የከበሩ ማዕድናትን ከማልማት ባሻገር ዕውቀትን ማጋራት

በኢትዮጵያ ከ40 በላይ የሚሆኑ የከበሩ ማዕድናት እንደሚገኙ ይታወቃል። ይሁንና ማዕድናቱን ለይቶ፣ አውቆና ተረድቶ ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ እምብዛም አይስተዋልም። ማዕድናቱ በተለያዩ አካባቢዎች ቢገኙም አብዛኛው ማኅበረሰብ ለይቶ ስለማያውቃቸው ላለፉት በርካታ ዓመታት ጥቅም ላይ ሳያውላቸው ቀርቷል።

ይሁን እንጂ ስለ ማዕድናቱ ቀድሞ የገባቸው ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በየአካባቢው አሉ። እነዚህ ጥቂት ሰዎች ታዲያ ማዕድናቱን አልምተው ጥቅም ላይ ለማዋል ብዙ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። ማዕድናትን ለይተው፣ አውቀውና ተረድተው ጥቅም ላይ ለማዋል ከፍተኛ ትረት ከሚያደርጉ ባለሙያዎች መካከል የዝና በከፊል የከበሩና የከበሩ ማዕድናት ጌጣጌጥና ተዛማጅ ሥራዎች አምራችና ላኪ ድርጅት አንዱ ነው። አቶ የዝና ማሞ የድርጅቱ መሥራችና ባለቤት ናቸው።

አቶ የዝና የስዕል፣ የቅርጻቅርጽ፣ የሽመናና የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት ናቸው። ረጅም ጊዜያቸውን በእነዚህ ሙያዎች እየሠሩ ያሳለፉ በመሆናቸው ወደ ከበሩ ማዕድናት ሥራ ለመግባት ጊዜ አልፈጀባቸውም። ስለከበሩ ማዕድናት የሚያስፈልጋቸው እውቀትና ልምድ ለመቅሰም ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ነበር። እ.ኤ.አ በ2011 በሀገረ ቻይና ጌጣጌጦች መሥራት የሚያስችል ስልጠና አግኝተዋል። ሥልጠናውን ካገኙ በኋላ የጌጣጌጥ ሥራን ወደ ገበያ ይዘው ለመግባት ቢያስቡም ቀላል አልሆነም። ከፍተኛ ካፒታል የጠየቃቸው በመሆኑ ያሰቡት ሳይሳካ ቀርቷል። ተስፋ ሳይቆርጡ በጌጣጌጥ ሥራው አጋር የሚሆናቸውን ባለሙያ አፈላልገው ማግኘት አልቻሉም። በዚህም የባለሙያ እጥረት እንዳለ መረዳት አስችሏቸዋል። የከበሩ ማዕድናት ሥራ በሀገር ውስጥ እምብዛም ያልተሠራበት መሆኑን የተረዱት አቶ የዝና፤ የተማሩት ትምህርት ለውጥ ማምጣት የሚችልና ውጤታማ እንደሚሆን ዕምነታቸው ነበር። ሆኖም ተስፋ ሳይቆርጡ የግል ጥረጥ በማድረግ ወደ ሥራው ገቡ። ከብዙ ጥረት በኋላ ተሳክቶላቸው በከበሩ፣ ማዕድናት እውቀትና ልምድ ማካበት ጀመሩ።

ወደ ጌጣጌጥ ሥራ ሲገቡ የከበሩ ማዕድናት ማስዋቢያ ወይም አብረዋቸው ሊሄድ የሚችሉ አቃፊ ሙያዎች አስፈልገዋቸዋል። ይህንን ለማወቅ ታዲያ ትምህርት መማር ነበረባቸውና የከበሩ ማዕድናትን ማስዋብ (ላፒደሪ) ለማጥናት በድጋሚ ወደ ቻይና ተመለሱ። ‹‹መጀመሪያ የተማርኩት የጌጣጌጥ ለመሥራት የሚያስችል ትምህርት ነበር። ጌጣጌጦች ሥራውን ስጀምር ግን ጌጣጌጦችን የሚያስውቡበት የከበሩ ማዕድናት እንደሚያስፈልጉ መረዳት ቻልኩ፤ ከዚያም ወደ ቻይና ተመልሼ ተማርኩ ››ይላሉ።

ቀደም ሲል የጌጣጌጥ ሥራን የተመለከተ ትምህርት የተማሩ ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ ተመልሰው ሲሄዱ በጌጣጌጦች ላይ ማዕድናትን ጨምሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ማስዋብ (ላፒደሪ) በተመለከተ በተደጋጋሚ አጭር ትምህርት መውሰድ ችለዋል። አቶ የዝና ‹‹የተለያዩ ትምህርቶችን መማሬ ስለማዕድናት በደንብ እንዳውቅ፣ ወደ ሥራው ጠልቄ እንድገባና እንድሠራ አድርጎኛል›› ይላሉ።

በ2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ መንግሥት ባመቻቸው ጥቃቅንና አነስተኛ በመደራጀት የማምረቻ ቦታ ተሰጥቶቸው ወደ ሥራ መግባታቸው ይናገራሉ። ይህም ሌሎችንም ሥራዎች እየሠሩ ወደዚህ ሥራ ለመግባት የሚያስችል መንደርደሪያ እንደሆናቸውና አሁን ለደረሱበት ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተላቸው ይገልጻሉ። ቀደም ሲል ትልቁ ችግራቸው የነበረውን የማምረቻ ቦታው ካገኙ በኋላ ማዕድናት ወደ መሥራት ሥራ በሰፊው መግባታቸው አስረድተዋል።

ወደ ሥራው ከገቡ በኋላ የሠሯቸውን ሥራዎች ለማሳየትም ሆነ ለማዳበር ምቹ ሁኔታዎች እንደተፈጠሩላቸው የሚናገሩት አቶ የዝና፤ አውደርዕዮች፣ ባዛሮችና የተለያዩ አጋጣሚዎች በመጠቀም ሰዎች ማዕድናቱን እንዲመለከቱና እንዲያለሙ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉም እንደነበር ይገልጻሉ። በዚህ ሂደት የሚያገኙትን ጊዜ በመጠቀም ገንዘባቸውን, በማጠራቀም በሰፊው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥራ ጀምረዋል።

አቶ የዝና እንደሚሉት፤ አሁን ላይ በድርጅቱ ከ60 አይነት ያላነሱ የከበሩ ማዕድናት አሉ። የከበሩና በከፊል የከበሩ ተብለው የሚታወቁ ብዙ አይነቶች ማዕድናት ይገኛሉ። ድርጅቱ በአብዛኛው በከፊል የከበሩ ማዕድናትን የሚሠራ ሲሆን እነዚህንም ከወርቅና ከብር ጋር አድርጎ ይሠራል። የከበሩ ማዕድናት እንዲሁ በገበያ ደረጃ ለኤክስፖርትና በተለያዩ መንገድ ጥቅም ላይ ያውላል። በከፊል የከበሩ የሚባሉት ሁሉንም በሚባል ደረጃ በመጠቀም የአንገት፣ የጣት ቀለበት፣ የእጅ እና የመሳሳሉ ጌጣጌጦችን ይሠራል።

ድርጅቱ የአንገት ሀብሎች፣ የጣት ቀለበት፣ የእጅ ጌጣጌጦች ከማምረት ባሻገር የቁልፍ መያዣና በቆዳና በቆዳ ውጤቶች ላይ የሚደረጉ ሌሎች አክሰሰሪዎችንም ከከበሩ ማዕድናት ጋር አባሪ አድርጎ ይሠራል። ጌጣጌጥ በብዛት ስለሚሠራ ማዕድናቱን ለጌጣጌጥ ሥራ ጥቅም ላይ ያውላል ብለዋል።

ማዕድናቱ ላይ እሴት ከተጨመረ በኋላ ለውጭ ገበያ ይላካሉ የሚሉት አቶ የዝና፤ ገበያውም ቀደም ካሉት ጊዜያት በጣም የተሻለ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን ይናገራሉ። ከሦስት ዓመታት በፊት የመጀመሪያው የማዕድን ኤክስፖ ከተካሄደ በኋላ ስለ ማዕድናቱ ያለውን ግንዛቤ እየሰፋ መጥቷል። በየዓመቱ መካሄዱም ግንዛቤው እንዲሰፋና እንዲዳብር ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓታል።

ድርጅቱ የማዕድናት ዓለም አቀፍ ስታንዳርዱን በጠበቀ መልኩ ስለሚሠራቸው እንደማንኛውም ማዕድን ገበያ ላይ ወጥተው መሸጥ እንደሚችሉ ይገልጻሉ። የገበያ መዳረሻዎቹ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ሆንግ ኮንግ ና ቻይና ናቸው። አሜሪካ የተወሰኑ ለመሥራት ናሙናዎች ተልከዋል። ‹‹ማዕድናት የፋብሪካ ውጤት ስላልሆኑ ሌላ ሀገር ላይ ቢኖርም ባይኖርም በኛ ሀገር ያለው ማዕድን መሸጥ ይችላል። ምክንያቱም ተፈጥሮ ስለሆነ በእኛ ሀገር በተፈጥሮ የተገኘውን ማዕድን ሌላ ሀገር ላይ መድገም አይቻልም›› የሚሉት አቶ የዝና፤

ማዕድናቱ ደረጃቸውን ጠብቀው በሚፈለገው ስታንዳርድ እስካልተሠሩ ድረስ ገበያው አስቸጋሪ እንደሆነ አንስተዋል። አንዳንድ ማዕድናት በማዕድናት መሥሪያ /በፔንፕሌት/ የሚሠሩ ቢሆኑም ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲሠሩ ይጠበቃል። ይህ ማለት ማዕድናቶቹ የራሳቸው የመሥሪያ ቁጥር ስላለቸው በዚያ መሠረት ተሠርተው ከቀረቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚቀርበው ጋር ተመሳሳይ ይሆናል።

አቶ የዝና እንዳብራሩት፤ በማዕድናት ላይ የሚታየው ትልቁ ችግር የእውቀት ክፍተት ነው። በውጭ ሀገራት ማዕድኑን ከማውጣት ጀምሮ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በከፍተኛ ጥንቃቄ ይሠራል። ‹‹በእኛ ሀገር ማዕድኑ እንደተገኘ ተቆፍሮ ስለሚወጣ የተለያዩ ችግሮች የተጋለጠ ነው። ይህ ደግሞ በዓለም አቀፉ ገበያ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ማዕድኑ ከአፈር ውስጥ ሲወጣ ጀምሮ ጥንቃቄ ሊደረግለት ያስፈልጋል። በከበሩም ሆነ በከፊል የከበሩ ማዕድናት የሚሠሩ ሥራዎች እየተላመደና ልምድ እያካበትን ስንመጣ በተመሳሳይ ደረጃ ማምረት ይቻላል›› ብለዋል።

መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተግባራዊ ካደረገ በኋላ በማዕድን ዘርፉ መነቃቃትን ፈጥሯል። በተለይም በከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ያለው ግንዛቤ፣ እውቀቱ አመለካከቱ እየሰፋ ነው። ሕብረተሰቡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ልክ እንደ እንቅፋት ቆጥሯቸው የማያስተውላቸው ማዕድናት በጥልቀት በመመልከት ወደ ባለሙያ ወስዶ ለማሳየት ጥረት መጀመሩን ያነሱት አቶ የዝና፤ እነዚህ ማዕድናት የሚጠበቀውን ያህል ተሰርቶባቸው ወደ ውጤት ማምጣት ቢቻል ደግሞ ለሀገር ኢኮኖሚ ምንጭ ሆነው ከፍተኛ ገቢን የሚያስገኙ ሀብቶች ከመሆናቸው ባሻገር ለብዙ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር የሚችሉ መሆናቸው አጽዕኖት ሰጥተው ይናገራሉ።

ከፌዴራል እንዲሁም ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ከአፋር እና ከሌሎችም አካባቢዎች ወደ ድርጅቱ ለስልጠና የመጡ ብዙ ሰልጣኞች እንደነበሩ አስታውሰው፤ በጌጣጌጥና በከበሩ ማዕድናት ከጌጣጌጦች ጋር የማዋሀድ ሥራን 600 ለሚደርሱ ሰዎች ስልጠና መስጠት ችለዋል። ከሰልጣኞቹ መካከል ማዕድን ፈላጊዎች፣ አውጪዎች፣ ቆፋሪዎች፣ ፈቃድ ሰጪዎች፣ የክልል ቢሮ ኃላፊዎች ስለነበሩ ድርጅቱ በእነርሱ አማካኝነት የጥሬ እቃ አቅርቦት እንደልቡ እያገኘ መሆኑን አመላክተዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ አጫጭር ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን ለአንድ ወር ያህል የሚፈጁ ስልጠናዎች ይሰጣል። ሰልጣኞቹም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የጌጣጌጥ ሥራውን አውቀው ቤታቸው መሥራት የሚችሉበትን አቅም ይዘው ይወጣሉ። ሜዳ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር 93፤ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር 66 የሚሆኑ ሰልጣኞችን አሰልጥኗል። እነዚህ ሰዎች ሰልጥነው ሲወጡ ማዕድናትን ለማስፋፋት ትልቅ እድል ይፈጥራል። በአሁን ወቅት ስልጠና ላይ ያሉ ሰልጣኞች አሉ።

በግላቸው መጥተው የሚሰለጥኑ ሰዎች ቢኖሩም ለእነዚህ ሰልጣኞች የእውቅና ፈቃድ ስለሌለን መስጠት አንችልም የሚሉት አቶ የዝና፤ ‹‹ሙያውን ማሰልጠን የሚያስችል መሳሪያ ቦታና እውቀቱም አለኝ፤ በማምረቱ ብሠራም በሌላ በኩል ከመንግሥት ጋር በመደጋገፍ ስልጠናውን እሰጣለሁ፤ በፈቃደኝነት ነው እያሰለጠንኩ ያለሁት እንጂ የስልጠና ፈቃድ የለኝም። ›› ይላሉ።

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት 21 የሚደርሱ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፤ ለ22 ሠራተኞች ስልጠና እየሰጠ ነው የሚሉት አቶ የዝና፤ ድርጅቱ በከፊል ከከበሩ ማዕድናትና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናት ለቻይና ለመላክ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል። ድርጅቱ አሁን ላይ ዘመናዊ የማዕድን መሥሪያ ማሽኖችን ከሚያመርተው ድርጅት ጋር አብሮ የመሥራት ስምምነት ያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ‹‹እነርሱ ማሽን ሲያዘጋጁ እኛ ደግሞ ለጥሬ እቃ ግብዓት የሚሆኑ በኤክስፖርት ደረጃ ለማቅረብ ዝግጅት ላይ ነን። በሌሎች የገበያ መዳረሻዎች ደግሞ እሴት የተጨመረባቸው በከፊል የከበሩ ማዕድናትን ለማቅረብ ታቅዷል። ሰልጥነው የሚወጡ ሰዎች በቀጥታ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማሽኖች ለማስመጣት አስበናል›› ብለዋል

አቶ የዝና እንዳብራሩት፤ አንድ ሰው በከፊል የከበረ ማዕድን ለመሥራት የመቁረጫ ማሽን፤ እሴት የሚጨመርበት /ላፒደሪ/ የሚሠራበት ባለስድስት ዌል ማሽን፣ የመብሻ ማሽን እና የመሳሳሉ በአጠቃላይ አምስት ማሽኖች ያስፈልጉታል። እነዚህ ማሽኖች መጠነኛ የሆኑ በጎጆ ኢንዱስትሪው ውስጥ ሊሠሩ የሚችሉ ናቸው።

ማዕድናት እሴት ጨምሮ መላክ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው የሚሉት አቶ የዝና፤ እሴት መጨመሩ ለአምራቹ ሆነ ለሀገሪቷ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ነው። ብዙ ዜጎች ማሳተፍ የሥራ እድል በመፍጠር ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው። በአዲስ አበባ ደረጃ ብቻ እንኳን ብንወስድ ከ50 እስከ 60ሺ በላይ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር ያስችላል። ዘርፉ ማዕድኑ ከሚያወጡት ጀምሮ ባለው ሰንሰለት ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል ሲሉ ያብራራሉ።

ማዕድናቱን በደንብ የማወቅና የመረዳት ክፍተቶች አሉ የሚሉት አቶ የዝና፤ እነዚህ ማዕድናት ከውጭ የሚመጣውን ምርቶች በተለይ እንደወርቅና ብር አይነቶችን መቶ በመቶ የሚተኩ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ማዕድናቱን ኤክስፖርት ማድረግ አንድ ነገር ቢሆንም ከውጭ የሚገባውን በማስቀረት የውጭ ምንዛሬን ማዳን መቻል በራሱ ትልቅ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሕዝቡ ግንዛቤ እንዲኖረው በመሥራት ውስጥ ሰርጾ እንዲገባና ብዙ ሰዎች አውቀውት መሥራት ቢችሉ የተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ያመላክታሉ።

ሁሉንም የከበሩ ማዕድናት በመሥራት ሕብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ሊገዛቸው እንዲችል አድርጎ መሥራት እንደሚያስፈልግ አቶ የዝና ያመላክታሉ። ምክንያቱም ዋጋቸው አነስ ባሉት ማዕድናት ከጀመርን በጣም ውድ ወደሆኑት የከበሩ ማዕድናት መሄድ አያዳግትም። ‹‹በእነዚህ ጀምረን ሕብረተሰቡ ጣቱ፣ አንገቱ እና እጁ ላይ እንዲያጌጥበትና እንዲለማመዳቸው እያደረግን እስካልሄድን ድረስ ወደዚህ መምጣትና ማወቅ አስቸጋሪ ይሆናል ››ይላል።

አቶ የዝና እንዳብራሩት፤ ድርጅቱ አሁን ላይ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ደርሷል። ወደፊት ወደ ኢንዱስትሪ በመሸጋገር ለማሳደግ ታቅዷል። በኢንዱስትሪ ደረጃ ተመርቶ ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ ለመላክ ታስቦ እየተሠራ ነው። ከትናንሽ የቤት እቃ ጀምሮ እስከ ማጌጫ ድረስ የተለያዩ ነገሮች ለመሥራት ታስቧል። ይህም ለ320 ሰዎች ማለትም ለ120 ሰዎች በቋሚነት፣ ለ200 ሰዎች ደግሞ በጊዜያዊነት የሥራ እድል የሚፈጥር ይሆናል። ድርጅቱ ከ2017 እስከ 2022 ዓ.ም ባሉት አምስት ተከታታይ ዓመታት 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል የሚያንቀሳቅስ ትልቅ ኢንዱስትሪ እንዲሆን ራዕይ ይዞ ሰንቆ እየሠራ ነው።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You