የኢትዮጵያ ነጻነት፣ ሉዓላዊነት እና በየዘመኑ ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን ቅርጽና ይዘት ከወሰኑ የኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ድሎች መካከል ከዓድዋ ቀጥሎ ከፍ ያለ ድርሻ ያለው የካራ ማራው ድል ነው። የካራ ማራው ድል እየተባለ የሚጠራው ድል በኢትዮጵያ እና በወራሪዋ ሶማሊያ መካከል የተደረገ ጦርነት ላይ የተገኘው ሲሆን፤ መነሻውም የሶማሊያው የወቅቱ መሪ ታላቋን ሶማሊያ የመመሥረት ሕልም ይዞ የተነሳው እና በውጭ ኃይሎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ታግዞ ኢትዮጵያን ለመውረር ያለውን ፍላጎት ለማሳካት በወቅቱ በኢትዮጵያ ያለውን ክፍተት ተጠቅሞ በ1979 ዓ.ም ላይ ኢትዮጵያን የወረረበት አጋጣሚ ነበር።
ኢትዮጵያ ይሄን መሰል በየዘመናቱ ከውስጥም ከውጭም የማይተኙላት በርካቶች ቢሆኑም፤ አንዳቸውም ኢትዮጵያን አሸንፈው፣ የኢትዮጵያውያንንም አንገት አስደፍተው አያውቁም። ከዓድዋው ዘመን ወራሪዎች በኋላ የኢትዮጵያን ሕልውና የተጋፋው የሶማሊያው መሪ ጄኔራል ዚያድ ባሬ ታላቋን የሶማሊያ ሪፐብሊክ ለመመሥረት እና ከኢትዮጵያ መሬት ቆርሶ ለመውሰድ እስከ አዋሽ ያደረገው ግስጋሴም የዚሁ የጠላቶቿ አርፎ ያለመተኛት አንድ ማሳያ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያንም በዚህ ወራሪ ላይ የተጎናጸፉት ድል የዓድዋ አባቶች ልጆች መሆናቸውን ለዓለም ያረጋገጡበት የአልደፈርም ባይነት የደም ውርሳቸው ነው።
ከ1969 ዓ.ም እስከ 1970 ዓ.ም ለስምንት ወራት የቆየው ጦርነት፣ ሶማሊያን ለ21 ዓመታት የመሩት ጄኔራል ዚያድ ባሬም ሆኑ ከእሳቸው በፊት የነበሩት የአገሪቷ መሪ በውስጣቸው የቋጠሩት የራስን ግዛት ለማስፋት በሌሎችን ላይ የሚፈጸም ክህደትን ያዘለ ክፉ ምኞት የወለደው ሁነት ነበር። ይህ ሕልም ታዲያ በዘመነ ዚያድ ባሬ እውን ሊሆን እንዲገባ አምነው በመነሳት ኦጋዴንን በመጠቅለል ታላቋን ሶማሊያ ላንድ የመመሥረት የቆየ ህልማቸውን ለማሳካት ተንቀሳቀሱ። እናም በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተለይም ኢትዮጵያ በገንጣይ አስገንጣዮች ትግል ተዳክማለች ብለው ባሰቡበት ወቅት ወረራውን ጀመሩ።
ይሄን ሕልማቸውን ለማሳካት ወደ ኢትዮጵያ ከመሠማራታቸውና በ1969 ወረራ ከመፈጸማቸው በፊት ግን፤ በውጪ ኃይሎች አጋዥነት ራሳቸውን በጦር ኃይል ከማጠናከር ጎን ለጎን ኢትዮጵያን ያዳክሙልኛል ያሏቸውን የውስጥ ተገንጣዮች ለመፈልፈል ያልተጠቀሙት ስልት፣ ያልነደፉት ሴራና ያላደረጉት እገዛ አልነበረም። በዚህም የዛሬውን አሸባሪውን ሕወሓት ጨምሮ ከጎናቸው ያሰለፏቸውን በርከት ያሉ ተገንጣይ አስገንጣዮች ማፍራት ችለዋል። በሂደቱም በህቡዕ በተደራጁ ኃይሎችና ተገንጣዮች አማካኝነት ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘር የኢትዮጵያን የመከላከያ ኃይል የማዳከም ተግባር ሲፈጽሙም እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዚህ በኋላ የዚያድ ባሬ መንግሥት ግልጽ ወረራና ጦርነት ባወጀበት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሶማሊያ ጦር ጅግጅጋ፣ ሐረርና ድሬድዋ መድረስ ችሎ ነበር። ይህ ግስጋሴው በአሜሪካና ሸሪኮቿ የታገዘ ከመሆኑ አንጻር፤ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ደግሞ የነበረውን ሥርዓት ለጫና ዳርጎ ስለነበር የተገኘ ሲሆን፤ ኋላ ላይ በውስጥ ያደራጃቸው የተገንጣይ ኃይሎች እገዛ እያደረጉለት እስከ አዋሽ ዘልቆ ለመግባት እድል አግኝቶም ነበር።
ከዚህ ባለፈም የውጪ ጫናው ከውስጥ አስገንጣይ ኃይሎች ትንኮሳ ጋር ተዳምሮ በወቅቱ በኢትዮጵያ እና የሶማሌ ጦር መካከል ሰፊ ልዩነት እንደነበር ይነገራል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በውስጥም በውጪም በነበረባት ሰፊ ጫናና የቤት ሥራ አቅሟም፣ ኃይሏም በሚፈለገው ደረጃ የተደራጀ አልነበረም። በአንጻሩ ሶማሊያ ከ70 ሺህ በላይ ተዋጊ ኃይል፣ ከ250 በላይ ታንኮች፣ ከ350 በላይ ልዩ ልዩ ብረት ለበሶች፣ ከ600 በላይ መድፎች፣ ከ40 በላይ ተዋጊ አውሮፕላኖች በኢትዮጵያ ላይ አዝምታ ነበር። ይሁን እንጂ ምንም እንኳን የኃይል አለመመጣጠኑ ድል ላያስገኝ እንደሚችል ቢታሰብም፤ ይሄን መሰል ጥቃትና ወረራ መሸከም ባህሉም፣ ልምዱም ያልሆነው ኢትዮጵያዊ፤ ለማይቀረው ድል ራሱን አዘጋጀ።
ቀድሞም የአገሩ ነገር እንቅልፍ የሚነሳው ሕዝብ፣ ሚያዝያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም “የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ታፍራና ተከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ ተደፍራለች፤… ለብዙ ሺህ ዓመታት አስከብሮን የኖረው አኩሪ ታሪካችን በዚህ አብዮታዊ አዲስ ትውልድ ጊዜ መጉደፍ የለበትም። አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊት! የኢትዮጵያ ሕዝብ! ለክብርህንና ነፃነትህን ለመድፈር አገርህን ለመቁረስ የተጀመረው ጣልቃ ገብነትና ወረራ ከመለዮ ለባሹ ጋር ተሰልፈህ ለመደምሰስ የምትዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው። ተነስ! ታጠቅ! እናሸንፋለን!” በሚል የተላለፈለትን የወቅቱን ፕሬዚዳንት ጓድ መንግስቱ ኃይለማርያምን ጥሪ ሲሰማ የማሰቢያ ጊዜ እንኳን መውሰድ አልፈለገም።
እናም ከዳር ዳር ተነቃነቀ፤ በአጭር ጊዜ ዝግጅትም ወደማይቀረው የድል መንገድ ተቀላቀለ። ድል ብርቁ ያልሆነው ኢትዮጵያዊም ከውጪም፣ ከውስጥም ታግዞ እስከ አፍንጫው ታጥቆ በአየርም፣ በምድርም በእግረኛና ሜካናይዝድ ታግዞ አዋሽ የደረሰውን ወራሪ ኃይል በመጣበት መንገድ ለመመለስ ከሰማይም ከምድርም የሚለቀቀው እሳት ምክንያት አልሆነበትም። ወራሪው የሶማሊያ ጦርም በአየርም ሆነ በምድር ባለው የገዘፈ ሜካናይዝድ መታገዙ የኋሊት ሩጫውንም ሆነ በየስፍራው ተንጠባጥቦ ከመቅረት የሚያድን ፋታ አላስገኙለትም። ምክንያቱም በሰማይም በምድርም እሳት ከሚተፉ የጦር መሣሪያዎች በበዛ እጥፍ የኢትዮጵያውያን ወኔና ጀግንነት የሚለበልብ፤ ወኔን የሚሰልብ ሆነበት እንጂ።
ሐምሌ 19 ቀን 1969 ዓ.ም ላይ “አገሬ መመኪያ ክብሬ፤ አትደፈርም ዳር ድንበሬ፤” ብሎ የወጣው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይል፤ ስምንት ወራትን ከዘለቀ እልህ አስጨራሽ ውጊያ በኋላ በመጋቢት 26 ቀን 1970 ዓ.ም በተለመደው የኢትዮጵያ አናብስቶች ድል አድራጊነት መቋጫውን አገኘ። እናም “ይህ ነው ምኞቴ እኔስ በሕይወቴ፣ ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ፤” ሲል የድል ዜማውን እያዜመ ለዳር ድንበሯ መከበር በተዋደቀላት በነጻ አገሩ ላይ መኩራት መራመድ ጀመረ። ከጎኑ ተሰልፈው ለነጻነቱ አጋርም አጋዥም ከነበሩ የኩባ ወታደሮች ጋር የድል ጽዋውን አነሳ።
ይህ ጦርነት በኢትዮጵያውያን ከፍ ያለ የጀግንነት ተጋድሎ በተለመደው የኢትዮጵያውያን አሸናፊነት የተጠናቀቀ ቢሆንም፤ ጦርነት በባህሪው ክፉና አውዳሚ ነውና ሰፊ ቁሳዊም ሰዋዊም ጉዳት አድርሶ ማለፉን በርካታ ሰነዶች ያሳያሉ። ለምሳሌ፣ ከሰው ኃይል አኳያ ሲታይ በጦርነቱ በኢትዮጵያ ወገን 18ሺህ 200 ኢትዮጵያውያን ተሰውተዋል፤ 29ሺህ 100 ቆስለዋል። ከዚህ ባለፈም ከኢትዮጵያውያን ጎን ተሰልፈው ሲዋደቁ ከነበሩት የኩባ እና የየመን ወገኖችም ዋጋ የከፈሉ ሲሆን፤ በዚህም 100 የመናውያን፣ 163 የኩባ ተወላጆች ለኢትዮጵያ ሕይወታቸውን ሰውተዋል። ከወቅቱ ወራሪ ሶማሊያ በኩል ደግሞ 15ሺህ 900 ሞተዋል፣ 26 ሺህ ቆስለዋል፤ አንድ ሺህ 785 ተማርከዋል።
ይህ በመስዋዕትነት የታጀበ የካራ ማራ ድል፤ የኢትዮጵያውያንን የቀደመ የአሸናፊነት ታሪክ ያጸና ሲሆን፤ በተቃራኒው የወራሪዎችን እና የቅኝ ግዛት አቀንቃኝ በቀልተኞችን እንደ ዓድዋው ሁሉ ለዳግም ውርደት የዳረገ ሕያው የኢትዮጵያውያን ዳግም ዓድዋ የድል ቀንዲል ነው። ለዚህ ሁነት መታሰቢያ፣ ለነጻነት ትግል ለተሰዉ ወገኖች ማስታወሻ እንዲሆንም በአዲስ አበባ ሐውልት የቆመ ሲሆን፤ የኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት አደባባይ ሐውልት በመባልም ይታወቃል።
ይህ ሐውልት ደግሞ ድሉን እና የድሉን ተሳታፊዎች የሚዘክር ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያውያን ድሉን ለማሰብ፣ እለቱን ለማስታወስ በየዓመቱ የካቲት 26 የሚሰባሰቡበት መድረክም ነበር። በዚህ ረገድ በደርግ ሥርዓተ ዘመን ድሉንም ባለ ድሎቹንም የማሰብ ሥነሥርዓቱ በወጉ ሲከወን እንደነበር ከታሪክ ገጾች መታዘብ የተቻለ ቢሆንም፤ ከደርግ ውድቀት ማግስት በመጣው የኢሕአዴግ ሥርዓት ግን ድሉንና ባለድሎቹን ማክበር ቀርቶ ማሰብ በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ መታለፉ የአደባባይ ምስጢር ነው። ለዚህ ሁነኛ ማሳያው ደግሞ ድሉንም ሆነ ባለ ድሎቹን ለማሰብ የቆመው ሐውልት ሳይቀር ትኩረት በማጣቱና አስታዋሽ ባለማግኘቱ የተነሳ ዓመታትን ዳዋ ለብሶ ማሳለፉ ነው።
ይህ ደግሞ የሥርዓቱ ታሪክም ሆነ ባለታሪኮችን ጠል መሆኑን ከማሳየቱ ባሻገር፤ በወቅቱ በአሜሪካና ምዕራባውያን ትከሻ ላይ ተረማምዶ መጓዙን ዘንግቶ ታግዬ ለድል በቃሁ በሚልበት ወቅት ድል አድርጌዋለሁ በሚለው ሥርዓትና ሠራዊት የተገኘች የነጻነት ድል ዓርማ አራክሶና አኮስሶ የተመለከተበትን የዝቅጠት ደረጃ ፍንትው አድርጎ ያሳየ ሆኗል። ሆኖም ይህ ሥርዓት የዘነጋው ነገር ኢትዮጵያውያን ለነጻነትና ሕልውናቸው የከፈሉት ማናቸውም ዋጋ በቀላል የመጣ፤ በቀላሉም ተሸፍኖ የሚቀር አለመሆኑን ነው።
ይሄን ሐቅ ያልተገነዘበው የኢሕአዴግ ሥርዓት ግን የአገርንና ሕዝብን ታሪክና ገድል ከሥርዓት ጋር አብሮ ይነሳል፣ ይህ ከሆነ ደግሞ ያሸነፍኩት ሥርዓት ገድል እየተዘከረ የእኔ ውሽልሽል ታሪክ ከስሞ ይቀራል በሚል ተልካሻ ምክንያት ከፍ ያለውን ገድል አሳንሶ፤ የሕዝብን ገድል ለሥርዓት ሰጥቶ ለሕዝብም ለታሪክም ያለውን የወረደ ክብርና ቦታ በገሃድ ገልጧል።
ነገሩ እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል ሆነና፤ ኢትዮጵያውያን የማይዘነጉት ተጋድሏቸው የእነሱ እንጂ የሥርዓት ያለመሆኑን ያውቁት ነበርና ጊዜ ቆጥረው፣ ቀን ጠብቀው ከተቀበረበት የታሪክ አረንቋ ጎትተው፣ የተጫነበት ዳዋ ገልጠው አደባባይ አወጡት። በጊዜው ውብ ሆኖ የተሠራውን አኩሪ ገድል፤ ጊዜ ሊጥለው ቢሞክርም ሳይሳካለት፣ ቀን ሲወጣ፤ አዲስ ሥርዓት በለውጥ ሲመሠረት ወደ ዳግም ገናናነቱ ከፍ እንዲል መንገድ ተጠረገ። እናም በካራማራ የተፈጸመው ተጋድሎና ጀብድ የተጫነበትን የታሪክ አፋኝ ግግር አስወግዶ ዛሬ ላይ በታሪክ ዘካሪ ልጆቹ ሊዘከር አደባባይ ይወጣ ጀምሯል።
በዚህም ለሦስት አስርተ ዓመታት ገደማ ታሪኩ እንዳይወሳ ተደርጎ ዳዋ የተጫነበት የካራ ማራው ድል ዛሬ ላይ በመጣው ለውጥ አማካኝነት በተከፈተው እድል ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ከዓመት ዓመት መሻሻል በታየበት መልኩ እየተከበረ፤ ድሉም ባለድሎቹም እየታሰቡና እየተዘከሩ ይገኛሉ። ይህ ይበል የሚያሰኝ፤ የታሪክ ጉድፎችን አርሞ መልካሙን ለማጽናትና ትምህርት ለመውሰድ የሚያግዝ ጅማሮ፤ የዛሬው ትውልድ የትናንት አባቶቹንና እናቶቹን ተጋድሎ ተገንዝቦ የራሱን የታሪክ ምዕራፍ አሳምሮ እንዲፈጽም መንገድ የሚጠርግለትን አቅም የሚፈጥር ነው።
ዘንድሮም ትናንት ለ44ኛ ጊዜ ታስቦ የዋለው የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት በኢትዮጵያውያን ብርቱ ክንዶች የበላይነት በድል የተጠናቀቀበት እለት በኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት አደባባይ ተከብሮ ውሏል። በዚህ መድረክም በርካታ መልዕክቶች የተላለፉበት ሲሆን፤ በተለይ አባቶቻችን ጥቃቅን ልዩነታቸውን እና የየግል ሕመሞቻቸውን ወደ ጎን ትተው ኢትዮጵያን ነጻነቷና ሉዓላዊነቷ ተከብሮ እንድትቆም በአንድነት ታሪክ ሠርተው ያስረከቡን እንደመሆኗ፤ ይሄንን ታሪክ ሠሪ ትውልድ መዘከርም፤ ታሪኩን ለትውልድ ማሳወቅና ከታሪኩ ተምረው የራሳቸውን ታሪክ እንዲሠሩ ማድረግ ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አትኩሮት የተሰጠበት ነበር።
በተለይ ዛሬ ላይ የቀደሙት አባት እናቶቻችን ለአገራቸው ነጻነትና ሉዓላዊነት የከፈሉትን ዋጋ መዘከር፤ እነሱ የሠሩትን ታሪክ ማክበር አቅቶን በመንደርና ጎሳ ተከፋፍለን፣ በጥላቻ መርዝ ውስጥ ተለውሰን አድገን በመገዳደልና መገፋፋት አዙሪት ውስጥ ለወደቅነው ለዚህ ዘመን ሰዎች ከወደቅንበት የሰውነት ዝቅታ እንድንቃና፤ በታሪክ ጠልነትና አጠልሺነት ሥራ ላይ የተጠመዱ ኃይሎችም አካሄዳቸው እንደማያዋጣ አውቀውና ታሪክን መርምረው በእውቀት ላይ ተመሥርተን ከጭፍን ፍረጃና ጥላቻ እንድንፋታ የእውቀት ብርሃን ጮራ የሚሰጠን ነው።
ከዚህም ባለፈ አገር እንደ አገር፤ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ስለ ነገው ሲያስብና ሲሠራ የሌሎች ልምድና ተሞክሮን ብቻ ሳይሆን፤ የራሱን የኋላ ታሪክና ገድል መመልከት፤ ትውልዱን ከቀደመው ታሪኩ ማዕድ አቋድሶ ዛሬ ያለበትን እንዲፈትሽ እና የነገ መዳረሻውን አልሞ እንዲራመድ ማድረግ ተገቢ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው። ከዚህ አኳያ አሁን የታየው ቀደምቶችን የማክበርና የመዘከር፤ ከእነሱ ጠንካራውን እሴት ወስዶ የሚታረመውን አቃንቶ ለመጠቀም የሚቻልበትን ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት እንደሚገባ ያመላከተ ነው። በመሆኑም ይህ ጠላት ዳግም ያፈረበት፤ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ለትውልድ የሚተርፍ አኩሪ ገድል የፈጸሙበት የካራ ማራ ድል በልኩና በሚመጥነው አግባብ ትኩረት ተሰጥቶት ሊዘከር፤ ሊከበር ይገባል። አበቃሁ፤ ቸር ሰንብቱ!
የኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም