አዲስ አበባ፦ በአገሪቱ የኮንስትራክሽን ሥራዎች በአማካይ በጊዜ ሰንጠረዥ 400 በመቶና በወጪ በጀት ደግሞ 156 በመቶ ከታቀደው በላይ አንድ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ እየወሰዱ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኮንስት ራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አርጋው አሻ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በአገራችን የተገነቡ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰንጠረዥና በተመደበላቸው በጀት የተጠናቀቁ ሕንጻዎች እስካሁን ድረስ አለመኖራቸው በጥናት ተረጋግጧል፡፡
ይልቁንም ሥራዎቹ በአማካይ በጊዜ ሲሰላ 400 በመቶናበገንዘብ ስሌት ደግሞ 156 በመቶ ከእቅዳቸው በላይ ተጨማሪ ወስደው እንደሚጠናቀቁ የተደረገው ጥናት ማመላከቱን ተናግረዋል፡፡ ዶክተር አርጋው እንዳብራሩት የአገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በኩል ውስንነቶች አሉበት፡፡ 80 በመቶ በግንባታው አቅራቢያ ሲሚንቶ፣ውሃና ሌሎች ግብዓቶች ተጓጉዘው ቀርበው እየተቦኩ ግንባታው የሚከናወን ሲሆን 20 በመቶ ግን ከሌላ ቦታ ተገጣጥመው የሚመጡ ግብዓቶችን ይጠቀማል፡፡ የአካባቢውን ግብዓቶች በመጠቀም ወጪና ጊዜ በሚቆጥቡ ጥራትን በሚጨምሩ ምርምሮች አልታገዘም፡ ፡ይህ ሂደት ግንባታውን ጎድቶታል፡፡
የሌሎች አገራት ተሞክሮዎች የሚያሳዩት ግን በተገላቢጦሽ ነው፡፡ በግንባታው ሳይት የሚገጣጠሙት 20 በመቶ ሲሆኑ 80 በመቶው ደግሞ ተገጣጥመው የሚቀርቡ ግብዓቶችን እንደሚጠቀም ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩልም ዘርፉ የተቀናጀ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት አመራርና አሰራር ውስንነት፣ ባለድርሻን ያሳተፈ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ያለማድረግ፣ የስትራክቸራል፣ የመካኒካል፣ የኤሌክትሪካል፣ የሳኒተሪና የአርክቴክቸራል ሥራዎች ግጭትና ሁሉም ሥራዎች በውል በፕላኑ ላይ ተለይተውና ኡደታቸው ተጠብቆ ተግባራዊ ማድረግ አለመቻል ዘርፉን ለብክነት ከዳረጉት ምክንያቶች በአብይነት ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ዘርፉ ካሉበት ማነቆዎች መላቀቅ እንዲችል 11 ጥናቶች ተጠንተዋል ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት አመራርና አሰራርን በተቀናጀ ጥናትና ምርምር ማዘመን፣ ኮንስትራክሽን የሚማሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት የኢንዱስትሪውን ችግር ተገንዝበው መፍታት የሚያስችል አቅም እንዲኖራቸው ማድረግ፣ የፕሮጀክት ኡደትን መከታተል የሚያስችል ሶፍት ዌር መጠቀም፣የቤተሙከራ አገልግሎቶችን ማጠናከር፤ የማማከርና የምርምር ተግባራት ላይ ዩኒቨርሲቲዎች የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ ማስቻል ትኩረት ተደርጎባቸው በጥናት ከተዳሰሱ ጉዳዮች ጥቂቶቹ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ሀገሪቱ ከጎንዮሽ ይልቅ ወደ ላይ ሕንጻዎችን በመገንባት ላይ የምታተኩር መሆንዋን የገለጹ ሲሆን በ2025 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቤቶች ለመገንባት መታቀዱ ተጠቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 5/2011
በሙሐመድ ሁሴን