ዝክረ ታሪክ፤
ኢትዮጵያ የብዙ ቅርሶች ባለፀጋ መሆኗ ለክርክር አይቀርብም። ምናልባት ያከራክር ከሆነ ለሙግት የሚቀርበው አጀንዳ የቅርስ ውርርሱና አጠባበቁ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። በደምሳሳ ፍረጃ ጥቅል አስተያየት እንስጥ ከተባለ ግን በአገራዊ ቅርሶች ጠባቂነት፣ አስረካቢነትና ተረካቢነት ረገድ በየዘመናቱ የኖረው ትውልድ በሚገባ አደራውን ተረክቦ ለወርተረኛው ትውልድ ለማሸጋገር የነበረበትን ውሱንነት በመጥቀስ ልንዋቀስ እንችል ይሆናል። ቀደምቱ ትውልድ አደራውን ለመወጣት አቅም እያነሰው ጉልበቱ የተብረከረከባቸው ታሪካዊ አጋጣሚዎች በየትዬለሌ ቁጥርና ዓይነት ሊገለጹ እንደሚችሉ የዘርፉ ጠቢባን አዘውትረው ሮሮ ሲያሰሙ መደመጣቸውም ስለዚሁ ይመስላል።
የአገራችንን ዘመን አይሽሬ ቅርሶች በአደራ ጠብቆና አስጠብቆ በማስተላለፍ ረገድ በቀዳሚነት ሊመሰገኑ የሚገባቸው መሠረተ ሰፊዎቹ የእምነት ተቋማት (አይሁድ፣ እስልምናና ክርስትና) እንደሆኑ ይህ ጸሐፊ በጽኑ ያምናል። የተጠቀሱት የእምነት ተቋማት አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለየ ሁኔታ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በቅርሶች አመንጭነት፣ ጠባቂነትና አስተላላፊነት ልዩ ምስጋና ሊቸራት ይገባል።
ቀደምት ነገሥታቱ ሳይቀሩ የማዕረግ፣ የወግና የጽሑፍ ቅርሶቻቸውን በስጦታም ይሁን በልግስና መልክ በአደራ ያስተላልፉ የነበረው ለዚህቺው አንጋፋ ቤተ ክርስቲያን ነበር። ከርዕሰ ጉዳያችን ጋር የሚጎዳኘውንና ቁጥር ስፍር የሌላቸውን የብራና ጽሑፎችን ብቻ ነጥለን ብናወጣ እንኳን «እንደ ምድር አሸዋ የበዙ» እንደ ዘር እህል በመላው ዓለም የተበተኑት ቅርሶች ከዚህቺው ቤተ ክርስቲያን የተገኙ ስለመሆናቸው አስረግጦ መመስከር ይቻላል።
አድማሱ እጅግ የሚለጠጠው ይህ የነገረ ቅርስ እሰጥ አገባ ጉዳይ ከዋናው መነሻ ሃሳባችን ስለሚያዛንፈን ሃሳባችንን ሰብሰብ አድርገን በየሥርዓተ መንግሥታቱ ከቤተ መጻሕፍት ምስረታና አስተዳደር ጋር የተያያዙ አንዳንድ የቅርብ ዘመን ማስረጃዎችን አጣቅሰን ወደ መነሻ ሃሳባችን በመመለስ ለአብሮሆታችን ምስጋና አቅርበን ርእሰ ጉዳያችንን እንደመድማለን።
ከቅርብ ዘመናቱ የኢትዮጵያ ነገሥታት መካከል ዘመናዊና ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትን ለማቋቋም ቀዳሚ ርእይ የነበራቸው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ እንደነበሩ ታሪክ እማኝነቱን ይሰጣል። ንጉሡ ይህንን ታላቅ ህልም በተግባር ለመተርጎም በማሰብ በርካታ የብራናና የኅትመት ጽሑፎችን ሰብስበው እንደነበር በዜና መዋዕላቸው ውስጥ በግልጽ ተመልክቷል። ህልማቸው እንደምንና በምን ሁኔታ ሊከሽፍ እንደቻለ እነሆ ታሪኩ እንዲህ ይታወሳል።
«ከጄኔራል ናፒየር ጋር አፄ ቴዎድሮስ ያደረጉት የመጨረሻው የመቅደላ ግብግብ የተቋጨው ንጉሡ በራሳቸው እጅ ራሳቸውን ባጠፉበት ዕለት ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም ነበር። መይሳው ካሳ ከወደቁ በኋላ የብሪትሽ ሙዚዬም ተወካይ ሆኖ ከናፒየር ወራሪ ሠራዊት ጋር የመጣውና በሪቻርድ ሆምስ የተመራው የአንደኛው የዘረፋ ቡድን ተልዕኮውን ያሳካው በቤተ መንግሥቱ ሕንፃ ውስጥ ነበር።
ንጉሡ በሕይወት ሳሉ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ለማቋቋም የሰበሰቧቸውን እጅግ ብዙ መጻሕፍት እንደዚሁም በአሁኑ ጊዜ የብሔራዊ ቤተ መዛግብት መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ የመንግሥት ሰነዶችንና የተለያዩ መረጃዎችን ሳይቀር ዘርፈዋል። ከእነዚህም መካከል በተለይም ክብረ ነገሥት የተባለው ታላቁ መጽሐፍ ይገኝበታል። …ከዘረፏቸው ቅርሶች ይልቅ ጥፋት ያደረሱባቸው አመዝነው ታይተዋል።…ብዙ መጻሕፍትንም ቀዳደዋል። (Kasa and Kasa, IES, AAU, 1990 P. 210)” ቴዎድሮስ ይህንን መሰሉን ታላቅ ህልማቸውን ሳይቋጩ ማለፋቸው በአገራዊ ታሪካችን ላይ የፈጠረውን ክፍተት መገመት አይከብድም።
ሌላው ተጠቃሽ መሪ ለሥልጣኔና ለአዳዲስ ዕውቀቶች አእምሯቸውና ልባቸው ክፍት የነበረው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ናቸው። እኒህ ንጉሥ እንደ ቴዎድሮስ ሰፋ ያለ «ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት» የማቋቋም ርዕይ እንደነበራቸው በግልጽና በቅርብ የተመዘገበ ታሪክ ለማግኘት አዳጋች ቢሆንም ቤተ መንግሥታቸውን አጎራብተው ያነጹትና ዛሬም ድረስ በጓጉንቸር ቁልፍ እንደተከረቸመ የሚገኘው የመዛግብት አርካይቫቸውና በስማቸው በተሰየመው በመጀመሪያው የዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ውስጥ የተቋቋመውን ቤተ መጻሕፍት ስናስታውስ ህልማቸው ከፍ ያለ እንደነበር እንገነዘባለን።
ከአፄ ቴዎድሮስ ቀጥሎ ምናልባትም በብሔራዊ ደረጃ ቤተ መጻሕፍት በማቋቋማቸው ስማቸውን በወርቅ ቀለም ያጻፉት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ናቸው። ንጉሡ የብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍትን ለማቋቋም ቅድሚያ የሰጡት ፋሽስት ኢጣሊያ ድል በተመታ ማግስት በ1936 ዓ.ም ነበር። ተቋሙን ካቋቋሙ በኋላም በተለያዩ ጊዜያት 738 ያህል የግል መጻሕፍታቸውን አበርክተዋል። ሕዝቡ በቤተ መጻሕፍቱ እየተገኘ መጻሕፍትን እንዲያነብ ለማበረታታትም አልፎ አልፎ ሹማምንቶቻቸውን እያስከተሉ ወደ ቤተ መጻሕፍቱ ጎራ በማለት አንባቢዎችን ያበረታቱ እንደነበር ይነገራል።
የንጉሡን ወንበር ገልብጦ ሥልጣነ መንግሥቱን የተቆጣጠረው ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ሕዝቡ ከቀለም ትምህርት መሃይምነት እንዲላቀቅ ያደረገው በጎ ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትን በማቋቋም ረገድ ግን ቸልተኝነት ብቻ ሳይሆን ፊውዳላዊ የሚል የጥላቻ ቅጽል በመስጠትም ያወደማቸው የመጻሕፍት ቅርሶች ብዛት እጅግ በርካታ ስለነበሩ በታሪክ ፊት የጠቆረ ገጽታ ሊያላብሰው ግድ ሆኗል።
የመንግሥታዊ ሥርዓቱ ፍልስፍና የተቃኘው በሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ስለነበረ ይህንኑ ፍላጎቱን ለማሳካት ነባሮቹን የኅትመት ቅርሶች እያወደመ ስለ ሶሻሊዝም የተጻፉ የባዕዳኑን የጽሑፍ ሥራዎች በከፍተኛ ሁኔታ ያሰራጭ እንደነበርም አይዘነጋም። የደርግን ሥርዓት የሸኘው «ጭንብል ለባሹ» የኢህአዴግ መንግሥት በገፍ ባቋቋማቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ይገኙ የነበሩ አብያተ መጻሕፍትን ከማቋቋም ውጭ ለብዙኃኑ ሕዝብ የሚያገለግል ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ለማቋቋም ህልም ይኑረው አይኑረው ምንም ፍንጭ ለማግኘት አልተቻለም።
አብርሆት ቤተ መጻሕፍት – «እንደ ስሙ እንዲሁ»፤
አዲሱ የለውጥ መንግሥት መንበረ ስልጣኑን ተቆጣጥሮ ወደ ሥራ እንደገባ በመጀመሪያ ካቀዳቸው ሥራዎቹ መካከል አንዱ «አብርሆት» የሚል ስያሜ የተሰጠውን የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ለማቋቋም መወሰኑ በእጅጉ ያስመሰግነዋል። ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ታሪክ ጋርም በቅርበት ያመሳስለዋል። በቅርጹ ውበትም ሆነ በይዘቱ ተገቢው አንቱታ ቢቸረው የማይበዛበት የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ተመርቆ አገልግሎቱን የጀመረው ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንደነበር ይታወቃል። ስለ አገልግሎቱ በዝርዝር ከመተረካችን አስቀድሞ ቤተ መጻሕፍቱ ስለሚገኝበት አካባቢ ጥቂት ዳሰሳ ማድረጉ የተሻለ ይሆናል። ቤተ መጻሕፍቱ የቆመው ለአዲስ አበባ ከተማ ብቻም ሳይሆን ለመላው አገሪቱ ጭምር እምብርት (Hub) በሚሰኝ ስፍራ ላይ ነው። ከፍተኛ ጥናት ተደርጎበት እንደተወሰነም መገመት አይከብድም፤ ማሳያዎችን እንዘርዝር።
አብርሆት ቤተ መጻሕፍትን በቡና አጣጪ ጉርብትና የጋራ አጥር የሚጋራው የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አበርበኞች ማኅበር ሕንፃ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። አሥራ አምስት ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙት የተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችም ግንባር ለግንባር የተጋጠሙ ጎረቤቶቹ ናቸው። ትንሽ ዝቅ ብለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤትና የምኒልክ ቤተ መንግሥት ከቤተ መጻሕፍቱ ጋር የዐይንና የቅንድብ ያህል ተቀራርበው ይተያያሉ።
ትንሽ እልፍ ሲባል ደግሞ የኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት፣ የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የታሪካዊው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የቀድሞ አዳራሽ ሕንፃዎች አብርሆትን የሚመለከቱት ሽቅብ አንጋጠው ነው። ከሂልተንና ከሸራተን ሆቴሎች ቡና ቢታዘዝ የሚደርሰው ሳይቀዘቅዝ ነው። በታላቁ የምኒልክ ቤተ መንግሥት ውስጥ ዧ ብሎ የተዘረጋው የአንድነት ፓርክና የጓሮ ያህል የቀረበው የወዳጅነት ፓርክም ለቤተ መጻሕፍቱ ንጹሕ አየር ለመመገብ ታስቦባቸው የለሙ ይመስላሉ። ጥቂት ዝቅ እንበል ካልንም የመከላከያ ሚኒስቴር፣ አዲሱና ግዙፍ ሰማይ ጠቀስ የንግድ ባንክ ሕንፃና ነባሮቹ፣ ብሔራዊ ቴያትር፣ የባህል ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በቅርብ ርቀት ዙሪያውን ከበውታል።
በሰሜን አቅጣጫ አንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የአንድ ክፍለ ዘመኑ አረጋዊ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ቤተ መጻሕፍቱን የሚመለከቱት እጅግም ሳይንጠራሩ ነው። የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋክልቲና ታሪካዊው የዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ቤተ መጻሕፍቱን አዘቅዝቀው የሚመለከቱት አጋርና አጋዥ አገኘን በሚል ስሜት በፈገግታ ታጅበው ነው። ሽቅብ ከፍ ባለ ቦታ ላይ የሚገኘው የቤተ ክህነቱ ሕንፃም ቆሞ ቡራኬ የሚሰጠው ይመስላል። ህመሙን የሚያክምለት ሁነኛ መሪ አጥቶ ድምጹ የተዘጋው የፓርላማው ደውል ከእንቅልፉ ተቀስቅሶ ሥራውን በሚጀምርበት ወቅት ብዙዎችን ለንባብ እንደሚጠራ ተስፋ ይደረጋል።
በአጭሩ አብርሆት ቤተ መጻሕፍት በመልካም ጎረቤቶች የተከበበው ከማዕከላዊ መንግሥቱ መንበር እስከ የእንደራሴዎች ምክር ቤቶች፣ ከትምህርት መፍለቂያ እስከ ሃይማኖት ተቋማት፣ ከጀግኖች አርበኞች እስከ የጥበብና የኅትመት ተቋማት፣ ከመዝናኛና ከቱሪዝም መዳረሻዎች እስከ የፋይናንስ ተቋማት፣ ከአገልግሎት ሰጪ እስከ ታላላቅ ሚኒስቴር መ/ቤቶች መሆኑ በራሱ ልዩ ትርጉም የሚያሰጠው ነው።
እነዚህ ግዙፍና ታላላቅ ጎረቤቶቹ ከዓመታዊ በጀታቸው ቆንጥረው ላይብረሪውን በመጻሕፍት ቢያሟሉ «ደግ ጎረቤት ጎጆ ያወጣል» እንዲሉ የሚጎናጸፉት የታሪክ ክብርና የኅሊና እርካታ በቃላት የሚገለጽ ስላልሆነ ባዶ ሼልፎቹ በቅርቡ በመጻሕፍት ወጀብ እንደሚጥለቀለቁ ጸሐፊው እምነቱ የላቀ ነው። ራሱ ይህ ጸሐፊም በግል ሼልፉ ላይ የተደረደሩትን በመቶዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍት በስጦታ ሊያበረክት እያደራጀ መሆኑ ቢታወቅ ለታላቁ አብርሆታችን ውለታ ማስመዝገቡ ሳይሆን ግዴታው ጭምር ስለሆነ ነው።
ይህ ባለ አራት ደርብ ቤተ መጻሕፍት በውስጥ አደረጃጀቱ ያለምንም ማሞካሸት በየትኛውም ዓለም ከሚገኝ መሰል ተቋም በአቻነት ቢሰለፍ እንጂ ያንሳል የሚሰኝ አይደለም። በሕንፃው ውስጥ 2000 ያህል አንባቢያንን ከሕንፃው ውጪ እስከ 500 ተገልጋዮችን የማስተናገድ ብቃት አለው። በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት እንዲችልም ዜጎች ሁሉ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚገባ ማስታወሱ ተገቢነት ይኖረዋል። እያንዳንዱ አዲስ አበቤ ብቻ አንድ መጽሐፍ ይዞ «ቤት ለእምቦሳ» እያለ ቢመርቀው ታሪክ እንደመስራት የሚቆጠር ነው። ይህ ጸሐፊ በቅርቡ ባደረገው ጉብኝት ያስተዋላቸውን አንዳንድ ጉዳዮች በተከታታይ ለአንባቢያን ለማቅረብ ይሞክራል።
የክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ርእይ ውጤት የሆነውን ይህንን ታላቅ ፕሮጀክት አጠናቆ ሥራ ላስጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልባዊ ምስጋናችን ይድረሰው። አገሬ ሆይ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገውም ትውልድ አስበሽ ይህንን ታላቅ ስጦታ በከተማችን እምብርት ላይ እንዲቆም ለመሪነት የሾምሽውን ልጅሽን አነሳስተሽ ውጤቱ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገውም ትውልድ በረከት እንዲሆን በጎ ፈቃድሽን ስለገለጽሽልን እናት ዓለም ሆይ ገለታ ይግባሽ። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2014