ከእያንዳንዷ ማይክሮ ሴኮንድ ጅምሮ ሁሉም የጊዜ ቀመሮች የየራሳቸው ዋጋ ብቻ ሳይሆን ታሪክ፣ ሁነትና ኩነት አላቸው። ምናልባትም አልተጠኑም፤ ወይም አልተጠናላቸውም እንጂ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ያላቸው የወሳኝነት ሚና እንዲህ በቀላሉ ሊታይ የሚችል ላይሆን ይችላል። ምናልባትም ወደ ፊት ነገሮች በፀጉር ስንጠቃ ደረጃ እየተመረመሩ የሚታዩበት ጊዜ ሲመጣ ሁሉም ግልፅ ይሆናል።
አሁን ወርሐ የካቲትን ይዘን አብረን እንዝለቅ፤ አሁን ያለንበት የካቲት ማለታችን ነው። ሲባዛ ገድል የተመዘገበበት እንደ መሆኑ መጠን፤ ከታሪክ አኳያ በወሩ በአገራችን ምን ምን ታሪካዊ ክስተቶች ተከናውነው ነበር፣ ምን ምንስ ድክመቶች፣ ምንስ አይነት ጀብዱዎች ተስተውለው አልፈዋል፤ ለአሁኑና ለወደፊቱስ የሚያስተምሩት ምን አይነት አስተምህሮት አላቸው፣ ወይም ይኖራቸዋል? የሚሉትን በጋራ እናይ ዘንድ ክንውኖቹን እንደሚከተለው እንጠቅሳለን። ስንጠቅስ ግን ለማሳያ ያህል እንጂ ክሮኖሎጂካል በሆነ መልኩ እናቀርባለን ማለት እንዳልሆነ ከወዲሁ መናገር ተገቢ ነው።
የካቲት 2 ቀን 1930 ዓ.ም፣ ቡልጋ ጨመሪ ላይ እነ ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በላይነህ እና ሌሎችም አርበኞችና የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ገጥመው ትልቅ ውጊያ ተደረገ።
የካቲት ወር ከሴት መሪዎች አኳያ ስንመለከተውም የራሱ የሆነ ታሪክ ያለው ሲሆን፣ የካቲት 4 ቀን 1909 ዓ.ም፣ ንግሥት ዘውዲቱ፣ “ግርማዊት ዘውዲቱ፣ ንግሥተ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብለው በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ቅብዐ መንግሥት ተቀብተው የንጉሠ ነገሥቱን ዘውድ ጫኑ። በዚሁ ቀን፣ 1910 ዓ.ም፣ «ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ » በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁት የዳግማዊ ምኒሊክ ባለቤት፣ እቴጌ ጣይቱ ብጡል አረፉ።
ከተሰሚነት አኳያም በየካቲት ወር ታሪክ አለ። በዚሁ ቀን፣ 1955 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በኢራቅ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ለተተካው የኮሎኔል አብዱል ሳላም አሪፍ መንግሥት ሕጋዊ ዕውቀት መስጠቱን አስታወቀ። በዚሁ ቀን፣ 1982 ዓ/ም፣ ዘረኛው የደቡብ አፍሪካ ሥርዓት (አፓርታይድ) ለ27 ዓመታት በእስራት የቆዩት ኔልሰን ማንዴላ ተፈቱ።
ከዚሁ ከዲፕሎማሲው ዘርፍ ሳንወጣ ሌላም የየካቲትን ገድል እናገኛለን። “ከዛሬ መቶ አስር ዓመት በፊት የካቲት 5 ቀን 1898 ዓ.ም አዲስ አበባ ከጧቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ ብዛቱ ከስድስት ሺህ ያላነሰ የአፄ ምኒሊክ ጦር የዘመቻ ትጥቁን ታጥቆ በተጠንቀቅ የመጀመሪያ የሩስያ የዲፕሎማቲክ አባላትን ለመቀበል ይጠባበቃል። የሩስያ የልዑካን ቡድንም ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ ያለውን የደንከል በረሃ አቋርጦ ተራራና ገደሉን ተጉዞ በዋዜማው የካቲት 4 ከአዲስ አበባ መግቢያ ላይ ሰፍሮ ያደረ ሲሆን ከቀኑ አምስት ሰዓት አካባቢ የስዊድን ዜጋ በሆነው የአፄ ምኒሊክ አማካሪ እየተመራ ከከተማው ይገባል።” በማለት በዚህ በያዝነው ወር ረዥም እድሜና ታሪክ ያለው የኢትዮጵያና የሩስያ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት መጀመሩን ይነግረናል። በ1966 ዓ.ም፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ከቻይና ሕዝባዊ መንግሥት ልዑካን ጋር አዲስ አበባ ላይ የዕርዳታ ስምምነት ተፈራረመ።
የመላው ጥቁር ሕዝቦች ድል
በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በአጼ ምኒሊክ በተመራው የኢትዮጵያ ሠራዊትና ባህር አቋርጦ ከአውሮፓ ከመጣው የጣሊያን ሠራዊት ጋር የተካሄደው የዓድዋው ጦርነት በታሪክ ውስጥ ከሚጠቀሱት ጉልህ ክስተቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አርበኞች የዓድዋ ድል ጣሊያን አፍሪካ ውስጥ በተለይ ደግሞ በምሥራቁ የአህጉሪቱ አካባቢ ለማስፋፋት አቅዳ የተነሳችለትን ዘረኛና የቅኝ ግዛት ዕቅድን ያጨናገፈ ከመሆኑ ባሻገር፤ በዘመኑ የአውሮፓውያን ሠራዊት በአፍሪካውያን ከባድ ሽንፈት ሲገጥመው የመጀመሪያ በመሆኑ በነጩ ምድር ከፍተኛ ድንጋጤንም ፈጥሮ የነበረ ነው። እነሆ ይህ ድል እስከ ዛሬም ድረስ (ወደ ፊትም እንዲሁ) የአፍሪካውያን፤ እንዲሁም የመላው ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት እንደሆነ አለ፤ ይዘልቃልም።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም፣
ለኢጣሊያ ንጉሣዊ ቤተሰብ አንድ ልዑል በመወለዱ ምክንያት በጄነራል ግራዚያኒ ትዕዛዝ በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ከተሰበሰቡት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፤ ለፋሺስቶቹ ያደሩ ከሀዲ ባንዳዎችና መኳንንት፤ የፋሺስት ባለ ሥልጣናት ወታደሮች በተሰበሰቡበት መሐል፣ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ጀግኖች የእጅ ቦምብ ወርውረው አደጋ ሲጥሉ ግራዚያኒን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ተጎድተዋል። ይኸንን ድርጊት በመበቀል ሰበብ እዚያው ግቢ ውስጥ ከሶስት መቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተጨፈጨፉ፤ ቀጥሎም የተማሩ ወጣቶች፣ የጦር መኮንኖችና ካህናት፣ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት በሙሉ እየተለቀሙ ተጨፈጨፉ። ፋሽስቶች የአዲስ አበባንና የአካባቢውን ሕዝብ በጅምላ ጨፈጨፉት። በሶስት ቀናት ውስጥም 30ሺህ ሕዝብ መስዋዕትነት ተቀበለ። የስድስት ኪሎው ሐውልትም የሚነግረን ይሄንኑ ነውና ሁሌም በዚሁ ስሜት ውስጥ ሆነን እንመለከተዋለን። እናከብረዋለንም።
“ድሌ ማታ ነው ድሌ …” እንዲል ዜማው፣ ዞሮ ዞሮ ግን ጣሊያን የእጁን ከማግኘት አልዳነምና ከነሙሉ ውርደቱ ተሰናበተ።
የካቲት 13 ቀን 1535 ዓ.ም፣ በዕለተ ረቡዕ አሕመድ ግራኝ ወገራ ላይ የንጉሥ ገላውዴዎስን ሠራዊት ገጥሞ በፖርቱጋል ነፍጥ ተመቶ ሲሞት የተረፈው ሠራዊቱ ተሸንፎ ኮበለለ። በዚሁ ዕለት 1930 ዓ.ም፣ በአጋምሳ ላይ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ከፋሺስት ኢጣሊያ ጋር ውጊያ ገጠሙ።
የካቲት 15 ቀን 1952 ዓ.ም፣ ግብጽ እና ሶርያ የዓረብ ሪፑብሊክ ኅብረትን (United Arab Republic) መሠረቱ። ይሄ የሁለቱ አገሮች ኅብረት ከሦስት ዓመታት በኋላ ቢፈርስም የግብጽ መጠሪያ ስሟ ሆኖ ለብዙ ዓመታት ቆይቷል። (ግብፅ ዛሬም ድረስ ሰላማዊ አገራትን ለማተራመስ ይቻላት ዘንድ ልትጠቀምበት የምትሞክረውም ይህንኑ፣ በዛሬ ዳቦ ስሙ የዓረብ ሊግን ነው።)
የካቲት 21 ቀን 1970 ዓ.ም፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት በሶማሊያ ወራሪ ሠራዊት ላይ የካራማራን ድል ተቀዳጀ። በ1991፣ በዚሁ ዕለት የኢትዮጵያ ሠራዊት በኤርትራ ወራሪ ሠራዊት ላይ የባድመን ድል ተቀዳጀ።
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም፣ በዳግማዊ ምኒሊክ መሪነት የተሰለፈው የኢትዮጵያ ሠራዊት የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ዓድዋ ላይ ድል አድርጎ መለሰው። የካቲት 26 ቀን 1966 ዓ.ም፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥቱን አጥንቶ የሚያሻሽል ቡድን መሠየማቸውን ይፋ አደረጉ።
እነዚህ ከላይ ለማሳያ ያህል ብቻ የጠቀስናቸው እንጂ በአገራችን በየካቲት ወር የተከሰቱ ታሪካዊ ክስተቶችን በሙሉ የሚያጠቃልሉ አይደሉም። በዚህ ጽሑፍ ለማለት የተፈለገው እኛ ኢትዮጵያውያን በየካቲት ወር ያስመዘገብናቸው በርካታ የጋራ ድሎች አሉን። እንዚህ የጋራ ድሎች አሁን ላለንበት ዘመንና ታሪካዊ ወቅትም ስንቅ ሊሆኑንና ካለንበት አጠቃላይ ቀውስ አስፈንጥረው (“ስፕሪንግ ቦርድ” እንደሚባለው) በማውጣት ወደ ተሻለና ሰላማዊ ሁኔታ ሊያሻግሩን የሚገባ መሆኑን ለማመላከት ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም