አዲስ አበባ፡- የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት ኢትዮጵያን ለጉብኝት ከመጡት 380 ሺህ 376 የውጭ ጎብኝዎች 1 ቢሊየን 424 ሚሊየን 174 ሺ 744 የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን አሳወቀ፡፡
የኢፌዴሪ በባህልና ቱሪስም የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኽኝ አባተ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከተለያዩ የዓለም ሀገሮች 380 ሺህ 376 ጎብኚዎች የመጡ ሲሆን፣ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን የሚጠጋ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከመቸውም ጊዜ የተሻለ የቱሪስት ፍሰት እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ዲፕሎማቶችንና በተለያዩ ጉዳዮች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የውጭ ዜጎችን ታሳቢ ያደረገ እቅድ ይዞ እንደነበር ያወሱት ዳይሬክተሩ በተደረገው የማጥራት ሥራ ገቢው የተገኘው ለጉብኝት ከመጡት ብቻ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት፣የሆቴል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብቃት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ የማበረታታት፣አስጎብኚዎች የሀገር ግጽታን ሊገነባ የሚያስችል አገልግሎት እንዲሰጡ አቅም የመፍጠር ፣ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ የመሥራትና ቱሪዝምን አጠናክሮ የማስተዋወቅ ሥራዎች መሥራታቸው ለውጤታማነቱ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚው ዕድገት የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ560 በላይ የሚሆኑ አስጎብኚ ድርጅቶችና ባለ ኮከብ ደረጃ ሆቴሎች በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደተሰማሩ የጠቀሱት አቶ ገዛኽኝ ቱሪዝም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ምን ያህል አስተዋጽኦ እያበረከተ እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በመቶ ቀናት ካከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ስትራቴጂ መንደፍ፣ የቱሪዝምን የመረጃ ሥርዓት ማዘመን እና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተቀናጅተው እየሠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አሁን ባለው መዋቅር ሦስት ዘርፎች አጣምሮ እየሠራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርትን በማስተባበር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 5/2011
በኢያሱ መሰለ