አገራችን ወቅትን እየጠበቀ በሚከሰተው ድርቅ ስትፈተን ኖራለች። በተለይም በ1966 ዓ.ም በወሎ፣ ትግራይና ኦጋዴን አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ወደ ረሃብ ተሸጋግሮ በሰውና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ አይረሳም፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎችንም ፈጥሯል። የአጼ ኃይለስላሴ መንግሥት ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠቱን ተከትሎ ዙፋኑን ካነቃነቀው የተማሪዎች ተቃውሞ መካከል አንዱ በወቅቱ የተከሰተው ረሃብ ነው። ኢትዮጵያ ከአድዋ ድል አነጋጋሪ ታሪኳ በተቃራኒ በመጥፎ ገፅታ የዓለም መነጋገሪያ እንድትሆን ያደረጋት በወቅቱ የተከሰተው ረሃብ ነው።
ከአስር ዓመት ቆይታ በኋላ በ1977 ዓ.ም የተከሰተውም ድርቅ እንዲሁ ተመሳሳይ ጉዳት አድርሶ አልፏል። በተለይም በወቅቱ ጦርነት ሲካሄድባቸው በነበረው የትግራይ አካባቢዎች በርካታ ዜጎች ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል። ሕወሓት በተቆጣጠራቸው የትግራይ አካባቢዎች ለድርቅ ጉዳተኞች እርዳታ እንዲያደርስ ከተባባሩት መንግሥታት የተሰጠውን ገንዘብ ለራሱ ጥቅም በማዋል ለበርካቶች ህልፈት ምክንያት መሆኑ ታሪክ የሚረሳው አይደለም። እነዚህ በድርቅ ምክንያት ያሳለፍናቸው መጥፎ ገጽታዎች ናቸው። ዛሬም አሸባሪው ሕወሓት በትግራይ ክልል ሰው ሰራሽ ረሃብ በመፍጠር ዜጎችን ለከፋ ችግርና እንግልት እየዳረገ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም።
ድርቅ በተፈጥሮ የሚመጣ ችግር መሆኑ ይታወቃል፤ ተፈጥሮ ያመጣውን ተፈጥሮ እስኪመልሰው ዝም ብለን አንመለከትም። ሊከሰት የሚችለውን የምግብ፣ የውሃና የከብቶች መኖ እጥረት አስቀድመን በመገንዘብ መልስ መስጠት ግድ ይለናል።
ከሁለት ዓመት ወዲህ አገራችን በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ስትፈተን ከርማለች፤ አሁንም ከገባችበት አዙሪት አልወጣችም። ጎርፍ ፣ ኮቪድ አስራ ዘጠኝ፣ ጦርነት፣ ጦርነቱን ተከትሎ የተፈጠሩ ጫናዎች ፈትነዋታል። አሁን ደግሞ በሶማሌ ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ሁለት ተከታታይ የዝናብ ወቅት ባለመዝነቡ ምክንያት በተከሰተው ድርቅ እየተፈተነች ነው።
አስቀድሞ ድርቅን ታሳቢ በማድረግ የተሠሩት ሥራዎች ችግሩ እንዳይባባስ ማድረጋቸው እንዳለ ሆኖ ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ በመንግሥትና በሌሎች አካላትድጋፍ በማድረግ የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ ርብርብ መደረጉ ይበል የሚያስብል ነው። በዚህም አበረታች ውጤት እየታየ ነው። ድርቁ ወደ ረሃብ እንዳይሸጋገር በመደረጉ እስከ አሁን በሰው ህይወት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳይደርስ ሆኗል።
በ1966 እና በ1977 ዓ.ም የተከሰተው ድርቅ ወደ ረሃብ ተሸጋግሮ የሰዎች ሞትና መፈናቀል፣ የእንስሳት እልቂት የታየበት ይሁን እንጂ በ1993 እና በ2008 ዓ.ም ድርቅ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቷል፤ ይሁንና ቀደም ሲል ከነበረው ችግር ልምድ በመወሰዱ ድርቁ ወደ ረሃብ እንዳይሸጋገር ቅድመ ዝግጅቶች በመደረጋቸውና ከተከሰተም በኋላ ለተጎጂዎች ድጋፍ በማድረግ አደጋው የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ተደርጓል። ይህም መንግሥት ችግሩን የመቆጣጠር አቅሙና ልምዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ያሳያል።
እያንዳንዱ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት መስሪያ ቤት ችግሩን ለማቃለል የየድርሻውን ኃላፊነት ለመወጣት ርብርብ ማድረጋቸው ድርቁ ዋጋ እንዳያስከፍለን አድርጓል። ለምሳሌ ብሄራዊ የሚቲሮዎሎጂ ኤጀንሲ የዝናብ እጥረት ያለባቸውን ቦታዎች አስቀድሞ በመተንበይ በተባሉት አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶና አርብቶ አደሮች ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉና በመንግሥት በኩልም ተመሳሳይ ዝግጅት እንዲደረግ ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። የመስኖ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር የደን አካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ የአርብቶ አደር ኮሚሽን ወዘተ በሚሰሯቸው ሥራዎች ድርቅ የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ ባይቻል ኖሮ ዛሬ አገራችን መጥፎ ገጽታ ይኖራት ነበር።
በተለይም አርሶና አርብቶ አደሮች ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ አስቀድሞ ውሃ የማቆር ልምድ እንዲኖራቸው እገዛና ስልጠናዎችን ከመስጠት ጀምሮ በአንዳንድ ቦታዎችም የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር ችግሩን ለማቅለል የተሠሩት ሥራዎች ውጤት ያመጡ መሆናቸውን የአደጋውን ደረጃ አይቶ መረዳት አያስቸግርም።
ድርቅ ወደ ረሃብ በተሸጋገረባቸው 1966 እና 1977 ዓ.ም የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከሰላሳ እስከ ሃምሳ ሚሊዮን የሚገመት ነበር። ያኔም አሁንም የነበረን የተፈጥሮ ሀብት ተመሳሳይ ነው። ያን ጊዜ ሰዎችንና እንስሳትን ከእልቂት ማዳን ያልተቻለው እንደአሁኑ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን ቅድመ ዝግጅቶችን ባለማድረጋችን እንጂ የያኔው ድርቅ ከአሁኑ ደርቅ የከፋ ሆኖ አይደለም።
ዛሬ መንግሥትም ህዝብም ድርቅን የመከላከል ልምድ በማዳበራችን ከሰላሳ እስከ ሃምሳ ሚሊዮን ሆነን የሰው ህልፈት ያስተናገድንበትን ድርቅ ቢያንስ አሁን ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሆነን አንድም ሰው እንዳይሞት ማድረግ መቻላችን ድርቅን ድል የማድረግ ጅማሮ ላይ እንዳለን ያሳያል።
ያለፉት የድርቅ ወቅቶች በሰው ህይወትና በእንስሳት ላይ ጉዳት አስከትለው መጥፎ ጠባሳ የተዉልን ቅድመ ዘግጅት የማድረግ ልምድ ባለመዳበሩና ሁሉም አካል ከዳር እስከ ዳር ተንቀሳቅሶ የየራሱን አስተዋጽኦ የማበርከት ተሞክሮው አናሳ ስለነበር ነው። አገሪቱ ተደራራቢ ችግር ውስጥ ባለችበት በዚህ ሰዓት የተከሰተው ድርቅ ወደ ረሃብ ተሸጋግሮ ጉዳት እንዳያስከትል እየተደረገ ያለውን ጥረት ማበረታታት ጤናማ አስተሳሰብ ነው። ለምን ድርቅ ተከሰተ ሳይሆን ድርቁን ለመቆጣጠር ምን አይነት ስራዎች ተሰሩ? ምንስ ውጤት ተገኘ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።
ከአንድ ክልል ወደ ሌላው ክልል የምግብና የመኖ ድጋፍ በማድረግ ችግሩን ለመግታት የተደረገው መተጋገዝ የድርቁን አቅም ከማዳከም አልፎ በቀጣይ ድርቅ ቢከሰት እንኳን በመተጋገዝ ማለፍ እንደሚቻል ያስተማረ ነው። በመንግሥት በመደበኛነት ሲረዱ የነበሩት ሰዎች ርዳታቸው እንዳይቋረጥ በማድረግ፣ በድርቅ ምክንያት እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው አዳዲስ ተረጂዎችም ድጋፍ በማድረግ ችግሩ እንዳይባባስ ማድረግ መቻሉ የሚበረታታ ነው።
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ባለሀብቶችም ድርቁ ወደ ረሃብ እንዳይሸጋገር የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውም ችግሩን አቅልሎታል። ውሃ በቦቴ በማሰራጨት ፣ የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር ፣ የምግብና የመኖ ድጋፍ በማድረግ መረባረባቸው ድርቁ ወደ ረሃብ እንዳይሸጋገር ያደረገ አዲስ የትብብር መንፈስ ነው።
የድርቅ ችግርን በአገር አቀፍ ደረጃ በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት እየሠራቸው ያሉት የልማት ሥራዎች ተስፋ ሰጪዎች ናቸው። ለምሳሌ በአረንጓዴ ልማት የተተከሉት በቢሊዮን የሚቀጠሩት ችግኞች የተፈጥሮን ሚዛን ከመጠበቅ አንጻር የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ቀላል አይሆንም። የግብርናውን ዘርፍ በሜካናይዝድ ለማዘመን የሚደረገው ጥረትና የበጋው መስኖ ልማት ድርቅን ለመቋቋም አቅም የሚፈጥሩ ብቻ ሳይሆኑ ድርቅ እንዳይከሰት የሚያደርጉም ናቸው።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2014