“አብርሀም ሊንከን በኮንግረስ አባልነቱ አይረሴ ከሆኑ ንግግሮቹ አንዱ በ1848 እ.ኤ.አ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት የዴሞክራቲክ እጩ ሆኖ በቀረበው በጄኔራል ሊዊስ ካስ ላይ የሰነዘረው ትችት ነበር።
“የተከበሩ አፈ ጉባኤ! ጄኔራል ሊዊስ ለዚህ ማዕረግ ያበቁት ሜዳሊያዎች በአሜሪካ ጠላት ላይ ባስቆጠረው ድል ሳይሆን በአሜሪካ ገንዘብ ላይ ባሳየው ጀግንነት መሆኑን ላረጋግጥልዎ እወዳለሁ።”
የዚህን ሰው ገድል ማንሳት የፈለኩትም በመጀመሪያ አካላዊ ብቃቱን እንድታዩልኝ ነው።
ሊዊስ የብዙዎችን ሰዎች ሥራ በአንድ ሰዓት መከወን ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ርቀት የሚከናወኑ ሥራዎችንም በአንድ ሰዓት የመከወን ልዩ ችሎታ ያለው ሰው ነው።
ይኸም ብቻ ሳይሆን የመብላት ችሎታውም እንዲሁ የሚደነቅ ነው። ከኦክቶበር 1821 እስከ 1822 እ.ኤ.አ ባለው አንድ ዓመት ብቻ በሜችጋን ከተማና በዋሽንግተን በቀን የአስር ሬሽን ምግብ ተጠቃሚ ነበር።
ሁለቱ ከተሞች እየተመላለሰ ሲመገብ በመሀል መንገድ ደግሞ እንዳይርበው በሰዓት አምስት ዶላር ለምግብ ያወጣ ነበር። ከዚህ በላይ በአመጋገቡ ላይ የሚያሳየው ጥበብ ቢኖር ደግሞ ለሚመገበው ምግብ ከመክፈል ይልቅ ሌሎች እንዲከፍሉለት የሚያደርገው ዘዴ ነው።
የተከበሩ አፈጉባኤ! መቼም ሁላችንም በሁለት ከረጢት ድርቆሽና በመጠራጠር መካከል ቆማ በረሀብ ለመሞት ስለተቃረበላቸው እንስሳ(አህያ) ሳንሰማ አልቀረንም ለጄኔራል ሊዊስ ግን ከረጢቱን አንድ ሺ ማይልስ አርቀው ቢያስቀምጡበት እንኳን በቅጽበት ድርቆሹ ያለበት ድረስ ተጉዞ እንደሚበላው አይጠራጠሩ እንዲያውም እዚያ እስኪደርስ በመንገድ ላይ የሚበቅሉ ሳሮችም ሰለባው መሆናቸው አይቀርም። በማንኛውም መንገድ ቢሆን ይሄን ሰው ፕሬዚዳንታችሁ ልታደርጉት ይገባል ::
ምክንያቱም ከእሱ ምናልባት የሚተርፍ ነገር ካለ እንደሚሰጣችሁና እናንተም ጠግባችሁ እንደምታድሩ አልጠራጠርም…” ነበር ያለው ::
ልብ ያለው ልብ ይበል !!
እንደምን አላችሁልኝ ውድ የአዲስ ዘመን አንባቢዎች
ሰሞኑን ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን እስከ ሶሻል ሚዲያው ያለው የገበያው ወሬ ሙስና….ሙስና …..ሙስና ነው ::
ወሬ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ላይ ከፓርላማ እስከ ከተማ ከንቲባዋ ድረስ በመንግሥት ገንዘብ መንታፊዎች ላይ ጥርስ የሚያስነክስ ዛቻ ከጠዋት እስከ ማታ ጋዜጠኞቹ ሲያስጮሁት እየሰማ ፀረሙስና ኮሚሽኑ በአይን ቁራኛ ከማየት በዘለለ ጠንከር ያለ እርምጃ ባለመውሰዱ መንታፊ ባለስልጣኖቻችንን ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ አድርገው ሲመሽና ሲነጋ እያዩ የጠላት ወሬ ነው ከማለት ባለፈ እራሳቸውን ለመከላከል እንኳን ድፍረት አላገኙም::
በአጠቃላይ ሙስና የተሰኘው ህብረተሰባዊ ጠንቅ በአንድ ሀገር ወይንም በአንድ ክልል ብቻ የተወሰነ ፣ የክልሎች አስተዳደር ያልገደበው ወይም የማይገድበው አገራዊ ክስተት በመሆኑ አስሩም ክልሎችን፣የፈጠረባቸው ጫናና ያመጣባቸው ጣጣ አሳስቧቸው ፀረሙስና ኮሚሽን ኮሚቴ በማቋቋም በአገራችን ሙስናን በዘመቻ ለማጥፋት ሙከራ ቢደረግም አልተሳካም::
ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ ኪሳቸው የሞላውን ሚሊየነሮች በባዶ ኪስ ሙሰኞች ከመተካትና ለጥቂት ጊዜ ለማስደንገጥ ተሞከረ እንጂ ፀረ ሙስና ዘመቻዬ ተሳክቶልኝ ሌብነትን ከክልሌ አስወግጃለሁ ያለና አፉን ሞልቶ በድፍረት የሚናገር የክልል መንግሥት እስከ አሁን ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ አልሰማንም::
ላለፉት 27 ዓመታት በትግራይ ወያኔዎች የሙስና ወንጀል ታሪክ ውስጥ የሚፈጸሙት ሌብነቶች በሚስጥርና በጥንቃቄ ስለነበር ተረኞቹ ባለስልጣኖቻችን ደግሞ ወንጀሉን የሚያሳይ ምንም አይነት ምልክት እንዳይኖር በወኪሎቻቸው አማካኝነት የመረጃ ሰነዶቹን ሁሉ ለማጥፋት ከፍተኛ ዘመቻ ላይ እንደሆኑ መረጃዎች እየወጡ ነው:: ይህ ለምን የሚሆን ይመስላችኋል ? ::
የሙስናው ባለቤቶች ወንጀሉን የፈፀሙት በሚስጥርና በጥንቃቄ ስለሆነ በእርግጥ አጥፊውን ለመመርመር መነሻ ሊሆን የሚችል አሻራ እንዳይኖረው ቤተሰባዊ ሌብነት በመሆኑ የዘረፉበት ስልት ከደረቅ ወንጀሎች ጋር ሲነፃፀር ሚስጥሩ ከወጣ ሁሉም ተያይዘው እንደሚጠፉ ስለሚያውቁት የሌብነቱን ወንጀል ትንሽ ውስብስብነት ሳይኖረው እንደማይቀር ብንገምትም ትክክለኛ ፍትህ ለማግኜት ግን ህዝቡ እንደጓጓ መቅረት የለበትም :: ይሰማል ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ..ይሰማል ወይ ??
መንግሥትም ቢሆን፣ በአንድ ሳምንት በፀረ ሙስና ዘመቻና ጥቂት ሰዎችን ብቻ አስሮ ህግ ፊት በማቅረብ ሙስናን ማስወገድና ከስሩ ነቅሎ መጣል ይቻላል ብሎ የሚያምን ከሆነ እጅግ የዋህነት ይመስለኛል ::
ምክንያቱም ዋናው የችግሩ ምንጭ የመንግሥት የራሱ አሰራርና አወቃቀሩ በሪፎርም ሊለወጥ ሞከረ እንጂ ገና አልተለወጠም:: ሪፎርም ደግሞ ዘገምተኛ በመሆኑ ሙስናን ማጅራቱን ይዞ ለህግ ለማቅረብ፣የመንግሥትን ቁርጠኝነት ይጠይቃል::
መንግሥት ሙስናን ገንዘብ መስረቅ ወይንም ማባከን ወይንም በስልጣን ያለአግባብ መጠቀም ብቻ ሳይሆን ሙስና ፣ ሥራን በተገቢ ሁኔታ ባለመስራት ህዝብን በማጉላላት ከለውጡ ጋር ባለመደመር በኃላፊነት ተቀምጦ ለውጥ በማደናቀፍ ሌት ከቀን የሚሰሩ ናፋቂ ወያኔዎችን ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ድረስ ቤታችንን ማፅዳት ይኖርብናል :: ይሰማል ? ይሰማል ወይ?
ውድ የአዲስ ዘመን አንባቢዎች
ጣፈጠንም መረረንም ይህን ቁርጠኛ እርምጃ መንግሥት የማይወስድ ከሆነ ፣ ችግሮቻችን ውስብስብ ሆኖ እንዲስፋፉና እንዲያመረቅዙ የእርስ በእርስ እልቂት እንዲነሳ ሙሰኞቹ በዘረፉት የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት ለሽብር ድርጊት ሀገርን ለማተራመስ እንደሚዘጋጁ መንግሥት ሆይ ! ጠርጥር ::
ዛሬ ለሕይወት ዋጋ ካልሰጠናት ነገ ሕይወት በተራዋ ዋጋ ታስከፍለናለችና መዘናጋት ጨርሶ መታሰብ የለበትም በማለት እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል ::
በእርግጥ የህዝብ ችግርና መከራ በዚህ ትውልድ እንዲያበቃ የምንፈልግ ከሆነ መንግሥት ሆይ ትክክለኛ የሙስና ዘመቻው ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ::
በትክክል የሙስና ምንጠራ የሚጀመር ከሆነ ለጊዜው ጥቂቶቹን ሚሊየነር የመንግሥት ባለስልጣኖችን ባህር ማዶ ያከማቹት በቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብ ጨምሮ ሲታገድ ያን ጊዜ ፀረ-ሙስና ዘመቻ ሥራውን ጀመረ ብለን እናምናለን: : ለሚዲያ ፍጆታ አስባችሁት ከሆነ ግን ….. ሌባና ፖሊስ እንጫወት ቀልድ ይሆናል: :
ብዙዎቻችን በአካልና በቀለም ኢትዮጵያዊ ከመምሰል ባሻገር በነፍስና በድርጊት ኢትዮጵያዊ መሆናችንን ሙስናን ለመዋጋት በሚደረገው ዘመቻ መተባበራችንን ማረጋገጥ አለብን :: ካለበለዚያ ፣ ዛሬ ለሕይወትህ ዋጋ ካልሰጠናት ነገ ሕይወት በተራዋ ዋጋ ታስከፍለናለች ልብ ያለው ልብ ይበል ::
እኔም ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ በሌላ ዝግጅት እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን!።
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2014 ዓ.ም