከፍተኛ ቁጥር ርሃብን ሽሽት እየተሰደደ ባለበት ወቅት የሽብር ቡድኑ መሪዎች እያደረጉት ያለው «የጥፋት ትግል የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን» ሲደሰኩሩ ሰማን። የምን መጨረሻው ምዕራፍ ነው ? አልገባኝም ? ከስደት የተረፉትን የትግራይ ልጆች ልታስበሉ ይሆን ? ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያውያን የእብድ ስብስብ የሆነውን የሽብር ቡድን የመጨረሻ ምዕራፍ ለማየት ጓጉተዋል:: አፍጥኑት! እያሏችሁ ነው::
የሽብር ቡድኑ የትግራይ ሕዝብ ርሃብን ሽሽት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማፈን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እየታየ ነው:: ምክንያቱም የሽብር ቡድኑ የሚያስጨንቀው የትግራይ ሕዝብ በርሃብ ማለቁ አይደለም:: በርሃብ ምክንያት የትግራይ ሕዝብ ከቀየው ተፈናቀለ ተብሎ በውጭ አገር ከሚገኙ ደጋፊዎቹ የሚመጣውን ድጋፍ እንጂ ::
የትግራይን ሕዝብ በርሃብ መግደል ለሕወሃት አዲሱ አይደለም:: ለዚህ ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል:: ለዛሬው ግን አንዷን ብቻ ላስታውሳችሁ::
በደርግ ዘመነ መንግሥት በአገራችን በድርቅ ከተጎዱ ኢትዮጵያውያን መካከል የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሽ ነው:: በዚህ ወቅት አሸባሪው ሕወሓት ከተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች ረጅ ድርጅቶች የተገኘን እርዳታ ለትግራይ ሕዝብ ሲያደርስ የነበረውን የደርግ መንግሥት በመውጋት እርዳታ ለሕዝብ እንዳይደርስ እና እንዲስተጓጎል ሲያደርግ ነበር:: ይህን ተከትሎ ለትግራይ ሕዝብ ከተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች ረጅ ድርጅቶች የተገኘን እርዳታ በሕወሓት በኩል እንዲደርስ ማድረግ ተጀመረ። ካልሰረቀ እና ካልገደለ ማስተዳደር የማያውቀው የሕወሓት ቡድን ለትግራይ ሕዝብ እርዳታ የመጣውን ምግብ በመሸጥ የጦር መሳሪያ ገዛ:: በዚህም የትግራይን ሕዝብ ለከፋ ረሃብ እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን አርአያ ገብረ መድህን የተባሉት የሕወሓት አንጋፋ ታጋይ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መናጋራቸው የሚታወስ ነው።
የሽብር ቡድኑ ወደ ሥልጣን ለመምጣት የትጥቅ ትግል በሚያደርግበት ወቅት ለትግሉ ማሳለጫ መዘወሪያ በሆነው ማኒፌስቶው እንዳስቀመጠው ለትግራይ ሕዝብ መራብ እና ድህነት እንዲሁም መሰደድ ዋናው ተጠያቂ አደሃሪው የአማራ ሕዝብ ነው ይላል። በመሆኑም የአማራ ሕዝብን ሳያጠፋ እንደማይተኛም ይጠቁማል:: ይህን ፕሮፓጋንዳ በከበሮ ድለቃ አጅቦ ወደ ሥልጣን የመጣው የሽብር ቡድኑ ራሱ አገሪቱን በሚመራበት ወቅት ከርሃብ አወጣሃለው ያለው የትግራይ ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የክልሉ ነዋሪ ራሱን መመገብ እንኳን አቅቶት የሴፍትኔት ተጠቃሚ ነበር::
የትግራይ ሕዝብ በሽብር ቡድኑ የፕሮፓጋንዳ ከበሮ አይን እና ጆሮውን አፍኖ ከሽብር ቡድኑ የጥፋት መለከት ውጭ መስማት ተስኖት እና በመላው ኢትዮጵያ ብሎም በመላው ዓለም ምን እንደሚሰራት ማየት ተስኖት ለችግር ጊዜ ደራሾቹ የነበሩትን መከላከያን እና አጎራባች ክልሎችን በእውር ድንበሩ በመውረር ከፍተኛ ውድመት አደረሰ:: በዚህም የእራሱን ጉሮሮ በራሱ አነቀ:: የሽብር ቡድኑም ከራሱ ውጭ ለማንም ዴንታ ስለሌለው የትግራይ ሕዝብ የእራሱን ጉሮሮ በእራሱ እጅ ፈጥርቆ ሲይዝ ጥሩ ነው! በርታ! እያለ ከበሮውን ሲደልቅ እውነታን ማየት ያልቻለው የትግራይ ሕዝብም የጥፋት ቡድኑን የጥፋት ከበሮ በጭብጨባ ተቀበለው ::
«ገዳይ ጠፍቶ እንጂ ሟች ሞልቶ ነበር» እንዳለው የአገሬ ሰው የትግራይ ሕዝብ መፋለም ያለበት በስሙ እየነገዱ ሊዚህ ለከፋ ችግር የዳረጉትን የእብድ ስብስቦች ነው። የትግራይ ሕዝብ ነገሮችን ሲረዳ ለዚህ ችግር የዳረጉትን አረመኔዎች በእራሱ እጅ እንደሚፋለማቸው አያጠራጥርም:: አሁንም እውነታውን ሲረዳ መፋለም ጀምሯልና::
አዎ፣ የትግራይ ሕዝብ ከተጫነው ቀንበር ራሱን ማላቀቅ አለበት:: የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን ለጦርነትና ለስቃይ መዳረግን በቃን ሊሉ ይገባል:: የትግራይ ወጣቶችም እንደማንኛውም ወጣት ለነገ ስንቅ የሚሆኑ ተግባራት ላይ መሰማራት አለባቸው:: በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ ከዚህ በላይ መስዋዕትነትን መክፈል አይጠበቅበትም::
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን መጋት 1 ቀን 2024 ዓ.ም