ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቀበሌ ቤቶች ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ግለሰቦች ከግለሰቦች እና ግለሰቦች ከመንግሥት ቤቶች አስተዳደር ጋር እንዲሁም በአንድ ማህጸን ተጸንሰው ከአንድ ማሕጸን የተገኙ የአንድ ቤት ቤተሰብ አባላት እርስ በርስ መጣላት እና በየፍርድ ቤቶች መካሰስ አለፍ ሲልም መገዳደል እየተለመደ መጥቷል::
የዛሬው የፍረዱኝ ዝግጅታችንም ከዚሁ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው :: የዛሬው የፍረዱኝ እንግዳችን አቶ ምትኩ ኃይሌ ይባላል፤ በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ነዋሪ ነው::
ተምሮና አድጎ ለወግ ለማዕረግ የበቃውም በዚሁ ወረዳ ነው:: «ታላቅ ወንድሜ የሆነው አቶ ጥላሁን ኃይሌ ፤ እናት እና አባታችን በሕይወት እያሉ ስንኖርበት የነበረን የቀበሌ ቤት በማጭበርበር እና ወደ ግል ይዞታው በማዘዋወር ከልጅነት እስከ እውቀት ከአደኩበት እና ወግ ማዕረግ ከአየሁበት ቤት በግፍ እንድወጣ አድርጎኛል::
ከዚህ ጋር ተያይዞ በወንድሜ የተፈጸመብኝን በደል ኢትዮጵያ ሕዝብ ተመልክቶ ይፍረደኝ» ሲል አቶ ምትኩ ኃይሌ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቤት ብሏል::
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከሰዎች እና ከሰነዶች ያገኛቸውን መረጃዎች ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራ እና ቀኙን በማየት መፍረድ ይችል ዘንድ ዝግጅት ክፍሉ የደረሰበትን ሙሉ የምርመራ ውጤቱን እነሆ ብለናል:: መልካም ንባብ:: አቶ ምትኩ ኃይሌ ማን ነው
አቶ ምትኩ ኃይሌ ወላጅ እናት እና አባቱን አያውቅም:: ገና የአምስት ወር ሕጻን እያለ ወላጅ እናቱ ጎዳና ላይ ጥላው ትሰወራለች::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወይዘሮ በላይነሽ አስፋው የተባሉ እናት በጉለሌ ክፍለ ከተማ በቀድሞ መጠሪያው ቀበሌ 02 በአሁኑ መጠሪያው ወረዳ 01 እንጦጦ ኪዳነ ምህረት ወደ ሽሮ ሜዳ በሚወስድ ቦታ ላይ ወደ ገበያ ባቀኑ ሰዓት ያላሰቡት ነገር ይገጥማቸዋል::
አንድ ጨቅላ ሕጻን መንገድ ዳር ተጥሎ ሲያለቅስ ያያሉ:: ማጀታቸውን ለመሙላት ወደ ገቤ ያቀኑት እናት አንጀታቸው አልችል ብሎአቸው ከቤታቸው የወጡበትን ስራቸውን (ገበያ) ትተው መንገድ ዳር ተጥሎ ያለቅስ የነበረን ጨቅላ ልጅ ለማንሳት ይወስናሉ ::
ጨቅላውን አንስተውም ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ:: ከአብራካቸው ለወጣው ጥላሁን ኃይሌ ወንድም በማግኘታቸው እጅጉን ተደሰቱ:: ተጥሎ ያገኙትን ጨቅላም ልክ እንደልጃቸው ተንከባክበው አሳደጉት:: አስተምረው ለወግ ለማዕረግም አበቁት::
አቶ ምትኩም እናቱ ጉልበታቸው በደከመ ጊዜ በመንከባከብ ውለታቸውን ለመመለስ ደፋ ቀና ይል እንደነበር ይናገራል:: ለአቅመ አዳም በደረሰ ጊዜም በጊቢው በሚገኝ ባዶ ቦታ ላይ በ1994 ዓ.ም የራሱን ቤት እንደሰራ እና እስከ 2014 ዓ.ም በቤቱ እንደኖረበት ይገልጻል:: ይህንን ቤት የሰራው በራሱ ሙሉ ወጪ መሆኑን ያስረዳል።
የጸብ መነሻ
እንደ አቶ ምትኩ ገለጻ፤ የቅራኔው መነሻም አቶ ጥላሁን ኃይሌ የተባሉት የአቶ ምትኩ ታላቅ ወንድም የመንግሥት ቤቶች ያስተዳድረው የነበረውን እና ለዘመናት አቤቱታ አቅራቢው እና ወንድማቸው ለመንግሥት ኪራይ እየከፈሉ ሲኖሩበት የነበረን የቀበሌ ቤት ላይ በእናታቸው በወይዘሮ በላይነሽ አስፋው ስም ካርታ ማሰራታቸው እና ራሳቸውን የቤቱ ብቸኛ ወራሽ ማድረጋቸው ነው::
ይህን ተከትሎ በወንድማማቾች መካከል የከረረ ጸብ ይፈጠራል:: ቤቱ የቀበሌ ሆኖ ሳለ እንዴት በእናታችን ስም ካርታ ልታሰራ ቻልክ? እንዴትስ አንተ ብቻ የቤቱ ወራሽ ልትሆን ቻልክ? ሲል ታላቅ ወንድሙን አቶ ጥላሁንን መጠየቁን የገለጸው አቤቱታ አቅራቢው፤ አቶ ጥላሁንም ምን አገባህ ሲል እንደመለሰለት እና ከቤቱ እንዲወጣ እንዳዘዘው ያስረዳል:: አቶ ምትኩ ከቀበሌ ቤት አልወጣም ሲል ለወንድሙ እንደነገረው ይገልጻል::
ገላጋይ ያጡት ወንድማማቾች በዚህ መካከል የተፈጠረውን ችግር በንግግር መፍታት ባለመቻላቸው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዘውት ይሄዳሉ :: ፍርድ ቤትም ከወረዳ 01 የቀረቡለትን መረጃዎች ዋቢ በማድረግ ፍርድ አስተላለፈ:: በፍርድ ቤቱ ብያኔ መሰረትም የቤቱ ሕጋዊ ወራሽ አቶ ጥላሁን ብቻ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው::
እንደ አቤቱታ አቅራቢው ገለጻ ፤ አሳዳጊ እናታቸው ለአቤቱታ አቅራቢው ጭምር ኑዛዜ የተናዘዙ ቢሆንም ታላቅ ወንድማቸው አቶ ጥላሁን እናታቸው ተናዘው የነበረውን ኑዛዜ አጥፍቶ እና አሽሮ አዲስ ኑዛዜ እንዲናዘዙ አድርጓል ሲል አቤቱታ አቅራቢው ይናገራል::
የወንድማማቾች ቤተሰቦች ቤቱን እንዴት አገኙ?
እንደ የአቤቱታ አቅራቢው ገለጻ ፤ አሳዳጊ እናቱ ወይዘሮ በላይነሽ አስፋው ከወሎ ክፍለ አገር እንጦጦ ኪዳነ ምህረት ለጸበል ይመጣሉ :: ለጸበል የመጡት ወይዘሮ በላይነሽ አቶ ኃይሉ ወልደ ተክሌ የተባሉ ውሃ አጣጫቸውን በዚሁ በአዲስ አበባ ያገኛሉ::
ከአቶ ኃይሉ ጋር ትዳር ይመሰርታሉ:: ትዳርን በአዲስ አበባ የመሰረቱት ወይዘሮዋ አቶ ግርማ ወልደ ገብርኤል ከተባሉ የእንጦጦ ኪዳነ ምህርት አገልጋይ ደብተራ አሁን ላይ 875 እየተባለ የሚጠራውን ቤት ጠብቁልኝ ተብለው በነጻ ቤት ይሰጣቸዋል:: ቀን ቀንን እየወለደ ሲሄድ አቶ ግርማ ወልደ ገብርኤልም ወይዘሮ በላይነሽን እና ባለቤታቸውን በጥበቃ እየኖሩ ላሉበት ቤት የተወሰነች ኪራይ እየከፈሉ ይጠይቋቸዋል:: ባል እና ሚስትም ኪራይ ለመክፈል ተስማምተው በአቶ ሃይሉ ስም ከአቶ ግርማ ቤት ተከራይተው መኖር ይጀምራሉ:: ሕይወት በዚህ መልኩ እስከ 1967 ዓ.ም ቀጠለች::
በ1967 ዓ.ም ከንጉሱ አስተዳደር መውደቅ ጋር ተያይዞ 47/67 የተባለ አዋጅ አዲስ ነገር ይዞ ብቅ አለ:: አቶ ኃይሉ እና ወይዘሮ በላይነሽ ከአቶ ግርማ ወልደ ገብርኤል ተከራይተውት የነበረው ቤት የአቶ ግርማ ትርፍ ቤት በመሆኑ በመንግሥት ተወረሰ:: ቤቱም 875 የሚባል ቁጥር ተሰጠው :: ጥንዶቹም መንግሥት በወረሰው ቤት ለመንግሥት ኪራይ እየከፈሉ ኖሩ::
በዚሁ ቤት ልጅ ወልደው ለወግ ለማረግም ማብቃታቸውንም አቤቱታ አቅራቢው ይገልጻል:: በቤቱም ለቀድሞው ቀበሌ 02 ለአሁኑ ወረዳ 01 ለወረዳ ኪራይ እየከፈሉ ይኖሩ እንደነበር አሳዳጊ መስማቱን ይገልጻል::
ቤት የተወረሰባቸው ግለሰብ ምስክርነት
የአዲስ ዘመን ዝግጅ ክፍል ከሰነዶች ባለፈ ጉዳዩን ለሕዝብ ግልጽ አድርጎ ለማሳየት በሚንቀሳቀስበት ሰዓት በ1967 ዓ.ም በደርግ መንግሥት ቤት የተወረሰባቸውን የእድሜ ባለጸጋ ግለሰብ አግኝቶ አናግሯቸዋል:: የእድሜ ባለጸጋዋ ቤት የተወረሰባቸው ግለሰብ እማሆይ ጽጌ ገብረ ስላሴ ዘገየ ይባላሉ::
ነዋሪነታቸው በጉለሌ ክፍለ ከተማ በቀድሞ መጠሪያው 02 ቀበሌ በአሁኑ መጠሪያው ወረዳ 01 በተለምዶ እንጦጦ ኪዳነ ምህርት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ነዋሪ ናቸው:: እንደ እማሆይ ጽጌ ገለጻ ፤ ባለቤታቸው ደብተራ ግርማ ወልደ ገብርኤል በእንጦጦ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን አገልጋይ ደብተራ ነበሩ:: ደብተራ ግርማ በደብሯ እያገለገሉ እያሉ ሁለት ቤት ሰሩ::
አንዱ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ሲሆን ሁለተኛውን ደግሞ የሰሩት ከኪዳነ ምህረት ቤተክ ክርስቲያን ዝቅ ብሎ ወደ ሽሮ ሜዳ አቅጣጫ ነበር :: ነገር ግን የእማሆይ ጽጌ ባለቤት ደብተራ ግርማ ለቤተክርሲቲያኗ እንዲቀርባቸው በማሰብ እና ከቤተከርስቲያኗ አካባቢ የምትገኘውን ምንጭ ውሃ በቅርበት ለማግኘት ሲሉ ኪዳነ ምህርት ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ያለው ቤታቸውን ለመኖር መረጡ::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቤተክርስቲያኗ ወደ ሽሮሜዳ አቅጣጫ ያለውን ቤታቸውን ከወሎ ክፍለ ሃገር ለጸበል ለመጡት ለወይዘሮ በላይነሽ በጠብቁልኝ እንደሰጧቸው እማሆይ ጽጌ ይናገራሉ:: ሁለተኛውን ቤታቸውን በጠብቁልኝ ለወይዘሮ በላይነሽ የሰጡበት ዋና ምክንያትም በወቅቱ ቤቱ የተሰራበትን እንጨትእና ቆርቆሮ ሌባ እንዳይሰርቀው ለመከላከል መሆኑንም እማሆይ ጽጌ ያስረዳሉ:: በአጋጣሚ በጠብቁልኝ ቤት ውስጥ ወይዘሮ በላይነሽ ጋር አቶ ኃይሌ ወልደ ተክሌ የተባሉ ሰው በደባልነት ተቀመጡ:: ወይዘሮ በላይነሽ እና አቶ ኃይሌ ወልደ ተክሌም በዚሁ ቤት ተጋቡ::
ጊዜን ጊዜ ወልዶት የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በደርግ መንግሥት ይወድቃል:: የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት መውደቅ እና የደርግ መንግሥት መምጣቱን ተከትሎ የደርግ መንግሥት ትርፍ ቤት ያላቸውን ሰዎች በሙሉ 47/67 በሚል አዋጅ ነጥቆ ቤት ለሌላቸው ሰዎች በኪራይ አስተላለፈ::
በደርግ መንግሥት በትርፍ ቤትነት ተነጥቀው ለተከራዮች ከተላለፉ ቤቶች መካከል እነ ወይዘሮ በላይነሽ የተከራዩት ቤት አንዱ መሆኑን እማሆይ ጽጌ ይናገራሉ:: እንደ እማሆይ ጽጌ ገለጻ፤ በቤቱ አበል አልተበላበትም:: እነወይዘሮ በላይነሽ ከእነ እማሆይ ጽጌ የተወረሰውን ቤት ተከራይተው ለመንግሥት ኪራይ እየከፈሉ ይኖሩ እንደነበር የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል::
እንዴት ቤቱ ካርታ ሊወጣበት እንደቻለ ከአቤቱታ አቅራቢው አንደበት
በ2004 ዓ.ም ሰነድ አልባ ቤቶች ካርታ እንዲሰራላቸው የሚል መመሪያ ወጣ:: ይህን መመሪያ ተከትሎ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ አንድ ውስጥየፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ የነበረው አቶ ጥላሁን ኃይሌ በወረዳው የነበረውን ሥልጣን ተጠቅሞ በወይዘሮ በላይነሽ ስም በ2004 ዓ.ም በወረዳው የሰነድ አልባ ቤቶች ፋይል ያስከፍታል::
በእናንቱ ስምም ፋይል አስከፍቶ የቀበሌ ቤት የነበረን ቤት በሰነድ አልባ ስም ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር ወደ ክፍለ ከተማ ሰነድ አስላከ:: ይህን ተከትሎ ወይዘሮ በላይነሽ እና አቤቱታ አቅራቢው ወደ ክፍለ ከተማ ይጠራሉ::
የሰነድ አልባ ቤቶች ሃላፊ የነበሩት አቶ አሸናፊ ክንፈ በ2004 ዓ.ም ከዚህ ቤት ጋር ተያይዞ የሲ አይ ኤስ መረጃው የሚያመላክተው የቀበሌ ቤት እንደሆነ እንጂ የወይዘሮ በላይነሽ ንብረት አይደለም በማለት ለቤቱ ካርታ መስጠት እንደማችሉ በቁጥር ጉ/ክ/ከ/ው/ይ/ሬ/ፕ/ዴስክ/1069/2004 ቀን 8/9/2004ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ለወረዳው ይገልጻሉ::
ጉዳዩን ይበልጥ ለማጣራት የክፍለ ከተማው ሰነድ አልባ ቤቶች ሃላፊ የሆኑት አቶ አሸናፊ ከላይ ከተገለጸው ደብዳቤ ጋር አያይዘውም ስለቤቱ ከወረዳችሁ የሚሞላ ፎርም አለ በማለት ፎርም መሙያ ቅጽ ለወይዘሮ በላይነሽ ይሰጣቸዋል:: ይህንን ቅጽ ይዘው ወረዳ 01 ይሄዳሉ:: በዚያች ቅጽም ቤቱ ኪራይ ቀመስ መሆኑን በወረዳው ስራ አስኪያጅ አቶ ወልደማሪያም ባህረ አማካኝነት ወረዳው ምላሽ ሰጠ:: ወይዘሮ በላይነሽም ይህንን የወረዳ ምላሽ ይዘው ወደ ክፍለ ከተማ ሰነድ አልባ ቤቶች ቢሮ ይሄዳሉ::ክፍለ ከተማውም የወረዳውን ምላሽ ተመልክቶ ቤቱ የመንግሥት ስለሆነ ካርታ አይሰራለትም::
እንደውም ኪራይ ክፈሉ የሚል ምላሽ ይጣል:: ይህን ውሳኔ ተከትሎ ቤተሰቡ ለወረዳው እና ክፍለ ከተማው አንስቶት ነበረውን ጥያቄ በአለበት አቆመ:: ይሁን እንጂ በ2008 ዓ.ም ላይ በምን አይነት አካሄድ እንደሆነ ሳይታወቅ በወይዘሮ በላይነሽ ስም የመንግሥት ቤት ነው ተብሎ ተከልክሎ በነበረው ቤት ካርታ ወጥቶ ተገኘ:: ይህ ሲሆን ማንም የቤተሰብ አባል አያውቅም:: ካርታውን በወይዘሮ በላይነሽ ስም ያደረገበት ዋና ምክንያትም እራሱን ከተጠያቂነት ለማራቅ በማሰብ ነው::
ለቤቱ ካርታ ለማግኘት ፕሮሰስ የተደረገብት ሰነድ ላይ ሃሰተኛ ሰነድ ተገኘ:: ሰነዱም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ስራ እና የከተማ ልማት ሚኒስቴር የሚል ሰነድ ነው:: ሰነዱም በ1958 የተጻፈ መሆኑን የሚገልጽ ነው:: በ1958 ዓ.ም ፌዴራላዊ መንግሥት የለም:: ይህ መረጃ በወረዳ 01 መሬት አስተዳደር ፣ በክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር እና በጉለሌ ፖሊስ እጅ እንደሚገኝ አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ::
ወረዳ ላይ ያሉ ግለሰቦችን በመጠቀም በወረዳው የሚገኙ መረጃዎችን እንደፈለገ እንደሚያደርግም የገለጸው አቤቱታ አቅራቢው ፤ ይህን ተከትሎ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከአደገበት ቤት እንዲወጣ እንደተደረገ እና ይግባኝ ቢጠይቅም ውሳኔው እንደሚጸናበት ከፍርድ ቤት መነገሩን ያስረዳል:: በዚህ ውሳኔም ከወለደች አስር ቀን ያልሞላት አራስ ሚስቱን እና ሌላኛውን የሶስት ዓመት ልጁን ጎዳና ይዞ ለመውጣት መገደዱን ይናገራል:: ይህን ተከትሎ ከአቤቱታ አቅራቢው ከወንድሙ አቶ ጥላሁን ጋር ወደ ከፋ ጸብ ውስጥ አመሩ:: ጉዳዩም ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ እና ፖሊስ ወሰዱት::
የሰነድ መስረጃዎች
ዓቃቤ ህግ እና ፖሊስም በጉዳዩ ላይ ሚዛኑን የጠበቀ ፍርድ ለማስጠት በቁጥር 19/6595/2013 በቀን 21/05/2013 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የወረዳ 01 ሰራተኞች ተፈጠረ ስለተባለው ችግር ማብራሪያ ጠየቀ:: ዓቃቤ ሕግ እና ፖሊስም ለወረዳው ሶስት ጥያቄዎችን ጠይቋል::
የተጠቁት ጥያቄዎችም እንደወረደ የሚከተሉት ናቸው ፡- አንደኛ ፡- የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ቤቶች አስተዳደር የሚገኝ የቤት ቁጥር 875 ከመቼ ጀምሮ የግል ይዞታ እንደሆነ እና ወደ ግል ይዞታም ተዘዋውሮ ከሆነ በምን አግባብ እንደተዘዋወረ እና በ1998 ዓ.ም ለመንግሥት የቤት ኪራይ የተከፈለ መሆን አለመሆኑን እንድታረጋግጡልን የሚል ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ የጉለሌ ክፍለ ከተማ የውዝፍ ስራዎች ሬጉላራይዜሽን ፕሮጀከት ዴስክ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ቀበሌ 19/20/21 የቤት ቁጥር 875 በሚመለከት ያሉትን የሰነድ ማስረጃዎች እንድትልኩልን የሚል ነው::
በሶስተኛነት ዓቃቤ ሕግ እና ፖሊስም ለወረዳው ያነሳው ጥያቄ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 በቤት ቁጥር 875 የሚታወቀውን ቤት አስመልክቶ ቤቱ የማን እንደነበር ፣ ቤቱ መቼ ወደ ግል ይዞታ የተላለፈ እንደሆነ ፤ በምን አግባብ እንደተላለፈ አረጋግጣችሁ መልሱን አሳውቁን የሚል ነው::
አቃቤ ህግ እና ፖሊስ የጠየቀውን ጥያቄ መሰረት በማድረግ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 01 ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት በቁጥር ጉ/ክ/ከ/ወ1/አስ/ጽ/ ቤት/457/2013 በቀን 01/06/2013 ዓ.ም በሰጠው ምላሽ እንደተመላካተው በወረዳው በቤት ቁጥር 875 ተመዝግቦ የሚገኘው ቤት በወረዳው ሶፍት ዌር መመዝገቢያ ላይ ያልተመዘገበ ቢሆንም በቅጽ 000 ላይ ኪራይ ቀመስ መሆኑን የሚያሳይ እና በአቶ ኃይሌ ወልደተክሌ በሚል የተመዘገበ ሲሆን አከራይ ደግሞ ግርማ ወልደ ገብርኤል መሆኑን እንዳረጋገጡ ነገር ግን ከመቼ ጀምሮ ፤ በምን ሁኔታ እና እንዴት ወደ ግል ይዞታ እንደዞረ መረጃ እንደሌላቸው እና በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 01 ማይክሮ ግብር ከፋዮች ያገኙት መረጃ እንደሚያመላክተው ከ1998 እስከ 2013ዓ.ም ድረስ የአፈር ግብር እየከፈሉ ስለመሆናቸው አረጋግጠዋል::
አዋጆች እና መመሪያዎች ስለጉዳዩ ምን ይላሉ?
የአዲስ አባበ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ የመንግሥት ቤቶች አስተዳደር ረቂቅ መመሪያ ቁጥር 5/2011 በክፍል ዘጠኝ ክልከላ፣ ውል ማቋረጥ ፣ ተጠያቂነት እና አቤቱታ አቀራረብ የሚሉ መመሪያዎች ተቀምጠዋል:: በዚህ ክፍል ቁጥር 41 ንዑስ ቁጥር 6 በሕገወጥ መንገድ የተያዙ መኖሪያ ቤቶች ላይ የወረዳው አስተዳደር እርምጃ ሳይወስድ ማስቀመጥ የተከለከለ መሆኑን ያትታል::
በዚሁ ክፍል ቁጥር 41 ንዑስ ቁጥር 15 እና 17 ከዛሬው ጉዳያችን ጋር በቀጥታ የሚገናኙ መመሪያዎች ተላልፈውበታል:: በመሆኑም እነኝህ መመሪያዎች በወፍ በረር መመልከቱ ተገቢ ነው። ክፍል ዘጠኝ ቁጥር 41 ንዑስ ቁጥር 15 ፡- አንድን የመንግሥት ቤት መመሪያው ላይ ከተፈቀደው ውጪ መሸንሸንም ሆነ የቤት ቁጥር መስጠት የተከለከለ ነው::
ከዚህ መመሪያ ጋር ተያይዞ ከላይ በተጠቀሱት ከወረዳው የተገኙ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ቤቱ የአፈር ግብር ሲከፈልበት የቆየ እንጂ በ000 የተመዘገበ ኪራይ ቀመስ መሆኑን ያረጋግጣል::
ኪራይ ቀመስ ማለት ቤቱ በመንግሥት ቤቶች ስር ይተዳደር የነበረ መሆኑን ይጠቁማል:: ይህ ሆኖ እያለ አቶ ጥላሁን ቤቱን በእናታቸው ስም በማዘዋወር እና የቤቱን ነባር ይዘት ሙሉ በሙሉ በመቀየር እየተጠቀሙ ይገኛሉ:: ይህ ከመመሪያው አንጻር የክፍለ ከተማው ብሎም የወረዳው ቤቶች አስተዳደር ምን ማድረግ ነበረባቸው የሚለውን ፍርድ ለአንባብያን ትቼዋለሁ::
ሌላው በክፍል ዘጠኝ ቁጥር 41 ንዑስ ቁጠር 17 የተቀመጠው መመሪያ እንዲህ ይላል ፡- በቂ መረጃ ባልተገኘበት አንድን የመንግሥት ቤት የመንግሥት ቤት አይደለም ብሎ ምላሽ መስጠት የተከለከለ ነው ይላል:: ከዚህ መመሪያ በመነሳት እና ከላይ ለአቃቤ ሕግ እና ፖሊስ የወረዳው ቤቶች አስተዳደር ከሰጠው ምለሽ በመነሳት ቤቱ በቅጽ 000 የተመዘገበ ሆኖ ሳለ ስለቤቱ አጠራጣሪ ሁኔታ ባለበት ሁኔታ በቤት ቁጥር 875 ካርታ ሲወጣ የወረዳውም ሆነ የክፍለ ከተማው የቤቶች አስተዳደር ምን ሲሰራ ነበር? አሁንስ ቤቱን ለመስመለስ ስለምን እንዲሁ ቁጭ ሊል ቻለ? ይህንንም ፍርድ ለአንባቢያን ትቼዋለሁ::
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አስተዳደር ምላሽ
ከላይ የተጠቀሱትን መመሪያዎች እና ሌሎች በ2011 ዓ.ም የወጡ መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ እንዲሁም ወረዳው ለአቃቤ ሕግ እና ለፖሊስ ከሰጣቸው ምለሾች በመነሳት ለጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ኃላፊ ለሆኑት ወይዘሮ ህሊና ኃይሌ የአዲስ ዘመን ዝግጅት የተለያዩ ጥያቄዎችን አነሳንላቸው ::
ከጥያቄዎች መካከል አንደኛው ፤ የቤቶች አስተዳደር የሚያስተዳድራቸውን ቤቶች በተወሰኑ ዓመታት ልዩነት እየመዘገበ መያዝ እንዳለበት በመመሪያ ተጠቁሟል:: አሁን ላይ በአቶ ጥላሁን የተያዘው ቤት በ000 ቅጽ የተመዘገበ ሆኖ ሳለ ምን ስለቤቱ አላጣራችሁም ወደ በአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳዳር ስር ለማዘዋወር አልሰራችሁም ? በአዋጅ 5/2011 ዓ.ም ክፍል ዘጠኝ ቁጥር 41 ንዑስ ቁጥር 17 የተቀመጠው መመሪያ መሰረት በቂ መረጃ ባልተገኘበት አንድን የመንግሥት ቤት የመንግሥት ቤት አይደለም ብሎ ምላሽ መስጠት የተከለከለ ነው ይላል:: ከዚህ መመሪያ በመነሳት እና የወረዳው ቤቶች አስተዳደር ባረጋገጠው መሰረት በ000 የተመዘገ ቤቱ ኪራይ ቀመስ ነው የሚል ነው::
ይህ አጠራጣሪ ሁኔታ ባለበት በቤት ቁጥር 875 ካርታ ሲወጣ የወረዳውም ሆነ የክፍለ ከተማው የቤቶች አስተዳደር ምን ሲሰሩ ነበር? ወረዳው ለአቃቤ ሕግ እና ፖሊስ በሰጠው ምላሽ መሰረት ቀደም ብሎ ቤቱን አቶ ሃይሌ ወልደ ተክሌ የተባሉት ግለሰብ ከአቶ ግርማ ወልደ ገብርኤል ቤት ተከራይተው እንደነበር ተገልጿል:: ይህ ሆኖ ሳለ ስለምን ቤቱ በወይዘሮ በላይነሽ ስም ካርታ ሊወጣ ቻለ? የሚሉትን እና መሰል ጥያቄዎችን አንስተንላቸዋል::
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት አስተዳደር ኃላፊ ህሊና ኃይሌ ከቤት ቁጥር 875 ጋር ተያይዞ ካርታ ለማውጣት እንቅስቃሴ የተጀመረው በ2004ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን በመጥቀስ ፤ ካርታ ለማውጣት ካለው የጊዜ እርዝማኔ ጋር ተያይዞ በጉዳዩ ጋር የተገናኙ በርካታ ተዋናዮች እና መረጃዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገልጻሉ::
እነኚህን በርካታ ተዋናዮችም በርካታ ሰነዶችን ሊያንቀሳቀሱ እንደሚችሉ ይናገራሉ:: ስለሆነም ተፈጠረ ስለተባለው ችግር የተሟላምላሽ ለመስጠት ጉዳዩን ጊዜ ሰጥቶ መመርምር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ:: በቀጣይ ጉዳዩን በጥልቀት በመመርምር በምርመራ የተገኘውን ውጤት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፍርዱኝ አምድ እንደሚያስታውቁ አመላክተዋል::
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በቀጣይ በሚኖረን ፕሮግራም ከክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር እና የመሬት ልማት ማኔጅመንት እንዲሁም ከተለያዩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ወገኖች የሚገኙ ሰነዶችን በመመርመር የመጨረሻውን ክፍል ይዘን እንደምንቀርብ ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን :: ቸር እንሰንብት ! ሰላም!::
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን የካቲት 30 /2014