እየተመነደጉ የሄዱት ሥራ ፈጣሪዎች

ዜና ሀተታ

ሥራን ለመፍጠር ሃሳብን ማፍለቅና አካባቢን ማማተር የመጀመሪያው ተግባር ነው። ሰዎች በየአካባቢያቸው የሚገኙ ጸጋዎችን ተጠቅመው የሥራ እድሎችን እንዲፈጥሩ የሚያስችሉ አሠራሮች መበረታታት ከጀመሩ ወዲህ በርካቶች ውጥኖቻቸውን ወደ ተጨባጭ ውጤት በመቀየር ተጠቃሚ እየሆኑ መጥተዋል።

ከሰሞኑ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር 3ኛውን የአፍሪካ ጆብ ክሬሽን ፎረም በዓድዋ ሙዚየም ባዘጋጀበት ወቅት ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ 50 ጥቃቅንና አነስተኛ ሥራ ፈጣሪዎች፤ ወደ መካከለኛ ደረጃ መሻገራቸውን የሚያረጋገጥ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል። በመርሃ ግብሩ ላይ ካገኘናቸው መካከል ፍቅሩ ዘውዱ አንዱ ነው።

ፍቅሩ፤ በአማራ ክልል ደብረሲና ከተማ ብሎኬት እና ቴራዞ የሚያመርት ሥራ ፈጣሪ ነው። ወደ ማምረት ሥራ እንዲገባ የገፋፋው በአካባቢው ብሎኬት የሚያመርት ድርጅት ባለመኖሩና ከአዲስ አበባ ከተማ እያመጣ ሲሠራ በማየቱ እንደሆነ ይገልጻል።

ፍቅሩ ሥራውን አንድ ብሎ የጀመረው ከጓደኞቹ ጋር ቢሆንም፤ ጓደኞቹ ጫናዎችን መቋቋም አቅቷቸው ራሳቸውን ከሥራው በማግለላቸው፤ ብቻውን ሥራውን ለመቀጠል እንደተገደደ ይናገራል። በወቅቱ የወሰነው ውሳኔም አላሳፈረውም። ዛሬ ከጥቃቅን እና አነስተኛ ሥራ ፈጣሪነት ወደ መካከለኛ በማደግ በፌዴራል ደረጃ እውቅና ለማግኘት በቅቷል።

ፍቅሩ በሦስት መቶ ሺህ ብር ካፒታል ወደ ሥራ ሲገባ በአንድ ጊዜ አንድ ብሎኬት ብቻ የሚያመርት ማሽን እና ሦስት ሠራተኞችን ይዞ እንደነበር ያስታውሳል። አሁን ከሦስት ሠራተኛ ወደ 26 ቋሚ ሠራተኛ እና እንደአስፈላጊነቱም ጊዚያዊ ሠራተኞችን ቀጥሮ ያሠራል። በአሁኑ ጊዜ በሦስት ደቂቃ ስድስት ብሎኬት የሚያመርት ማሽን በመግዛት በቀን 3ሺህ ብሎኬት እያመረተ እንደሆነ ይናገራል።

ፍቅሩ አካባቢውን ማጤን መቻሉ እና በጥናት ላይ ተመስርቶ ሥራውን መጀመሩ ውጤታማ እንዳደረገው ይገልጻል፤“እኔ ሃሳብ ይዤ ስሄድ የመንግሥት አካላት ቦታ ባያመቻቹልኝ አሁን ወደ ደረስኩበት ደረጃ ላልደርስ እችላለው። ከእዚህ አንጻር ወጣቶች የሥራ ሃሳብ አመንጭተው ሲያቀርቡ ቦታና የገንዘብ ብድር ከመንግሥት አካላት ቢመቻች መልካም ነው።“ ይላል።

ሌላው ያነጋገርነው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ የቤተሰብ ማህበር መሥርቶ በዶሮ እርባታ ሥራ የተሠማራው አቶ አክሊሉ መሰለ ነው፤ ከአራት ዓመት በፊት ከባለቤቱ ጋር ተወያይቶ በቤት ውስጥ ዶሮ የማርባት ሥራ የጀመረው በአምስት መቶ ሺህ ብር ካፒታል እንደነበር ያስታውሳል።

ከባለቤቱ እና ከልጆቹ ጋር ቤት ውስጥ የዶሮ እርባታ ሥራ መሥራት የጀመረው፤ በሌሎች ሀገራት በተመሳሳይ ሥራ ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑ ሰዎችን ተሞክሮ በመውሰድ መሆኑን የሚናገረው አቶ አክሊሉ፤ የሥራውን ውጤታማነት የተመለከቱ የአካባቢው የመንግሥት አካላት 1ሺህ ካሬ ሜትር የመሥሪያ ቦታ እንዲሁም የመሸጫ ቦታ እንደሰጡት ይገልጻል።

ቦታውን ከወሰደ በኋላ ሥራውን በማስፋፋት ወደ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ኦሮሚያ ክልሎች የዶሮ ጫጩቶች ማሰራጨት መጀመሩን፤ እንዲሁም በስፋት የእንቁላል ምርትን በመሸጥ በዞኑ ተቀባይነት ማግኘት መቻሉን ይናገራል።

አቶ አክሊሉ በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ሲሆን፤ በተማረው ትምህርትም፤ በመንግሥት ሥራ መቆየቱን ገልጾ፤ ሁሉም የጀመራቸው ሥራዎች እንዳሰበው ውጤታማ ስላላደረጉት ወደ ዶሮ ማርባት ሥራ በመግባት ስኬታማ ሊሆን እንደቻለ ይገልጻል።

አሁን ካፒታሉ ወደ አራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር እንደደረሰና ዘጠኝ ሠራተኞችን በቋሚነት ቀጥሮ እያሠራ እንደሚገኝ ያስረዳል። ሠርቶ ገቢ ማግኘት ብቻ ሳይሆን፤ ያገኘውንም ከማካፈል ያልተገደበው አክሊሉ፤ 30 ያህል አቅመ ደካሞችን፤ አካል ጉዳተኞችን እና ወላጅ አልባዎችን በአስቤዛ ፣ በአልባሳት፤ እንዲሁም ተማሪ ለሆኑት ደብተር እና እስክሪፕቶ በመግዛት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ይናገራል።

ከዶሮ እርባታ በተጨማሪ እንደ ሽንኩርት፣ የሀበሻ ጎመን እና የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችንም ያመርታል፤ በሌላ በኩል 122 ሄክታር መሬት በኢንቨስትመንት እና በግል በመውሰድ፤ 20 ቋሚ እና 140 ግዜያዊ ሠራተኛ ቀጥሮ እያሠራ እንደሚገኝ ይናገራል።

የሀብታሙም፣ የደሀውም ልጅ የተሻለ ነገር አገኛለሁ ብሎ በማሰብ በስደት ይንገላታል ያለው አክሊሉ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ በስደት ከሚሄዱባቸው ሀገራት የበለጠ በርካታ የገቢ እድል ያላት ሀገር ናት ይላል።

ወጣቶች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ከመንግሥትም ሆነ ከግለሰብ መሬት ወስደው፤ ቤት ተከራይተው ፣ በጓሮ አትክልት፤ በከብት እና በዶሮ እርባታ ቢሰማሩ ከስኬት የሚያግዳቸው እንደሌለ ይገልጻል።

ሌላኛው ከጥቃቅን እና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ሥራ ፈጣሪነት የተሻገሩት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በግንባታ ሥራ የተሰማሩት አቶ ሻሜቦ ኢሊሎ ናቸው። በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡት በ50 ሺህ ብር ካፒታል እንደነበር ይገልጻሉ። አሁን ላይ ከማሽኖች ጋር ተደምሮ አጠቃላይ ካፒታላቸውን 6 ሚሊዮን ብር መድረሳቸውን ይናገራሉ።

ወደ መካከለኛ ደረጃ ለማደግ የካፒታል አቅም፤ የሥራ እንቅስቃሴ እና የሥራ ጥራት እንደሚታይ የሚናገሩት አቶ ሻሜቦ፤ ከማህበሩ አባላት እሳቸው በተለያየ የሥራ መስክ የሚሳተፉ ጭምር ስለሆነ ወደ መካከለኛ እንዲያድጉ መደረጉን ያስረዳሉ።

ወደ እዚህ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት በእዚህ ሙያ ዘርፍ በአንድ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ተቀጥረው ሲሠሩ እንደቆዩ እና ከእዚህ በኋላ ሥራቸውን ለቀው በማህበር በመደራጀት በ50ሺህ ብር ካፒታል በግል መሥራት መጀመራቸውን ይናገራሉ።

አቶ ሻሜቦ ከእዚህ ሥራ በተጨማሪ የከብት እርባታ ሥራ ጀምረው የነበረ ቢሆንም፤ ቦታ ባለማግኘታቸው ሥራውን ለማቆም መገደዳቸውን ይገልጻሉ።

አንዳንዴ የመንግሥት አካላት አንድ ግለሰብ ለመሥራት ሃሳብ ሲያቀርብ ለግል ጥቅም ብቻ እንደሆነ አድርጎ የማሰብ እና ያለመረዳት ችግር እንዳለ ጠቅሰው፤ ግለሰብም ሆነ ሀገር እንዲያድግ ከመንግሥት አካላት በኩል ብድር እና ቦታ ቢመቻች መልካም ነው ሲሉ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ።

በአመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You