አፍሪካን ዳግም አረንጓዴ ማድረግ (Regreening Africa) ፕሮጀክት በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት እ.ኤ.አ ከ2017 አስከ 2022 ለአምስት ዓመታት ኢትዮጵያን ጨምሮ በስምንት የምዕራብና ምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋልና ሶማሊያ 1 ሚሊዮን ሄክታር የተራቆቱ መሬቶችን በደን ለመሸፈንና ከ500 ሺ አባወራዎች ጋር በመሆን ደንና ግብርናን በጥምረት ለማካሄድ አልሟል፡፡
በኢትዮጵያም ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣በትግራይና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች በሚገኙ 25 ወረዳዎች ላይ 200 ሺ ሄክታር የተራቆቱ ቦታዎችን በደን ለመሸፈንና ከ120 ሺ አባወራዎችና እማወራዎች ጋር በመሆን ደንና ግብርናን በጥምረት ለማካሄድ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉበት ቆይቷል፡፡
የፕሮጀክቱ የአንድ ዓመት አፈፃፀም የስምንቱ ሀገራት ተወካዮች በተገኙበት ከሰሞኑ በአዲስ አበባ የተገመገመ ሲሆን፤ በግምገማው ወቅት የየሃገራቱ የፕሮጀክት አፈፃፀም ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ በግምገማው ወቅትም ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ከሚያደርጉ አራት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት መካከል ኒጀርና ጋና የተሻለ መፈፀማቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ ኬኒያና ርዋንዳ ፕሮጀክቱን በጥሩ ሁኔታ መፈፀማቸው ተጠቁሟል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሮጅቱን ተግባራዊ ለማድረግ የመነሻ ጥናቶች የተካሄዱ ቢሆኑም አፈፃፀሙ ግን ዝቅተኛ እንደነበር በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡
በመቂ ካቶሊክ የዴራ ቅርንጫፍ አካባቢ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አቶ አስናቀው ደበላ እንደሚሉት፤ በፕሮጀክቱ የአንድ ዓመት አፈፃፀም በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በሚገኙ ሲሬና ዶዶታ ወረዳዎች የመነሻ ዳሰሳ ጥናት በማካሄድ መረጃ የማሰባሰብ ሥራዎች ተካሂደዋል፡፡ ወርክሾፖችን በማዘጋጀት ፕሮጀክቱን የማስተዋወቅ ሥራ ሲከናወንም ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚሆነው በተያዘው በጀት ዓመት ሲሆን፤ 25 ሺ ሄክታር የተራቆቱ መሬቶችን በደን ለመሸፈንና ከ15ሺ አባወራዎች ጋር በመሆን ደንና ግብርና በጥምረት ለማካሄድ እቅድ ተይዟል፡፡ ከስምንቱ ሀገራት ከተውጣጡ የስቲሪንግ ኮሚቴ አባላትና ተወካዮች የፕሮጀክት አፈፃፀም ልምድ ለመቅሰም ተችሏል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ ፕሮጀክቱ በዘንድሮው በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ የሚተገበር በመሆኑ በትግበራ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ በቶሎ ወደሥራው ለማስገባት አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል በፕሮጀክቱ ጠቀሜታ ዙሪያ ለህበረተሰቡ በቂ መረጃዎችን መስጠት ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለአስፈጻሚ ባለድርሻ አካላት ስለ ፕሮጀክቱ በማሳወቅ በቶሎ ወደተግባር የማስገባቱ ሂደት ሊጓተት ስለሚችል በየጊዜው ክትትልና ግምገማ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ በደን ለመሸፈን የሚመረጡ ቦታዎች ከእርሻ መሬቶች ጋር ንክኪ ያላቸው በመሆኑ ሥራውን እንዳያዘገዩ ከወዲሁ ከአርሶ አደሮች ጋር ውይይት ማድረግም ያስፈልጋል፡፡
የመንግሥት ፖሊሲ የተራቆቱ ቦታዎችን በደን የመሸፈኑን ተግባር የሚደግፈው በመሆኑና ከዚህ በፊት የነበሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችም ውጤት ያመጡ መሆናቸውን የሚጠቅሱት ሥራ አስኪያጁ፤ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቅም በቀሩት አራት ዓመታት ውስጥ ፕሮጀክቱን ማሳካት ይቻላል፡፡ ፕሮጀክቱን ለማስፈፀም በጀት የፀደቀና የሰው ኃይል ቅጥር የተደረገ ሲሆን፤ በቀጣይ ህብረተሰቡንና የመንግሥት አካላትን በጋራ በማሰባሰብና ወርክሾፖችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ በተመረጡት ቀበሌዎች ላይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይደረጋል፡፡ ከበጀት ትንበያ በኋላ በመጪው ወር ፕሮጀክቱ የሚጀመር ይሆናል፡፡
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የአፈር ለምነት ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይሌ እንደሚገልጹት፤ አፍሪካን ዳግም አረንጓዴ የማድረግ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ መሠረታዊ የዳሰሳ ጥናት ሥራዎች ሲካሄዱበት ቆይቷል፡፡ በተለይም ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድርግ መነሻ የሚሆኑ ጥናቶች በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ ተሠርተዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ዘግይቶ ከመጀመሩ አኳያ አፈፃፀሙ የተጠበቀውን ያህል ሊሆን አልቻለም፡፡ 200ሺ ሄክታር የተራቆቱ መሬቶችን በደን የመሸፈንና 120ሺ አባወራዎችንና እማወራዎችን ያካተተ ደንና ግብርናን በጥምረት ለማካሄድ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በቀሩት ዓመታት ውስጥ ፈጣን ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡ በመነሻ ጥናቱ መሰረት ይህን የሚያስፈፅሙ አካላትም ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፕሮጀክቱን ከግብ በማድረስ ረገድም የተሠራው የመነሻ ዳሰሳ ጥናት ጉልህ አስተዋዕኦ ይኖረዋል፡፡
እንደ ዶከትር ምትኩ ገለጻ፤ የተራቆቱ መሬቶች ዳግም እንዲያገግሙና ወደ ቀድሞው ሁኔታቸው እንዲመለሱ የማድረጉ ጥረት በኢትዮጵያ አዲስ ባለመሆኑና የተለያዩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ከዚህ ቀደም ሲሠሩ በመቆየታቸው በቀሪዎቹ ዓመታት ውስጥ ፕሮጀክቱን ለማሳካት አዳጋች አይሆንም፡፡ የአምስት ዓመቱ ፕሮጀክት ከተጠናቀቀ በኋላ የፕሮጀክቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ሊቀጥል ስለሚችል ይህን ፕሮጀክት የመፈፀም ጥረት በቀጣዮቹ ዓመታት በተቀላጠፈ ሁኔታ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
ፕሮጀክቱን ለማሳካት የስኬት መለኪያዎች ተቀምጠዋል፡፡ የስኬት መለኪያዎቹ ከእቅድ ማውጣት ጀምሮ አስከመጨረሻው ያለውን የፕሮጀክቱን አፈፃፀም አጠቃለው ይይዛሉ፡፡ በተለይም በህበረሰተቡ ላይ በተሠሩ ሥራዎችና እና የተራቆቱ መሬቶችን ዳግም እንዲያገግሙ በማድረጉ ሂደት የመጡ ለውጦችን ለመግምገም መለኪያዎች ተቀምጠዋል፡፡ በእነዚህ መለኪያዎች መሰረትም የፕሮጀክቱ አፈፀፃም የሚገመገም ይሆናል፡፡ በየዓመቱ ፕሮጀክቱን እየገመገሙና የሚታየበትን ክፍተት እየለዩ መሄድ የሚቻል ከሆነ የተያዘውን አቅድ በቀላሉ ማሳካት ይቻላል፡፡
ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፤ ፕሮጀክቱን የሚያስፈፅሙ አካላት ከመንግሥት ጀምሮ የተለያዩ የልማት አጋሮችና የህብረተሰብ ክፍሎች በመሆናቸው ሁሉም በአንድ ዓይነት መንገድና ሃሳብ ይሄዳሉ ተብሎ አይገመትም፡፡ በመሆኑም እነዚህን የተለያዩ ሃሳቦች በአንድ በማስተባበርና በማቀናጀት መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ይህም በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በቀላሉ ለመፍታት ያስችላል፡፡ በዚህ ረገድ ህብረተሰቡ ጠያቂና ፕሮጀክቱን በቅርበት የሚከታትል ከመሆኑ አኳያ አፈፃፀሙ የተሻለ እንዲሆን የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ በተለይም ታች ያለው አመራር ህብረተሰቡን በማነቃነቅ ለፕሮጀክቱ ስኬት የበኩሉን ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡
የተራቆቱ መሬቶችን ዳግም እንዲያገግሙ የማድረጉ ሥራ በሁሉም የሃገሪቷ ክልሎች እየተሠራ መሆኑን የሚጠቁሙት ፕሮፌሰሩ፤ ይሁን እንጂ ሥራው ከቦታ ቦታ የመጠንና የስፋት ልዩነት ይታይበታል፡፡ በጣቢያ ደረጃ ያለው የታችኛው አመራር ፕሮጀክቶችን ለማስፈፀም አቅም አስከፈጠረና ድጋፍ አስከጠየቀ ድረስ በሁሉም ክልሎች ውስጥ ተመሳሳይ ሥራዎችን መሥራት ይቻላል፡፡ ሥራዎቹም በሌሎች አካባቢዎች ላይ ሊሰፉ ይገባል፡፡ ለዚህም የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ የተራቆቱ ቦታዎችን በደን መሸፈንና የአካባቢውን ስነ ምህዳር መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግም ይጠይቃል፡፡
በግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ሴክተር የቴክኒክ አማካሪ ዶክተር አወቀ ሙሉዓለም በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የአምስት ዓመቱን አፍሪካን አረንጓዴ የማድረግ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ለማሳካት በመንግሥት በኩልና በልማት አጋሮች የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አንድ ዓመት ቢሆንም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ሆኗል፡፡ በዓመቱ የመነሻ ሥራዎችን መሥራት ቢቻልም ወደ ትግበራ ግን መግባት አልተቻለም፡፡
እንደ አማካሪው ገለጻ፤ በፕሮጀክቱ ትግበራ ወቅት መዘግየት በመታየቱ በቀጣይ የተያዘውን ግብ ለማሳካት አዳጋች ሊሆን ስለሚችል መንግሥትና የልማት አጋሮች በጋራ በመሆን የሚያጋጥሙ ችግሮችን ቶሎ በመፍታት ቢቻል ከተቀመጠው ግብ በላይ ለመሄድ የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ በፕሮጀክቱ ትግበራ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ በመለየት ሥራዎችን ማከናወንም የግድ ይላል፡፡
በፕሮጀክቱ ከተቀመጠው ግብ በላይ ለመሄድ በርካታ ዕድሎች እንዳሉ የሚገልጹት አማካሪው፤ በተለይም በመንግሥት በኩል ፕሮጀክቱን ለማስፈፀም ያለው ቁርጠኝነትና የአርሶ አደሮችና ባለሞያዎች ተነሳሽነት ለፕሮጀክቱ ስኬት ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ እስከአሁን በዘመቻ ሲሠሩ የነበሩ ሥራዎች በዚህ ፕሮጀክት በሳይንሳዊ መንገድ ተደግፈው የሚሠሩ ከመሆናቸውም አኳያ ፕሮጀክቱን ከተያዘው እቅድ በላይ ለማሳካት የሚያስችል አቅም ይኖራል፡፡
አማካሪው እንደሚሉት፤ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል በተለይም በትግራይ ክልል የተራቆቱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ በርካታ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ የተሠሩ ሥራዎችም ወደተቀረው የሃገሪቷ ክፍሎች እንዲሰፉ ተደርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሥራው በቂ ባለመሆኑ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ መስፋት ይኖርበታል፡፡
ፕሮጀክቱ በስምንት የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ተግባራዊ ከመሆኑ አኳያ ከሌሎቹ የአፍሪካ ሀጋራት ጋር በንፅፅር ሲታይ የኢትዮጵያ አፈፃፀም ወደኋላ ቀርቷል፡፡ በመሆኑም ፕሮጀክቱን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ጥሩ አፈፃፀም ካሳዩ ሀገራት ልምድ መቅሰም ያስፈልጋል፡፡ ለፕሮጀክቱ ስኬት የመንግሥትና የልማት አጋር ድርጅቶች ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ በየደረጃው ያሉ አመራሮችም ፕሮጀክቱን ከሚፈፅሙ አካላት ጋር ተናበው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ ትግበራ የተሠራው የመነሻ ዳሰሳ ጥናትም በቀጣይ የታሰበውን ግብ ለማሳካት አጋዥ ይሆናል፡፡ አስናቀ ፀጋዬ