በአስተዳደሩ ለትምህርት ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል አድርጓል

አዲስ አበባ፡የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለትምህርት ዘርፉ የሰጠው ትኩረት የተማሪዎችን ውጤታማነትና ሥነምግባር እንዲሻሻል ማድረጉን የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የትምህርት አመራሮች የ2017 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም እና የ2018 ዓ.ም እቅድን መሠረት ያደረገ ግምገማዊ ሥልጠና ትናንት አስጀምሯል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር) በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ ትምህርት በግብዓት፣ በሂደትና በውጤት ይለካል።አስተዳደሩ ትምህርት ዘርፉ ላይ ያደረገው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የተማሪዎችን ውጤታማነትና ሥነምግባር እንዲሻሻል አድርጓል ብለዋል፡፡

በ2017 የትምህርት ዘመን ብቻ ከ150 በላይ ፕሮጀክቶች የማስፋፊያና የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ማስጀመር ሥራ መከናወኑን አስታውሰው፤ በኮሪዶር ልማት ምክንያት በተለያዩ የጋራ መኖሪያዎች ለገቡ ነዋሪችም በአጭር ጊዜ ትምህርት ቤት ተገንብቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል። በ‹ትምህርት ለትውልድ› ንቅናቄም ከ10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በዘንድሮው ዓመት በ6ኛ እና 8ኛ ክፍል የተመዘገበው አበረታች ውጤትም በተሠሩ ሥራዎች የተገኘ መሆኑን አመልክተው፤ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮች ድርሻም ከፍተኛ ነው።ግምገማዊ ሥልጠናውም በበጀት ዓመቱ የነበሩ ውጤታማ አፈጻጸሞችን ለማስቀጠል፣ በሂደት የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተሻለ ሥራ ለመሥራት እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።

የሂሳብና የሳይንስ ትምህርቶችን ውጤት ማሳደግ ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው ከሚገኙ ሥራዎች ተጠቃሽ መሆኑን አንስተው፤ ይህም ሥራ ፈጣሪ ዜጎችን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

የሚከናወኑ ሥራዎችን ቴክኖሎጂን መሠረት አድርገው እንዲሠሩ ለማድረግም የ‹e-school software› ተገንብቶ ሙከራ ትግበራ ላይ መሆኑም ለዘርፉ ውጤታማነት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመው፤ የመምራንን አቅም፣ አመለካከትና ክህሎት ለማሳደግም ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የወላጆች ተሳትፎም ለተማሪዎች ውጤታማነት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የ2017 የትምህርት ዘመን እቅድ አፈጻጸም ግምገማዊ ሥልጠናና 2018 እቅድ ውይይት መርሃ ግብር ቀጣይ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚረዳ ጠቅሰዋል፡፡

በ2018 የትምህርት ዘመን የታዩ ውጤታማ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በመድረኩም የነበሩ ስኬቶችን በመለየት የማጠናከርና ለነበሩ ተግዳሮቶች መፍትሔ የሚፈለግበት ይሆናል።ለእዚህም በትምህርት ዘርፍ ያሉ አመራሮች፣መምህራንና ወላጅ በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ግምገማዊ ሥልጠናው በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ከሁለት ሺህ 500 በላይ ርዕሳነ መምህራን፣ ምክትል ርዕሳነ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እና የክፍለ ከተማና ወረዳ ቡድን መሪዎች ተሳታፊ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You