‹‹አዋጁ ሙሉ በሙሉ ፕላስቲክን መጠቀም የሚከለክል አይደለም›› -ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ

 -ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

አዲስ አበባ፡አዲሱ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ሙሉ በሙሉ ፕላስቲክን መጠቀም የሚከለክል አይደለም ሲሉ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ ገለጹ፡፡

ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ እንደገለጹት፤ ተቋሙ የሕዝብና የሀገርን ደኅንነትና ተጠቃሚነት ማእከል ባደረገ መልኩ እንደ አዲስ ካዘጋጃቸው አዋጆች መካከል ባሳለፍነው ግንቦት ወር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ አንደኛው ነው።አዋጁ ሙሉ በሙሉ ፕላስቲክን መጠቀም የሚከለክል አይደለም ብለዋል፡፡

አዋጁ በተለይ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ ማምረት፣ለገበያ ማቅረብ፣ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣መሸጥ፣ማከማቸት ወይም መጠቀምን እንደሚከለክል የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ‹‹አዋጁን ባልተገባ መልኩ መረዳት አይገባም፤ አዋጁ መታየት ያለበትም ሕዝብና ሀገርን ከማትረፍ አንጻር ሊሆን ይገባል።ከሁሉ በላይ መረዳት የሚያስፈልገው አዋጁ ሙሉ በሙሉ ፕላስቲክን መጠቀም የሚከለክል አይደለም›› ብለዋል፡፡

‹‹ከ124 በላይ ሀገራት ለአንድ ጊዜ ጥቅም የሚሰጡ የፕላስቲክ ምርቶችን ከልክለዋል፤ ኢትዮጵያ ለእዚህ ክልከላ አዲስ አይደለችም›› ያሉት ኢንጂነር ለሊሴ፤ ለኢትዮጵያ የተሰጠ የእፎይታ ጊዜ አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣ ከስድስት ወር በኋላ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡

ዋነኛ ዓላማውም በአሁኑ ወቅት ከሰው ልጆች ዋነኛ የደኅንነት ስጋት የሆነውን የፕላስቲክ ብክለት መከላከል፣ከብክለት ነጻና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ አካባቢን መፍጠር መሆኑን አስገንዝበዋል።

አዲሱ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ በሚመለከት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በኩል የሚሠራጩ መረጃዎች ከእውነት የራቁና ሁለንተናዊ አላማውን የሳቱ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

እንደ ኢንጂነር ለሊሴ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት የፕላስቲክ ብክለት በሰው ልጆችና በእንስሳት ጤና፣ በአፈርና በውሃ እንዲሁም በሥነ ምህዳር ላይ ከባድ ጉዳትን እያስከተለ ይገኛል። እያንዳንዱ ፕላስቲኮች ምርቶች ከአምስት መቶ ዓመት በላይ ሳይበሰብሱ መቆየት የሚችሉ ናቸው። እንደ ሀገርም ባለፉት ዓመታት የፕላስቲክ አጠቃቀም በ400 በመቶ ጨምሯል።ይህም ከሕዝብ ቁጥር ጋር ተያይዞ ይበልጥ የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ አይደለም፡፡

ለፕላስቲክ ብክለት መፍትሔ ለመስጠት ጊዜው ነገ ሳይሆን አሁን መሆኑና ይህ ሳይሆን ቢቀር አደጋው ይበልጥ እንደሚከፋ ያስገነዘቡት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የፕላስቲክ ብክለትን መከላከልና መቆጣጠር ፅዱ ኢትዮጵያ በመፍጠርና ለትውልድ በማስተላለፍ ሂደት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው አስገንዝበዋል፡፡

የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅም እንደ ሀገር የፕላስቲክ ብክለትን መከላከልና መቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝም ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ያመላከቱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ይሁንና ከወዲሁ አዋጁን ባልተገባ መልኩ የመተርጎምና ተደራሽ የማድረግ ችግር ጎልቶ እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለአብነት ‹‹የማንኛውንም የፕላስቲክ ምርት ይዞ የተገኘ ሰው በሕግ ይቀጣል በሚል ዜና ሳይቀር ተመልክቻለሁ፤ ይህ ፈፅሞ ስህተት ነው፤ መታረም አለበት፤ መገናኛ ብዙኃን የአዋጁን ዋነኛ ዓላማና ሁለንተናዊ ፋይዳ በአግባቡ ተረድተው ኅብረተሰቡ በእዚሁ ልክ እንዲረዳ ማድረግ ይኖርባቸዋልም›› ብለዋል፡፡

‹‹በተመሳሳይ ለአንድ ጊዜ ጥቅም የሚሰጡ የፕላስቲክ ምርቶችን ከማገድ አስቀድሞ ኬንያ የሦስት ዓመት የጊዜ ገደብ ሰጥታለች››በሚል የተሳሳተ ዜና መሠራቱን ጠቁመው፤ ትክክለኛው ግን ሀገሪቱ የሰጠችው ስድስት ወር መሆኑን አስገንዝበዋል።

አዋጁ በተራዘመ የአምራችነት ተሳትፎ የግል ዘርፉን የሚገፋ ሳይሆን ይበልጥ የሚያቀርብና ብክለት በመከላከል ሂደት ይበልጥ ተዋናይ እንዲሆኑ የሚያስችል ስለመሆኑም አስምረውበታል፡፡

አዋጁ የሕዝብን ለሀገር ሁለንተናዊ ደህንነት፣ እድገትና ዘላቂ ልማት እውን ለማድረግ የሚደረግ ጥረት አካል መሆኑን ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት የሰጡት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ‹‹የፕላስቲክ ውጤቶች እያሳደሩት ካሉት ተጽእኖ አንጻር አምራቾችም ሆኑ ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ለአዋጁ ውጤታማ ትግበራ ተባባሪ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጋር በመተባበር ሁለተኛው ዙር “የጽዱ ኢትዮጵያን ባሕል ማድረግ” በሚል መሪ ሃሳብ ባሳለፍነው ሐምሌ 4 በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ላይ ለሁሉም የሚዲያ ባለሙያዎች እና ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡

በታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You